የሰብል ልማትን ከልማዳዊ አሰራር በመውጣት ስራውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና በምግብ እህል ራስን መቻል ተመራጭ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።በአገራችን ከ10 አመታት በላይ የዘለቀው የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማዘመን የሰብል ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ምንስ ውጤት ተገኘ? የዚህ ፅሁፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡
አቶ ደረሰ ተሾመ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኤክስቴንሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደሚሉት ተቋሙ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማመንጨት ጀምሮ፣ አባዝቶ፣ ለአርሶ አደሮችና ለሕብረተሰቡ ያስተዋውቃል።የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ የላቀ ሚና እንዳላቸውም ያስረዳሉ።ተቋሙ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አስር አዳዲስ የሰብል ቴክኖሎጂዎች እንዲተዋወቁ ትኩረት መደረጉን አስታውሰዋል።
እንደ አቶ ደረሰ ገለፃ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ እና ሩዝ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና በምግብ እህል ራስን በማስቻል የጎላ ሚና ያበረክታሉ በሚል በትኩረት ከሚሰራባቸው የሰብል ዝርያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።‹‹መልካ›› የተሰኘው የማሽላ ዝርያ ምርታማነትን የሚጨምር፣ ሌሎች ሰብሎች በተነሱበት ማሳ ላይ ተዘርቶ በ3 ወር የሚደርስና ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለው በመሆኑ ቴክኖሎጂው ተመራጭ ነው ብለዋል።
የኤክስቴንሽን ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ‹‹ቢ ኤች 660›› የተሰኘው የበቆሎ ዝርያ ከ90-120 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ በምርምር ቢረጋገጥም አርሶ አደሩ ከ60-80 ኩንታል ለረዥም ጊዜ እንዳመረተበት ይገልጻሉ፤ ‹‹ቢ ኤች 661 ›› የተሰኘው ቴክኖሎጂ ከ65-85 ኩንታል በሄክታር ምርት በመስጠት ላይ የሚገኝ ድቃይ ዝርያ ሲሆን ከ95-120 ኩንታል በሄክታር ምርት መስጠቱ በምርምር ተረጋግጧል ይላሉ፡፡
‹‹ቢኤች 546›› እና ‹‹ቢኤች 547››፣ የተሰኙት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በምርምር ከ85-95 በአርሶ አደር ደረጃ ደግሞ ከ55-70 ኩንታል በሄክታር ምርት የሚሰጡ ቢሆኑም በሰፊው ወደ ተግባር ሳይገቡ መቆየታቸውን ገልጸው አሁን ላይ በስፋት ተደራሽ መሆናቸውን ይናገራሉ።‹‹ኤም ኤች 140›› ደግሞ በቆላማና ዝናብ አጠር አካባቢዎች በሄክታር ከ80-120 ኩንታል ምርት መስጠቱ በምርምር የተረጋገጠና በመሰራጨት ላይ የሚገኝ ተስማሚ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው ይላሉ አቶ ደረሰ።
ከኢንዱስትሪ ሰብሎች የቢራ ገብስ ከውጪ የሚገባ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ግብአቶችን የጥራት ደረጃ የሚያሟላ ኢቦ 174/03 የተሰኘ በሄክታር 57 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ቴክኖሎጂ በመገኘቱ በስፋት አርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ጎጃም አካባቢዎች በኩታ ገጠም ሰርቶ ማሳያዎች በማስተዋወቅ የሚወጣውን ምንዛሪ ለማዳን እየተሰራ መሆኑን አቶ ደረሰ ያብራራሉ።አያይዘውም ከቅባት ሰብሎች አኩሪ አተር አንዱ ምንዛሪ የሚያስገኝ እና የሀገር ውስጥንም የዘይት ችግር የሚያቃልል በመሆኑ አዳዲስ የዝርያ ቴክኖሎጂዎች በቤኒሻንጉል ፓዊ፣ አሶሳ፣ጂማ፣ እና ጎንደር አካባቢዎች በስፋት እንዲተዋወቁ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ የሚገኙትን 14 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የመካናይዜሽን ተጠቃሚ በማድረግ 7 ሚሊዮን ጥማድ በሬዎችን ጉልበት 50 በመቶ ለመተካት ታቅዶ በሚፈለገው ደረጃ ተፈጻሚ አልሆነም።ተፈጻሚ የሆነው በአምስት ዓመታት 2 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ብቻ የመካናይዜሽን ተጠቃሚ ሆነዋል።
የግብርና ምርትና ምርታመነትን በማሳደግ ረገድ ባዮሎጂካል፣ኬሚካል እና መካኒካል የሆኑ ሶስት ዋና ዋና ቴክሎጂዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፤ መካኒካል ቴክኖሎጂዎችን ብቻ በመጠቀም እስከ 50 በመቶ የሰብል ምርት ማምረት የሚቻል ቢሆንም ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ቴክኖሎጂ ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን ብቻ ሲሆን የውጪ ምንዛሪ በማይጠይቀው ምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድም ቢሆን ሰፊ ስራ አለመሰራቱን ይናገራሉ፡፡
የአጨዳና የውቂያ ስራ 60 በመቶ በኮምባይነር ለማድረግ ቢታቀድም ሙሉ በሙሉ ከማጭድ አልተላቀቀም፤ ከባህላዊ አሰራር ፈቀቅ አላለም ባይ ናቸው የሜካናይዜሽን ዳይሬክተሩ፡፡
የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መካናይዜሽን፣ የመስኖ ሥራ፣ የተሻሻሉ ዘሮች፣ የአፈር ማዳበሪያ እና በመስኩ የሰለጠነ የሰው ሃይል አስፈላጊ መሆናቸውን የሚያነሱት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ አግሮ ኢኮኖሚክስ አስተማሪው ዶክተር ሚልኬሳ ዋቅጅራ፤ በጥናትና ምርምር የተገኙ የቴክኖሎጂዎች ውጤቶችም ከአርሶ አደሮቹ ዘንድ አልደረሱም ባይ ናቸው።የአርሶ አደሩ ሕይወት ሲሻሻልና ሲለወጥ አለመታየቱን በመከራከሪያነት ያነሳሉ።
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ በገብስ፣ በበቆሎ በስንዴና በሌሎችም ምርቶች በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን።የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያው በክህሎትም ሆነ በልምድ በሳል ባለመሆኑ አርሶ አደሩን መለወጥና ማሳመን የሚችል ቁመና እንዳልነበረውና አሁንም እንደሌለው ይገልጻሉ። በአንድ ሄክታር ላይ የሚበቅለው የበቆሎ ቡቃያ ብዛት እስከ 65 ሺህ መሆን ሲገባው አብዛኛው የኢትዮጵያ ገበሬ የሚያበቅለው ግን በሄክታር ከ20 ሺ አይበልጥም፤ በዚህ ምክንያት ምርት በግማሽ እንደሚቀንስ ያስረዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሰዓት ጠብቆ አለመዝራትና አለመሰብሰብ፣ የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂ በሰዓቱ አለማግኘት፣ የመንግስት አካላት ለገበሬው የሚያስፈልገውን ለይተው ድጋፍ አለማድረግና ሌሎች ችግሮች ምርታማነቱን ጎድተውታል ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ስንዴን በመስመር በመዝራት ብቻ ስድስት ኩንታል መጨመር እንደሚቻል ተማሪያቸው በተግባራዊ ጥናትና ምርምር እንዳረጋገጠላቸው የሚናገሩት ዶክተር ሚልኬሳ፤ አረምን መቆጣጠር ማስቻሉ፤ ሰብሉ አየር እንዲያገኝ እድል መስጠቱ፣ እህልን እንዲቀንስ ማድረጉ፣ ሳይንሱ በሚለው ብዛት ልክ መዝራት ማስቻሉ ለምርቱ መጨመር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምቹ ሁኔታዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ባለፉት አመታት መካናይዜሽኑ እንዲቀጭጭ ካደረጉት ተግዳሮቶች መካከል፡- በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መሳሪያዎችን የሚያንቀሳቅስ የሰለጠነ በቂ የሰው ሃይል አለማምረት፣ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ከውጪ ለማስገባት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ግብዓቶች ዝርዝር አለመኖር፣ በቅርቡ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት እንዲቻል ቢፈቀድም የውጪ ምንዛሪ ቅድሚያ ከሚያገኙት ተርታ አለመካተት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012
ሙሐመድ ሁሴን