ነጋሽ ከመቐለ ወደ ዓዲግራት በሚወስደው አውራ መንገድ 50 ኪ.ሜትር ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ናት፡፡ በተራራ ላይ የተቆረቆረችው ይቺ ከተማ ነፋሻማና ከቀደምት ከተሞች አንዷ ናት፡፡
የነጋሽ ታሪክ የሚጀምረው ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ነብዩ መሐመድ በሀገራቸው እስልምናን በሚያስተምሩበት ወቅት ተከታዮቻቸው ቁረይሽ በተባለ የዚያው ሃገር ጎሳ አባላት እየታደኑ ይታረዱና ይገረፉ ነበር፡፡ ነቢዩ መሐመድ ተከታዮቻቸውን ከጥቃት ለማዳን ሲሉ «እንግዳ ተቀባይና ቸር ህዝብ» ወደሚኖርባት የሐበሻ ምድር እንዲሰደዱና ጥገኝነት እንዲጠይቁ አመላክተው ላኳቸው፡፡ ስደተኞቹ በሁለት ሂጅራ /ጉዞ/ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች አስራ አንድ ወንዶችና አምስት ሴቶች ነበሩ፡፡ ጊዜውም እ.አ.አ በ615 ነበር፡፡ እነዚህ ስደተኞች የቁረይሽ ጎሳ አባላት የእስልምናን ሃይማኖት ተቀብለዋል የሚል የተሳሳተ መልዕክት ስለደረሳቸው ከሦስት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ሁለተኛው የስደተኞች ቡድን 101 /83ቱ ወንዶች/ ሙስሊሞችን ያቀፈ ነበር፡፡ ከስደተኞቹ መካከል የነቢዩ መሐመድ ሴት ልጅ ሩቂያ፣ ሃላ የነቢዩ ሚስቶች የሆኑት ሐቢባና ሠላማ/ ሂንዲ/ እንደዚሁም የእሳቸው የአጎት ልጅ ጃዕፈር አብኒ አቡጣሊብ ይገኙበት ነበር፡፡
ስደተኞቹን በመከታተል ከቁረይሾች የተላኩ ሁለት መልዕክተኞች ወርቅና ሌሎች ገፀ በረከቶችን ይዘው ንጉሥ ዘንድ በመቅረብ ስደተኞቹን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ይሁንና የሐበሻው ንጉሥ ስደተኞቹን አሳልፎ እንዲሰጥ በቁሪይሾች ቢጠየቅም «ተራራ ያህል ወርቅ ብትሰጡኝም አሳልፌ አልሰጥም» በማለት እንደመለሳቸው ይነገራል፡፡
ነብዩ መሐመድ ከኢትዮጵያዊው ንጉሥ ጋር የደብዳቤ ልውውጥ ያደርጉ እንደነበረም ጀዋሒረል ኢሕሳን ፈታሪከል ሐበሻና የመሳሰሉ በርካታ የዓረብኛ መፃሕፍት እንዲሁም አቶ ከበደ ሚካኤል በጻፉት «የዓለም ታሪክ» በተሰኘ መጽሐፍና በሌሎች በርካታ መፃሕፍት ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ሲቲዋርት ሙንሮ ሄይ የተባለ ተመራማሪ «አክሱም ኤንድ አፍሪካን ሲቪላይዜሽን ኦፍ ሌት አንቲኩቲ» በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ እንደጻፈው ከሆነ የደብዳቤው ይዘት ዳንሎፕ በተባለ አሳታሚ ድርጅት እ.አ.አ በ1940 ታትሞ ወጥቷል፡፡ የሐበሻው ንጉሥም በበኩላቸው ሙስሊሞች በቁረይሾች ይደርስባቸው በነበረው ጥቃት ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማበረታታት በማሰብ ግጥም ፅፈው እንደላኩላቸው ተመራማሪው ጨምሮ ጽፏል፡፡ ነቢዩ መሐመድ የኢትዮጵያ ንጉሥ እንግዳ ተቀባይነትና ፍትሐዊነት በማድነቅ ኢትዮጵያን ከጀሃድ ጦርነት ነፃ እንድትሆን ትዕዛዝ እንደሰጡም ይታወቃል፡፡
ውቅሮና ነጃሺ በ10 ኪ.ሜ ብቻ ነው ተራርቀው የሚገኙት፡፡ ከሳዑዲ ዓረቢያ በስደት ወደ ሀገራችን የመጡት ሙስሊሞች በነጃሺ ከተማ እንደተቀበሩ የአካባቢያችን ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ስለዚህ ነጃሺ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም መኖሪያ የነበረችና ኋላም አስከሬና ቸውን በክብር እንዲያር ፍበት በአላህ የተመረጠች ቅድስ ከተማ እንደሆነች ሁላችንም ልናውቀውና ልንኮራበት የሚገባ ነው፡፡
ይህ በሃገራችን በቅድስነቱና በቀደምትነቱ በተለይ ከፍተኛ እውቅናና ክብር በዓለም ሙስሊሞች ዘንድ የተጎናፀፈው የነጋሽ መስጊድ ሁለተኛ መካ በመባል እንደሚታ ወቅም መገንዘብ ያሻናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በነጃሺ ከተማ አንድ ትልቅ መስጅድ፣ ሁለት ደሪሖች /ሬሳ ያረፈባቸው ሕንፃዎችና/ በርካታ መቃብሮች ይገኛሉ፡፡ በዚህ 12 ሜትር ርዝመት ያለውና ዙሪያውም በብረት አጥር የታጠረ መቃብር፡፡ ከሳዑዲ ዓረብያ በስደት መጥተው እዚያው የቀሩ ሙስሊሞች ይገኙበ ታል፡፡ በተለይ በሁለተኛው ደሪሕ ውስጥ የተቀበሩት አስሃባ ትልቅ ደረጃ እንደነበራቸው ይታመንበታል፡፡ እሳቸው በነጋሽ በሞቱ ጊዜ ንብረታቸው ለዘመዳቸው ለማውረስ ሲባል ከነቢዩ መሐመድ የተላኩ መልዕክተኞች የሟቹን ንብረት /ልብስ ሳይቀር/ ስብስበው እንዲያመጡ በታዘዙት መሰረት ንብረቱን ወደ ሃገራቸው በመውሰድ የእስልምና እምነት በሚያዘው መሠረት ንብረታቸው ለቤተሰቦቻቸው እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡ ይኸው የማውረስ ህግ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነውም በእኚህ ሙስሊም ላይ መሆኑን ታሪክ ያወሳል፡፡
ከጥንታዊ መስጅድ ውጪ አንድ ዘመናዊ መስጅድ የተሠራ ሲሆን፤ አሠሪውም አንድ ምግባረ ሰናይ ሰው ናቸው፡፡ የመስጊዱና የመቃብሩ ዓመታዊ የጉብኝት /የዚያራ/ ቀን በዓረቦች አቆጣጠር መሃረም 10 ቀን ወይም በዓሹራ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ21/2011