የዛሬው የዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ አቅራቢ ወይዘሮ ሙሉ መኮንን በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 በርበሬ ተራ አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ዕድሜያቸው በ60ዎቹ ይገመታል። እርጅና፣ የኑሮ ጉዳትና ታማሚነት ተጋግዘው አቅማቸውን እንዳዳከሙት ገጽታቸውና አካላቸው ይመሰክራል።
ወይዘሮ ሙሉ ሳግ እየተናነቃቸውና እያነቡ የደረሰባቸውን በደል ይናገራሉ። የሚኖሩበት አንድ ክፍል የቀበሌ ቤት እንዲታደስላቸው በተደጋጋሚ ለቀበሌው ቢያመለክቱም በጥያቄያቸው መሰረት ሊታደስላቸው አልቻለም። የእርሳቸው ቤት ሳይታደስ ከእርሳቸው የተሻለ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች ቤታቸው እየታደሰላቸውና ተቀያሪ ቤት እየተሰጣቸው መሆኑን አይተዋል። ከዛሬ ነገ ይታደሳል እየተባሉም ተጉላልተዋል፤ ባለመታደሱም ችግር ላይ ወድቀዋል።
እርሳቸው ችግራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ አድጎ ለባሰ ችግር መጋለጣቸውንም ነው የሚገልጹት። በተለይም ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ እና ከአካባቢው የሚደፋው ቆሻሻ እጣቢ ቤት ውስጥ ገብቶ እየረበሻቸውና ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጋቸው መሆኑን፤ ፋታ ሊሰጣቸው ባለመቻሉም ቅያሪ ቤት እንዲሰጣቸው ቢያመለክቱም የተሰጣቸው ምላሽ አልነበረም።
ችግሩ እየተባባሰ በመሄዱ ለወረዳቸው ልማት ኮሚቴ አመልክተዋል። ልማት ኮሚቴውም መኖሪያ ቤታቸውን ከተመለከተ በኋላ ቤቱ እንዲቀየርላቸው መወሰኑን ተናግረዋል። ‹‹ሐምሌ ወር ዝናብ ሲጥል ኑሮዬ የጭንቅ ነው። በእኔ የቤት ችግር ከእኔ አልፎ ጎረቤቶቼ እየተቸገሩ ይገኛሉ። ዝናብ ሲጥል ፍሳሹ ወደ ቤታቸው ይገባል›› ይላሉ ።
ኑሮአቸውን የሚመሩት በሚደረግላቸው ድጋፍ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ ሙሉ ‹‹የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ ወደ ቤቴ እየገባ እየሸተተኝ ለባሰ በሽታ እየተዳረግኩኝ በመሆኑ ቀበሌው እልባት ሊሰጠኝ ይገባል፤ ከእኔ የተሻሉ ሰዎች ቤት እየተቀየረላቸው እና እየታደሰላቸው ነው። እኔ ግን መብቴ እየተጨቆነ ይገኛል›› ሲሉ ዕንባ እየተናነቃቸው ይናገራሉ። እርሳቸው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ቤቱ እንዲታደስ እያመለከቱ ቢቆዩም ውሳኔ ባለመሰጠቱ ለከፋ ብልሽት ስለተዳረገ ፍላጎታቸው ተቀያሪ ቤት እንዲሰጣቸው ነው።
ለልማት ኮሚቴ አመልክተው ኮሚቴው አመልካቿ በነባር ቀበሌ 30 በቤት ቁጥር 847 ነዋሪ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ኮሚቴው ግለሰቧ የሚኖሩበት አካባቢያቸው ምቹ ያልሆነ መሆኑን፣ እንዲሁም በጤናቸውም ላይ ያለባቸውን ችግር ገልጾ ደብዳቤ ጽፏል። የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ ግለሰቧ ታማሚ በተለይም ደካማ አረጋዊ መሆናቸውን ግምት በመውሰድ ቅያሪ ቤት እንዲሰጣቸው ቢገልጽም ምላሽ እንዳላገኙ ነው ወይዘሮ ሙሉ የሚናገሩት።
ቤቱ ቢታደስም ያው ነው የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዋ፤ ‹‹ክረምትን የምዘልቀው በጭንቅ ነው። ቤቱ ሊቀየርልኝ ይገባል›› ሲሉ ችግራቸውን ነግረውናል። የኤች አይቪ ታማሚ እንደሆኑ፣ ስኳር እና ደም ግፊትም በተደራራቢነት እንዳለባቸው፤ እንዲሁም ደካማ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ቤታቸው እንዲታደስላቸው በመጠየቃቸው በወረዳው ባለው የመልካም አስተዳደር ችግርና የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል መጉላላትና በደል እንደደረሰባቸው ነው የነገሩን። ‹‹ቤቱ ይቀየርልኝ፣ ቢሰራም ችግሩ ያው ነው። መፀዳጃ ቤቱ ጣሪያም ግድግዳም የለውም ቶሎ ቶሎ የሚሞላ በመሆኑ ቢመጠጥም ተመልሶ ይሞላል። ሲሞላም ወደ እኔ ደጃፍ መፍሰሱ አይቀርም›› በማለት በምሬት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሙሉን በቅርበት የሚያውቋቸውና በአካባቢው የሚኖሩት ወይዘሮ መቅደስ ጌጤ ቅሬታ አቅራቢዋ በጣም በከፋ ድህነት የሚኖሩና ህመምተኛ መሆናቸውን እርሳቸውም ሆኑ ሁሉም የአካባቢው ህብረተሰብ እንደሚያውቀው ይመሰክራሉ። ቤቱ ለመኖሪያነት ምቹ አለመሆኑን፣ መፀዳጃ ቤት በቅርበት ያለበት፤ ንጽህናውም የተጠበቀ ስላልሆነ ወረዳው ሊያያቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ። ከተቻለ ወረዳው ቤቱን ቢቀይርላቸው፤ ካልቻለም ደካማ ስለሆኑ ተመልክቶ ተገቢውን ድጋፍ ሊያደረግላቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ልጃቸው ጠቅለው አዳነ እናቱ ቀበሌው ቤቱን እድሳት ሊያደርግለት አልያም ቅያሪ ፈልጎ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ያስታውሳል። የወረዳው አመራሮች ቤታቸውን በመመልከት ‹‹በወረዳው ከእዚህም የባሰ ሰው ኑሮውን እየገፋ ይገኛል›› ብለው መሄዳቸውን ይናገራል።
አመራሮቹ ቤቱ እድሳት ሊደረግለት እንደሚችል መግለጻቸውን የሚያስታውሰው ጠቅለው፤ በገቡት ቃል ምላሽ አልሰጡዋቸውም። እርሱ የለውዝ መሸጫ ወረቀት እየጠቀለለ በማዞር የሚነግድ ቢሆንም ገቢው ያን ያህል ጠብ የሚል እንዳልሆነና እንኳን ቤተሰቡን ሊያግዝ ራሱን በተገቢው ሁኔታ የሚደጉም ባለመሆኑ እናቱን ሊደግፋቸው እንዳልቻለ ያስረዳል።
እንደ እርሱ ፍላጎት ከተቻለ ተቀያሪ ቤት፤ ካልተቻለ ግን እንደማንኛውም የሚታደስ ቤት እድሳት ቢደረግ መልካም መሆኑን የሚናገረው ጠቅለው ‹‹ ስድስት ሰዎች ሆነን በአንድ ክፍል የምንኖር በመሆናችን ግድግዳው ተሰንጥቆ ለከፍተኛ ቅዝቃዜ ተጋልጠናል ፤ እንዲሁም ፍሳሽ ገብቶ እየረበሸን በመሆኑ ፈጣን እልባት ቢሰጠን መልካም ነው ›› ይላል።
ወይዘሪት እዋዌ አዳሙ ከወይዘሮ ሙሉ ጋር በጉርብትና መኖር ከጀመረች አራት ዓመታትን ደፍናለች። እርሷ እንደምትለው አማራጭ በማጣት እንጂ አካባቢው ለኑሮ ምቹ አይደለም። ከመፀዳጃ ቤት ሞልቶ የሚፈስሰው ቆሻሻ በጣም የሚረብሽ በመሆኑ ከመፀዳጃ ቤት ፍሳሹ በላይ የእንስሳት ዕርድ የሚያከናውኑ ሰዎች የሚደፉት ቆሻሻ እቤት ውስጥ እንደሚገባና ቤታቸው ቢታደስላቸው አልያም ቅያሪ ቤት ቢሰጣቸው መልካም እንደሆነ ትናገራለች።
በፌዴራል በጎ አድራጎት እና ማህበራት ኤጀንሲ 1393 በምዝገባ ፍቃድ ቁጥር ተመዝግቦ እየሰራ የሚገኝ በሕዝብ ተሳትፎ የተቀነባበረ ዘላቂ የልማት ድርጅት (ሲቢሲዶ) የተባለ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም አረጋውያንን፣ ወጣቶችን፣ ወላጅ አልባ እና ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን፣ የአካል ጉዳተኛ ልጆችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልም ሰፊ የልማት ስራዎችን በማከናወን የሚገኝ ነው።
በዚሁ ሥራው በአሁኑ ሰዓት 200 የሚደርሱ የኢኮኖሚ ምንጭ የሌላቸው፣ የደሀ ደሃ የሆኑና ጧሪ ቀባሪ ያጡትን አረጋውያንን እየደገፈ እንደሚገኝ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ተገኔ ይጠቅሳሉ። በድርጅቱ ከሚደገፉ 200 ሰዎች መካከል አንዷ የዛሬው የፍረዱኝ ዐምድ አቤቱታ አቅራቢ ወይዘሮ ሙሉ መኮንን በአረጋውያን መርሀ ግብር ታቅፈው እየተደገፉ ይገኛሉ ።
የወረዳው ምላሽ
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገናናው አለሙ፤ ጽህፈት ቤታቸው በዋናነት አረጋውያን ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራና በወረዳው ያሉ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ከልደታ ክፍለ ከተማና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም ይገልጻሉ።
አቶ ገናናው ወረዳ 05 ሰፊ የሆነ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ በርካታ ዜጎች እንዳሉበት ይገልጹና፤ የሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ ቅሬታ ሊኖር እንደሚችሉ ያብራራሉ። ‹‹በክፍለ ከተማው ካሉ 10 ወረዳዎች በጣም የከፋ ችግር የሚታይበት፣ አብዛኛው ህብረተሰብም በጣም በከፋ ችግር ውስጥ የሚኖርበት ወረዳ በመሆኑ ወይዘሮ ሙሉ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል ነው። ሰዎች መኖር በሚገባቸው በተሻለ ሁኔታ የሚኖሩበት አካባቢ አይደለም። በመሆኑም አብዛኛው የወረዳው ነዋሪዎች ለኑሮ የተመቸ ቤት እንደሚያስፈልጋቸው እናምናለን›› ይላሉ።
እንደ አቶ ገናናው ማብራሪያ፤ ወረዳው ለኑሮ የተመቸ አይደለም። አሁን እንኳን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ 900 የሚሆኑ ሰዎች ተመዝግበዋል። 70 አካል ጉዳተኞች ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ይገኛሉ። 1ሺ 200 የሚደርሱ አረጋውያንም የሚገኙበት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 200 አረጋውያኖች በሕዝብ ተሳትፎ የተቀነባበረ ዘላቂ የልማት ድርጅት በ(ሲቢሲዶ) የሚደገፉ ናቸው።
‹‹ ቅሬታ አቅራቢዋ ወይዘሮ ሙሉ በአረጋውያን ድርጅቱ የሚደገፉ ሲሆኑ፤ እርሳቸው በእርግጥም በተለያየ በሽታ የተጎዱ ታማሚ ናቸው። አልፎ ተርፎም ኑሯቸው ችግር ያለበት ነው። ይህንንም አይተናል። ግን ችግራቸው ከሌላው የአካባቢው ህብረተሰብ ችግር እንደማይበልጥ ተገንዝበናል። ከእርሳቸው ችግር የበለጠ አንገብጋቢና ጊዜ የማይሰጥ በጣም ችግር ላይ የወደቁ ሰዎች አሉ።
ደረጃ ስናወጣ በጣም ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች በመኖራቸው ለእነርሱ ቅድሚያ እንሰጣለን። በመቀጠልም ደረጃ በደረጃ ለሌሎቹ ችግሮች ምላሽ እንሰጣለን። በክረምቱ ወቅት በበጎ ፍቃድ የወጣቶች አገልግሎትና ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት 49 ቤቶችን እድሳትና ጥገና አከናውነናል። የታደሱት ቤቶች ግን ከእርሳቸው የከፋ ችግር ውስጥ የነበሩ ናቸው›› ይላሉ አቶ ገናናው።
ሀቢታትፎርሂውማኒቲ ኢትዮጵያ በወረዳው የሚሰራው ስራ መኖሩን አቶ ገናናው ጠቅሰው፤ ድርጅቱ የራሱ የሆነ የሚለካበት መስፈርት መኖሩን ይናገራሉ። እኛም እንደወረዳ በጣም የተቸገረ ሰው ካለ ከባለሃብቶች ገንዘብ በማፈላለግ ቤታቸውን እየጠገንን እንዲሁም እያደስን እንገኛለን። ወይዘሮ ሙሉ አሁን ባለባቸው ችግር በሲቢሲዶ ይረዳሉ። አረጋዊ በመሆናቸውም በቀጥታ የሚያገኙት ድጋፍ አለ። አሁን ልንመዝን የምንችለው በጣም የከፋ ችግር ላይ የወደቀውን ብቻ እንደሆነ አቶ ገናናው ያስረዳሉ።
ቤት ሲታደስ መስፈርቱ ምንም የገቢ ምንጭ የሌላቸው፣ ቤታቸውን ማደስ የማይችሉ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። የቤተሰብ ብዛት ሌላው መመዘኛ ነው፤
የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ የሚያስቸግራቸው ሰዎችም ምዘናው ውስጥ ይካተታሉ። ይህንንም የቀጠና ኮሚቴ እና የልማት ኮሚቴ አረጋግጠው መላክ ይጠበቅባቸዋል። ካቢኔው መዝኖት ከተጣራ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ይሆናል።
በሌላ በኩልም ሀቢታትፎርሂውማኒቲ ኢትዮጵያ አሁን የሰጣቸው ዕድል እንዳለ የሚገልጹት አቶ ገናናው፤ አቤቱታ አቅራቢዋ እንዲታደስላቸው ለቀጠናቸው ልማት ኮሚቴ ያመለከቱበት ደብዳቤ ለጽህፈት ቤቱ የደረሰው ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑን ነው የተናገሩት። ጽህፈት ቤቱ ማመልከቻው እንደደረሰው ቤታቸውን ተመልክቶና አኗኗራቸውን ታዝቦ የእርሳቸው ቤት ከሌሎቹ ትንሽ የተሻለ በመሆኑና ከእርሳቸው በጣም የባሰ ችግር ላይ የወደቁ በመኖራቸው እነርሱን ማስቀደም እንዳለበት ማመኑን አቶ ገናናው ይጠቅሳሉ።
‹‹ከእርሳቸው የሚቀድሙ የባሰ ችግር ውስጥ የወደቁ ሰዎች በወረዳችን መኖራቸውን በምላሻችን አሳውቀናቸዋል። በእዚህም ተበሳጭተው ሄደዋል። አላስፈላጊ ነገርም ተናግረውን ነበር። ግን እንችለዋለን። ምክንያቱም እዚህ የተቀመጥነው ሰው ለማስተናገድ በመሆኑ ማንም የፈለገውን ቢናገር ብሶቱ እና ችግሩ የሚያናግረው በመሆኑ ማሳለፍ ግድ ይለናል። ወረዳው ግን በጣም ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች ቢደገፉ፣ ቤታቸው ቢቀየርላቸውም ሆነ ቢታደስላቸው ፍላጎታችን ነው›› ይላሉ አቶ ገናናው።
እንደ አቶ ገናናው ምላሽ አካባቢው በሙሉ በመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ የተበከለ ነው። በተለይም ክረምት ሲገባ ቤቶች ተደራርበው እና ተጨናንቀው በመሰራታቸው ይህ ችግር በስፋት ይስተዋላል። በጤናቸው እና በህይወታቸው ላይ አደጋ የተጋረጠባቸውን ሰዎች በማስቀደም የአቤቱታ አቅራቢዋ የቤት እድሳት ቀጥሎ የሚታይ ይሆናል።
አቶ ገናናው፤ የወይዘሮ ሙሉ ቤት ከሌሎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለእድሳት አስቸጋሪ እንደሆነ በመጥቀስ ከክፍለ ከተማው ጋር በመነጋገር ተመጣጣኝ ቤት ከተገኘ እንደሚቀይሩላቸው፤ ካልሆነ ደግሞ ዕድሳት እንደሚደረግላቸው፣ መቼ ሊታደስ ወይም ሊቀየርላቸው እንደሚችል ግን ቁርጥ ያለ ጊዜ ለማስቀመጥ እንደሚቸገሩ፤ ነገር ግን የእርሳቸው ቤት ዕልባት እንዲሰጠው በመርሀ ግብሩ ውስጥ መካተቱን ነው የገለጹት።
የጋዜጠኛው ምልከታ
የወይዘሮ ሙሉ ቤት አንድ ክፍል ሲሆን፤ በውስጡ ተደራራቢ አልጋ ይታያል። የቤቱ ግድግዳ ፈራርሷል፤ መጥፎ ጠረን ወይም ሽታ የሚገባ በመሆኑ ቤት ውስጥ በር ከፍቶ ለመቀመጥ እንደሚያስቸግር መገመት አይከብድም። ከወረዳው ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገናናው ጋር አካባቢውን እና ቅሬታ የቀረበበትን ቤት ለመመልከት በተገኘንበት ወቅት ከወይዘሮ ሙሉ ቤት የባሰ ለችግር ተጋላጭ ሆነው ኑሯቸውን የሚገፉና ህጻናትን የሚያሳድጉ እናቶችን ጭምር ተመልክቻለሁ።
በአካባቢው የመፀዳጃ ቤትና የቆሻሻ ፍሳሽ የሚያልፍበት በመሆኑ የተበከለ ነው። በዚያ ስፍራ ለመኖር ቀርቶ ለማለፍም እጅግ በጣም የሚከብድ ነው። በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ እስከ ዘጠኝ እና ከዚያም በላይ ሰዎች የሚኖሩ እንዳሉ ይስተዋላል።
ወረዳውን እና አቤቱታ አቅራቢዋን እያከራከረ ያለው የቤት እድሳት ጉዳይ እልባት ሊሰጠው ይገባል። ነገር ግን የቅደም ተከተል ጉዳይ እንጂ መቀየር ወይም መታደስ እንዳለበት ወረዳውም አልካደም። ይኸው ጉዳይ ከወረዳው አስተዳደር አልፎም የጤና ጉዳይን የሚመለከተውም አካል ሊያየው ይገባል።
ወይዘሮ ሙሉ የወረዳው ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት እንዲሁም በየደረጃው ያሉና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር አልሄዱም። ምክንያቱም ችግሩን የወረዳው የጤና ጽህፈት ቤት አያውቀውም። ወረዳውም ከአቅሙ በላይ ሆኖበት ለሚመለከተው የበላይ አካል አላሳወቀም።
በኢፌዴሪ ህገ መንግስት በግልጽ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ንጹህ እና ምቹ በሆነ ስፍራ መኖር ይጠበቅበታል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ስንመለከትም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ስምምነት ዲክላሬሽን የመኖሪያ ቤትን አስመልክቶ ማንኛውም ሰው ንጽህናው በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ዓላማዎች በሚለው በአንቀጽ 92 ድንጋጌው ስር ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ያስቀመጠው በአንቀጽ ቁጥር አንድ የተመለከተው መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህ እና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት። ይህ ማለት ግለሰብም የራሱን የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር ሚና ይኖረዋል እንደማለት ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅም3/2012
ዘላለም ግዛው