አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል በደርግ ዘመነ መንግሥት 10 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ የተገነባው የአልዌሮ ግድብ እንደተፈለገው ለልማት አለመዋሉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሎው ኦቡት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፣ በግድቡ በአሁኑ ወቅት ማልማት የተቻለው አንድ ሺ ሁለት መቶ ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡
ሳውዲ ስታር የተሰኘው ኩባንያ ግድቡን በተወሰነ መልኩ እያለማው እንደሚገኝ የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፣ የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎችም በአነስተኛ መስኖ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እያካሄዱ ሲሆን፣ ከክልሉ ፍጆታ ባያልፍም ዓሳ እየተመረተበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ከግድቡ በሚፈለገው መጠን መጠቀም ላለመቻሉ ክልሉ የሚወስደው የራሱ ድክመት አለ›› ያሉት ዶክተር ሎው ፣ የሚመለከታቸው የሀገሪቱ አካላት ለግድቡ የሰጡት ትኩረትም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህን መቀየር ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረው፣የጋምቤላ ክልልም በተለይ ወጣቶችን ከግድቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ልዩ የትኩረት አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጸዋል፡፡
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ከተማ ጥላሁን በበኩላቸው ‹‹አልዌሮ ግድብ በክልሉ ጥቅም ሊሰጡ ከሚችሉ ነገር ግን ካልተሰራባቸው የአገር ሃብቶች መካከል ይመደባል›› ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ መስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሐሪም፣የአገሪቱ ሰፋፊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጡ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ የአልዌሮ ግድብም ይህ ነው የሚባል ጥቅም እንዳልሰጠ አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣በዚህም ‹‹አልዌሮን የመሳሰሉ ከፍተኛ ሃብት የማያስወጡ መጠነኛ ማሻሻያዎች በማድረግ ብቻ ወደ ሥራ መግባት የሚያስችሉ ግድቦች ታሳቢ ተደርገዋል››ብለዋል፡፡አልዌሮና ጎዴን የመሳሰሉ ግድቦች ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ለወጣቶች የማስተላለፍ ሥራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
ታምራት ተስፋዬ