አዲስ አበባ፡- እስካሁን ለስምንት ዓመት ያህል በምርምር ሲሰራበት የቆየው የአየር ፀባይ መተንበያና የግብርና ምክረ ሐሳብ ማሰራጫ ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውና ግብርናውንም ለማዘመን እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የአገሪቱን ግብርና ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ የታመነበት የአየር ፀባይ መተንበያና የግብርና ምክረ ሐሳብ ማሰራጫ ቴክኖሎጂ ትናንት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይፋ ሆኗል።
ቴክኖሎጂው ይፋ በሆነበት ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ይፋ የተደረገው የአየር ፀባይ መተንበያና የግብርና ምክረ ሐሳብ ማሰራጫ የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቱ ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፣ለአገሪቱ ግብርና መዘመን የበኩሉን ሚና ይጫወታል።
ቴክኖሎጂው የአየር ለውጥን የመተንበይ ዓላማን ይዞ የተዘጋጀ ሲሆን፣እንደ ዝናብ እና ሙቀት ያሉ መረጃዎችን ወስዶ ለሚጠቀሙ አካላት በኤሌክትሮኒክስ እንዲደርስ ለማድረግ ያስችላል።ውሳኔ ለመስጠት ጠቀሜታው ያላቀ ሲሆን፣ለፖሊሲ አውጪዎችም ግብዓት በመሆን ሊያገለግል ይችላል።
‹‹የአየር ንብረት ጉዳይ ድንበር ዘለል ነው።አገሪቱ የምትጠቀምባቸው የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደጊያ ግብዓቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በመረጃ መታገዝ አለባቸው።›› ያሉት ዶክተር ድሪባ፣ ‹‹ማደባሪያን፣ምርጥ ዘርንም ሆነ ሌላውን ግብዓት መጠቀም ቢቻልም በየትኛውም መለኪያ ቢታይ የአገሪቱ የግብርና ሥራ ግንኙነቱ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዘ ነው›› ብለዋል። ያለመረጃ ግብዓት ብዙ ርቀት መሄድ እንደማይችልም ጠቅሰው፣የአየሩን ሁኔታ አስቀድሞ ማወቅ በብዙ ድካም የተዘራውን ምርጥ ዘርም ሆነ ማዳበሪያ ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።
የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ አቶ ጀማል ሰይድ በበኩላቸው፤የቴክኖሎጂው ትልቁ ዓላማ የአየር ፀባይና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀት ምክረ ሐሳቦችን ማሰራጨት መሆኑን ጠቅሰው፣በቅድሚያ ለአርሶ አደሩ ቀጥሎም ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
መፃፍና ማንበብ ለሚችሉ አርሶ አደሮች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በመልዕክት እንዲደርሳቸው እንደሚደረግ ፣ቴክኖሎጂውን ማንበብ ለማይችሉት ደግሞ ቀጥታ ደውለው የሚፈልጉትን መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚረዳ አብራርተው፣ይህ አይነት አሰራር ለኢትዮጵያ አዲስ መሆኑንና በተለያዩ አገራት ግን እንደሚሰራበት ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂው ላለፉት ስምንት ዓመታት በምርምር ላይ ሲሰራበት መቆየቱን ጠቅሰው፤ በጭፍን ከሚተገ በረው የግብርና ሥርዓት መረጃን መሰረት ወደ አደረገ ሥርዓት መምጣቱ ግብርናውን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢያሱ አብርሃ፣ ግብርናው ላይ እየተሰራ ያለው የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ትራንስፎርሜሽን ደግሞ ሁለት ነገሮች አሉት።አንደኛው የተትረፈረፈ ምርት ማምረት ሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ ለገበያ ሊሆን የሚችል ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ ነው።››ሲሉ አብራርተዋል።
ግብርናውን ለማዘመን ዋና ማነቆ የሆኑት ምንድን ናቸው ተብለው እንደተለዩም ጠቅሰው፣ምርጥ ዘር፣ መካናይዜሽን፣ማዳበሪያ አጠቃቀምና ሌሎች ተለይተው መቀመጣቸውን በአብነት አመልክተዋል።
ቀደም ሲል ድርቅ ይከሰት የነበረው በአስር ዓመት አንዴ መሆኑን ጠቅሰው፣አሁን በየሶስት ዓመት መከሰት መጀመሩንም ጠቁመዋል።ይህም እየሆነ ያለው አርሶ አደሩ በአግባቡ መረጃ ባለማግኘቱ መሆኑን ተናግረው፣አርሶ አደሩ ጥንቃቄ ያደርግ የዚህ ቴክኖሎጂ ወደ ሥራ መግባት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቴክኖሎጂው ኢንስቲትዩቱና ግብርና ሚኒስቴር ከተለያዩ የልማትና የምርምር አጋሮች ጋር በመሆን ግብርናው በሚዘምንበት መንገድ ላይ በጋራ እየሰሩ መሆናቸው ታውቋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 2/2012
አስቴር ኤልያስ