ኢትዮጵያ የውሀ ማማ ሆና ሳለ ዜጎቿ የሚጠሙባት፣ ዓመቱን ሙሉ ወንዞቿ እየፈሰሱ ዝናብ ጠብቃ ብቻ በማምረት የምትታወቅ ሀገር ናት። ተፈጥሮ የለገሰቻት በርካታ ለመስኖ ልማት ጭምር የሚውሉ ወንዞች ቢኖሯትም የሚጠቀምባቸው አጥተው ሲባክኑ ኖረዋል።
በአንዳንድ ክልሎች ለመስኖ አገልግሎት በሚል ግድቦች ቢገነቡም የታለመላቸውን ሳያሳኩ በርካታ ዓመታትን አስቆጥረዋል። በተፈጥሮ ሃብት በሚታወቀው የጋምቤላ ክልል የሚገኘው የአልዌሮ ግድብ ለእዚህ ተጠቃሹ ነው። ከጋምቤላ ከተማ አርባ አራት ኪሎ ሜትር በምትርቀው አቦቦ ወረዳ አቅራቢያ የሚገኘው ይህ ግድብ በደርግ ዘመነ መንግስት 10 ሺ ሄክታር መሬት እንደያለማ ታቅዶ መገንባቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም የግድቡን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ያነጋገራቸው አካላት አልዌሮ ካለው አቅም አንፃር ሲታይ ጥቅም ላይ አለመዋሉን አስታውቀዋል። ግድቡ ከተገነባ ከሩብ ምእተ ዓመት በላይ ማስቆጠሩ ቢገለጽም፣ ሊሰራበት ቀርቶ ስሙን እንኳን የሚያውቁት ጥቂቶች መሆናቸው ነው የሚገለጸው።
በሰፊው ተንጣሎ የሚገኘው ይህ ግድብ የመስኖ ልማት ቢሰራበት ለአገር የሚተርፍ ከፍተኛ አቅም እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ክልሉም ሆነ አገሪቱ በግድቡ በሚፈለገው መጠን እየጠቀሙ አይደለም። በእርግጥ ሳውዲ ስታር የተሰኘ ድርጅት ግድቡን እንደተጠቀመበትም ይነገራል። ግድቡ ከፍተኛ የዓሳ ሃብት ክምችት እንዳለው ቢታወቅም የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ለእለት ፍጆታ እንደሚጠቀሙት ነው የሚታወቀው።
የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኦቡት እንደሚሉት፤ ግድቡ በደርግ ዘመነ መንግስት 10 ሺ ሄክታር መሬት ለመልማት ታቅዶ ነው የተገነባው። በአሁኑ ወቅት ማልማት የተቻለው አንድ ሺ ሁለት መቶ ሄክታር ብቻ ነው። የግድቡ አካባቢ ነዋሪዎች በአነስተኛ መስኖ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እያካሄዱ ሲሆኑ፣ ከክልሉ ፍጆታ ባያልፍም ዓሳ እየተመረተበትም ይገኛል።
ከሰው ሰራሹ ግድብ በሚፈለገው መጠን መጠቀም ላለመቻሉም ክልሉ የሚወስደው የራሱ ድክመት እንዳለ ዶክተር ሎው ጠቅሰው፣ የሚመለከታቸው የሀገሪቱ አካላት ለግድቡ የሰጡት ትኩረትም ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህን መቀየር ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረው፣ ‹‹የጋምቤላ ክልልም በተለይ ወጣቶች ከዚህ ግድብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለየ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል ››ይላሉ።
‹‹አልዌሮ ግድብ በክልሉ ጥቅም ሊሰጡ ከሚችሉ ነገር ግን ካልተሰራባቸው የአገር ሃብቶች መካከል ይመደባል›› ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ከተማ ጥላሁን ይጠቁማሉ። ምን ያህል የዓሣ ሀብትና ምን ዓይነት የዓሣ ዝርያዎች እንደያዘ በተደራጀ መልኩ ጥልቅ ጥናት እንዳልተካሄደበት ጠቅሰው፣ በዘርፉ ያለውን አቅም መጠቀም የሚያስችል ተገቢው ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም እንደሚጠራጠሩም ያመለክታሉ።
ዩኒቨርሲቲው የክልሉን የሃብት አጠቃቀም እንክብካቤና አያያዝ ለማጎልበት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረው፣ የአልዌሮንም ሆነ የባሮ ወንዞችን ሃብት እንዴት መጠቀም ይቻላል፣ አገሪቷ ከዚህ ሀብት እንዴት መጠቀም ትችላለች የሚሉትን በአግባቡ ለማወቅ የተደራጀ ጥናት እያካሄደ መሆኑም ይጠቅሳሉ።
‹‹እስካሁን ያንቀላፋንባቸው ጊዜያት ያስቆጫሉ፣ ክልሉንም አገሪቱን ሊመግብ የሚችል ሃብት አለን፣ ከሃብቱ ለመጠቀም ግን ከሁሉም አስቀድመን ልናውቀው ይገባል ›› ያሉት ዶክተር ከተማ፣ በአሁኑ ወቅት ግድቡ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ መሆኑንና ከትሩፋቱ ለመጠቀም ጠንክራ ስራዎችን መከወን የግድ እንደሚልም ያስገነዝባሉ።
የፌዴራል መስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሚካኤል መሐሪም፣ የአልዌሮ ግድብ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳይሰጥ ስለመቆየቱ ይስማማሉ። ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት፤ በአገሪቱ የሚገኙ ሰፋፊ የመስኖ ፕሮጀክቶች እስካሁን ድረስ ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጡ ቆይተዋል። የመስኖ ልማት ዘርፉ ብዙ ትሩፋቶች ያሉት ሲሆን፣ የተጠቀመው ማህበረሰብ ግን በጣም ትንሽ ነው።
ህብረተሰቡም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለመስኖ ያላቸው አመለካከት ጥሩ የሚባል አይደለም ያሉት ዶክተር ሰለሞን፣ ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው ኮሚሽን በዘርፉ የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት ለመቀየር በትጋት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ ኮሚሽኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች በውጤታማ የመስኖ ልማት እቅድ ትግበራ ያላቸውን ጥንካሬና ድክመት በሚገባ በመለየት ጥንካሬያቸውን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያግዙ አማራጮችንና አቅጣጫዎችን እያመላከተ ነው፣ ከስራ እድል ፈጠራ ባሻገር ነባር ፕሮጀክቶችን የማሻሻል፣ ምርታማነትን የማጎለበትና ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ አሰራር መከተል ጀምራል።
ለነባር ፕሮጀክቶች ትኩረት በመስጠት ረገድ ‹‹አልዌሮን ከፍተኛ ሃብት የማያስወጡ መጠነኛ ማሻሻያዎች በማድረግ ብቻ ወደ ስራ መግባት የሚያስቻሉ ግድቦችን ታሳቢ ተደርገዋል›› የሚሉት ዶክተር ሰለሞን፣ ከኮሚሽኑ ቀጣይ ትኩረቶች አንዱም አልዌሮና ጎዴን የመሳሰሉ ግድቦች ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግና ለወጣቶች ለማስተላለፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የመስኖ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ አቅም ምን ይህል ነው የሚለው በአግባቡ በማወቅና በማጥናት ረገድ ውስንነቶች ይስተዋላሉ። ይህን ተግዳሮት ለማስወገድ በፕሮጀክቶቹ ላይ ክለሳ ለማድረግ ጥናት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ኮሚሽኑ አልዌሮን የመሳሰሉ የተረሱ የመስኖ ግድቦች ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ብቻውን አቅም እንደማይኖረው ዶክተር ሰለሞን ጠቅሰው፣ በዚህ ላይ ክልሎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አጋርነት ወሳኝ እንደሆነም ያመለክታሉ።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ባለፈው ግንቦት በሰጡት መግለጫ፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ጊዳቦ፣ ኦሞ ኩራዝ፣ በለስ፣ ኩለን፣ አሬቦ፣ ጎዴና አልዌሮን በመሳሰሉ የመስኖ ግድቦች እንዲሁም ራያ ሸለቆ እና ሽንሌ ከርሰ ምድር ውሃ በመጠቀም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ 12 ሺህ ወጣቶችን የሚያሳትፍ ዘመናዊ የመስኖ እርሻ ፕሮጀክት እንደሚተገበር መናገራቸው ይታወሳል። በዚህም አልዌሮም ቀን ሊወጣለት ይመስላል።
አዲስ ዘመንኅዳር 2 /2012
ታምራት ተስፋዬ
Muchas gracias. ?Como puedo iniciar sesion?