አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተመሰረተ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 33 ተማሪዎችን በመቀበል ስራ ጀመረ። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው 50 ሺ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል። ተቋሙ በየጊዜው በሚያሳየው መሻሻልና ለውጥ በጥናትና ምርምር አገሪቱ የምትፈልገውን የተማረ የሰው ሃይልና ቴክኖሎጂ ለማሟላት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ስር 13 ካምፓሶች፣ 10 ኮሌጆች፣ ሁለት የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች፣ 12 የምርምር ኢንስቲትዩቶችና ሁለት ከፍተኛ የማስተማሪያና ህክምና መስጫ ሆስፒታሎች ይገኛሉ። በነዚህ ውስጥ 73 የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት መስኮች፣ 345 የድህረ ምረቃ ትምህርት ዓይነቶች እና 96 የጥናትና ምርምር መስኮች የሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ይገኛሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ዩኒቨርሲቲው ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አስረኛ ደረጃ ማግኘቱን ተከትሎ መግለጫ ሰጥተው ነበር። በመግለጫቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ዳሰዋል። ዩኒቨርሲቲው ባካበተው የረጅም ጊዜ የጥናትና ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ባሳየው ውጤታማ ስራ አለም አቀፋዊ ሽልማቶችን ማግኘቱን ጠቅሰዋል። እአአ 2014 ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 18ኛ ደረጃ እንዲሁም እአአ 2015 ደግሞ ከአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 16ኛ ደረጃ አግኝቶ ነበር። እአአ 2020 በአፍሪካ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአስረኛ ደረጃን ያገኘ ሲሆን በአለም ከሚገኙ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች 618ኛ እንዲሆን አስችሎታል።
ሰላምና መረጋጋት
ፕሮፌሰር ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማ ሂደቱን ያለምንም ችግር እያከናወነ ይገኛል። በሌሎች ተቋማት ታይተው የነበሩ አለመረጋጋቶች በዩኒቨርሲቲው አላጋጠሙም። ችግሩ እንዳይፈጠር ያደረገው የመጀመሪያው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተጠናከረ ግንኙነት የተመሰረተ በመሆኑ እና ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት ክትትል በማድረጉ ነው። ተቋሙ ከተማሪዎች ጋር በማንኛውም ጉዳዮች ላይ በቅርበት እየሰራ ስለሚገኝ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሯል። የተቋሙ መምህራን ለተማሪዎች አርአያ እንዲሆኑ በሚያስተምሩበት ወቅት ግጭትን የሚያስወግድና ሰላም በሚፈጥር መልኩ መሆን አለበት። መምህራኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ተጋብዘው ንግግር ወይም ሃሳብ ሲሰጡ ህብረተሰቡ በሰላም እንዲኖር የሚያደርጉ ታሪኮችን ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
የትምህርት ጥራት
የትምህርት ጥራት ጉዳይ በሁሉም አለም አገራት የሚስተዋል ችግር ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የትምህርት ጥራት ችግሮች ያሉበት ሲሆን ተመርቀው የሚወጡት ተማሪዎች የፅንሰ ሀሳብ እውቀት እንጂ የተግባር እውቀት እንደሌላቸው ተስተውሏል። ተማሪዎች የተግባር እውቀት አግኝተው እንዲወጡ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የተማሪዎች የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል በመክፈት ለተማሪዎች የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች በተከታታይ እየተሰጡ ይገኛሉ።
የመምህራንን እውቀት ለማጎልበት ደግሞ መምህራን በምርምር ስራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል። ለመምህራን የምርምር ስራ በዓመት እስከ 65 ሚሊዮን ብር ድረስ በመመደብ እየተሰራ ሲሆን እያንዳንዱ መምህር በሁለት ዓመት አንድ የምርምር ስራ እንዲሰራ ይደረጋል። የምርምር ስራውን በአለም አቀፍ መፅሄቶች ላይ እንዲያሳትሙ በማድረግ የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት አስተዋፅኦ አድርጓል። አንድ መምህር የምርምር ስራውን አለም አቀፍ መፅሄት ላይ ሲያሳትም የአስር ሺ ብር ማበረታቻ ይሰጠዋል።
በተጨማሪም በስራ ላይ የሚገኙ ሰዎች እራሳቸውን እንዲያሻሽሉ በማታ መርሃ ግብር ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። ዩኒቨሲቲው ከማታ የትምህርት መርሃ ግብር ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን የመማር ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እድሉን እንዲያገኙ ለማድረግ ነው። በዚህም ከመደበኛው ተማሪ እኩል የሚሆኑ ተማሪዎች በማታው መርሃ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታሉ ይገኛሉ። በማታው መርሃ ግብር የሚሰጠው ትምህርት ጥራት እንዲኖረው ለማስቻል የተወሰነ የገንዘብ ክፍያ ጭማሪ እንደተደረገበት በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
ድጋፍና ተግዳሮቶች
ተቋሙ አዳዲስ የሚከፈቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመርዳትና አብሮ ለማደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። የድህረ ምረቃና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርቶችን በማስፋት ከዩኒቨርሲቲዎቹ መምህራንን እየተቀበለ ያሰለጥናል። ይህ ሁኔታ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በፍጥነት እንዲያድጉ እያደረገ ይገኛል። በሌላ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር በየዓመቱ ዩኒቨርሲቲዎችን እያወዳደረ ደረጃ ይሰጣል። ዩኒቨርሲቲዎች መገምገም የሚገባቸው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ቢሆንም ፖለቲካዊ የሆኑ መስፈርቶች በመብዛታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአገሪቱ አንደኛ ደረጃ አልያዘም። ነገር ግን በአለም አቀፍ መስፈርት ሲወዳደር ግን የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በተቋሙ በተማሪዎችና በተገልጋዮች የሚነሱ ቅሬታዎች ያሉ ሲሆን የሚነሳውን ያክል ባይሆንም የአሰራር ችግሮች ይስተዋላሉ። ችግሮቹን ለመፍታት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ አድርጓል። ከተማሪዎች መማክርት ጋር በመሆን አሰራሮችን ለማስተካከል እየተሰራ ይገኛል። ከመምህራን ይሁን ከተማሪዎች የሚመጡ ቅሬታዎች የሚፈቱበት አሰራር የተዘረጋ ሲሆን ችግሮች ካሉበትም ለማስተካከል ተቋሙ ዝግጁ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ የሚገኙ ተማሪዎችን ብቻ እየተቀበለ ያስተምራል የሚባለው ነገር የተሳሳተ ግንዛቤ ሲሆን በተያዘው ዓመት ከተቀበላቸው 3500 ተማሪዎች ውስጥ የአዲስ አበባ ተማሪዎች 600 ብቻ ናቸው። ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል። በሌላ በኩል ተቋሙ ከራሱ ወጪ በማድረግ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች እየደገፈ በማስተማር ላይ ይገኛል። ለዚህ ስራ ከመንግስት የሚገኝ በጀት ባይኖርም ዩኒቨርሲቲው በራሱ ወጪ የሚሰራው በመሆኑ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያመላክታል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 1 / 2012
መርድ ክፍሉ