የመልካም አስተዳደርና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ ሥራዎች ከተሞች ከሚፈተኑባቸው ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሲታጣ ደግሞ ስራውን የበለጠ ውስብስብና ከባድ ከማድረጉም በላይ የከተሞችን ልማት የሚጎዳ፣ የነዋሪዎችን ወጥቶ የመግባት ሕልውናም አደጋ ላይ የሚጥል፣ የወጣቶችንም ሰርቶ የማግኘት ህልም የሚያመክን ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
በስራ እድል ፈጠራም ሆነ በሰላም ረገድ አዳማ መልካም ገጽታ እንደነበራት የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በከተማዋ የሰላም እና የስራ እድል ፈጠራ ተምሳሌትነት ዙሪያ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሰራቸው ስራዎች ማሳያ ናቸው፡፡
በከተማዋ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የግጭት ክስተት ግን ይህንን የቀደመ ስሟን የማይመጥን እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በተመለከተ ከአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደሜ ጋር ባደረግነው ቆይታ ያደረሱንን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ እንደገለፁት የከተማ አስተዳደሩ አዳማን እንደ ስሟ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ ለዚህም በዝግጅት ምዕራፍ ጊዜው ለዚህ ሂደት ምን መስራት አለብን የሚለው በአግባቡ ተለይቷል፡፡ በዚህም የመልካም አስተዳደር ችግርን መፍታት፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራ ማከናወን፤ የነዋሪውን በተለይም የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግሮችን መቀነስ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው የሚገኙ ጉዳዮች ናቸው፡፡
እቅዱ ሲያዝ ያለፈው በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፤ ጠንካራ ልምዶች ተጠናክረው እንዲጓዙ ድክመቶችም ተለይተው እንዲታረሙ አቅጣጫ ተቀምጦ፣ ከባለድርሻዎች ጋር ተመክሮበትና የጋራ አቅድ ተደርጎ ወደስራ እንዲገባ ተደርጓል። ለምሳሌ፣ ባለፈው ዓመት ተጀምረው ከነበሩ 35 ፕሮጀክቶች ውስጥ 24ቱ እንዲጠናቀቁ በታሰበው መሰረት 23ቱን ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ ይህ መልካም የሚባል ነው፡፡ በአንጻሩ የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም አዳዲስ የስራ እድሎችን ከመፍጠር አኳያ የታዩ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመተግበርና የተያዙትንም ቶሎ ከመጀመር አንጻር ክፍተቶች ነበሩ፡፡
እነዚህንና መሰል ክፍተቶችን በመለየት በዚህ ዓመት በጥቅሉ 61 ፐሮጀክቶችን ለመተግበር እቅድ ተይዟል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ግን ከተማ አስተዳደሩ ስለፈለገ ብቻ የሚከናወኑ ሳይሆን የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥያቄ መሰረት ያደረጉ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፤ በዚህ ሂደት ከዲዛይን ጋር ተያይዞ የሚስተዋል ችግርን ለማቃለል እንደ ክልልም ሆነ እንደ ከተማ አስተዳደር የፕሮጀክት ዲዛይኖች በክረምቱ ወቅት እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ በተቀመጠው መሰረት ተሰርቷል፡፡ በጀት ተይዞላቸውም የ28 ፕሮጀክቶች ጨረታ ወጥቶላቸው ሰነዶችን የማጥራት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የእነዚህ ፕሮጀክቶች በወቅታቸው መከናወንም ከመልካም አስተዳደርና ከመሰረተ ልማት ችግሮች ጋር በተያያዘም(ለምሳሌ፣ ከመንገድ ጥጋና፣ ከመንገድ ዳር መብራት፣ ከውስጥ ለውስጥ ድልድዮች፣ ከመጠጥ ውሃ እና ከጎርፍ መከላከል ጋር የተያያዙ) የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፕሮጀክቶች ጥራትም ሆነ መጓተት ጋር ያሉ ችግሮች የተለዩ ሲሆን፤ በተለይ ፕሮጀክቶችን የሚያጓትቱ ተብለው ሁለት ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡
አንደኛው፣ ከኮንትራክተሮች አቅም ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ ግንባታውን ለማስጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቅቆ የፕሮጀክቶቹን አካባቢዎች ነጻ ካለማድረግ(ከወሰን ማስከበር) ጋር የተያያዘ በመንግስት በኩል የሚታይ ችግር ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማቃለልም የከተማ አስተዳደሩ በየዘርፉ ኮሚቴ በማዋቀር ሂደቶችን እየገመገመ እየሰራ ሲሆን፤ የአዳማ ከተማ ደግሞ የዓለም ባንክ የልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆኗ ችግሩን በትጋት ለመፍታት አቅም ይሆናል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሲደረጉ የህብረተሰቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመመለስ ባለፈ፤ የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራና ተጠቃሚነት ማዕከል ባደረገ መልኩ የሚከናወኑ ናቸው። ለምሳሌ፣ ከእነዚህ ውስጥ 7ቱ ብቻ በኮንትራክተሮች የሚሰራ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ (የፕሮጀክት ዋጋቸው ከ10 ሚሊየን ብር በታች የሆነ) ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቁ ወጣቶች ማህበራት እንዲከናወን አቅጣጫ ተቀምጦ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይሄም ከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም በከተማ ጽዳትና ውበት ላይ ወደ 140 ማህበራት አሉ፤ በአረንጓዴ ስራፍዎች ስራም በተመሳሳይ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡
በመሆኑም በዚህ ዓመት በእነዚህና ሌሎችም ዘርፎች ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል አበረታች የስራ ጅምር አለ፡፡ በኢንቨስትመንት፣ በቤት አቅርቦትና ሌሎች ዘርፎች ላይም ትኩረት በማድረግ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት፤ ለወጣቱም የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ በተለይ የህዝቡንም ጥያቄ ከመመለስም ሆነ የስራ እድልን ከመፍጠር አኳያ ኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ ስላለው በትኩረት እየሰራበት ሲሆን፤ በዚህ ረገድ መሬት ወስደው ወደስራ ያልገቡት አልሚዎች ላይ እርምጃ በመውሰድና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች እንዲበራከቱ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የልማት ስራዎች ሊሳኩ፤ ህዝቡም ጥያቄው ሊመለስና ወጣቱም ስራ ሊፈጠርለት የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ አዳማ ሰላም በመሆኗ የኮንፍረንስ ማዕከል እንድትሆን ብቻ ሳይሆን በቀን ቢያንስ ከ65 ሺ ሰው በላይ ወደከተማዋ ገብቶ የሚወጣባት ናት፡፡ ሆኖም በቅርቡ በከተማዋ ተከስቶ የነበረው ችግር ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ ከትቶት፤ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ስራና አገልግሎቶች እንዲሁም የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲቀዛቀዙ አድርጎ ነበር፡፡
ይህ ደግሞ የከተማዋ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድርና ገብቶ በሚወጣው አካል ላይም ስጋት የሚያጭር፤ የከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና ድርጅቶችም ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ገቢ የማግኘት አቅምንም የሚያዳክም ነው፡፡ በመሆኑም ለከተማዋ ልማት እውን መሆን፣ ለህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ለሰላም ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ ለዚህም በየደረጃው ያለ አካል፣ ህብረተሰቡ፣ ወጣቱ ባጠቃላይ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ ሊሰራ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 1 / 2012
ወንድወሰን ሽመልስ