አዲስ አበባ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸው በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና ቀጣዩም ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሶማሌና በአፋር ክልሎች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓቲዎች በትብብር ለመሥራት ያደረጉት ስምምነት በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚያግዝ አስተያየታቸውን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲዎቹ በስምምነት መሥራታቸው ቀጣዩ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተተካ በቀለ እንደሚናገሩት፤ በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ስምምነት የመዋሃድ ወይም ግንባር የመሆን አይደለም:: በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያግባቧቸው ሃሳቦች ላይ በትብብር ለመሥራት ያደረጉት ስምምነት ነው፡፡
ስምምነቱ ሰላምን በማይፈልጉ ኃይሎች በአማራ ህዝብ ላይ እየተደረጉ ያሉ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋምና ተቀራርቦ ለመሥራት እገዛ እንዳለውም አቶ ተተካ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ተተካ ገለጻ፤ ስምምነቱ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ህልውናቸውን ለማረጋገጥ ከሚያደርጉት ትግል በተጓዳኝ ስልጣን ለመያዝ ሲወዳደሩ በሰለጠነ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ መሰረት ይጥላል:: በአማራ ህዝብ ላይ የተደቀኑትን አደጋዎች በጋራ አቅም ለመከላከል እና የህዝቡን ህልውና ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡ በዚህ ደግሞ ክልሉ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል::
ስምምነቱ ክልሉን እና ህዝቡንም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የጠቀሱት አቶ ተተካ፤ ተመሳሳይ በሆኑ ጉዳዮች አብሮ ለመታገል እና በሚያለያዩ ጉዳዮች ደግሞ ተከባብሮ በክልሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ በር እንደሚከፍት ጠቅሰዋል:: የፓርቲዎቹ ተባብሮ መሥራት ዴሞክራያዊ መንገዶችን በመክፈት ጤናማ የሆነ የፉክክር መንፈስ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ከመንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት የአምስት ድርጅቶች ስምምነት ነው፡፡ ሁሉም ድርጅቶች በአጠቃላይ ልዩልዩ ሃሳቦች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በዋናነት በኦሮሚያ ውስጥ በጋራ እንዴት መሥራት እንደሚቻል፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ለውጥ ወደፊት ለማራመድ ምን መደረግ እንዳለበት እና የድርጅቶቹ ተሳትፎ በምን መልኩ መሆን እንደሚገባው፣ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ምን መሠራት አለበት በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል:: በአገሪቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲመጣ፣ ዴሞክራሲዊ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
እንደ አቶ ቶሌራ አባባል፤ ስምምነቱ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሥራዎቻቸውን እንዲካሄዱና በሚንቀሳቀሱበት ወቅትም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ድርጅት ዓላማውን ለህብረተሰቡ እንዲገልጽ በማድረግ በኩል መተጋገዝ እንዲኖር፣ አንዱ ድርጅት በሌላው ላይ አላስፈላጊ የሆኑና የሚያራርቁ ትችቶችና ርምጃዎችን ከማድረግ እንዲቆጠብ እና ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል እና በአፋር ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን በየክልሎቻቸው ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ በትብብር እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2012
መርድ ክፍሉ