አዲስ አበባ፡- በባህልና ጥበባት ዘርፍ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትና በዘርፉ ዘላቂነት ያለው ስራ ለማከናወን የባህልና ጥበባት ምክርቤት መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በባህልና ጥበባት ዘርፍ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ከትናንት በስቲያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል። በወቅቱ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የህግ ባለሙያው አቶ ፍቅረስላሴ ጌታቸው እንደተናገሩት፤ የምክር ቤቱ መቋቋም በዋናነት በባህልና ጥበባት ዘርፍ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ይረዳል። በተጨማሪም የጥበብ ባለሙያዎች በስራዎቻቸው ሊያገኟቸው የሚገቡትን ሞራላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማረጋገጥና ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ያስችላል።
እንደ አቶ ፍቅረስላሴ ገለጻ፤ ምክር ቤቱ የጥበባት ባለሙያዎች በተበታተነ ሁኔታ የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹበትና መንግስትም ለመደገፍ የሚቸገርበትን ሁኔታ ይቀይራል። በመሆኑም በተደራጀ መልኩ መንግስት ጥበቡን እንዲያግዝ እድል ይፈጥራል። በተመሳሳይ የጥበብ ስራዎች የመንግስትን የልማት ስራዎች እንዲደግፉ መንገድ ያመቻቻል።
«አሉታዊና መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከልና ሉላዊነት በሀገር በቀል ዕውቀትና ባህሎች ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ምክርቤቱን ከማቋቋም ውጪ አማራጭ የለም» የሚሉት ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባህልና ጥበባት ለማንነት ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የምክር ቤቱ መቋቋም አስፈላጊ ነው።
በተጨማሪም ባህላዊ ስርዓቶችን በማዳበር በማንኛውም የሃሣብና የአመለካከት ልዩነቶች ሠላማዊ በሆነ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲመቻች እድል ይሰጣል። በሌላ በኩል በባህል ልማት አደረጃጀቶች ውስጥ ያለውን ዝቅተኛ የህብረተሰብ ተሳትፎ ለማጠናከርና ህብረተሰቡ ያለውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። በየጊዜው የሚከሰቱ አዳዲስና ለልማት ጠቃሚ የሆኑ የባህል አስተሳሰቦች በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርጹ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የባህል ተመራማሪው አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ መቋቋም በባህል ፖሊሲና በፊልም ፖሊሲ የባህልና የጥበባት ምክር ቤት ለማቋቋም የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል። በባህል ዘርፉ የሚታዩትን ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታትና ዘላቂነት ያለው የባህል ልማትን ለማምጣት ጉልህ ሚና እንደሚኖረውና ባህልን ለሰላምና ለዴሞክራሲ ግንባታ ለማዋል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ በርካታ የሚጎሉ ነገሮች ቢኖሩትም በአሁኑ ወቅት መታሰቡም ቢሆን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተረድቶ ክፍተቶቹን በመሙላት ለተፈጻሚነቱ መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ሲቋቋም ከተለያዩ መስሪያቤቶች፣ ድርጅቶች፣ ማኀበራትና ልዩ ልዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አባላትን ይኖሩታል። ባህላቸውን የበለጠ የሚያውቁበት፣ ስለባህላቸው እድገትና ህልውና የሚወያዩበት፣ ስለ ጥበባት እድገት እና ተግዳሮቶች የሚመክሩበት ይሆናል ተብሎለታል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው