የበረታህ ዕለት አድናቂህም አድማቂህም ይበረክታል
አሻም!ጤና ይስጥልኝ ኢጆሌ ኢትዮጵያ እንደምን ከረማችሁ?እኔ ዋቃ ገለታ ይግባውና በጣም ደህና ነኝ። ዘንድሮ መቸም የኢትዮጵያ ሠርግ ነው። እጅግ ደስ ይላል። ለእኔ ደግሞ ድርብ ደስታ ነው። ምን ተገኘ ያላችሁ እንደሆነ አርባኛ ዓመቴን ባለፈው ግንቦት አክብሬያለሁ። ተመስገን ነው። ሐምሌ 22 ደግሞ የራሴን እና የኢትዮጵያን ሠርግ አንድ ላይ ደግሻለሁ። በአርባኛው ዓመቴ አርባ ችግኞችን በመትከል በደማቅ ሁኔታ አክብሬው አልፌያለሁ።
ኢትዮጵያዬ ዘንድሮ እንደ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ የፅናት ጉዞዋን በደማቅ አሻራ ለመፃፍ አንድ ብላ ተነስታለች። እቺ የነገ ተስፋ የሆነችው አዲሲቷ ምድር የዓለምን በሽታ ለመፈወስ መቀነቷን ጠበቅ አድርጋለች። ምድራችን በሰው ሠራሽ የመከራ መዓት በከፋ ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ፍቱን መድኃኒት ይዛ ብቅ ብላለች። ችግኝ። የችግሮቻችን ሁሉ ማስወገጃ የሆነውን ችግኝ።
ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በዘንድሮው ክረምት እስከ አራት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዛቸውን ስንሰማ ብዙዎቻችን የተዋጠልን አልነበረም። ስንት የሚወራበት አጀንዳ በሞላበት እርሳቸው ስለ ተክል ማውራታቸው መንግሥትነትን እንዳሳነሱ አድርገን የቆጠርን ሰዎች ጥቂት አልነበርንም። ዛፍ መትከልን፣ አፈር መነካካትን የአርሶ አደር ወይም የገጠር ሰዎች ሥራ ብቻ አድርገን ለምንወስድ ዜጎች ጠቅላያችን ምነው ተራ ነገር ላይ አተኮሩ ብለን ስናጉተመትም የነበርን በርካቶች ነን። እኛን አልገባንም። ሰውየው በጣም ታይቷቸዋል፤ ቀድሞም ገብቷቸዋል። የችግሮቻችን ሁሉ መነሻና መድረሻም ከተፈጥሮ ጋር መጣላታችን ነውና።
ምድራችን ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ በሚያሻት ወሳኝ ወቅት ውስጥ እንደምንገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያችን ያሳደናችው የሐምሌ 22ቱ የአረንጓዴ አሻራ ድግስ የዓለም ሐገራትን ያነጋገረ ክስተት መሆኑ በቂ ማስረጃ ነው። በድርቅ እና በርሃብ ስሟ በአያሌው የሚነሳውን የሀገሬን ገፅታ የቀየረ ደማቅ አሻራ የተጣለበት ዕለት፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ህዝቡ ስለ ፍቅር ጥሪ ይሁንታውን ሰጥቶ ለመሪው የተንበረከከበት ዕለት።
በግሌ ከዚህ ቀደም የችግኝ ተከላ ክብረወሰን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለመኖሩ ምንም መረጃ አልነበረኝም። የተባበረ የህዝቦች ክንድ ከራስም አልፎ የዓለምን ታሪክ የሚቀይር ታላቅ ገድል እንደሚሠራ እና የአዲስ ክብረወሰን ባለቤትም መሆን እንደሚቻል ያረጋገጠልኝ ክስተት ነበር ዕለቱ። እንኳንስ ሰው ውሻ የምንለው የቤት እንስሳ ሳይቀር የተሳተፈበት የምድራችን ታላቁ ድግስ ብንለው የማያንስበት ቀን በሀገሬ ፊትአውራሪነት እና በልጆቿ ጀግንነት ለተፈጥሮ የተከፈለ ውለታ መሆኑ ኢትዮጵያዊነቴን እጅግ አድርጌ እንድወደው እና የላቀ ኩራት እንዲሰማኝ ያደረገ ዳግም የተወለድኩበት ዕለት ነው።
በዋዜማው ከፍተኛ ጉጉት የነበረኝ እንደመሆኑ መጠን በዕለቱ ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ላይ ከእንቅልፌ ስነቃ ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ ነበር። ከእንቅልፋምነቴ ጋር ተዳምሮ ይጫጫነኝ ጀመር። በቃ ይሄ ነገር ላይሳካ ነው አልኩኝ በልቤ። አሁን ማነው በዚህ ዝናብ ያውም በማለዳ ወጥቶ የሚተክል አልኩኝ። ማታ አብረን ለመትከል ከተቀጣጠርን ጓደኞቼ ጋር ለመነጋገር ብደውል አያነሱም። ተስፋ እንደመቁረጥ አደረገኝ። ብዙም ሳይቆይ የእጅ ስልኬ ጮኸ። አንዱ ጓደኛዬ ነበር። “አልተነሳህም እንዴ” አለኝ ጮክ ባለ ድምፅ። “ኧረ ተነስቻለሁ” አልኩት ቀድሜ መንቃቴን ለማረጋገጥ። አንተስ ስለው “ሳር ቤት ደርሻለው” አለኝ በኩራት ወደ ተዘጋጀው መትከያ ሥፍራ እየሄደ እንዳለ አረጋገጠልኝ።
እኔ ጠፋሁ ኢትዮጵያዬ! ብዬ ለዕለቱ ያዘጋጀሁትን የደንብ ልብስ ለብሼ መኪናዬን አስነሳሁና ወደዚያው አቀናሁ። ስደርስ ገበያው ደርቷል። የሰው ሞራል እጅግ ይገርማል። ከእያንዳንዳንዱ ሰው ፊት የኃይሌ ገብረሥላሴ የ “ይቻላል” መንፈስ ደምቆ ይነበባል። ዝናብ እና ብርድ እያሉ እንደሌሉ የተሸማቀቁበት ዕለት ቢኖር ያን ዕለት ነው። ሁሉም ይሯሯጣል። የሰው እጅ አካፋ እና ዶማ የሆነበት ዕለት ነው ሐምሌ 22። ወደ ቤት ስመለስም ቀደም ሲል እንደነገርኳችሁ ባለቤቴ የተወለድኩበትን ቀን ከዚሁ ዕለት ጋር ልታከብርልኝ አስባ ነበር እና ቀደም ብዬ ባዘጋጀሁት ሠላሳ ጉድጓድ ላይ አሥር ጨምራ አርባ እንዲሞላ አድርጋ ጠበቀችኝ። አንድም የልደቴ ቀን ነው ወዲያ ደግሞ እምዬ ኢትዮጵያ የምትሞሸርበት ዕለት ነው። ሰርፕራይዝ ይሉሃል ይሄ ነው።
እንግዲህ በዚህ መልኩ ከነፍሰጡሯ ባለቤቴ እና ከልጄ ጋር ሁነን ወደ ምዕራፍ ሁለት ተከላ ገባን። በነገራችን ላይ ዘጠነኛ ወሯን ይዛለች፤ አላህ ካለ ከሰሞኑ አንድ ቄሮ ወይም ቀሬ ዱብ ታደርጋለች እና ጠብቁ። በፀሎታችሁ አደራ እንግዲህ አትርሱኝ። በአርባኛው የልደት በዓሌ የተከልናቸው አርባ ችግኞች ከብሔራዊው ጋር ቢደመሩ ደግሞ ሌላ ድል ነው ብለን ጓጓን። አርባ ፍሬ መሆኗን አትዩ። ዋናው ዓላማ ነውና፤ ህልማችን ዘመን ተሻጋሪ ነውና።
ሐምሌ ሃያ ሁለት ካበሰረልን ድንቅ እሴት አንዱ ህብረብሔራዊነታችንን ያጠናከርንበት እና ለአንድ ቀንም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራችንን ከየአቅጣጫው እየናጣት የሚገኘውን የዘረኝነት ወረርሽኝ ያስታገሰልን ህመም መስበሪያ ወይም “ፔይን ኪለር” መሆኑ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከክልል አልፎ ተርፎም ከሀገርኛ ሳጥን ወጥቶ እንደ ሰው ያሰብንበት የቀናት ሁሉ አንጋፋ ቀን ነው ሐምሌ ሃያ ሁለት። ሌላው ደግሞ የኢትዮጵያን የበኩር ልጅ ኦሮሚያን የሰጠንን አምላክ ዳግም የምናመሰግንበት ዕለት መሆኑ ነው። ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ክልሎች ኦሮሚያ በመርሐግብሩ የአንበሳው ድርሻ እንደነበረው አይተናል።
ልክ በአትሌቲክሱ፣ በጦር ሜዳ ገድሉ፣ በአቃፊነቱ ወዘተ የአንጋፋነት ሚናውን ሲወጣ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል በዚህኛው የአረንጓዴ አሻራ ድግስም የሀገር አለኝታነቱን አስመስክሯል። እንደሀገር በኦሮሚያ ደረጃ የሚሠራው ማንኛውም ሥራ የሀገር ግንባታ መሠረት መሆኑን ያረጋገጠ ክልል ነው። በአጠቃላይ ከተተከሉት 350 ሚሊዮን ችግኞች ከስድሳ በመቶ በላይ የሚሆነውን የሸፈነው ይኸው ክልል ነው። የአማራ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልሎች በሁለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ይህንን እንደ መነሻ ከወሰድን ለሀገር ህልውና በዋና ዋናዎቹ ክልሎች ላይ አተኩረን መሥራት እጅግ ውጤታማ ያደርገናል።
በመግቢያዬ ላይ ስለ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጠቀስ ያደረኩትን አሁንም ልድገመው። የተስፋይቱን ምድር ህልም የማሳካት ጉዞ ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም። ጅማሮው ግን የስኬት እንደሆነ ከወዲሁ ያመላክታል። ኃይሌ በሩጫ ህይወቱ 27 ክብረወሰኖችን ሰብሯል። በዚህ በማያቋርጥ የስኬት ሂደት ለአፍታም ሳይዘናጋ ሌት ተቀን ከፍተኛ ትግል ማድረጉ ለዚህ እንዳበቃው ነግሮናል። ኢትዮጵያ ከዚህ ውድ ልጇ አሁን መማር ያለባት ይመስለኛል። ትናንት ያስመዘገብነው ድል በሌሎች ክብረወሰኖችም መታጀብ አለበት።
ከዚያ በፊት ይህኛውን ድል እራሱ በአግባቡ መጠበቅ ቀዳሚው የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል። ጠቅላይ ሚኒስትራችን በምስጋና መልዕክታቸው እንዳስቀመጡት ወልዶ ማሳደግን የሚያውቅበት ህዝባችን ችግኙንም እንደ ልጁ ተንከባክቦ እና አሳድጎ ለቀጣይ የክብረወሰን ድል ማብቃት አደራ የሚባል ነጥብ ነው።
ገለቶማ! የሳምንት ሰው ይበለን
አረንጓዴ ሁንልኝ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት29/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ