«በባህላዊ የእርቅ ስርዓት የኦሮሞ ማህበረሰብ የገዳ ስርዓት ታዋቂ ነው፡፡ በአማራ ማህበረሰብ ሽምግልና፣ ዘመድ ዳኛ፣ ቅቤ፣ አባጋራ፣ ደም አዳራቂ፣ አውጫጪኝ የሚባሉት ደግሞ ተጠቃሽ ናቸው። እንዲሁም በአፋር ህዝብ ደግሞ መንድሃንን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች ግጭት እንዳይከሰት ቀድመው የሚከላከሉና ግጭት ከተከሰተ በኋላም የማህበረሰብን ሰላም፣ አብሮነትና መቻቻል ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡» ይላሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ጋሻው አይፈራም።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት መፍቻና የእርቅ መፈጸሚያ ስርዓቶችና ዘዴዎች አሉ፡፡ ባህላዊ የሚባሉት በልማዳዊ ህገ ደንብ ከማህበረሰቡ በመነጩ በህዝቡ በጎ ፍቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ፤ህዝቡ በወግና በልማድ የሚገለገልበት ስርዓት ወይም ህገ ደንብ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ደግሞ በሃይማኖት ህገ ደንብ መሰረት በሃይማኖት አባቶች የሚደረግ የግጭት አፈታት ስርዓት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ቤተ እምነቶች የእርቅና የሰላም እሴቶች ጎልተው የሚታዩባቸው ብዙ ሥራዎች ለዘመናት ሲሠሩ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
እርቅ ጸብን በሰላም፣ጥላቻን በፍቅር፣አለመግባባትን በስምምነት፣ጥርጣሬን በመተማመን፣የተራራቁትን በማቀራረብ፣ ኩርፊያንና ግጭትን አቀራርቦ በማነጋገር የሚፈታበት ሂደት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ፍትህና ርትዕ ከእግዚአብሄር ነው፡፡ በእርቅ ውስጥ በደልን ይቅር ማለት አለ፡፡ እርቅ ሲባል የበደለው የሚክስበት፣ በደለኛው የሚካስበት ሁለቱ ወገኖች ደግሞ ከእርቁ በፊት የነበረውን ግጭት ረስተው ይቅር የሚባባሉበት ህይወት ማለት ነው፡፡
እርቅ ሲባል በደልን መተው፣ መርሳት ነው፡፡ ወደ ስምምነትና ወደ አንድነት መግባት ማለት ነው። በሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እርቅ የሚፈጸምባቸው ብዙ ስርዓቶች መኖራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡ በምሳሌነት ያነሱት ‹‹ይቅር በል እርሳው›› ከሚሉት የደቡብ አፍሪካዎች መርህ ትምህርት መውሰድ ይገባል ይላሉ ቀሲስ ሳሙኤል፡፡ እንደ ቀሲስ ሳሙኤል ማብራሪያ ህግ ተገቢ ነው፡፡ በህግ ውስጥ ፍትህ መስጠት ይገባል፤ የእርቅና የሰላም ጉዳይ አብሮ መተግበር አለ በት፡አጥፊም መቀጣት ይኖርበታል፡፡ ዳኝነት መኖር አለበት፡፡ በፍትህ ውስጥ ደግሞ ይቅርታ ያስፈልጋል፡፡ ፍትህ አጥፊን ጥፋተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።
ይቅርታ ደግሞ ስለበደሉ የሚቀርብ ስጦታ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች ከተነጣጠሉ እንደ አገር ለመቀጠል ያስቸግራል፡፡ በፍትህ ውስጥ ሰዎች ይቅርታ ማግኘት አለባ ቸው፡፡ የፍትህ ስርዓቱ እርቅን የማስፈን ሥራንም በጥምረት መሥራት ይኖርበታል፡፡
አቶ ጋሻው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመቻቻል ተምሳሌ ነው። ይህ የሆነው በህብረተሰብ መካ ከል ግጭትን የሚፈታ፣ ግጭት እንዳይከሰት የሚያ ደርግ የራሳቸው ዘዴ ህገ ደንብ ስለነበራቸው ነው፡፡ መደበኛ የፍትህ ስርዓት እስከአሁን ተደራሽ አይደለም፡፡ የራሱ የሆነ ህጸፆችም አሉበት፡፡ ስለዚህ ህዝቡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚገጥመውን አለመግባባት የሚፈታው በራሱ መንገድ ነው፡ይሄም አንድም ባህላዊ ሌላው በሃይማኖታዊ የእርቅና የግጭት መፍቻ ዘዴ ነው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የእርቅና የግጭት መፍቻ በህዝብ ቅቡልነት አለው፡፡
እርቅ የሚፈጸመው በማስገደድ አይደለም፡፡ እንደ መደበኛ የፍትህ ስርዓት በፖሊስ ተይዞም የሚዳኝበት አይደለም፡፡ እርቅ ፈጻሚዎች ወደ ስርዓቱ የሚገቡት አካባቢው ላይ ባሉ እርቅ በሚፈጽሙ አካላት ተጠይቀው ለማህበረሰቡ ሰላም እርቅ ማስፈለጉን አምነውበት ነው፡፡ ለማህበረተሰቡም ይገዛሉ። ይሄ የራሱ የሆኑ መሰረታዊ መርሆዎች አሉት። በውጤት ስንመለከተው ከመደበኛ የፍትህ ስነ- ስርዓት አኳያ የተሻለ ነው፡፡ የመደበኛ የፍትህ ስርዓት አንድ ነገር ከተፈጸመ በኋላ የማህበረሰብ ሰላም ላይመልስ ይችላል፡፡ በቀልም እስከመጨረሻው አይደርቅም። ባህላዊና ሃይማኖታዊ የእርቅ ስርዓቶች ግን ማህበረሰቡ ወደ ነበረበት ሰላም እንዲመለስ፣ መተማመን እንዲኖራቸው፣ ቂም በቀል ከምንጩ እንዲደርቅ፣ አብሮነታቸው እንዲጎለብት ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ አቶ ጋሻው ይናገራሉ፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓት ሲከናወን በግጭት ተዋንያን፣ በጎሳዎች ወይም በብሄር መካከል ፍጹም እርቅ ይከናወናል፡፡
ከአካባቢ አካባቢ ቢለያይም እርቅ ሲከናወን ለምለም ሳር ወይም ቄጤማ ይያዛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ተስፋ፣ ልምላሜ፣ ሰላማዊ መስተጋብርና አብሮነት እንደሚመለስ ተስፋ ማድረግን ነው፡፡ በብዙዎቹ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ላይ ያለውን ስንመለከት እንስሳ ታርዶ ሁለቱ የግጭት ተዋንያን አካላት ደም ነክተው እንዲጨባበጡ ይደረጋል፡ ፡ ይህ ትግበራ የግጭት ተዋንያን አካላት ሁለተኛ በደም እንዳይፈላለጉ ቃል ኪዳን የሚገቡበት ነው፡ ግጭቱ ዳግመኛ እንዳይነሳ የራሳቸው ህገ ደንብ ነው፡፡ ከመደበኛ የፍትህ ስርዓት አንጻር ግጭት በመፍታት፣ ከስሩ እንዲደርቅ፣ የማህበረሰቡ ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ በማድረግ የተሻለ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ይሄ በመደበኛው የፍ ትህ ስርዓት አይደረግም፡፡ ሞት፣ ዘረፋ ወይንም ሌላ ግጭት ከተፈጸመ ህግ በዳይ ላይ ይወስናል፡ ተበዳይም ቂም ስለሚይዝ ያንን የሚመልስበትን መንገድ ነው የሚያስበው፡፡
በመሆኑም ግጭቱ ላይቆም ይችላል፡፡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት መፍቻ መንገድ ወጪ፣ጉልበትና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑም ሌላው ጠቀሜታ አለው፡፡ ፍርድ ቤት መመላለስ ብዙ እንግልት አለው፡፡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመቋጨት ከሁለት ዓመት በላይ ሊፈጅ ይችላል፡፡ እርቅም አይከናወንም፡፡ በባህላዊ ወይም ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ከሆነ ግን ማህበረሰቡ የተቀበላቸው በቅርበት ያሉ አስታ ራቂዎች እርቁን በማግስቱ ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች ውስጥ በዋናነት ሦስት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ሁሉ እውነትና ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ሁለተኛ ምህረት የማውረድና እርቅ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ በሶስተኛነት ደግሞ እውነት ከተረጋገጠ በኋላ ተበዳዩ ምህረት ያደርጋል፤ከዛ እርቅ ይፈጸማል፡፡ በዚህ ጊዜ እርቅ እንዲሁ አይፈጸምም፡፡ በበዳይና ተበዳይ በኩል ያሉ ቤተሰቦች፣ጎሳ ወይንም ብሄር ብሄረሰቦች ተሰብስበው ማዕድ ይቆርሳሉ፡፡
እህል ውሃ ይቀርብላቸውና አብረው ይቃመሳሉ። ከዚህ በኋላ ወደ ነበሩበት መስተጋብር ተመለሱ ማለት ነው፡፡ በመደበኛው የፍትህ ስርዓት ግን እንዲህ ዓይነቱ አይታይም፡፡ ቀሲስ ሳሙኤል እንደሚሉትም፤ የእርቅ የመጨረሻ ግብ በማህበረሰቡ ውስጥ ፍቅርን ማስፈን ነው፡፡ ፍቅር በማህበረሰብ መካከል መተማመንና መተሳሰርን ይፈጥራል፡፡ በእርቅ ውስጥ ፍቅር ሲያሸንፍ መግባባት ይኖራል፡፡ ፍቅር ሲኖር መቻቻል ይሰምራል፡፡ ከይቅርታ በኋላ ፍቅር ሲጸና ችግሮች ቢነሱ እንኳን እንደቀድም አይጠነክርም፡፡
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አስፈሪ ችግሮች እየተነሱ ነው፡፡ እርቅና የፍትህ ስርዓትን ጎን ለጎን በማስኬድ እነዚህን ችግሮች መፍታት ይቻላል። እርቅና ሰላምን ማምጣት የሚቻለው በፖለቲካ ብቻ አይደለም፡፡ ለመፍትሄው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች መሥራት ይገባቸዋል። መደመጥም አለባቸው፡፡ በዕድሜ የበለጸገን ሰው ማክበር ያስፈልጋል፡፡ ለእርቅና ለሰላም ራስን ማዘጋጀትም ከወጣቱ ይጠበቃል፡፡ አቶ ጋሻው፤ በአሁኑ ወቅት ባህላዊና ሃይማኖታዊ አገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች በአገር አቀፍ አተገባበራቸው አናሳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መንግሥት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭት ሲፈጠር አለመግባባቱ መፈታት ያለበት በአገር ሽማግሌዎች ወይም በሃይማኖት አባቶች እንዲሆን በማሰብ እንዲሳተፍ ያደርጋል፡፡ ችግር ከሌለ ግን ብዙም ሲፈለጉ አይታይም፡፡ ከዚህ አንጻር ውስንነቶች አሉ፡፡
የተለያዩ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው በተለያዩ አካባቢዎች ንብረት ሲወድምና ሰው ሲፈናቀሉ ይታያል፡፡ ይሄ ያለንን የግጭት መፍቻ በአግባቡ እንዳልተጠቀምንበት ያሳያል፡፡ ባግባቡ ብንጠቀምበት ኖሮ አሁን በተለ ያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን መቀነስና ማስተካከል ይቻል ነበር፡፡ መንግሥት እውቅና ከመስጠት፣ የህግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አሠራር እንዲ ኖራቸው በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለበትም ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ፡፡ በዚህ ውስጥ የሚያለያዩ እና አንድ የሚያደርጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ አንድ የሚያደርጉንን መልካም እሴቶች በማንሳት መግባባት መፍጠር እና የእርቅ ስርዓቶቹን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ የግጭት መፍቻና የእርቅ ማስፈጸሚያ ስርዓቶችና ዘዴዎችን በመጠቀም እርቀ ሰላም እንዲመጣ መሠራት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተለያየ መልክ ያላቸው ግጭቶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ግጭቶች ይፈታሉ ብዬ የማምነው አንድም በአገር በቀል የባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ነው፡፡ ሌላው በመደበኛ የፍትህ ስርዓት ነው፡፡ አብዛኞቹ ግጭቶች በአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎች የሚፈቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ስርዓቶች ህዝብ የሚቀበላቸው ናቸው፡፡
ይህ እንዲሰምር ግን መንግሥት የራሱን ሚና መወጣት አለበት ይላሉ አቶ ጋሻው፡፡ በይቅርታ ወይም በእርቅ ጊዜ ከሁለቱ የግጭት ተዋንያን አካላት በተውጣጡና ያለማንም ጣልቃ ገብነት ግጭቱ ቢፈታ ወደ ሰላም የሚቀየርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በሁለት አካላት መካከል የተከሰተ ግጭት ሆኖ ከመንግሥት አቅም በላይ ሲሆን፤ ከሁለቱም አካላት የተውጣጡ ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን ወይም አባገዳዎችን በማሳተፍ ግጭቱን እንዲፈቱ እውቅና በመስጠትና አስፈላጊ በሆነ መንገድ በመደገፍ ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጎን ለጎን እንዲሠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ፡፡
ቀሲስ ሳሙኤል እንደሚሉትም፤ በመንግሥት በኩል እየታዩ ያሉ የፍቅር፣ የመደመር፣ የአንድነት ሃሳቦች ጠቃሚ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ ይቅርታን ከፍ በማድረግ ቁርሾን በመተው ህዝቦች በኢትዮጵያ ተስማምተው እንዲኖሩ፣ ግጭትን ከሚያራግቡ ጉዳዮች እንዲቆጠቡ ማድረግ ይገባል።
የመን፣ ደቡብ ሱዳን ሶሪያ ከግጭት ያተረፉት ውጤት ቢኖር ስደት፣ እልቂት፣ ውድመት፣ ክብርና አገር አልባ መሆን ነው።ይቅር በመባባል ተግባብቶና ተቻችሎ መኖር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ወጣቱ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መተማመን እንዲፈጠር መስራት አለበት፡፡ ሰላማዊ የማህበረሰብ መስተጋብር በዘላቂነት መፍጠር የሚቻለው ማህበረሰቡ ሲሳተፍበት ነው፡፡ መንግሥት የሚያመጣቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች ግጭቱን ለጊዜው ሊያበርደው ይችል እንደሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይችላል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ በመሆኑም ሃይማኖታዊና ባህላዊ የግጭት መፍቻና የእርቅ መፈጸሚያ ተቋ ማት አቅማቸው እንዲጎለብት ሁሉም አካላት መሥራት አለበት መልዕክታቸው ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2011
ዘላለም ግዛው