ሳይንስ የዘመንን ገጽታ ይለውጣል። ያረጀን ዘመን በአዲስ ይተካል:: ሳይንስ መንገድ ነው፤ እሩቅ ይወስዳል:: የራቀን ያቀርባል:: መገልገያ ቁሳቁስን እያደሰ ቀድሞ የተፈጠረውን በዛሬ፤ የዛሬውን ደግሞ በነገ እየለወጠ በአጠቃቀምና ባያያዝ ቀለል፤ ምቹና ከፍ እያደረገ ሄዷል::
ብራና በወረቀት መተካቱ ሳይንስ ያሰገኘው ለውጥ ነበር:: ጊዜን በጊዜ ሲተካ፤ ወቅት በሌላኛው ሲለወጥ ሳይንስም ይሄን ግኝቱን ወደ ሌላ ከፍ ያለ ውጤት አሸጋገረው:: ትናንት የፍየል ቆዳ ፀጉሩን አርግፎ በብራና ፈጠራው የተደነቀው ትውልድ ዕድገት አልፏል::
የዛሬ ትውልድ ደግሞ ብራናን በተካ የወረቀት ምርት ተጠቅሞ ሳያበቃ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነውና ሌላ አማራጭ ቀርቦለታል:: ኧረ እንዲያውም ወረቀቱን ወርውሮ ያለእስክሪብቶ መጻፍ የሚችልበት፤ ወረቀት ሳያንኮሻኩሽ የሚያነብበት አማራጭ ቀርቦለታል:: ዛሬ ወረቀት መጠቀም ግድ ካልሆነ በስተቀር በመቅረት ላይ ይገኛል:: ዓለም ወረቀትን በመራቅ ትኩረቱን በዲጅታል መሣሪያዎች ላይ አድርጓል::
መረጃን በፖስታ ከመለዋወጫ ዘመን በየትኛውም ያህል ርቀት ላይ ለሚገኝ ሰው በተለያዩ ዘዴዎች በሰከንድ ውስጥ መልዕክት ማድረስ ወደሚቻልበት፤ ኮምፒዩተርን ብቻ በመጠቀም መረጃ እንደፈለጉ በአስገራሚ ፍጥነት መለዋወጥ የሚቻልበት ዘመን ላይ እንገኛለን::
ይህ ቴክኖሎጂ እንደበረከቱ ሁሉ በጥንቃቄ ካልተያዘ የሚያስከትለው ግለሰባዊ፤ ሰፍቶም አገራዊ ክስረቱ ለመተመን የሚከብድ ስለመሆኑ ይነገራል:: የመረጃ ማሳለጫ በልዩ ልዩ ዘዴ ተቆራኝቶ ጥቅሙ የጎላው የመረብ ዝረጋታ አንዱን ከሌላው አስተሳስሮ መረጃ ለመቀባበልና አስፈላጊ የሆኑ የግንኙነት ተግባራት ለመከወን እንደቀለለ ሁሉ፤ በዘርፉ ተመሳስለውና ጭንብል አጥልቀው መረጃ የሚመነትፉ ወገኖች መምጣታቸው፤ የሀገርን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ሥጋት አብሮ መፈጠሩ አልቀረም::
የቴክኖሎጂው አበርክቶ የላቀውን ያህል ያለጥንቃቄ ከተተገበረ የግለሰቦችና የተቋማት መለያ የሆነውን የሚስጥር ቁጥር ሰብሮ በመግባት ሀብቶቻቸውን የሚመዘብሩ የሰይበር ቀማኞች ተበራክተዋል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቴክኖሎጂው ጋር እራሳቸውን በመቀያየርና በቁጥር በማበራከት በረቀቀ የወንጀል መፈፀሚያ መንገድ አንድ ቦታ ሆነው በዓለም ላይ ያለን የራሳቸው ያልሆነ ሀብት ይመዘብራሉ፤ መረጃዎችን ጠልፈው ላልተገባ አገልግሎት ወይም ለራሳቸው ግልጋሎት ያውላሉ::
ባለፈው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራት የመረጃ መረብ በመበጣጠስ አንዱ የሌላውን ሚስጥር ለመፈልፈል የሚያደርገውን ትግል ማሳያ በመሆን ሰሜን ኮሪያ ከታላቋ አሜሪካ ጋር የተፋጠጠችበት ሁኔት አይዘነጋም:: ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢሜልና መሰል መረጃዎች ስትበረብር አሜሪካ ምላሽ በሚሆን መልክ የሰሜን ኮሪያን የሚስጥር ቁልፎች በመሰባበር ያሻትን መረጃ ስትቃርም ዓለም ጆሮውን አቅንቶ ሰምቷቸዋል::
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው የሳይበር ምንተፋ ይፋዊ መነጣጠቅ ያለዳኛ ጋብ ያለው ለሁለቱም አዋጪ መስሎ ባለመታየቱ ቢሆንም፤ ባላንጣነታቸው ረገብ ብሎም ቢሆን መቀጠሉ በስውር እያደረጉ ያሉትን አንዱ በሌላኛው ላይ የሳይበር ጥቃት የመፈፀም ተግባር ማቆማቸው ላይ ግን አሁንም ጥርጣሬ ይፈጥራል::
ሳይበር በአግባቡ ካልተመራና ለጥቃት ከተዳረገ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በወጉ የተረዱ አገራት የሳይበርን ጥቃት ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች ማድረጋቸው አልቀረም:: በተለያዩ የዓለም ክፍለ አህጉራት ከሳይበር ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙትን ትላልቅ ወንጀሎች ለመከላከል ጥረት ቢደረግም፤ ሙሉ በሙሉ ማስቆም ግን ከባድ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል:: ከወንጀሉ ውስብስብነት አንፃርና የሳይበር ጥቃት ፈፃሚዎቹ ከሚከተሉት አዳዲስ የጥቃት መፈፀሚያ ስልት አንፃር ቁጥጥሩንና መከላከሉን ከባድ እንዳደረገው ይነገራል::
የግለሰቦችን፤ የተቋማትንና የአገራት ሥራ በማስተጓጎል ከፍተኛ ውድመት የሚያስከትለውን የሳይበተር ምንተፋ በዘመናዊው ዓለም ለመከላከል የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ብቻ ነው። እንዲህ ከሆነ ጉዳቱን ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች በመፍትሔነት የሚጠቁሙት ጉዳይ ነው::
ይህንን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል እንደ ሀገር ኢትዮጵያም ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች:: የሳይበርን ጥቃት ለመከላከል ብቁ የሆነ ተቋማዊ አመለካከት የተላበሰና ሙያዊ ብቃት ያለው የሰው ሀብት ማፍራት ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ:: በመሆኑም፤ ጠንካራ የሳይበር ጥቃት መከላከያ መንገድ ለመወጠን የሰለጠነ የሰው ሀብት ወሳኝ መሆኑ ነው:: በዚህ ረገድ ገና በጅምር ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በመሥራት ላይ ትገኛለች::
ሳይበር የጠቀሜታውን ያህል የጥቃቱ አሳሳቢነትም ከፍ እያለ የመጣው ይህ ዘርፍ ትኩረት ያሻዋልና ሰሞኑን በሀገር ደረጃ ለመጀመሪያ ጌዜ በመከበር ላይ ይገኛል:: በዓለም ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው ይህ የሳይበር ደህንነት ሳምንት ለማህበረሰቡ ስለሳይበር ጥቃት እና መከላከያ ዘዴዎቹ ግንዛቤ ማስጨበጫ ልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸው ተገልጿል::
ይህ “ትኩረት ለሳይበር ደህንነት” በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ዓለም አቀፋፋዊ /ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት በኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከትላንት በስቲያ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል:: ኤጀንሲው የሳይበር ጥቃትን ከመከላከልና የተለየዩ ግንዛቤዎችን የመፍጠር ሥራዎች ከመሥራት ባሻገር መሰል መድረኮች ማዘጋጀቱ ስለ ሳይበር ያለን እሳቤ ለማሳደግ ትልቅ አጋጣሚ ይፈጥራል:: የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤፍራህ አሊ፤ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫውን ሳምንት ለማክበር የታሰበበት ዋንኛ አላማ በሳይበር ደህንነት ላይ ያለውን ንቃተ-ህሊና ለማሳደግ እንደሆነ ያስረዳሉ::
በሀገሪቱ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደ ጌዜ መጠኑ እየጨመረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ለሳይበር ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ እራሱንና ተቋሙን ከሳይበር ጥቃት ሊከላከል እንደሚገባውም ተጠቁሟል። ይህም የችግሩን አሳሳቢነት እና ሊወሰድ የሚገባውንም መፍትሄ ያመላክታል::
ዶ/ር ሰለሞን ጓዴ የኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ጥናት ዲቪዥን ኃላፊ በበኩላቸው፤ በዓለማችን ካሉ አሳሳቢ ጥቃቶች ውስጥ የሳይበር ጥቃት 5ኛውን ደረጃ እንደያዘ ይናገራሉ:: ይህም የሳይበር ጥቃት ምን ያህል ስፋት እንዳለው ማመላከቻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
ዶ/ር ሰለሞን በሳይበር ጥቃት ረገድ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ሲዘረዝሩ፤ በዘርፉ ብዙ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅባት ያመላክታሉ:: በሳይበር ዘርፍ ካሉና ዋና ዋና ተግዳሮቶች ተብለው ከሚጠቀሱ ማሳያዎች ውስጥ የልማት ሥራዎች የሳይበርን ደህንነትን ታሳቢ ያላደረጉ መሆናቸው፤ ተቋማት ዓለም አቀፍ የሳይበር ደህንነት ደረጃዎችን አለማሟላታቸው፤ የመንግሥትና የግል ተቋማት ለሳይበር ደህንነት ማስጠበቂያ የሚሆን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሌላቸው መሆኑ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳይበር ደህንነት ላይ ማስተማር የሚችሉ ሙያተኞች እጥረት ያለባቸውና የበጀት ውስንነት እንደሀገር የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው::
በሳይበር ጥቃት የሚከሰተውን ሀገራዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም ይቻል ዘንድ ጥቃቱን የሚመጥን አቅም መገንባት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። በተለይም ከቴክኖሎጂ ጋር መራመድ የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ዋነኛ ጉዳይ ሊሆን ይገባል መልዕክታችን ነው:: ቸር ያቆየን !
አዲስ ዘመን ጥቅምት28/2012
ተገኝ ብሩ