በኢትየጵያ ውስጥ የከርሰ ምድርን ውሃ ሳይጨምር 123 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ ሀብትና ከ36 ሚሊየን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ጥናቶች ያመላክታሉ:: እነዚሁ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በሰብል የለማው የአገሪቱ መሬት ግን 16 ሚሊየን ሄክታር ገደማ ብቻ ነው:: ከዚህ ውስጥም በመስኖ የለማው መሬት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊየን ሄክታር ያህል ነው::
በኢትየጵያ ስንዴ ከጤፍ፣ ከበቆሎና ከማሽላ ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ የሚመረት የሰብል አይነት ነው:: በስንዴ ምርት የሚለማው መሬትም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሄክታር ይጠጋል:: ከዚህም የሚገኘው የስንዴ ምርት አምስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፤ ብሔራዊ የስንዴ ልማት ምርት መጠኑም በሄክታር 27 ኩንታል ነው:: ይህ አገሪቱን በአፍሪካ በስንዴ ምርት ልማት በሦስተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ ያስቻላት መሆኑን የኢትየጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል:: ይህም ሁሉ ሆኖ ግን፤ ኢትየጵያ እስካሁን ድረስ ለዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ተገዳለች::
በዚህም የፍጆታዋን 25 በመቶ ከውጭ የምታስገባ ሲሆን፤ ለዚህም በአማካይ እስከ 600 ሚሊየን ዶላር እንደምትከፍል መረጃዎች ያሳያሉ:: ኢትየጵያ ስንዴ ለማምረት የሚያችል በቂ መሬት፤ ለም አፈር፤ ውሃ፤ አምራች ኃይልና ሌሎችም ለግብርና ልማት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችና ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶች ቢኖሯትም፤ የግዥ ስንዴ ለማስገባት የምታወጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሯል:: ይህን ቁጭት ለመወጣት ባለው ተነሳሽነትም መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና ለመካከለኛና ለከፍተኛ መስኖ ሥራ 20 ቢሊየን ብር በመመደብ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይሁን እንጂ፤ 43 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የእርሻ መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ በመሆኑ፤ ከዘርፉ መገኘት የሚገባው የምርት መጠን እንዳይገኝ እንቅፋት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በኢትየጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ከጎዛመን እና ከአነደድ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር የአርሶ አደሮች የመስክ ጉብኝት በዓል ተዘጋጅቷል:: ከጉብኝቱ በኋላ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ የደብረ ማርቆስ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ያለው ማዘንጊያ እንደተናገሩት፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን በአጠቃላይ 127 ሺ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የሚሸፈን ሲሆን፤ ከዚህም ሦስት ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የዞኑ መሬት የአሲዳማነት መጠን ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ በአሲድ የተጠቃ በመሆኑ የሚገኝው ምርት ግን በሄክታር 25 ኩንታል ስንዴ ብቻ ነው።
የአገሪቱ ብሔራዊ የስንዴ ልማት ምርት መጠን በሄክታር 27 ኩንታል መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ከዞኑ ምርታማነት ጋር ሲነፃፀር በሁለት ኩንታል ብልጫ ያለው ነው:: ነገር ግን ባለፈው ዓመት የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ከአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በዞኑ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች ላይ አሲዳማውን መሬት በኖራ በማከምና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ በተሠራው ሥራ በአማካኝ 51 ኩንታል ስንዴ በሄክታር መገኘቱን ይናገራሉ።
“ኢትየጵያ 25 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍጆታ ከውጭ በማስገባት ወደ 600 ሚሊየን ዶላር ወጪ ታወጣለች” በማለት የሚያስረዱት አቶ ያለው፤ በዞኑ በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት በኖራ በማከምና ማሳዎችን በኩታገጠም በማደራጀት ቴክኖሎጂዎች ከተተገበሩ የዞኑን ምርታማነት በእጥፍ ማሳደግ አያዳግትም:: በዚህም ከዞኑ ብቻ ተጨማሪ ሦስት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማግኘት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
ኃላፊው፤ የዞኑ ተጨማሪ ምርት ከውጭ የሚገባውን 15 በመቶ ያህል የሚሸፍን መሆኑን ጠቁመው፤ የዞኑን ምርት በማሳደግ ብቻ አገሪቱ የምታወጣውን 90 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ይቻላል ይላሉ። ስለዚህ መንግሥት ለኖራ ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ በአቅርቦቱ ላይ ቢሠራ፤ በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ አክሞ በመዝራት ምርትና ምርታማነት በእጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ይገልፃሉ።
የኢትየጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ 45 በመቶ የስንዴ ምርት ከኦሮሚያ ክልል አርሲና ባሌ ዞኖች፤ እንዲሁም ከአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኝ ነው:: ነገር ግን እነዚህ ዞኖች በከፍተኛ አሲዳማነት በመጠቃታቸው አገሪቱ ማግኝት የሚገባትን ምርት እያገኝች እንዳልሆነ ይናገራሉ።
በእነዚህ ዞኖች ኖራንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ያስፈልጋል። በዚህም በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ በማከም የምርቱ መጠን በእጥፍ ለማሳደግ ይቻላል ይላሉ:: አገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን 25 በመቶ የስንዴ ፍጆታ በእነዚህ ዞኖች ብቻ በመሸፈን ለግዥ የምታወጣውን 600 ሚሊየን ዶላር ለማስቀረት እንደሚያስችላትም ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ከአርሶ አደሮችና ከባለድርሻ አካላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው፤ 43 በመቶ የሚሆነውንና በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ በማከም የአገሪቷን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን ገልፀዋል።
ይህ አሠራር መፍትሄ እንደሆነ ተለይቶ ቢታወቅም ኖራን አምርቶ ወደ ገበሬው ማሳ ማጓጓዝ ትልቅ ችግር መሆኑን አቶ ሳኒ ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት መንግሥትና እያንዳንዱ ኖራ በማምረትና በማጓጓዝ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል የህብረተሰብ ክፍል በሙሉ እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩን መንግሥት ብቻውን ይፈተዋል ማለት የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም፤ ኖራን የማምረትንና የማቅረብን ሥራ የግሉ ዘርፍ ተሰማርቶበት ለገበያ ያቅርብ ቢባል፤ አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያገኘውና ሊጠቀምበት እንደማይችል አስገንዝበው፤ ለተወሰኑ ዓመታት መንግሥት፤ ድርጅቶችና ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል::
ሚኒስትር ዲኤታው፤ ዓመታዊ የኖራ ሳምንት በየዓመቱ በማዘጋጀት፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኖራን በማምረትና በማጓጓዝ የበኩላቸውን አገራዊ ተልዕኮ እንዲወጡ ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተቀየሰ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት28/2012
ሶሎሞን በየነ