የዓለም ባንክ በ2020 ለኢንቨስትመንትና ምቹ ቢዝነስ ከባቢ ያላቸውን ሀገራት ደረጃን በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ደረጃውን ለማውጣት የዓለም ባንክ አስር መመዘኛዎችን እንደመስፈርት ተጠቅሟል፡፡ በኢትዮጵያ ቢዝነስ ለመጀመር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ፣ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና የንብረት ምዛገባ ዘመናዊነት፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ችግሮችን መቅረፍ፣ የብድር አቅርቦት፣ የግብር አከፋፈልና የተቀላጠፈ የጉሙሩክ አገልግሎት እንደመስፈርት ከተያዙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዓለም ባንክ መስፈርት መሰረት ኢትዮጵያ ከ190 ሀገራት ውስጥ 159ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የባንኩ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሪት ፋንቱ ፋሪስ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ይህን ደረጃዋን ማሻሻል እንድትችል ብሄራዊ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋቁሞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ የተሰሩ በርካታ ስራዎች በዓለም ባንክ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
በተለይም በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች በግንባታ ዘርፍ 24 ደረጃዎችን እንድታሻሽል ያስቻላት ሲሆን፤ በንብረት ምዝገባ ዙሪያ የተተገበሩ ማሻሻያዎችም ኢትዮጵያ መሻሻል እንድታሳይ እንዳስቻላት የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ወይዘሪት ፋንቱ አብራርተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአንዳንድ ዘርፎች አሁንም ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት ወይዘሪት ፋንቱ፤ በኩባንያዎች ውስጥ አነስተኛ ድርሻ ላላቸው ባለሃብቶች የሚሰጠው ከለላ ዝቅተኛ መሆን ደረጃዋ እንዳይሻሻል ካደረጉት አንዱ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ ሊከናወኑ የሚገቡ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ዛሬም በተግዳሮቶች ከተከበቡት አንዱ ነው የሚሉት ወይዘሪት ፋንቱ፤ ትራንስፎርመር ለማግኘት ጥያቄ ከቀረበ በኋላ የሚፈጀው ረጅም ጊዜ ዛሬም ችግር ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የግል ባለሃብቶች ኤሌክትሪክ የሚያቀርቡበት አሰራር እንዲዘረጋ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
እንደ ወይዘሪት ፋንቱ ማብራሪያ፤ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የቆየው የንግድ ህግ ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተፋጥነው ህጉ አለመሻሻሉም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላላት ዝቅተኛ ደረጃ የበኩሉን አበርክቷል።
ከሁለት ወር በፊት በመካከለኛ ደረጃ መተግበር አለባቸው ተብለው የተቀመጡ ማሻሻያዎች አገልግሎቶችን በኦንላይን መስጠት ላይ ያተኮሩ ቢሆንም ማሻሻያዎቹ ታህሳስ መጨረሻ ላይ መጠናቀቅ ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ አተገባበራቸው ሲታይ በርካታ ችግሮች እንደሚስታዋሉ ወይዘሪት ፋንቱ ገልጸዋል፡፡ ከንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳት ጋር በተያያዘ ኦንላይን አገልግሎቱ 80 በመቶ ቢተገበርም የግብር መክፈያ መለያ ቁጥርን የሰነዶች ማረጋገጫና ክፊያ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች መተሳሰር ካልቻለ የቢዝነስ ድባቡን ምቹነት አያረጋግጥም ብለዋል፡፡
ለቢዝነስ አመቺ ከባቢን ለመፍጠር የተቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ደረጃ ለማሻሻል በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ችግሮች መኖራቸውንም አብራርተዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደሚሉት፤አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ መተግበሪያዎችን የማበልጸግ ስራዎች በሚኒስቴሩ ተሰርተዋል። አንዱ ማነቆ የነበረው የኔትወርክ ችግር ነው፡፡ ሌሎች ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚጠበቁ ስራዎችን በአንድ ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
የኮሚቴው የቁርጠኝነት ማነስ ችግር አለ የሚሉት ኢንጂነር ጌታሁን፤ ኮሚቴው ተሰብስቦ በአዳራሽ ውስጥ የተወያየባቸውን ነገሮችን ወጥቶ በመተግበር ረገድ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አብራርተዋል። በአዳራሽ ውስጥ በተነጋገረው ልክ የመንቀሳቀስ ሁኔታ አይታይም፤ ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አመራሮች የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር አፋጣኝ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ዳተኛ መሆናቸው ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች ሳይሰሩ እየቀሩ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ምቹ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት አዳጋች ነው፡፡ ግባችን የሀገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ማሻሻል እንደመሆኑ መጠን መወያየት ብቻ ሳይሆን በፍጥነት መስራት አለብን ብለዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር ጌታሁን ማብራሪያ፤ አዳዲስ ነገሮች በድሮ የችግር አፈታት አይፈቱም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሚጠበቀው በላይ ሄደን ልንሰራ ይገባል፡፡ በህግና ስርዓት ብቻ ተተብትበን መንቀሳቀስ አንችልም፡፡ ግብ አስቀምጠን ያንን ግብ ለማሳካት ለየት ያሉ ውሳኔዎች መወሰንም አለብን፡፡ የተቋማት ዝግጁነት ሁኔታ መታየት አለበት፡፡ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አፋጣኝ ድጋፍ፤ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ተጠያቂ እያደረጉ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር ሁሉም ተቋማት እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊሰሩ ይገባል፡፡ ቅንጅታዊ አሰራር ከሌለ አሁንም ምቹ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር የተያዘውን ግብ ለማሳካት አዳጋች ነው ብለዋል፡፡ አንዱ ቢሰራና ሌላኛው ባይሰራ የሁሉም አፈጻጸም ተያይዞ መውረዱ የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም በጋራ መንቀሳቀስ ለቢዝነስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡
የብሄራዊ ኮሚቴ አባልና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ ካለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው አንዳንድ የማሻሻያ ተግባራት ለዓለም ባንክ በወቅቱ ባለመድረሱ እና በሚገባ ባለመተግበራቸው በዓለም ባንክ ደረጃ አወጣጡ ስራ ላይ ሳይውል መቅረቱን አንስተዋል። ዘንድሮም መከናወን የሚገባቸው ተግባራት በወቅቱ ተከናውነው እስከ ታህሳስ ባሉ ጊዜያት ውስጥ ሊላክ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ ከታህሳስ ወር በኋላ የሚመጡ ሪፖርቶች የመያዝ እድላቸው አነስተኛ በመሆኑ በጊዜ የለኝም መንፈስ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አገሪቱ የቢዝነስ ከባቢን ምቹ ለማድረግ እየሰራች ያለው ስራ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያ 24 ደረጃዎችን እንድታሻሽል ያስቻላት ሲሆን፤ በንብረት ምዝገባም የተተገበሩ ማሻሻያዎችም ተጠቃሽ እመርታ ነው፡፡ በመሆኑም በሌሎች ዘርፎች ለማስመዝገብ የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ሳይቋረጥ ሊቀጥል ይገባል፡፡
ምቹ የቢዝነስ ከባቢን በመፍጠር ሂደት የሀይል አቅርቦትን ማሳካትና የንግድ ስርዓቱን ማዘመን ትልቅ ድርሻ አላቸው፤
አዲስ ዘመን ጥቅምት27/2012
መላኩ ኤሮሴ