ኀሙስ መስከረም ሰባት ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ አመት ቁጥር 215 እትም “አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ” በሚል ርዕስ ተከታዩን ዜና አስነብቦ ነበር፡፡
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ
የቤተሰብን ጤንነትና አካል እንዲጠብቅ ተብሎ በጸሎት መልክ የቀረበውን አዲሱን የኀዘን ዜማ አንዳንድ አልቃሾች መቃወማቸው ተገለጸ።
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ኮርስ ወስደው እንዲያጠኑ ተጠይቀው ፍቃደኛ ሆነው አልተገኙም። አዲሱ ዜማ አንድ ሰው ሲሞት በህብረት ዝማሬ እየተዜመ ሙታንን ለመሸኘት የሚያስችል ነው። በተለይም አንድ ሰው በሞተ ጊዜ የሟቹ ቤተሰቦች ደረት በመደለቅ ፤ መሬት በመፈጥፈጥና ፊት በመንጨት የሚደርስባቸውን ከባድ ጉዳት የሚያስወግድና ሥርዓትና መልክ ያለው ነው። ዜማውን የደረሱት አቶ አብርሃም መኮንን የመንደር አልቃሾች እንዲያጠኑት ቢጠይቋቸው “ብላችሁ ብላችሁ በእንጀራችን መጣችሁ ? ቄሶቹ በአንድ በኩል ያወግዛሉ፤ እናንተ ደግሞ ይህን ትላላችሁ ለእኛ ስራችን ነው” ብለው እንደወቀሷቸው ተናግረዋል።
… የአሁኑ የአልቃሾች ዜማ ወንዱና ሴቱ ተለይቶ አይነገርበትም። የሞተችው ሴት የሆነች እንደሆነ ለወንድ ያለቅሱበታል። ሟቹ አርበኛ የሆነ እንደሆነም አቶ እገሌ እህል ሲያመርት ፤ እርፍ ሲይዝ እንዲህ አልነበረም ተብሎ ሙሾ ይቆምበታል። በጠቅላላ ዜማው ሥርዓት የሌለው ነው። ነገር ግን በህብረት እየተዘመረ የሚዜመው የለቅሶ ዜማ በአልቃሾች ቢጠና ጥቅሙ እንደሚያመዝን አንዳንድ አልቃሾች ተናግረዋል።
**************
ማክሰኞ ጥር አንድ ቀን 1965 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 32ኛ አመት ቁጥር 10 እትም ስታስነጥስ ከነበረባት የመስማት ችግር ስለተላቀቀች ወጣት ሮይተርስን ጠቅሶ ተከታዩን አስነብቦ ነበር፡፡
22 ዓመት ሳትሰማ የኖረችው በማስነጠስ መስማት ቻለች
ጂን ሔይምስ የተባለች የ22 አመት ቆንጆ በኃይል በማስነጠሷ የተነሳ የወደፊቱ ኑሮዋ ከፍተኛ ለውጥ ሊያገኝ መቻሉን ሮይተርስ ኮቤንትሪ ከተባለችው የኢንግላንድ ከተማ ገለጠ። የፋብሪካ ሰራተኛ የሆነችው ጂን ማስነጠሱ ሲተዋት በደንብ ለመስማት ችላለች። ከተወለደች ዕለት ጀምሮ እስከ አስነጠሳት ቀን ድረስ መስማት የተሳናት ነበረች።
እሁድ ዕለት የመረመሯት ሀኪሞች በኃይል በማስነጠሷ የተነሳ ተዘግቶ የነበረው የጆሮዋ የውስጥ አካል ቧንቧ ሊከፈት ችሏል ብለዋል። በአሁኑም ወቅት ጂን ስትተኛ ጆሮዋን በጥጥ መጠቅጠቅ ግድ ሆኖባታል። ይኸውም በምትተኛበት ወቅት ሰምታው የማታውቀው የማንኮራፋት ድምጽ ከእንቅልፏ ስለሚነቀንቃት ነው ፤ ግን አትማረርም።
**************
አርብ ጥቅምት 10 ቀን 1954 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 21ኛ አመት ቁጥር 247 እትም የማነ በየነ የተባሉ ሰው ስራ ፈትተው ጊዜያቸውን በየቡና ቤቱ በካርታ ጨዋታ በሚያሳልፉ ሰዎች ተቆጥተው “የካርታ ጨዋታ” በሚል ርዕስ የጻፉትን ተግሳጽ እንዲህ አስነብቦ ነበር፡፡
የካርታ ጨዋታ
በየቡና ቤቱ ጠረጴዛዎች ላይ የካርታ ወረቀቶች ተከምረው ይታያሉ። እነዚህ ካርታዎች ሰባቱንም ቀናቶች ስራ ፈትተው አይገኙም። መቼም ሰው ሳይበላ ሳይጠጣ አቅም አያገኝምና በስራ ሰዓትም ቢሆን የቡና ወይም የሌላ የመጠጥ ሱስ ያለበት አንድ ጊዜ በቁሙ ጨልጦ ወደስራው ለመመለስ ወደ አንድ ቡና ቤት መሄዱ አይቀርም። ነገር ግን በስራ ሰዓት በዚህ ጠረጴዛ ላይ የተከመሩትን ካርታዎች ሲጠፈጥፍ የሚውለው ምን ጊዜ እየሰራ ነው ? በካርታ በሚገኝ ሳንቲም ችግሩን ማስወገድ ችሎ ይሆን ወይስ እንዲሁ የሚዛቅ ገንዘብ አግኝቶ ? አይደለም። በጠቅላላው በስራ ሰዓት በካርታ ወረቀት ላይ ተጣብቀው የሚውሉት ሁሉ በስንፍና የተሞሸሩና ለአገሪቱ ከባድ ሸክሞች ናቸው ከማለት በስተቀር ሌላ ዝርዝር ምክንያት ማተት አያስፈልግም።
የየረርና ከረዩ አውራጃ ግዛት አዣንስ የማነ በየነ
አዲስ ዘመን ጥቅምት26/2012
የትናየት ፈሩ