በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ፕሮግራም የተጀመረው እ.አ.አ በ2003 መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ትምህርቱ በአብዛኛው ሲሰጥ የቆየውም ልምድ ባላቸው ተመራማሪዎችና ፍቃደኛ ፕሮፌሰሮች እንደነበረም ይታወቃል።
በወቅቱ ዩኒቨርሲቲዎችን ማስፋፋት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ ይሰራበት የነበረ ሲሆን፣የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና መስጠት በመንግሥት ደረጃ ጠቃሚ ነው ተብሎም አይታሰብም ነበር። ይሁንና ከቅብር ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች በሀገሪቱ እየተስፋፉ ሲመጡ መነቃቃት በመፈጠሩ የድህረ ምረቃ ትምህርቶችም አብረው መስፋፋት ጀምረዋል። በሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጠው ሥልጠና ግን በሚፈለገው ልክ አድጓል ማለት አይቻልም።
በዚህም መነሻነት ከሰሞኑ በጤናው ዘርፍ ላይ አተኩረው በሚሰጡ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠናዎች ዙሪያ ባሉ ተግዳሮቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና በቀጣይ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና ኖርዌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ኮንፍረንስ ተካሂዷል።
በአዲስ ኮንቲኔንታል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የማነ ብርሃነ የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሙን በኢትዮጵያ ማስፋፋት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው ይላሉ።በተለይም ዘመኑ የእውቀት ነው ተብሎ እስከታሰበ ድረስ እውቀትን በራስ ማፍለቅ ካልተቻለ የታሰበው ደረጃ ላይ መድረስ እንደማይቻል በመጥቀስም፣ለሥልጠና ፕሮግራሙ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ያሳስባሉ።
በዋናነትም የሦስተኛ ዲግሪ የጤና ትምህርት ሥልጠናን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑንና ሥልጠ ናውን በማስፋፋት ሂደትም ምክክር ማድረግ እንደሚገባም ይገልፃሉ። በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ሰልጥነው የሚወጡ ባለሙያዎች በእውቀት የበቁ ሆነው ለጤናው ዘርፍ መሻሻል አስተዋፅኦ ማበርክት እንደሚጠበቅባቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ይህንንም ለማሳካት ከጤና ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ፕሮግራሞችን እንደልብ ለማስፋት ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት ከታች ጀምሮ ለትምህርት ጥራት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው። በመሆኑም ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች በትምህርት ሂደት በሚፈለገው ጥልቅ ሃሳብ ውስጥ ስለማያልፉ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አስተሳሰብና ልምድ ሳይዙ ይመጣሉ። ይህም የሥልጠና ፕሮግራሙን ለማስፋት ሌላኛው ተግዳሮት ሆኖ ይጠቀሳል። በመሆኑም ተማሪዎች በጥልቅ ምርምርና ሃሳብ ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግም ያስፈልጋል።
በመንግሥትም በኩል ብዙ ጊዜ የሚታየው በጀት ሲመደብ፣መምህራን ሲቀጠሩና ተቋማዊ መሠረተ ልማቶች ሲሟሉ ብቻ ነው። ይሁንና በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ሥልጠና ለመስጠት ሲታሰብ እውቀት ማመንጨት ላይ ትኩረት መደረግ ይኖርበታል።እውቀት ደግሞ ሊመነጭ የሚችለው በጥናትና ምርምር በመሆኑ በቂና የተሻለ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል በጀት በመንግሥት በኩል ሊመደብ ይገባል። ለጥናትና ምርምር የሚውለውን ገንዘብም ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ጥናትና ምርም ሮችን በተናጠል ከመስራት ይልቅ ሰብሰብ አድርጎ ጥሩ ልምድ ባላቸው ተመራማሪዎች እየተመሩ በሁሉም ደረጃ ያሉና ከወጣት እስከ መካከለኛ ደረጃ ያሉ ተመራማሪዎች እንዲሳተፉ በማድረግ መስራት ቢቻል የሚፈለገውን የምርምር ውጤት ማግኘት ይቻላል። ለዚህም በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች የሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውንና ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ምሁራንን በአግባቡ ሊይዟቸውና ሊጠቀሙባቸው ይገባል። ይህም ምሁራኑ ሌሎች የሦስተኛ ዲግሪ ምሁራንን ለማፍራት ያስችላቸዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ዘርፉን ከማሻሻል አኳያ የሚጫወቱት ሚናም ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚሰጡ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ ባልተቀናጀ መልኩ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችን ትብብር በመፍጠር አቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል። የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት እንዲሁ በቀላሉ የሚስፋፋ ባለመሆኑ በዚህ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ምሁራን በማሰባሰብ ጥራት ያለው የሕክምና ትምህርት እንዲሰጡ ማገዝም ይገባል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አዱላ በቀለ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በአብዛኛው በመንግሥትም ሆነ በግል ትኩረት የሚደረገው ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ሥልጠናዎች በመሆኑ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ያን ያህል እድገት አላሳየም። በዚህ ፕሮግራም የሚሰለጥኑ ተማሪዎችም ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ይታወቃል።ይሁንና በአሁኑ ወቅት በሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ፕሮግራም ላይ የማስፋፋት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከስምንት ዓመት በፊት የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና የማይሰጡ ዩኒቨርሲቲዎችም በአሁኑ ወቅት ሥልጠናውን መስጠት ጀምረዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንደሚገልፁት፤በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ሥልጠና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የአስተዳደር፣ የመዋቅር፣ የጥራትና የተማሪ አማካሪ ችግሮች ይታያሉ። እነዚህ ችግሮች የዩኒቨርሲቲው ችግሮች ብቻ አይደሉም፤በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎችም የሚታዩ በመሆናቸው ሌሎችንም ዩኒቨርሲቲዎች ያካተተ ቡድን ተቋቁሞ በችግሮቹ ዙሪያ ጥናት ተካሂዷል። በጥናቱም ችግሮቹ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል። ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑንም የጥናት ቡድኑ ተስማምቷል። በዚሁ ስምምነትና በጥናቱ መሠረት ዲዛይን ከተሰራ በኋላ ወጥ የሆነ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ሥርዓት እንዲኖር ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
አዲሱ የሦስተኛ ዲግሪ ሥልጠና ሥርዓት በቅድሚያ በጤናው ዘርፍ ላይ አተኩሮ የሚሰራበት ሲሆን፣ለጤናው ዘርፍ አገልግሎት ጥራት መጨመር የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል። በዘርፉ ዙሪያ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በመረጃ የተደገፉ እንዲሆኑም ያስችላል። በዋናነትም ተማሪዎች መረጃዎችን እንዲለዩ ያግዛል። የሚያቀርቡት የጥናትና ምርምር ወረቀትም እውነት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ይረዳል። በዚህ ላይ ተንተርሰው የሚቀመጡ የፖሊሲ አቅጣጫዎችም የተሳኩ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት25/2012
አስናቀ ፀጋዬ