ኢትዮጵያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ (ሪፎርም) በዚህ ዓመት ይፋ አድርጋለች፡፡ ማሻሻያውም እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች ለመፍታትና አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር ብሎም የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ደረጃ ማሻሻል ታሳቢ በማድረግ የተቀመረ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍና ማህበራት ምክር ቤትም፣ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር አገር በቀል የማሻሻያ ሪፎርሙን በሚመለከት ሰሞኑን በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ አማካሪ አቶ ፋንታሁን በለው የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ይዘት፣ በዘርፉ ተመዝግበዋል ካሏቸው ውጤቶች ጎን የፍትሃዊነት መጓደልና በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ችግር እንደነበርም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
እንደ አቶ ፋንታሁን ገለጻ፣ ባለፉት 15 ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከስድስት ዕጥፍ በላይ የሆነ የነፍስ-ወከፍ ገቢ ዕድገት ታይቷል፤ ከ15 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከድህነት ተላቅቀዋል፡፡ ዕድገቱ መዋቅራዊ ለውጥን ከማምጣት አንፃር ግን እምብዛም ስኬታማ አልነበረም፡፡
በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከግሉ ዘርፍ ይልቅ የመንግሥት እጅና ኢንቨስትመንት ጎልቶ ታይቷል፡፡ ኢኮኖሚው በበርካታ መዋቅራዊና የዘርፍ ማነቆዎች የተተበተበ በመሆኑ፣ የተገኘውን ዕድገት ዘላቂ አድርጎ ማስቀጠል የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የገቢ ዕድገት በዋናነት የመነጨው በሀብት ክምችት በመሆኑ አነስተኛ ምርታማነት ነው የታየው፡፡
‹‹የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምርታማነት እድገት ማነቆዎች ከመዋቅራዊና ተቋማዊ ድክመቶች የመነጩ ናቸው›› የሚሉት አቶ ፋንታሁን፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የፋይናንስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረቶች፣ ውስን የብድር አቅርቦት ከማነቆዎቹ መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ፋንታሁን ማብራሪያ፤ ከፍተኛ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶችን ፋይናንስ ለማድረግ የተሄደበት መንገድ የዕዳ ጫና አሳድጓል፤ የሀገር ውስጥ ፋይናንስን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በመንግሥት ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች ብቻ እንዲውል አድርጓል፤ ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መልኩ ማስተዳደር አለመቻሉ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ተከስቷል፡፡
የገቢ ዕቃዎች ፍላጎት ሲጨመር፣ የወጪ ንግዱ አፈጻጸሙ ደካማ መሆን የንግድ ሚዛን ጉድለት እንዲሰፋና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ የውጭ ብድር ከሀገሪቱ ጠቅላላ ምርት ያለው ድርሻ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ከፍተኛ ነው ባይባልም፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደካማ መሆን እያሽቆለቆለ ከመጣው ከገቢ ንግድ አፈጻጻም ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ሁኔታ ከከፍተኛ ስጋት ደረጃ እንዲመደብ አድርጎታል፡፡ ከአገር ውስጥ መንግሥት በስፋት የወሰደው ብድር የግሉን ዘርፍ የመበደር ዕድል አጥብቦታል፡፡
ይህ በሆነበት አገር በቀል ማሻሻያው ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በተቀናጀና ትርጉም ባለው መልኩ ምላሽ መስጠትን አላማው ያደረገ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት አቶ ፋንታሁን፣ በተለይ የማክሮ-ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ፣ የወቅቱን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ያገናዘበ የፊስካል ፖሊሲን ቁመና የማስጠበቅ፤ የታክስ አስተዳደሩንና ፖሊሲን በማጎልበት የታክስ ገቢን ማሻሻል፤ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ውጤታማነቱን ማሻሻል፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ሥራን መተግበር፤ እንዲሁም ቀደም ሲል የተጀመሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንደሚተጋ ነው ያብራሩት፡፡
በማክሮ-ኢኮኖሚያዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች በተለይ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በማቃለል ረገድ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር፣ ረጅም የችሮታ ጊዜ ያላቸውና ጫና የማይፈጥሩ የውጭ ብድሮችን መውሰድ፣ የወጪ ንግድን ማጎልበት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር፣ ለግሉ ዘርፍ አስመጪዎች የውጭ ምንዛሬ ሽያጭ አቅርቦትን ለማሳለጥ ትኩረት ይሰጣል፡፡
‹‹እነዚህ የማክሮ-ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎቹ ውጤታማ የሚሆኑት መዋቅራዊ ማሻሻያዎቹ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እገዛ ሲያደርጉ ነው›› የሚሉት አማካሪው፣ በዚህ ረገድም የቢሮክራሲና የቁጥጥር ሥርዓትን ማሳለጥ፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ መሠረተ ልማት አቅርቦት ማዘመን፣ ሥራ ላይ የዋሉ ማበረታቻዎችን የመመርመር፤ የአገር ውስጥ ግብዓቶችን ለሚጠቀሙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አምራቾች ቅድሚያ የመስጠት፤ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ አምራቾችን የመደገፍ፤ ከሁሉ የኢንዱስትሪ ሰላምን ማጎልበት ሥራዎች እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ፤ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጎልበት ትልቅ ትኩረት ይደረጋል›› ነው ያሉት፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በእቅዱ ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ የዳን ቴክኖ ክራፋት ባለቤት አቶ ዳንኤል መብርሃቱ፣ ኢኮኖሚው በሚችለው አቅም መጠን እንዲያድግ በሥራ ፈጠራ፣ በዕድገትና ዕድሎችን በማመቻቸት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ አደናቃፊ አሠራሮችና ሕጐችን መቀየር፣ ዝርፊያን መከላከል፣ በትጋት፣ በጥበብና በጽናት መስራትና በአጠቃላይ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማስተካከል በቂ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡
የቤካስ ኬሚካል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ በቀለ ፀጋዬ፣ በማሻሻያው የኬሚካል ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስፈላጊውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የግሉ ዘርፍ ፊት አውራሪ እንዲሆን መንገድ የመጥረጉን ሂደት በማድነቅም፣ በማሻሻያው ላይ ግልፅነት እንዲኖር የማድረግ ጥረትም ይበልጡን መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍና ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚውን ፈተናዎች ለመሻገርና የግሉን ዘርፍ የተሳትፎ እድገት ለማጎልበት ወሳኝ ስለመሆኑ በመጠቆም፣ ‹‹ከሁሉ በላይ የመንግሥትን የተሳትፎ መጠን በመቀነስ የግሉን ዘርፍ የሚያጎለብት መሆኑም በሁሉም ዘርፍ የሚኖረንን ተሳትፎ ያሳድግልናል›› ብለዋል፡፡
‹‹የማሻሻያው አንዱ አቅጣጫም የመንግሥትን እጅ መቀነስና የግሉን ዘርፍ በዋናነት በኢኮኖሚ ውስጥ ማሳተፍ፣ መበላለጥ ሳይሆን መደጋገፍን መፍጠር፣ ያለፈውን ማረምና ሳንካዎችን ማስወገድን ያለመ ነው›› ያሉት አቶ ፋንታሁን፣ የማሻሻያ የመጨረሻ ግብም ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር ሁሉን አካታች ልማትና ድህነት ቅነሳ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና የባለ ድርሻ አካላት ርብርበ አስፈላጊ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት25/2012
ታምራት ተስፋዬ