በሸዋው ንጉስ መርድ አዝማች አምሀእየሱስ በ1733 ዓ.ም እንደተመሰረተች የታሪክ መዛግብት በማይነትበው ገፆቻቸው ላይ አስፍረዋል። ከሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሀን በምስራቅ በኩል 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ታሪካዊቷ የነገስታት መቀመጫ እና የስልጣኔ ጎህ ቀዳጅ አንኮበር ከተማ። ይህቺ የሰሜን ፈርጥ ከአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ እስከ የአፄ ምኒልክ ድረስ ታላቁ ቤተመንግስቷ ውስጥ በማኖር የኢትዮጵያን ጉልህ የታሪክ ድርሻ ትጋራለች።
ዛሬ ፊታችንን የእምቅ የባህል መገኛ፣የስርአተ መንግስት ምስረታ እርሾ፣የነገስታት ገድል ባለቤት እና የውብ ተፈጥሮ ማማ ወደ ሆነችው አንኮበር አዙረናል። ልብ ብሎ ላስተዋላት እና ችግሯን እህ ብሎ ላዳመጠላት አንኮበር የቅርብ ሩቅ ሆና በትውልዱ የምናብ ትውስታ ውስጥ ለመጨላለም ዳር ዳር እያለች ትመስላለች። በመሰረተ ልማት ግንባታ እጅጉን ወደኋላ ቀርታና ታሪኳ ተድበስብሶ በጉያዋ የምታኖረው ማህበረሰቧ በድህነት ስንክሳር ውስጥ ይገኛል። ኧረ እንዲያውም ባለፈው ዘመን በጎ ታሪክ በተስፋ ብቻ ነፍስ ዘርቶ የሚኖር ይመስላል።
ከላይ ያነሳነው እውነታ በስፍራው ተገኝተን ካደረግነው ምልከታ የሚቀዳ ነው። ሀቁ የዛሬ ታሪክ ቢሆንም የሰሜን ሸዋ አንኮበር በአገር ግንባታ ላይ ያሳረፈችው አሻራ ቀለም ላይለቅ በኢትዮጵያውያን ላይ የተነቀሰ በመሆኑ አቧራ እንደሸፈነው ወርቅ አዲሱ ትውልድ ትቢያዋን አራግፎ ከክብር ከፍታ ላይ እንደሚያወጣት እናምናለን። ተነግሮ የማይጠገበው ታሪኳን ከስልጣኔ ጋር የሚያዋህድ የነዋሪዎቿን ጩኸት የሚደመጥበት ዘመን ሩቅ እንደማይሆን የሚጠቁሙ ምልክቶችም አስተውለናል። ለዛሬ ይህን ጉዳይ እዚህ ላይ ቋጭተን ከአንኮበር ገፀበረከቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን እና የአናብስቱን ድርሻ የሚወስደውን ቀደምት የነገስታት መቀመጫ ቤተ መንግስት ታሪካዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ልናስቃኝ ወደድን።
ኑ ወደ ቤተ መንግስቱ እንሂድ
በአምስት ቀናት ቆይታችን በሰሜን ሸዋ ምድር ካየናቸው በርካታ የታሪክ፣ የተፈጥሮ እና የቅርስ ፈርጦች ውስጥ አንኮበር የሚገኘው የነገስታት መቀመጫ ቤተ መንግስት ቀዳሚው ነው። ከአድካሚና ረጅም ጉዞ በኋላ ያለፈውን ድንቅ እውነታ የሚያስታውስ እና በተፈጥሮ መንፈስ ከሚያድስ ከፍ ያለ መልክአ ምድር ላይ ተገኘን። እዚያ ደግሞ ዘመናትን የተሻገረ ጆሮ ገብ ታሪክ አገኘን። የስፍራውን ዙሪያ ገባውን ስንቃኝ የታሪክ ዶሴዎችን ስንገልጥ፤ የሚታየውን ስናይ የሚዳሰሰውን ስንነካ ቆየን። በቆይታችን የቤተ መንግስቱ አስጎብኚ የሆነችው ወጣት ብርቱካን አይችልሁም ለሰሚው ማራኪ በሆነ መንገድ የታሪኩን ሚስጢር ገለጠችልን። እኛ ደግሞ በዚህ መልክ ለእናንተ እንዲደርስ አደረግን።
በሁሉም አቅጣጫ ራቅ ብሎ መመልከት በሚያስችል ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ይገኛል። ወደ ቤተ መንግስቱ ለመድረስ ከ400 ደረጃዎች በላይ ሽቅብ መውጣትን ይጠይቃል። ወደዚህ ቤተ መንግስት ለመግባት ሁለት በሮች ተዘጋጅተውለታል። የመጀመሪያው ‹‹ፊት በር›› የሚል ስያሜ ሲኖረው ነገስታቱ ወደ ቤተ መንግስቱ ለመግባት ነዋሪው ደግሞ ግብር ለመክፈል ሲመጣ የሚጠቀምበት ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ሚስጢር በር›› የሚል ስያሜ ሲኖረው ይህን መጠሪያ ያገኘው ለንጉሶቹ ሚስጢራዊ መልዕክት ሲኖር ብቻ ስለሚጠቀሙበት በዚያ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። ይህ የመግቢያ በር 471 ደረጃዎች አሉት።
በምድረ ግቢው ውስጥ ሁለት ባህላዊ ይዘታቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶች ያሉ ሲሆን በተለምዶ እላይ ቤት እና እታች ቤት እየተባሉ ይጠራሉ። እላይ ቤት የሚባለው ዋናው የንጉሶቹ እና ቤተሰቦቻቸው መቀመጫ የነበረው ሲሆን እታች ቤት ደግሞ እልፍኝ አስከልካይ፣ አማካሪዎች እና የቅርብ ዘመዶች የሚኖሩበት ነው።
‹‹ታች ቤት›› ከሚገኙት አስሩ ቤቶች እድሳት ሲደረግላቸው አንደኛው ብቻ አንኮበርን በመሰረቱት ንጉስ መርዕድ አዝማች አምሀእየሱስ ስም ሲሰየም ሌሎቹ ይህን ቤተ መንግስት አድሰው ወደ መዝናኛ ሎጅ በቀየሩት በአካባቢው ተወላጅ ኢንጂነር ተፈራ ራስወርቅና ቤተሰቦቻቸው ተሰይመዋል።
በአንኮበር ቤተመንግስት እስከ ንጉስ ዩኩኖ አምላክ ድረስ 25 ነገስታት መቀመጫ ነበር። ግራኝ መሀመድ ስፍራውን ሲቆጣጠጠረው መቀመጫነቱ አብቅቶ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ በንጉስ መርድ አዝማች አምሀእየሱስ ከተማዋ ተቆርቁራ የነገስታት መኖሪያነቱ እንዲቀጥል ሆኗል። በዚያም አስፋው ወሰን ሰገድ፣ንጉስ ሳህለ ስላሴ እንዲሁም አፄ ምኒልክ በዚህ ቤተ መንግስት መቀመጫቸውን አድርገዋል። ይህ ጥንታዊ ሀብት በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ፋሽስት ኢትዮጵያን በወረረበት እና ለአምስት ዓመት በጦርነት በቆየበት ጊዜ በ1928 ዓ.ም አፈራርሶት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
በ1992 ዓ.ም የአካባቢው ተወላጅ በሆኑት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ በድጋሚ እድሳት ተደርጎለታል። በ1998 ዓ.ም ደግሞ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ ስራ ጀምሯል። በግቢው ውስጥ በተለየ መንገድ ጎብኚዎችን የሚማርከው የግብር ማብያ አዳራሹ ሲሆን ከእርሱ ቀጥሎ ደግሞ ሳህለ ስላሴ እልፍኝ የአፄ ምኒልክ ማደሪያ ቦታ ሌላኛው አይን ውስጥ የሚገባ ነው። በዚያው ግቢ ውስጥ የሸዋ ነገስታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፍርድ የሚሰጡበት ስፍራ ይገኛል። ሌላኛው የቤተመንግስቱ አጥር ሲሆን በወቅቱ ከእንቁላል እና ከኖራ ተቦክቶ እንደተሰራ ይነገራል።
ሌላኛው ማራኪው እይታ የሚሆነው የቤተ መንግስቱ መቀመጫ እንዲሆን የተመረጠው ቦታ ወይም መልከአምድር ነው። ስፍራው ለጠላት ጥቃት እንዳያመች እና በአንፃሩ ደግሞ ጠላትን ለመከላከል የሚያመች መሆኑን ልዩ ያደርገዋል። የስፍራው ከፍታም ከ2870 ከባህር ጠለል በላይ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን ከፍታው ከዚህም በላይ እንደነበረና በተለያዩ ጊዜያት ለመኖሪያ ምቹ እንዲሆን ከሶስት ጊዜ በላይ ተቆርጦ ተስተካክሏል።
አፄ ምኒልክ በዚህ ቤተመንግስት ውስጥ በመሆን የኢትዮጵያን ግዛት በስፋት ለመቆጣጠር ያመቻቸው እንደነበር ይገለፃል። በተለይ ከቁንዲ እስከ አዋሽ ድረስ 150 ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት መመልከት ይቻላቸው ነበር። የአፄ ምኒልክ መገልገያዎች እና በቅርስነት የተቀመጡ የተለያዩ ታሪካዊ እቃዎች በአንኮበር መድሀኒያለም እና በአዲስ አበባ በሚገኘው እንጦጦ ብሄራዊ ሙዚየም ይገኛሉ። በአንኮበር ቤተመንግስት ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የታሪክ ማስረጃዎች አስረጂ ፎቶዎች መሆናቸውን በስፍራው የተገኘ ማስተዋል ይችላል።
ታሪካዊ ምስሎች
አፄ ምኒልክ በንግስናቸው ዘመን የተለያዩ የስልጣኔ ጎህ የቀደዱ መሳሪያዎችን ወደ አገራቸው በማስገባት ማህበረሰቡን ማንቃት የቻሉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። ይህን ከሚያመለክቱት ውስጥ በአንኮበር ቤተ መንግስት የተቀመጡ ምስሎች ቀዳሚዎቹ ናቸው።
በተለይ እቴጌ ጣይቱ እና አፄ ምኒልክ ጋብቻቸውን በአንኮበር መድሃኒአለም ባደረጉበት ወቅት አንዲት ፈረንሳዊት ሴት ምስላቸውን በፎቶ በማስቀረት በስጦታ መልክ አበርክታላቸው ነበር። በዚህ ምስል ላይ ሁሉቱን 18 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሊሻን የሚል ስያሜ ያለው የወርቅ ካባ ለብሰው ይታያሉ። በዚሁ ቦታ ንጉሱ የክተት አዋጅ የሚያስነግሩበት 44 ነጋሪት የነበራቸው ነበራቸው። ከዚያ ውስጥ አንዱ ብቻ ቀርቶ በዚሁ ቤተ መንግስት ውስጥ ይገኛል። ከዚህ ሌላ አፄ ምኒልክ በ1888 ዓ.ም የጣሊያን ወረራን ለመከላከል የክተት አዋጅ ያስነገሩበት የብራና ፅሁፍ በምስል ማግኘት ይቻላል።
የአፄ ምኒልክ ፈረስ የሆነው ‹‹አባ ዳኘው›› ምኒልክ ጣይቱ ወይም ‹‹ሚጣ›› በሚል ማህተም ተደርጎበት የሚያሳይ ምስልም ማግኘት ይቻላል። በተለይ በወቅቱ የንጉሱ ፈረሶች ልዩ ምልክት ይደረግባቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ምክንያቱ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ እነዚህን ፈረሶች ከአካባቢያቸው ርቀው ቢያገኛቸው ወደ ቤተመንግስት መልሶ እንዲያስረክብ ለማስቻል እንደነበር ይነገራል።
ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ስንሄድ 1066 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ታላቁ ጦርነት የተደረገበትና ታላቁ ድል የተገኘበት ሥፍራ አድዋ ከተማና የከተማው ግድም ገመገሞች ይገኛሉ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ይህ ጦርነት ተደርጎ በአጼ ምኒልክ የሚመራው የጦር አርበኛ ድል ነስቷል። ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል።
ይህን ታላቅ ክብር የሚያሳይ እና ንጉሱ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደ ጦር ሜዳው ሲጓዙ የሚያመለክት የተለያዩ ምስሎችም በዚሁ በአንኮበር ቤተ መንግስት ማግኘት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን በምናብ ወደ ኋላ ተመልሶ በስፍራው ያሉ ያህል የጋራ ድልን ማጣጣም የሚስተካከል እርካታን ያጎናፅፋል።
የምኒልክ አያት ንጉስ ሳህለ ስላሴ በ1840 የወጪና ገቢ ንግድ መሰረት በማድረግ ከቤተ መንግስቱ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአልዩ አምባ ዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ ስርአት መጀመሩ የሚያሳዩ መረጃዎች በዚሁ ስፍራ ላይ ማግኘት ይቻላል። በተለይ እኚህ ንጉስ የውጪ ዲፕሎማሲያዎችን የሚያጠናክር ኢምባሲዎች እንዲከፈት ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ይነገራል። በዚህም ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና ብርቲሽ መክፈታቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎችም ማግኘት ይቻላል። ከዚህ ውጪ ዘመናዊ ፅሁፍ በብራና ላይ እና ቤተ ክርስቲያኖችን ማነፅ መጀመሩን እንዲሁ የሚያሳዩ ምስሎች በስፍራው ይታያሉ።
አፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ በነበሩበት ወቅት አጎታቸው ራስ ዳርጌ ‹‹ሰላሌ››አካባቢን ያስተዳድሩ ነበር። ንጉስ ሃይለመለኮት ደግሞ ከ1840 እስከ 1848 ሸዋን ማስተዳደራቸውን የሚያመለክቱ በርካታ ምስሎችንና የታሪክ ድርሳናትን በአንኮበር ቤተ መንግስት ማግኘት ይቻላል። ሸዋ የኢትዮጵያ የታሪክ ሆድቃ መሆኗን ለማየት በዚህ ቤተ መንግስት መገኘት ብቻ በቂ መልስ የሚሰጥ ነው።
የቤተ መንግስቱ ባለውለታ
ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የአንኮበር ቤተ መንግስት ከፈራረሰበት እና ከወደቀበት ተነስቶ አሁን በድጋሚ መስህብ እንዲሆን የዜግነት ድርሻቸውን የተወጡ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው እድሳት ከማድረጋቸው በላይ በኢትዮጵያ የቴሌግራም ፋክስን በአማርኛ ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ በ1960 ዓ.ም መቀየር የቻሉ ናቸው። በበጎ ፍቃድ ሃላፊነቱን በመውሰድ የአካባቢውን የቱሪስት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና የስራ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።
በዚህ ስራቸው ከማህበረሰቡ ክብር እና ከፍተኛ ምስጋናም የተቸራቸው መሆኑን በስፍራው የተገኘ ሁሉ መገንዘብ ይችላል። በግለሰብ ጥረት ይህን ያህል መነቃቃት መፍጠር ከተቻለ የዞኑ፣ የክልሉም ሆነ የፌደራል የባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤቶች እንዲሁ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በንቃት መሳተፍ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ጥረት ብዙ ሊማሩ ይገባል። የመዳረሻ ልማት ቢስፋፋ የኢትዮጵያን ፈርጥ አንኮበር ቤተ መንግስት እና ታሪካዊውን ምድር የለበሰችውን ዳዋ ገፍፎ እንድታንፀባርቅ ለማድረግ ቅንነት ብቻውን በቂ ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት23/2012
ዳግም ከበደ