– የፋይናንስ አቅም ውስንነት ተፈታትኖታል
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት በተቋሙ መሰረተ ልማቶች ላይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ብቻ 156 ዘረፋዎች ተፈፅመውበታል፡፡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማዳረስም የፋይናንስ አቅም ውስንነት ተግዳሮት እንደሆነበት ተገልጧል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ 31 ትራንስፎርመሮች ተዘርፈዋል፡፡ በኤሌክትሪክ ማሰራጫ ኬብሎች ላይ 39 ጊዜ ስርቆት ተፈጽሟል፡፡ በሌሎች ልዩ ልዩ የተቋሙ መሰረተ ልማቶች ላይ የተካሄደውን ዘረፋ ጨምሮ በአጠቃላይ 156 ዘረፋዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ በዚህም 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ አንድ ትራንስፎርመር በአማካኝ 400 ሺህ ብር የሚያወጣ ሲሆን፣ ከ20 እስከ 25 ዓመት አገልግሎት ይሰጣል። እንዲሁም፣ አንዱ ትራንስፎርመር በትንሹ እስከ 200 አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ፤ በመዲናዋና በዙሪያዋ ባለፉት ስድስት ወራት 31 ትራንስፎርመሮች በመዘረፋቸው ተቋሙ ሰባት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ከመክሰሩም በላይ 44 ሺህ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደተቋረጠባቸው ታውቋል።
በተጨማሪም፣ በአዲስ አበባና በዙሪያው ብቻ በኤሌክትሪክ ማሰራጫ ኬብሎች ላይ 39 ጊዜ በደረሰው ዘረፋ ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ተቋሙ ያጣ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ በድርጅቱ ንብረቶች ላይ 156 ዘረፋዎች በመካሄዳቸው የ17 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት ገልጸዋል።
ዘረፋው የተቋሙን ሰራተኞች የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)በመልበስና በክሬን ጭምር በመታገዝ በተወሰኑ ህገወጦች ሲፈጸም ነበር:: ከነዚህ ውስጥ በህብረተሰቡ ጥቆማ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መኖራቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ ይሄንን ተገንዝቦ ኤሌክትሪክ የሚጠግንም ሆነ የሚነካ ማንኛውም አካል ሲያጋጥመው የሥራ ትዕዛዝ መያዙን በመጠየቅ መሰረተ ልማቱን እንደራሱ ሀብት መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
በሌላ በኩል፤ ዓመታዊ የማህበረሰቡ የኃይል ፍላጎት በየዓመቱ 13 በመቶ እያደገ ቢሆንም፣ ተቋሙ በሰው ሰራሽና ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ለነባርና ለአዳዲስ ደንበኞቹ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ ለማስቻል አለመቻሉን ተናግረዋል።
የኃይል መቆራረጡ ከባለፉት ዓመታት እየተሻሻለ ቢመጣም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀረፈ የተናገሩት አቶ መላኩ፤ “አብዛኞቹ የኃይል መቆራረጥ ምክንያቶቹ የፋይናንስ እጥረትና የተቋሙ የውስጥ አሰራር በቴክኖሎጅ የተደገፈ አለመሆኑ ናቸው” ይላሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ሶሎሞን በየነ