አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባን እና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችን የመጠጥ ውሃ በእጥፍ የማሳደግ አቅም ያለው የሲቢሉ ግድብ ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ ሳይገነባ ለአስራ አምስት ዓመታት መቆየቱ የውሃ እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ የቀድሞው የሲቢሉ ግድብ ጥናት እንዲቆም የተደረገው በርካታ ሰዎችን ስለሚያፈናቅል በመሆኑ በታችኛው የወንዙ ክፍል ላይ አዲስ ጥናት ተሰርቶ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጿል።
የቀድሞው የኦሮሚያ ውሃ ቢሮ ኃላፊ እና የቀድሞው ኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ከ15 ዓመታት በፊት በሱሉልታ ከተማ ከሚገኘው ሲቢሉ ወንዝ ላይ ትልቅ የመጠጥ ውሃ ግድብ ለመገንባት ጥናት ተሰርቷል። ይሁንና ባልታወቀ ምክንያት የወቅቱ የኢህአዴግ አመራሮች ግንባታው ይቁም በማለታቸው ጥናቱ መክኖ ሊቀር ችሏል።
<<እኔ የኦሮሚያ ውሃ ቢሮ ኃላፊ ከመሆኔ በፊት የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ቢሮ ባልደረባ በነበርኩበት ወቅት ጥናቱን አከናውኛለሁ>> የሚሉት አቶ ጁነዲን፤ በወቅቱ ከካናዳ አገር በመጡ መሳሪያዎች ተጠንቶ 620 ሺ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በቀን ማቅረብ እንደሚችል በወቅቱ እራሳቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። ውሃውንም ከእንጦጦ ተራራ ስር በሚሰራ ዋሻ አማካኝነት እንዲተላለፍ ታቅዶ ሲሰራ ቢቆይም ያለምንም አሳማኝ ምክንያት በአንድ ጊዜ ይቁም መባሉ ስህተት እንደነበር ገልጸዋል።
ሲቢሉ ግድብ በተጠናበት ወቅት ግንባታው ቢከናወን 2 ቢሊዮን ብር ብቻ ይበቃው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጁነዲን፣ ይሁንና በባለስልጣናት ትዕዛዝ ባልታወቀ ሁኔታ ይቅር በመባሉ አሁን ላይ ይሰራ ቢባል በርካታ ቢሊዮን ብሮችን ሊጠይቅ እንደሚችል ገልጸዋል። ጥናቱን አሁን ላይ ተግባራዊ በማድረግ ከ40 በመቶ በላይ ንጹህ ውሀ የማያገኘውን የከተማዋን የኦሮሚያ ዞን ነዋሪዎችን የተሻለ ንጹህ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።
መንግሥት ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶት መደርደሪያ ላይ የቀረውን የግድቡን ጥናት ወደ ተግባራዊነት በመቀየር የአዲስ አበባን እና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችን ውሃ ችግር መቀነስ እንደሚችል አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ኃላፊ አቶ ስዩም ቶላ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ቀድሞ የተጠናው የሲቢሉ ግድብ በርካቶችን ከቀያቸው የሚያፈናቅል እና ከፍተኛ የካሳ ክፍያ ወጪ የሚጠይቅ ሆኖ ተገኝቷል። ከሰዎች በተጨማሪ ወደሰሜን ኢትዮጵያ የሚወስደው መንገድ ጭምር የሚነካ ነበር።
በሌላ በኩል የቀድሞው ግድብ የታሰበበት ቦታ ላይ በርካታ ፋብሪካዎች የተቋቋሙ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በቀድሞው ጥናት መሰረት ሲቢሉን ለመገንባት አይታሰብም። በመሆኑም ከቀድሞው ቦታ በተለየ አቅጣጫ በወንዙ የታችኛው ክፍል ላይ አዲስ የመጠጥ ውሃ ግድብ ጥናት እየተከናወነ ይገኛል።
እንደ አቶ ስዩም ገለጻ፤ አዲሱ የሲቢሉ ግድብ ጥናት ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ የዓለም ባንክ ለጥናቱ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጎበታል። ጥናቱም እየተጠናቀቀ በመሆኑ የዓለም ባንክ በቀጠራቸው ሰዎች አማካኝነት እንዲገመገም ይደረጋል።
ከጥናቱ በኋላ ዋነኛው ተግባር ግድቡን የመገንባት ሥራ ነው። ለግንባታው የሚሆን የገንዘብ ምንጩ እስከአሁን ባይታወቅም የተለያዩ የፋይናንስ አቅራቢዎች እንዲሳተፉበት ይደረጋል። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን መጠጥ ውሃ ከማቅረብ በተጨማሪ በተለይ የአዲስ አበባን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በእጥፍ የመጨመር አቅም ያለውን ይህን ግድብ ለመገንባት አሁን ላይ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልጋል።
ግድቡም ሲጠናቀቅ በቀን 528 ሺ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች ያመርታል ተብሎ ታቅዷል።
በተያያዘ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በገርቢ ወንዝ ላይ የመጠጥ ውሃ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል። የቻይና መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሰራው ይኸው ግድብ ከ73ሺ እስከ 100 መቶ ሺ ሜትር ኩብ ውሃ በቀን የማምረት አቅም አለው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ጌትነት ተስፋማርያም