ሌሊቱ በጭርታ ተውጧል። በስፍራው ኮቴም ሆነ ድምጽ እየተሰማ አይደለም። አልፎ አልፎ በመንደሩ ውርውር የሚሉ ውሾች ግን ዛሬን በተለየ መጮህ ይዘዋል። ምክንያታቸው በውል ባይታወቅም አንድን ስፍራ በተለየ እየዞሩ ያለማቋረጥ ይጮሀሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸው የገቡት ገና በጊዜ ነው። የንግድ ቤቶች፣ ሱቆችና የመጠጥ ግሮሰሪዎች በራቸውን ዘግተው መብራታቸውን ካጠፉ ቆይተዋል።
በርካቶች ለዕንቅልፍ ተሸንፈው በድካም በወደቁበት ሌት የመንደሩ ውሾች ጩኸት ከጆሯቸው አልራቀም። ብዙዎቹ ጉዳዩን ከልምድ ቆጥረው ችላ ብለውታል። አንዳንዶችም በሰላማቸው መረበሽ ተናደው መነጫነጭ ጀምረዋል። ውሾቹ ግን አሁንም ያለማቋረጥ ይጮሃሉ።
የሰኔ ወር እየተጋመሰ ነው። አልፎ አልፎ ከበድ ብሎ ‹‹መጣሁ›› የሚለው ዝናብ በቀላል ካፊያ ተሸንግሎ ይመለሳል። አንዳንዴ ደግሞ ሳይታሰብ ዶፉን አውርዶ እግረኛውን መድረሻ ያሳጣል። እንዲህ እንደአሁኑ ምሽቱን ውድቅት ሲረከበው ደግሞ ድንገቴው ዝናብ ሰፈሩን በጩኸት አድምቆ የስፍራውን ዝምታ ይሰብራል። ዛሬ ግን ከእሱ ሀይል ይልቅ የውሾቹ ድምጽ በርትቷል። እንደዋዛ እየተቀባበሉ የቆዩበት ደማቅ ጩኸት እስከ ንጋቱ ያለማቋረጥ ቀጥሏል።
ሰኔ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ጠዋት
የማለዳዋ ጸሀይ እንደሰሞኑ ደምቃ አልወጣችም። ገና ብቅ ሳትል ሸብቦ የያዛት ዳመና በወጉ እንዳትፈካ እንቅፋት ሆኗል። በዚህ ሰአት ማልደው የሚንቀሳቀሱ በርካቶች ወደየጉዳያቸው ለመሄድ መንገዳቸውን ጀምረዋል። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ ግን ጉዟቸውን ከሚገታ አንድ አጋጣሚ ጋር መፋጠጣቸው አልቀረም።
መንገደኞቹ ባሻገር የሚያዩትና በውሉ ያልተለያቸው አንድ ነገር መኖሩን አስተውለዋል። ከነዚህ መሀል ግን ደፍሮ ለመጠጋት የሞከረ የለም። ጥርጣሬው እየጨመረና የመንገደኞች ቁጥር እየታከለ ሲሄድ ግን ጥቂቶቹ ሰብሰብ ብለው ወደ ውሀ መውረጃ ቱቦው ተጠጉ።
አንድ ወጣት በውሀ መውረጃ ቱቦው ተንጋሎ ወድቋል። ቅዝቃዜ ያደረበት ስፍራ ቀድሞ በፈሰሰና ቆይቶ በረጋ ደም ተለውሷል። ጭንቅላቱ ላይ የተጫነበትን ድንጋይ በአይናቸው አልፈው ጉዳቱን ለማወቅ ሲሹ ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም። በድንጋጤ ወደኋላ ለመመለስ እርስ በርስ ተገፋፉ። እንደምንም ለመረጋጋት የሞከሩት ደግሞ የግለሰቡን ትንፋሽ ለማድመጥ ቀረብ ብለው አረጋገጡ። ህይወት አልባው ሰው እየተንቀሳቀሰ አልነበረም።
ጥቁር ጂንስ ሱሪን በቀይ ቲሸርት የለበሰው ወጣት ወፈር ያለ ሰማያዊ ጃኬቱ ከአጠገቡ ወድቆ ቀኝ እጁ ክፉኛ ተጎድቷል። ከስፍራው እምብዛም ሳይርቅ የተረጨው ደም ወንጀሉ በጭካኔ ስለመፈጸሙ ያመላክታል።
በመንገዱ ዳርቻ ላይ ወድቆ የሚታየው የሰው ልጅ አካል መሆኑ ሲታወቅ መንገደኛው ከቦ መላቀስ ጀመረ። አብዛኞቹ ከአካባቢው ስጋትና እስካሁን ከነበረው ልማድ ተነስተውም ግለሰቡ የተገደለው በዘራፊዎች መሆኑን ገመቱ። አንዳንዶችም የራሳቸውን መላምት እየደረደሩ ይሆናል ያሉትን እውነት አስቀመጡ።
ከነዋሪዎች አስቸኳይ የስልክ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ‹‹ገርጂ›› ልዩ ቦታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲደርስ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ከአምስት እያለ ነበር። ፖሊስ ወጣቱ ከወደቀበት ቱቦ ተጠግቶ ሁኔታውን እንዳረጋገጠም የከበቡትን ተመልካቾች ከስፍራው አርቆ ለቴክኒካዊ ምርመራ ስፍራውን አዘጋጀ።
አስከሬኑ ስፍራውን ከመልቀቁ አስቀድሞ በቦታው የተገኘው የፖሊስ ቡድን ተገቢውን የቴክኒክ ምርመራ ማካሄድ ጀመረ። አስፈላጊ የሚባሉ ስፍራዎችን ለይቶም ምስሉን በፎቶግራፍ እያስቀረ የአይን እማኞችን ቃል ተቀበለ። ለተጨማሪ ምርመራዎች አስከሬኑን ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ልኮም የጉዳቱን አይነትና መጠን የሚጠቁም መረጃን የማግኘት ጥያቄን አቀረበ። ውጤቱ ከመምጣቱ በፊት ግን ሟች ማነው? ለምንስ በጭካኔ ተገደለ? የሚለውን ለመመለስ አሰሳውን ማካሄድ ግድ አለው።
ከሁለት ወራት በፊት
ሁለቱ ወጣቶች በተያዩ ቁጥር ይገለማመጣሉ። በመሀላቸው የተፈጠረው ቂምና ጥላቻ ከእነሱ አልፎ የሌሎችን ትኩረት እየሳበ ነው። በተለይ የሺጥላ ‹‹ባላንጣዬ›› የሚለውን ደበበን ባየው ጊዜ ጥርሱን እየነከሰ ይዝትበታል። እጁን በእጁ እያጋጨና ራሱን እያወዛወዘም ጥላቻውን ያሳየዋል።
ደበበ በበኩሉ የየሺጥላን ሁኔታ የሚያየው በተለየ ስሜት ሆኗል። በመሀላቸው ያለውን ቂምና ጥላቻ ያውቃልና እርምጃው ሁሉ በተለየ ጥንቃቄ መሆን እየጀመረ ነው። እንደሱ ሆኖ ግን ባየው ቁጥር በንዴት እየጋየ አይብሰለሰልም። በድንገት ሲገናኙም በሁኔታው እየተገረመ በርቀት ሊሸሸው ይሞክራል። ደበበ የየሺ ጥላን ሁኔታ እየለመደው ቢሆንም ሰሞኑን የሚያሳየው ባህርይ ግን ከወትሮው መለየቱን አስተውሏል።
ሁለቱ ወጣቶች ከቀናት በፊት በመሀላቸው በተፈጠረው ያለመግባባት ለጠብ ተፈላልገው ተደባደቡ። አያያዛቸው የከፋ ሆኖም ለገላጋይ አስቸገሩ። ሁኔታቸውን ያዩ አንዳንዶች መሀል ገብተው መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም። አንዳቸው ሲጥሉ፣ ሌላቸው ሲወድቁ እያዩ ዝምታን መረጡ። ጥቂቶች ደግሞ የሁለቱን መካረር አይተው ሊገላግሏቸው ሞከሩ። የእነሱ ትግል ያስከተለው ውጤት ከበድ ያለ ነበር። ከሁሉም ግን የየሺጥላ ጉዳት አይሎ እጁ ለስብራት ተዳረገ። በዕለቱ ጠበኞቹ በግልግል ተለያዩ። ውሎ አድሮ ግን የሺጥላ በደበበ ላይ ክስ መስርቶ ፖሊስ ጣቢያ አሳሰረው።
ደበበ በፈጸመው የድብደባ ወንጀል ለቀናት ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ቆየ። ድርጊቱ በምስክሮች መረጋገጡ በህግ እንደሚያስጠይቀው ገምቶም በሀሳብ ሲብከነከን ቆየ። የሺጥላ በበኩሉ በድብደባ እጁን የሰበረውን ሰው እያሰበ በእስራት የሚያስቀጣበትን አማራጮች ሲያልም ከረመ። ህመሙ በተሰማው ቁጥርም ጠበኛውን እያስታወሰ በንዴት ይጋይ ያዘ።
የሺጥላ ጉዳት ያጋጠመውን እጁን እያስታመመ የባላንጣውን በፍርድ ቤት ተከሶ መቆም ናፈቀ። ይህኔ ከእጁ መዳን ይልቅ የጠበኛው በእስር መቆየት ውስጣዊ እርካታ ሰጠው። እንዳቀደው ሀሳቡ ከተሳካለትም ቁስሉ እንደሚሽር እርግጠኛ ሆነ።
ከቀናት በኋላ የሺጥላ የደበበን ከእስር መፈታት በድንገት ሰማ። ይህን ሲያውቅም ጆሮውን ማመን ተስኖት በትካዜ ቆየ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን እውነታውን በአይኖቹ አይቶ መፈታቱን አረጋገጠ። ይህን እንዳወቀ ስለምን ሊል ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገሰገሰ። በስፍራው ሲደርስ የተሰጠው ምላሽ ስለጉዳቱ የሚያስረዳ የህክምና ማስረጃ ባለማቅረቡ ተከሳሹ በዋስ መለቀቁ ነበር።
የሺጥላ ይህን ሰምቶ ከፖሊስ ጣቢያ ሲወጣ በውስጡ የጥላቻና የበቀል ስሜት ሲጠነሰስ ተሰማው። ባላንጣውን በእጥፍ የሚበቀልበትን አጋጣሚ እያሰበም ያዳፈነውን እሳት ሊቆሰቁስ ተዘጋጀ። ከዛን ቀን ጀምሮ ደበበን በድንገት ሲያገኘው የሚሰማው ሁሉ የተለየ ሆነ። በየደረሰበት እየተገኘም ቂሙን ሊወጣ እንደሚሻ ምልክቶችን ያሳየው ጀመር።
ደበበ የጠበኛውን ሁኔታ ካየ በኋላ ፍራቻ ይሰማው ጀምሯል። ባየው ቁጥር በፊቱ ላይ የሚያነበው ጥላቻ ስር መስደዱን አስተውሎም በሩቁ ለመሸሽ እየሞከረ ነው። ይህን የሚያውቁ ባልንጀሮቹ ራሱን እንዲጠብቅና እሱ ባለበት ስፍራ እንዳይገኝ ሲመክሩት ቆይተዋል። ዘወትር በጓደኞቹ አጀብ የሚጓዘው የሺጥላም ጠበኛውን በሩቁ እያሳየ ራሱን መወዝወዙን ቀጥሏል።
ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓም ምሽት
የሰኔ ቅዝቃዜ ማየል ጀምሯል። ካፊያ የዋለበትን ቀን ምሽቱ ሲረከበው ሰማዩ እንደጠቆረ ዘልቋል። ነጎድጓዱ እያስገመገመ መብረቅ ብልጭ እያለ ነው። አስቀድሞ ወደየቤቱ የገባው ነዋሪ ሰፈሩን በጊዜ ጭር አድርጎታል። አልፎ አልፎ በመንገዱ የሚያልፉ ሰዎችም ቢሆኑ ዛሬ ቁጥራቸው እምብዛም ሆኗል።
በአንድ ጥግ ያደፈጡት የሺጥላና ጓደኞቹ ግን ‹‹መጣሁ›› እያለ የሚያስፈራራው ዝናብ ምናቸውም አልሆነም። ለእነሱ ብርድና ቅዝቃዜው እየተሰማቸው አይደለም። አይኖቻ ቸውን ከመንገዱ ዳር ጥለው ብቅ ከሚሉት መሀል እየመረጡ የሚሹትን ሰው ይፈልጋሉ።
ሰአቱ እየመሸ ጨለማው እያየለ ነው። አሁን በመንገዱ የሚሰማ ድምጽ የለም። ይህ መሆኑ ለጨለማው አድፋጮች የተመቻቸው ይመስላል። አራት ሰአት ተኩል እንዳለ ድንገት ሁለት ሰዎች ብቅ ሲሉ ተመለከቱ። ይህኔ የሁሉም ዓይኖች በንቃት አነጣጥረው አፈጠጡ። ከሁለቱ መሀል አንደኛውን ሲናፍቁት እንደቆዩ ያውቃሉ። አብሮት ያለውን ግን ያለ ዛሬ አላዩትም።
ደበበ ከቅርብ ጓደኛው ጋር እየተጨዋወተ ወደሰፈሩ ተቃርቧል። ድንገት ከአንድስፍራ ሲቃረቡ ግን እርምጃቸው ሊገታ ግድ ሆነ። ሁለቱም በድንጋጤ ርደው ባሉበት ቆሙ። ጥግ ይዘው ከሚያይዋቸው መሀል የሺጥላን መለየት አላቃታቸውም። ወዲያው በሩጫ ርምጃ መፍጠን ጀመሩ። ሶስቱ በበኩላቸው እንዳላዩ ሆነው በዝምታ ሊያሳልፏቸው ሞከሩ።
የደበበ ባልንጀራ መከተላቸውን እንዳየ መሀል ለመግባት ሞከረ። እንደማይችላቸው ሲያውቅም እርዳታ ሊጠይቅ በአካባቢው ካሉ መኪና ጠባቂዎች ዘንድ ደረሰ። እውነታውን አስረድቶም ጓደኛውን እንዲታደጉለት ተማጸነ። ሰዎቹ የሚጠብቁትን ጥለው መሄድ እንደማይችሉ ቢነግሩት ተስፋ ቆርጦ ወደጨለማው አፈጠጠ። ያየውም ሆነ የተሰማው ድምጽ አልነበረም።
ሶስቱ ጓደኛሞች ደበበን በእጃቸው እንዳስገቡ አሳልፈው ለባልንጀራቸው አስረከቡት። ይህኔ የሺጥላ ባላንጣውን የጎንዮሽ እያየ ከበስተኋላው ሰንዝሮ ከመሬት ዘረረው። ከወደቀበት ለመነሳት ሲሞክር ባለዱላ ባልንጀራው ደርሶ አናቱ ላይ አሳረፈበት። ሁሉም በየተራ ዱላውን እየተቀባበሉ ደበደቡት። ደበበ በደከመ ድምጽ እንዲተውት ተማጸናቸው። ደሙ ከግንባሩ አልፎ በፊቱ መውረድ ሲጀምር ከወደቀበት ጥለውት ከአካባቢው ራቁ።
የሺጥላና ጓደኞቹ በደም ተነክሮ የወደቀውን ሰው በንቀት እያዩ ወደ አንደኛው ቤት ለማደር ጉዞ ጀመሩ። የሺጥላ አሁንም በባላንጣው ላይ የሆነው ሁሉ የበቃው አይመስልም። እሱን ዳግም በህይወት ማግኘት እንደማይሻ እየተናገረ በንዴት መዛት ጀምሯል። ይህን እየሰሙ ከአንደኛው ቤት ሲደርሱ ባልንጀሮቹ ምኞቱን ለመሙላት ያስችላል፣ ያሉትን ዕቅድ ነገሩት።
የሺጥላ ሀሳባቸውን ሲሰማ ፊቱ በደስታ ፈካ። ባመጡት አዲስ ዕቅድ ተስማምቶም ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ደበበ እንዲመለሱ አጣደፋቸው። ይህ ከመሆኑ በፊት ለዕቅዳቸው ማሳኪያ ይሆናል ያሉትን ረጅም ቢላዋ ያዙ። ቀድሞ የነበረውን ዱላ አክለውም ግቢውን ከፍተው ወጡ። ጨለማውን ጥሰው በፍጥነት እየተራመዱም ተደብዳቢው ከወደቀበት ስፍራ ደረሱ።
በደም የተነከረው ተጎጂ በደመነፍስ ዳግም ሲያያቸው በፍርሀት ተንቀጠቀጠ። ደበበ መነሳትና መሸሽ ተስኖት በከባድ ጉዳት እያቃሰተ ነበር። ሶስቱ ሰዎች አጠገቡ እንደደረሱ ጊዜ አላጠፉም። በያዙት ቢላዋ እጆቹን እየገዘገዙ ክፉኛ አሰቃዩት። ጎንና ደረቱን እየወጉም በደም እስኪነከር ጠበቁት። ደበበ የሚማጸንበት አቅም አጥቶ ራሱን ሲስት እንዳሰቡት ሆነላቸው። ያሻቸውን አድርገው ሲበቃቸው ቢላዋውን በርቀት ወርውረውና ትልቅ ድንጋይ በራሱ ላይ ጭነው ለአዳር ወደመጡበት ተመለሱ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በስፍራው ደርሶ መረጃዎችን ከወሰደ በኋላ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚስችለውን አሰሳ ማካሄድ ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። ስለ ሟች ማንነት ከአካባቢው ሰዎች መረጃ ደርሶታል። ስለባህርይውና ከሌሎች ጋር ስለነበረው ቅርበትም ለማወቅ ችሏል። ይበልጥ ግን ሟቹ በተገኘበት ዕለት ከጣቢያ ተገኝቶ ያየውን ከተናገረው የደበበ ጓደኛ የተሻለ መረጃን ማግኘት ችሏል። ፖሊስ መረጃውን ከተቀበለ በኋላ የጠቋሚ ጓደኛው ማንነት እስኪታወቅ ከማረፊያ ቤት አቆይቶ አቅጣጫውን ወደ ተፈላጊዎቹ መለሰ።
ከቀናት በአንዱ ቀን ፖሊስ ከተጠርጣሪዎቹ መሀል አንደኛውን ሲጠጣ ከነበረበት ጠላ ቤት ደርሶ በቁጥጥር ስር አዋለው። ከግለሰቡ ቃልም ከድርጊቱ በኋላ ሶስቱም ተገናኝተው እንደማያውቁ ተረዳ። ጥቂት ቆይቶ ግን ቀሪዎቹን በእጁ ለማስገባት አልዘገየም። ከየሚገኙበት ስፍራ እያደነ በህግ ጥላ ስር አዋላቸው።
አሁን መርማሪው ምክትል ኮማንደር ታፈሰ ዘበርጋ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 956/07 በተከ ፈተው ፋይል ላይ አስፍረው አጠናቀዋል። የተጠርጣሪዎቹ ድርጊት ለክስ የሚያበቃ በመሆኑም ጉዳዩን ወደ ዓቃቤ ህግ በማስተላለፍ ፍርድ የሚያገኙበት ሁኔታ ተጠናቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
መልካምስራ አፈወርቅ