ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። የመጀመርያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተማ ተከታትለዋል። በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቅቀዋል። እንዲሁም በአካባቢያዊና ማህበረሰብ ልማት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚሁ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል። ከኦክስፎርድ ዮኒቨርሲቲ በአለም አቀፍ ሕግና ሰብአዊ መብት ሕግ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት አጠናቅቀው በማዕረግ የተመረቁ ሲሆን፤ እዚሁ ዮኒቨርሲቲ ውስጥም በአለም አቀፍ ሕግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በሰብአዊ መብቶችና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ልማት ተመራማሪና አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቋም የሰብአዊ መብት ከፍተኛ አማካሪ፣ በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ሰብአዊ መብት ዲቪዠን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። በአክሽን ኤይድ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ቢሮ የፖሊሲ ጥናትና ምርምርና ግሎባል ኮል ፎር አክሽን አጌነስት ፖቨሪቲ ስራ አስኪያጅ ሆነው ከሰሩባቸው ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው።
በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር በስፋት በግላቸው የተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ በወቅቱ በቁጥጥር ስር ውለው ሁለት ዓመታትን በማረሚያ ቤት አሳልፈዋል። ሃሳብን የመግለጽ ኢንዴክስና የማርቲን ኢናልስ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ወይም ተከላካይ ዘርፍ ሽልማትን አግኝተዋል። ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው ከተሾሙት የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ዳንኤል በቀለ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተከመረ ዕዳ አለበት። እርስዎ ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የተሻለ ስራ በመስራት ጥሩ ገቢ ማግኘት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድና ብቃት አለዎትና ኃላፊነቱን እንዴት ተቀበሉት?
ዶክተር ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ የፖለቲከ ምዕራፍ ተከፍቷል። ከእዛ ወዲህ እጅግ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ተካሂዷል። ከዚህ በፊት በአገሪቱ ከነበረው ጨቋኝ የፖለቲካ አስተዳደር ወጥተን አዲስ ነጻ የፖለቲካ አስተዳደር ተጀምሯል። በዚህ ላይ የሃሳብ ልዮነት ያላቸው ሰዎች እንዳሉም ይገባኛል። ያንን የፖለቲካ ልዮነትም አከብራለሁ። ነገር ግን በእኔ እምነት እጅግ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ነው የተከፈተው። ይህንን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የጀመሩት የለውጡ አመራሮች በርካታ ተጨባጭ ውጤቶችን አሳይተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለመጀመር የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ፈቃደኝነቱን አሳይተዋል።
ስለዚህ አዲስ በተከፈተው የፖለቲከ ምዕራፍ ልቤ ቅርብ በሆነው ጉዳይ ማለትም በሰብአዊ መብት ማስፋፋት እና ማስጠበቅ ስራ አገሬን እንዳገለግል ጥያቄ ቀርቦልኛል። አገርና ሕዝብ ማገልገል ትልቅ ኃላፊነትና ድልም ነው። የተፈጠረውን መልካም ዕድል በመጠቀም በአገር ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋማትን በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ለማጠናከር ለሚደረገው ስራ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት የቀረበልኝን ጥሪ በበጎ መልክ ለመቀበል ወስኛለሁ።
ይህ ማለት የተወሰነ መስዋዕትነት የለውም ማለት አይደለም። ከቤተሰብ እና ከግል ሁኔታ አንጻር ተጽእኖ ይኖረዋል። ግን ተገቢ መስዋዕትነት ነው ብዬ አስባለሁ። አሁን የደረስንበት ምዕራፍ በብዙ ትግል የተገኘ ነው። ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን፣ ደህንነታቸውን፣ አካላቸውን፣ ንብረታቸውን ያጡበት ሂደት ነው። በመሆኑም በእዚህ ወቅት ያለን ሰዎች ደግሞ ይህንን ጊዜ በኃላፊነት ስሜት ተረክበን የምንችለውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን። ወደእዚህ ተመልሼ በእዚህ ስራ ላይ ለመሰማራት የወሰንኩትም በእዚሁ ስሜት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አዲሱን ኃላፊነት እንዴት አገኙት? በተለይ ጠብቀውት ከነበረው ግምትዎ ጋር ሲያነጻጽሩት በተግባር ምን ይመስላል?
ዶክተር ዳንኤል፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ከእዚህ በፊት በስራዬ ጸባይ የተነሳ በርቀትም ቢሆን በተወሰነ መልኩ አውቀዋለሁ። ተቋሙ ኢትዩጵያ ውስጥ ሲሰራ የነበረበትን የፖለቲካ አውድን የምናውቀው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በሙሉ ፍጹም በሆነ የመንግስት ቁጥጥር ስር ወድቀው ያለነጻነት የሚሰሩ ተቋሞች እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይ የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው የሚታሰቡት እንደምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የመሳሰሉት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ስር ሆነው የመንግስት መጠቀሚያ መሳሪያ ወይንም የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ እየሆኑ ሲያገለግሉ እንደነበሩ ይታወቃል።
ቢሆንም ባለው ሁኔታ ውስጥም የተወሰነ ስራ አልተሰራም ማለት አይደለም። በተለይ ግንዛቤ በማስፋፋት፣ በማስተማር ስራ እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ስልታዊ ክትትል በማድረግ የተወሰነ ስራ ለመስራት ጥረት ሲደረግ ነበረ። ግን እስካሁን ተቋሙ ሲሰራ ከነበረበት የፖለቲካ አውድ የተነሳ ያዳበራቸው ባህሪዎችና አሰራሮች አሉ። እንዲሁም ተቋሙ ሲሰራበት ከነበረው አውድ የተነሳ ለስራው የሚያስፈልጉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ለመሳብና ይዞ ለማቆየትም ባለመቻሉ የሰው ሃይል አቅሙ እጅግ የተዳከመ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። አደረጃጀቱ፣ አወቃቀሩ፣ የሰው ሀብት አስተዳደሩ እንዲሁም የበጀት አስተዳደሩም ለስራው በሚገባው መጠን የተደራጀ ሆኖ አላገኘሁትም። እናም በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማዋቀር ስራ እንደሚያስፈልገው ተረድቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡-ተቋሙን በአዲስ የማደራጀትና የማዋቀር ስራው አሁን ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ምን ያህል አስቻይ ነው ይላሉ?
ዶክተር ዳንኤል፡- በተወሰነ መጠንም ቢሆን ባለሙያዎች አሉበት። ሆኖም አደረጃጀቱ ከዋናው አደረጃጀት ይልቅ የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ላይ ያመዘነ ነው። ከዋናው ባለሙያዎች ይልቅ የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በዝተው መገኘታቸው አሁን እንደተረዳሁት በብዙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያለ ጸባይ ይመስላል። ይህ መስተካከል የሚገባው ነው።
ነገር ግን የሰው ሃይል አስተዳደሩን እና የበጀት ነጻነቱን ለማረጋገጥ ለስራው የሚያስፈልገው ብቃት፣ ክህሎት እና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰዎችን መሳብ ያስፈልጋል። አሁን ያለው የበጀት አስተዳደሩ፣ የሰራተኞች ጥቅማ ጥቅም ሁኔታ ከገበያው ለስራው የሚያስፈልገውን አይነት ከህሎት፣ ብቃት እና የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሰዎች ለማቆየት የሚያስችል አይነት አይደለም። ይህ አሁን አዲስ በማዋቀር እና በማደራጀት ስራው ውስጥ አንድ ተግዳሮት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ እንዴት ይተገበራል? ኮሚሽኑ በህግ ከተሰጡት ስልጣኖች አንጻርና ከአለም አቀፍ አቻ ተቋማት አሰራር ጋር ምን ያህል የተጣጣመ ነው?
ዶክተር ዳንኤል፡- በከፊል ከአንድ ዓመት ወዲህ ስልጣን የተረከበው የለውጥ መንግስት በወሰዳቸው ርምጃዎች በርካታ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታዎች ተሻሽለዋል። በተለይ የፖለቲካ
እስረኞች በስፋት መፈታት፤ለማንኛውም ዜጋ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ፤ ጨቋኝ ህጎች እንዲሻሻሉ መደረጉና ሌሎችም ህጎች በማሻሻል ሂደት ላይ መሆናቸው፣ ሃሳብን በነጻነት የመያዝ፣ የመግለጽና የሚዲያ ነጻነት እጅግ በጣም በተሻለና በተለየ ሁኔታ መከበር መጀመሩ በጎ ርምጃ ነው።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዲስ በወጣው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት መልሰው በአዲስ መልክ መቋቋም፣ መደራጀትና በነጻነት መሰባሰብ መቻላቸውና የመሳሰሉትን ተግባራትን ስንመለከት ብዙ መሻሻሎች ታይተዋል ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ አሳሳቢ የሆነ የሰብአዊ መብት ተግዳሮት እያጋጠሙ መሆኑ ደግሞ በእለት ተዕለት ህይወታችን የምንመለከተው ነው። ስለዚህ ከሰብአዊ መብት ችግር ኢትዮጵያ ነጻ ወጥታለች ማለት አይደለም።ይልቁንም እጅግ ውስብስብ የሆነ የሰብአዊ መብት ችግሮች እያጋጠሙን መጥተዋል።
ኮሚሽኑ ከአለም አቀፍ አቻ ድርጅቶች ጋር ሲነጻጸር በየአገሩ ይህንን የመሰለ ተመሳሳይ ተቋማት አሉ (National human right institutions) ብሄራዊ የሰብአዊ መብት ተቋሞች ይባላሉ። በየአገሩ እንዲህ አይነት ተቋማት ከስራ አስፈጻሚው ዋና ቁጥጥር ስር ነጻ ሆነው ሰብአዊ መብትን በማስከበርና በማስፋፋት በነጻነት የሚሰሩ ተቋማት ናቸው። እንደየአገሩ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የተቋሞቹ ድካምና ጥንካሬ የተለያየ ቢሆንም በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ በሆኑ አገሮች ውስጥ እንዲህ አይነት ተቋማት እጅግ ጠንካራ የሰብአዊ መብት ማስከበሪያ፣ ማስፋፊያና ማስጠበቂያ ተቋማት ናቸው።
የፖለቲካ አውዱ በማይፈቅድበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበረው አይነት በመንግስት ተጽእኖ ስር ወድቀው የሚሰሩ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ያልሆኑ ተቋሞች ናቸው። ስለዚህ አሁን አዲስ በተፈጠረው የፖለቲካ ምዕራፍ ግን ይህንን ሁኔታ እንደመልካም ዕድል በመጠቀም ተቋሙን በሌሎች አገሮች እንደሚታወቀው ሁሉ የዕውነት ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ጠንካራና ውጤታማ ለማድረግ ዕድል አለ ብዬ አምናለሁ። በእዚህ መሰረትም ይህንን ለማድረግ የሚያስችለውን የመሰረት ድንጋይ ጥለናል።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነትና ተልዕኮ ለመወጣት ገለልተኝነቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ዳንኤል፡- አሁን ባለንበት ወቅትና የፖለቲካ ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ነጻ እና ገለልተኛ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ኮሚሽኑን በኃላፊነት ለማስተዳደር ምክር ቤቱ አደራና ኃላፊነት ከሰጠኝ ጀምሮ ምን መስራት፣ እንዴት መስራት፣ ምን ማለት እንዳለብኝና እንደሌለብኝ የሚያዝዘኝ ማንኛውም አይነት የመንግስት ባለስልጣን የለም፣ ሊኖርም አይችልም ቢኖርም አልቀበልም። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ተቋማት ከመንግስት መመሪያ እየተቀበሉ ለመስራት አልተቋቋሙም፣ አላማቸውም ይህ አይደለም።
ስለዚህ እኔ የምመራው በተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት፣ በተሰጠው ተልዕኮ፣ ተግባርና ስልጣን መሰረት ነው። ከእዛ በመቀጠል የምመራው ደግሞ በአገሪቱ ህገ መንግስትና ኢትዮጵያ በተቀበለችውና ባጸደቀቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችና ሰነዶች መሰረት ነው። ስለሆነም አላማችን በህገ መንግስቱና በአለም አቀፍ ሰነዶችና ስምምነቶች መሰረት የታወቁትን ሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታወቁ ማስፋፋት፣ ማስተማርና ማሳወቅ ነው። እንዲከበሩ እና እንዲጠበቁ ደግሞ የማስከበርና የማስጠበቅ ስራዎችን መስራት ነው። ይህ ስራ ወደ ዝርዝር ስራዎች ሲገባ የምርመራ ስራውን ጨምሮ ብዙ አይነት መልክ አለው። በእዚህ ስራችን ውስጥ ጣልቃ የሚገባ የመንግስት አካል የለም።
ነገር ግን ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የተቋሙ አደረጃጀት፣ የበጀት አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ ለማድረግ የማቋቋሚያ አዋጁን መልሶ መፈተሸ ያስፈልጋል። ይህንን ጥናት በማድረግ ላይ ነን። አሁን ባለው አደረጃጀትና አወቃቀር በተለይ በፋይናንስ አስተዳደሩ ሙሉ ለሙሉ የበጀት ነጻነቱ ባለመረጋገጡ በስራ አስፈጻሚው ተጽእኖ ስር ሊወድቅ ይችላል። ይህ መሻሻል የሚገባው መሆኑ ታምኖበት የማሻሻል ስራም ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙን በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል?
ዶክተር ዳንኤል፡- የጊዜ ሰሌዳ አላስቀመጥንም። የህጎች ማሻሻያ ስራዎችን የሚያከናውን በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ስር አንድ የተቋቋመ ግብረ ሃይል አለ። የተለያዮ የሚሻሻሉ ህጎችን በሚመለከት ጥናት በማድረግ የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየትና ረቂቅ በማዘጋጀት ለመንግስትና ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት እየቀረበ እንዲጸድቅ የማድረግ ሂደት ተጀምሯል። ለምሳሌ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል ወደ ስድስት ወራት ያህል ፈጅቷል። የሚዲያ ህግን፣ የጸረ ሽብር ሕግን ለማሻሻል በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል። እነዚህና በርካታ ህጎች በግብረ ሃይሉ በመሻሻል ላይ ናቸው።
የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ የማሻሻያ ስራም በእዚህ ሂደት ውስጥ ነው የሚያልፈው። ብዙ በመሻሻል ላይ ያሉ ህጎች ስላሉ እርግጠኛ የሆነ በእዚህ ጊዜ ያልቃል የሚባል የጊዜ ሰሌዳ የለውም። ግን ፍላጎታችን በተቻለ ፍጥነት ባስቸኳይ እንዲጠናቀቅ ነው። በተለይ ይህ ሁሉ ስራ ከመጪው ምርጫ አስቀድሞ በተቻለ ፍጥነት ቶሎ ተጠናቅቆ ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማዋቀር ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ለአንድ ብዙሃን መገናኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ በጸረ ሽብር ሕጉ የሚከሰስ ሰው አይኖርም ብለው እንደነበረ አስታውሳለሁ። ግን አሁንም በርካቶች በአዚህ ሕግ እየተጠየቁ ይገኛልና ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ዳንኤል፡- የወንጀል ክስ የማቅረብ ስልጣን እና ኃላፊነት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሳይሆን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ስልጣን እና ተግባር ነው። እኔም በወቅቱ ገልጬ የነበረው ኢትዩጵያ ውስጥ አዲስ ከተከፈተው የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር በእዛ በተነቀፈና በተወገዘ የጸረ ሽብር ሕግ አማካኝነት ወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ክስ ሊቀርብ እንደማይገባ፣ ያ ሕግ ሊሻር እና ሊስተካከል እንደሚገባ ነበር የገለጽኩት። አሁንም ይህንን አምናለሁኝ። መንግስትም ሊሻሻሉ ይገባቸዋል ብሎ ካሰባቸውና ቅድሚያ ከሰጣቸው አንዱ ሆኖ በግብረ ሃይሉ ጥናት ተደርጎበት በመሻሻል ላይ ካሉ ህጎች መካከል አንዱ የጸረ ሽብር ህጉ ነው።
ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዐቃቤ ሕግ ከባድ በተባሉ ወንጀሎች ተጠርጥረዋል ብሎ በያዛቸው ሰዎች በሚመለከት በጸረ ሽብር ሕጉ መሰረት የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ለመጠየቅ ፍርድ ቤት አመልክቶ በእዛ መሰረት ተጨማሪ የማሰሪያ ጊዜ እየተፈቀደለት የቆየ መሆኑን ተመልክተናል። በእኔ አስተያየት በእዛ በተነቀፈ፣ በተወገዘና እንደሚሻሻል ታምኖበት በመሻሻል ላይ ባለ ሕግ አማካኝነት የተጨማሪ ምርመራ የእስር ጊዜ መጠየቅ ትክክል ነው ብዬ አላስብም። ስህተት ነው። ነገር ግን መታወቅ ያለበት ሌላው ነገር ደግሞ ፖሊስ ምርመራውን ማጠናቀቅ የሚያስችለውን ጊዜ መጠየቁ ነው። የማውቀው በሕጉ መሰረት የቀረበ ክስ መኖሩን አላረጋገጥኩም፤ ያለም አልመሰለኝም። ካለም ማወቅ አለብኝ።
እንደሚመስለኝ ፖሊስና ዐቃቤ ህግ ሕጉን የሚጠቅሱት ለጉዳዮቹ ከሰጡት ክብደትና የጸረ ሽብር ህጉ በምርመራ ሂደት ከመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ረዘም ያለ ጊዜ ስለሚፈቅድ ረዘም ያለውን ጊዜ በመጠቀም ምርመራውን ለማጠናቀቅ የበለጠ ይጠቅመናል ከሚል ጉጉት የመነጨ ይመስለኛል። በመሆኑም ከመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ከመጠየቅ ይልቅ በጸረ ሽብር ሕጉ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየጠየቁ መሆኑን ተረድቻለሁ። በእኔ እምነት ግን ይህም ቢሆን ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቂያ ምክንያት መሆን አልነበረበትም።
አሁንም ተስፋ የማደርገው ዐቃቤ ሕግ ክስ ለማቅረብ የሚፈልገው በወንጀል የጠረጠራቸው ሰዎችን በመደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ክስ ያቀርባል ብዬ አስባለሁ። የሆነ ሆኖ ግን አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር በጸረ ሽብር ሕጉ መሰረት ሊቀርብ የሚገባ ሕግ አለ ብዬ አላምንም። የኢትዮጵያ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ደግሞ የማይሸፍናቸው የጥፋትና የወንጀል አይነቶች የሉም። ስለዚህ ተፈጽሟል ተብሎ የሚታሰብና የሚታመን በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል ወንጀል ካለ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ነው መታየት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ከሚነሱበት የህግ ክፍተቶች አንዱ በጥቆማም ሆነ በተነሳሽነት የሚቀርቡለትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ መረጃውን ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ ከማድረግ ውጪ ሌላ ሚና አለመኖሩ የተሟላ አያደርገውም ብለው የሚተቹ አሉና እርስዎ ጉዳዮን እንዴት ይመለከቱታል?
ዶክተር ዳንኤል፡- ከዚህ በፊት ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ ምርመራ አካሂዶ የምርመራ ውጤቶቹንና ምክረ ሃሳቦቹን ለሕዝብ ሳይሆን ይፋ ሲያደርግ የነበረው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለመንግስት ብቻ ነበር የሚያሳውቀው። ግን ይህ የተሳሳተ አሰራር ነበረ። በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ኮሚሽኑ ይህንን እንዲያደርግ የሚል ነገር አልነበረውም። ይሄ ከኮሚሽኑ የተሳሳቱ ወይንም መጥፎ አሰራሮች፣ ባህሎችና ልምዶች ውስጥ አንዱ ነበረ። ሕጉ ግን ይህንን አይደግፍም።
ይልቁንም ሕጉ በግልጽ የሚያስቀምጠው ሆነ ማናቸውም የሰብአዊ መብት ተቋሟት እንዲያደርጉ የሚጠበቀው ጥናትና ምርመራ ማድረግ፣ በሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ ላይ ጥሰት ተፈጽሟል ተብሎ በባለሙያ አቤቱታም ሆነ በራስ አነሳሽነት በሚደረጉ ምርመራዎች መሰረት የሚገኙ ውጤቶችንና ምክረ ሃሳቦችን በይፋ ለሕዝብ ማሳወቅ ነበር ህጉ የሚደግፈው። በይፋ መታወቅ ያለበት ወደፊትም የምንሰራው በእዚህ መንገድ ነው። ግኝቶች በሙሉ ይፋዊ መግለጫ ነው የሚሆኑት።
ይህ ማለት ኮሚሽኑ ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይፋዊ ባልሆነ መንገድ አይገናኝም፣ አይወያይም ነገሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት አያደርግም ማለት አይደለም። ያንን ዘዴም እንጠቀማለን። ዋናው የሚፈለገው የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንዲሻሻል፣ እንዲለወጥ ወይም በተደጋጋሚ እንዳይፈጸም ተገቢው የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አጥፊዎችንም ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግ ሁል ጊዜ የግድ እያንዳንዱ ጉዳይ በሙሉ በአደባባይ መመዘገብ አለበት ማለት አይደለም።
እንዳስፈላጊነቱ ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ የሚመለከተውን መስሪያ ቤት ኃላፊ በመጥራት በማነጋገር፣ ምክረ ሃሳብ በመስጠት፤ ጉዳዮ እንዲለወጥ እንዲሻሻል የማድረግ ስራ እንሰራለን። ከዚህ በተጨማሪም እንደየነገሩ ሁኔታ ዋና ዋና የምርመራ ግኝቶችና ውጤቶቻችን እንዲሁም ምክረ ሃሳባችንን አስፈላጊ በሆነ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያለንን አስተያየት በይፋ ለህዝብ የሚገለጽ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብርን ከማስፈጸምና ከመከታተል አንጻር ሚናችሁ ምንድን ነው? ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ በአስፈጻሚው አካል ተጽእኖ ስር ወድቋል ብለው የሚተቹ አሉ ምን አስተያየት አለዎት ?
ዶክተር ዳንኤል፡- የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ሰነዱ የመንግስት መርሃ ግብር ነው። መንግስት ስል የስራ አስፈጻሚው አካል ማለቴ ነው። ይህ ማለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ልዮ ልዮ የመንግስት ተቋማትን ይጨምራል። ስለዚህ ያ የድርጊት መርሃ ግብር እነዚህ ሁሉ የመንግስት የስራ አስፈጻሚ አካላት በእለት ተዕለት ስራቸው የሰብአዊ መብትን እንዴት እንደሚያስከብሩ፣ እንደሚያስጠብቁ የሚመሩበት የድርጊት መርሃ ግብር ነው።
የኮሚሽናችን አላማ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላት ያንን የድርጊት መርሃ ግብር እንዴት ስራ ላይ አዋሉት ወይም አላዋሉትም። እንዴት ስራ ላይ ሊውል ይገባል የሚለውን ስልታዊ በሆነ መንገድ ይከታተላል። ይህንን በአዲስ መልክ መስራታችንን እንቀጥላለን።
መንግስት ሰብአዊ መብትን እንዴት እንደሚያስከብርና እንደሚያስፈጽም የድርጊት መርሀ ግብር መኖሩ ተገቢ ነው። በመንግስት ተጽእኖ ያረፈበት ብቻ ሳይሆን ሰነዱ የመንግስት ሰነድ ነው፣ የመንግስት መሆንም አለበት። መንግስት ሰብአዊ መብትን እንዴት እንደሚያስከብርና እንደሚያስፈጽም ያወጣው መርሀ ግብር ነው።
የመንግስት ተጽእኖ ያረፈበት ነው የሚለው ትንሽ ብዥታ ያለው ይመስለኛል። ሰነዱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አውጥቶት መንግስት የሚመራበት ተደርጎ ታስቦ ከሆነ የተሳሳተ ነው። መንግስት ሰብአዊ መብትን እንዴት እንደሚያስተገብርና እንዴት ስራ ላይ እንደሚያውል የሚያወጣው የራሱ መመሪያ ነው። የእኛ ሚና መርሃ ግብሩን በማጎልበት ሂደት በማማከርና ሃሳብ በመስጠት ልናግዝ እንችላለን። ዋነኛው ሚናችን ግን መንግስት ቃል የገባበትን የድርጊት መርሃ ግብር፣ ግዴታና ኃላፊነቱ የሆኑትን በህገ መንግስቱና በአለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ስምምነት የተመለከቱትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዴት እያከበረ እንደሆነና እንዳልሆነ ስልታዊ በሆነ መንገድ መመርመርና መከታተል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት የተለያየ መልክ ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ ብለው የሚናገሩ አካላት አሉ።እውን ሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሉ ወይ ? ይህንን ጉዳይ ከመከታተልና ከመከላከል አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው?
ዶክተር ዳንኤል፡- በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት አሁን ዋነኛው ትኩረታችን ኮሚሽኑን ከተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር በአዲስ መልክ ማደራጀት፣ ማዋቀር፣ ማጠናከርና አቅም መገንባት ላይ ነው። ሰፋ ባለና
ስልታዊ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት አያያዝን ምርመራና ክትትል የማድረግ ስራ በሙሉ አቅም አልገባንበትም። የሚፈለገውን አይነት ስራ ለመስራት መጀመሪያ አቅም ያለው ተቋም መገኘት አለበት። ይህ ማለት ግን በዕለት ተዕለት ስራችን የሰብአዊ መብት ችግሮችን አንመለከትም ማለት አይደለም። በተወሰነ መጠን ዋና ዋና መስለው በሚታዮ የሰብአዊ መብት አሳሳቢጉዳዮች ላይ መጠነኛ የሆነ ክትትል ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው። የተወሰኑ ስራዎችን ግኝቶችንና ምክረ ሃሳቦቻችንን ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማሳወቅ በተጨማሪ አንዳንዶቹን ግኝቶችና ምክረ ሃሳቦችን በይፋ ጭም ር ማሳወቅ ጀምረናል።
አዲስ ዘመን፡- ከግኝቶችና ምክረ ሃሳቦቻችሁ መካከል ሊጠቅሱልኝ የሚችሉት ካለ?
ዶክተር ዳንኤል፡- በአዲስ አበባ ከተማና ከከተማ ውጪም በእስር የሚገኙ ሰዎችን ጎብኝተናል። በእዚህ ሂደት ውስጥም ስለእስር ቤቶች አያያዝና ስለተለያዮ አሳሪዎች ታስረው ስለሚገኙበት ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርገናል። በተለይም በፖለቲካ አቋማችን፣ በፖለቲካ ስራችን፣ በአስተሳሰባችን፣ በሙያችን ጋር በተያያዘ ነው የታሰርነው እንጂ መንግስት እንደሚለው በሌላ ወንጀል የታሰርን ሰዎች አይደለንም ብለው ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ጉዳይ በሚመለከት ጉዳያቸው ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ጥረት አድርገናል።
ያደረግናቸው ጉብኝቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በተለመደው መሰረት የቅድሚያ ማስታወቂያ ሳይሰጥ በድንገት የተደረገ ጉብኝት ነበረ። ማረሚያ ቤቶቹም ያለቅድሚያ ማስታወቂያ ተቀብለው አስተናግደውናል። ገብተን የእስር ቤቶቹን ሁኔታም ለማየት ችለናል። የታሳሪዎች ጉዳይ በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ለማየት ችለናል። በኮሚሽኑም ውስጥ ስልታዊ ክትትል የሚያደርገው የስራ ቡድንም በተለያዮ እስር ቤቶች አስቀድሞ ማስታወቂያ እየሰጠም ጭምር ስልታዊ ክትትል ማድረጉን ቀጥሏል። የሰብአዊ መብት ግንዛቤ ማስፋትም ቀጥሏል። የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል ብለው አቤቱታ ከሚያቀርቡ ሰዎችም የመመርመርና የማጣራት ስራዎች ቀጥለዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ ከተማና ከከተማ ውጪም በእስር የሚገኙ ላይ ድንገተኛ ጉብኝት ያደረጉባቸውን ስፍራና እነማን እንደሆኑ ሊገልጹን ይችላሉ?
ዶክተር ዳንኤል፡- በአዲስ አበባ ከተማ ድንገተኛ የእስር ቤትና የታሳሪዎች ጉብኝት ያደረግኩት በፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ተጠርጥረው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስር በአደራ እስር ይገኛሉ የተባሉትን ተጠርጣሪዎችን ነው። ለምሳሌ ደጋፊዎቻቸው፣ ድርጅታቸውና ራሳቸውም እስሩ ከፖለቲካ ስራችን ጋር በተያያዘ ነው ብለው የሚያምኑትንና መንግስት ደግሞ በፖለቲካ ስራቸው ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከተከሰተው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው የሚላቸውን የአብን የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባሎችን ነበር።
የምርመራ ስራው በዐቃቤ ሕግ በኩል መከናወን አለበት። ነገር ግን የእስር ሁኔታና ጉዳያቸው የሚገኝበትን ሁኔታ ለማጣራት እስረኞቹን ተመልክተናል። በሌላ በኩልም መንግስት ከእዚሁ ግድያ ጋር ተጠርጥረው ተይዘዋል የሚላቸው ግን የፖለቲካ ወይንም የሲቪል ማህበረሰብ ጓደኞቻቸው ደግሞ በስራቸው ምክንያት ኢላማ ተደርገዋል ብለው የሚያምኑት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የባልደራስ ምክር ቤት አባላት የሚባሉትን እስረኞችን ጎብኝተናል።
በሌላ በኩልም መንግስት ከኦነግ ሸኔ ቡድን ጋር በተያያዘ የወንጀል ተግባር ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ ያሰራቸው ነገረግን ታሳሪዎቹ ደግሞ አንድ አከራካሪ መጽሐፍ በመጻፍ ሂደት በነበረን ተሳትፎ ነው ተጠርጥረን የታሰርነው የሚሉ ሰዎችን እንዲሁም የመጽሐፉ ጸሐፊ ነው ተብሎ የተጠረጠረ ነገር ግን መጽሐፉን አልጻፍኩም ብሎ የሚልን ሰውና ሌሎችም በመጽሐፉ ህትመት ውስጥ የተለያየ ሚና የነበራቸው የማተሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ የሆነ ሰው፣ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ሰው፣ መንገድ ላይ መጽሐፉን የሸጠ ሰው በሌላ ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ አይደለንም ብለው የሚሉ ሰዎችንና የመሳሰሉ ጉዳዩችን ለመመልከት ችዬ ነበረ።
ከአዲስ አበባ ወጪም ለምሳሌ ብጠቅስ በሲዳማ ጥያቄ ጉዳይ ሐዋሳ ከተማና ሲዳማ ዞን ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ረብሻ የተነሳ በተፈጠረው ግድያና ንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ ረብሻውን በማንቀሳቀስና በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ነገር ግን ሰዎቹ በሲዳማ ጥያቄ ውስጥ በነበረን የመሪነት ሚና ከፊሎቹ ደግሞ በሚዲያ ስራ በነበረን ሚና ምክንያት ታስረናል የሚሉ ሰዎችን ጉዳይ ተመልክቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) አመራሮችና አባላት ጉዳይ ሲነሳ የቀድሞው ተሞክሮ ቀጥሏል የሚል ቅሬታ እየተነሳ ነውና በጥቅሉ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር ዳንኤል፡- ይህንን ጉዳይ ኮሚሽኑ ምንም እንኳን ስልታዊ ክትትልና ምርመራ ባያደርግበትም በተወሰነ መልኩ ጉዳዮን ለማጣራት ባደረግነው ሂደት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከጎበኘናቸው እስረኞች ውስጥ ቢያንስ ሶስት ሰዎች በጋዜጠኝነት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች መኖራቸው እጅግ አሳስቦኛል (ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው ጥቅምት 18 ቀን ማለዳ ላይ ሲሆን በዕለቱ ታስረው የነበሩት ተፈትተዋል)።
እርግጥ መንግስት የተጠረጠሩበት ሌላ ወንጀል አለ የሚለውን ብገነዘብም እስካሁን ተጠርጣሪዎቹ ላይ ከተደረገው የምርመራ ስራና ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንጻር አብዛኛው ከመደበኛ ስራቸው ጋር የተገናኘ ስለሚመስል ጋዜጠኞቹ እስር ላይ መሆናቸው እጅግ አሳስቦኛል። ሌሎችም ታሳሪዎች የእስር ሁኔታቸው ከመደበኛ የፖለቲካ ወይንም የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋች ስራቸው ጋራ የተያያዘ ሆኖ ከተገኘ እጅግ አሳሳቢ ነው።
የእኔ አስተያየት እጅግ ያሳሰቡኝ ሁለት ነገሮች በአንድ ወንጀል የተጠረጠረ ሰው መንግስት ወንጀል ፈጽሟል ብሎ የሚያምን ከሆነ ወንጀሉን የመመርመር፣ የማጣራትና ተገቢውን ክስ የማቅረብ ተግባርና ኃላፊነት አለው። ይህ አይካድም የታሰሩት ሰዎችም ቢሆኑ መንግስት የዚህ አይነት ኃላፊነት እንዳለው አይክዱም። ሆኖም እየተለመደ የመጣው የሆነው አሰራር ጉዳዮን ከማጣራትና የተጠረጠሩ ሰዎችን በቂ ማስረጃ ሲገኝባቸው ከመክሰስና ከማሰር ይልቅ አስቀድሞ ማሰርና የምርመራና የማጣራት ሂደት ማካሄድ አንዱ ነው። ይህ አዲስ ከተፈጠረው የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር ተገቢ አካሄድ አይደለም።
እንደሚታወቀው ቃል ተገብቶ የነበረው፣ ትክክለኛና ሊሆን የሚገባው ነገር ከባድ ወንጀል ሲፈጸም ካልሆነና በህግ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ካልሆነ በስተቀር አንድን ሰው አስሮ ሳይሆን መመርመርና ማጣራት የሚያስፈልገው ከእስር በፊት ነው። ስለዚህ አሁን ሰዎችን አስረን ምርመራ እናካሂዳለን የሚለው ከዚህ በፊት የነበረው የምርመራ ስራ እየተለመደ እንዳይሄድ አሳስቦኛል። ሁለተኛው ከታሳሪዎቹ ከፊሎቹ የፖለቲካ፣ የሚዲያና በሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋችነት ስራ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች መሆናቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ሌላው የሚያሳስበኝ ጉዳይ የጸረ ሽብር ሕጉ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያት መሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ እነዚህ የተለያዮ ታሳሪዎች ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር በሕግ የሚፈቀደው ምርመራውን የማጠናቀቂያ ጊዜ የአንዳንዶቹ እስረኞቹን በሚመለከት ተገባዷል፤ አንዳዶቹ ደግሞ ሙሉ ጊዜው አልቋል። ይህ ከሆነ ታሳሪዎቹ ወይም ተአማኒ በሆነ ክስ መከሰስ አለባቸው ወይንም የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ወይም እንደአግባብነቱ ያለዋስትናም ቢሆን ከእስር ሊለቀቁ ይገባል። ይህ የማይፈጸም ከሆነ ደግሞ ይህም ያሳስበኛል።
በእርግጥ መንግስት አሁን አገሪቱ ውስጥ ከተፈጠረው ጠቅላላ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በሚፈለገው መጠን የወንጀል ጉዳዮችን በአጭር ጊዜ ለማጣራትና ፍርድ ቤት የማቅረብ አቅም ውስን ሊሆን ይችላል። ብዙ ቦታዎች ውስብስብ የሆኑ ጥፋቶች እየተፈጠሩ ስለሆነ የእዚህ አይነት ተግዳሮት ሊኖር እንደሚችል ይገባኛል። ይህ ማለት ግን የሰዎች መሰረታዊ መብቶቻቸው ሊከበሩ አይገባም ወይም ሊጣሱ ይገባል ማለት ስላልሆነ በተቻለ መጠን የመንግስት የወንጀል ምርመራና ማጣራት ስራ በተለይ ዋነኛ በሚባሉ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ማተኮርና ሰዎች አላግባብ እንዳይጉላሉ የዋስትና መብትም መከበር አለበት ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይታይባቸው የነበሩ ዘርፎች ከለውጡ በኃላስ ምን ያህል መሻሻል ታይቶባቸዋል?
ዶክተር ዳንኤል፡- በእኔ እምነት ጥሩ እርምጃ ነው ተብሎ የሚገለጸው አሁን ድረስ በእስር ቤቶች ካደረግነው ክትትል ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች ካደረጉት ስልታዊ ክትትል ከተገኘው መረጃ በመነሳት እኔ እራሴም ታሳሪዎችን በማነጋገር ለመረዳት የቻልኩት ከእዚህ በፊት ይሰማ የነበረና ታሳሪዎች ላይ ይፈጸም የነበረ የአካል ጥቃት አሁን አይሰማም።
ታሳሪዎች ረጅም ጊዜ አላግባብ ቆይተናል፣ እስር ቤት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፣ የፍርድ ቤት ሂደቱ በሚገባው መጠን እየተፋጠነ አይደለም፣ የታሰርነው አላግባብ ነው ከሚሉ ቅሬታዎች ውጪ በእስር ቤት የእዚህ አይነት የአካል ጥቃት ደረሰብን የሚል አቤቱታ አልሰማንም። ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ይታወቁ የነበረው በአካል ጥቃት በማድረስ፣ አሰቃቂ የማሰቃየት ተግባር በመፈጸም ጭምር ነበረ። ይህ ከእንግዲህ ሊፈጸም፣ ሊሰማም የሚገባው አይደለም። ይህ አንድ መሻሻል ነው።
በሌላ በኩል ታሳሪዎች ከወዳጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ከዘመዶቻቸው፣ ከህግ አማካሪዎ ቻቸው ወይም ከሃይማኖት አባቶቻቸው ጋር በማንኛውም ጊዜ በነጻነት የመገናኘትና የመጎብኘት መብት እንዳላቸውም ተገንዝበናል ይህም ጥሩ መሻሻል ነው። መሻሻሎች አሉ ግን ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉም አይካድም። የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታ በተለይ ማረሚያ ቤቶች በተቻለ መጠን ደረጃቸውን ከሚጠበቀው አለም አቀፍ መስፈርት ጋር ለማስተካከል ጥረት እየያደረጉ መሆኑን እገነዘባለሁ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአቅም ውስንነት የተነሳ አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶችና እስር ቤቶቻችን በአለም አቀፍ ደረጃ በሚጠበቀው ልክ የተሟሉ እንዳልሆነ ይታወቃል።
ማረሚያ ቤቶቹ በተለያየ ደረጃ ላይ ናቸው። መሰረታዊ የሆኑ የአቅርቦት ችግር አለባቸው። የተሟላ የመታጠቢያ ቤት፣ መመገቢያ ስፍራ፣ ክፍሎቹ እስረኞቹን በበቂ ሁኔታ የሚያስተናግዱ አለመሆናቸው፣ እስረኞቹ ጤንነታቸውን ጠብቀው ለመኖር በሚያስችላቸው አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት በቂ ቦታ አለመኖር፣ የተሟላ የጤና እና የምግብ አቅርቦት በሚመለከት አብዛኞቹ እስር ቤቶች እነዚህን መስፈርቶች አያሟሉም። ይህ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ሊያያዝ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ እየተከሰተ ካለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ የሚሉት ነገር ካለ ?
ዶክተር ዳንኤል፡- በተወሰነ መልኩ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የሰብአዊ መብት ቀውስ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ የፖለቲካ ቀውሱ ውጤት ነው። ስለዚህ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሻሻል የሚችለው የፖለቲካ ቀውሳችን እስከ ተፈታ ድረስ ነው። የፖለቲካ ቀውሱ መፍትሄ ካላገኘ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታው አይሻሻልም።
ይሁንና ቅርብ ጊዜ አዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ከተሞች ላይ የተከሰተው ውዝግብና አመፅ የተቀላቀለበት ነውጥ በይዘቱም በውጤቱም ትንሽ ለየት ያለ ነው።ለየት የሚያደርገውም የህግ የበላይነትን በአደባባይ የተገዳደረ ክስተት መሆኑ ነው። በዚህም ሂደት ቁጥራቸው ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች እስካሁን ድረስ መሞታቸው ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ ወደ 10 የሚያህሉት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግብግብ በጥይት ተመተው የሞቱ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታና ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በየቤታቸው፥ በየመንገዱ ላይ በዱላና በስለት ተደብድበው የተገደሉ ሰዎች ናቸው። ሌሎችም ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ እና መካከለኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የግለሰቦች የህዝብ የመንግስት ንብረት በእሳት ተቃጥሎ እንዲወድም ተደርጓል።
የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ ተጠቅተዋል፣ ወድመዋል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ስንመለከታቸው በጣም አሳሳቢ የሆነ የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያ ናቸው። ይህም የህግ የበላይነትን በከፍተኛ ሁኔታ ተፈታትኗል። ስለዚህ በዚህ ጥፋት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ መቻል አለበት። በምርመራ ሂደት ውስጥ ንፁህ ሰዎች ተቀላቅለው እንዳይጠቁ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብዬ አምናለው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ኢትዮጵያ በለውጥ ላይ የሚገኙ አገራት አንዳንድ ችግሮችን ለማረም ሲባል የሽግግር ፍትህ (Transitional justice) ሊተገበር ይገባል የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህ ምን ማለት ነው?
ዶክተር ዳንኤል፡- የሽግግር ወቅት የፍትህ አስተዳደር ወይንም (Transitional justice mechanism) ብዙ አገሮች ከአንድ ግጭት ወጥተው በተለይ የእርስ በእርስ ግጭት የነበረባቸው አገሮች ከእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ወጥተው ወደ ሰላማዊ አስተዳደር በሚገቡበት ጊዜ ወይንም ጨቋጭ የነበረ የፖለቲካ አስተዳደር የነበረበት አገር ውስጥ ከፖለቲካ አስተዳደሩ በመውጣት ወደ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ አስተዳደሩ በሚደረገው የሽግግር ጊዜ ያለፉትን የእርስ በእርስ ጦርነት ወይንም ጨቋጭ የፖለቲካ አስተዳደር ጊዜ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚመለከት ፍትህ አካሄድ ነው። መደበኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በሚደረግባቸው ዴሞክራሲያዊ አስተዳደሮች ውስጥ ማንኛውም አይነት ወንጀል ሲፈጸም በመደበኛው የወንጀል አስተዳደር ስርዓት ይተዳደራል። አጥፊዎች ይጠየቃሉ፣ ነጻ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ይረጋገጣል።
ግን ሰፊና ውስብስብ የሆነ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የነበረ ወይም ሰፊና ውስብስብ የነበረ ጨቋኝ የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ እጅግ በጣም ሰፊ፣ ውስብስብ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲከናወንበት የነበረ አገር ውስጥ ከእዛ ምዕራፍ ወጥተህ ወደ አዲስ ምዕራፍ በምትሸጋገርበት ጊዜ ባለፈው ምዕራፍ ወቅት ተፈጽመው የነበሩ ነገሮችን ምን ይደረጋሉ? የሚለው ውስብስብ ይሆናል። ይህ ውስብስብ የሚሆነው ከሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ ውስብስብነትና ጸባይ አንጻር ነው። አንዳንድ ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጻሚው በሌላ መልኩ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባም ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩም የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰፊና ብዙ ቁጥር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ለመደበኛው የወንጀል አስተዳደር ከባድና ውስብስብ ይሆናል። ይህንን ችግር ለመፍታት ብዙ አገሮች የሽግግር ወቅት የፍትህ አስተዳደር የሚል ጽንሰ ሃሳብ ይተገብራሉ።
የሽግግር ወቅት የፍትህ አስተዳደር አራት መሰረታዊ አላማዎቹ አሉት።ባለፈው የፖለቲካ ምዕራፍ ተፈጸመ የተባለው ነገር እውነት ስለመፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ እውነትን ማውጣት (discovery of the truth) አንዱ ነው፣ ፍትህን ማረጋገጥም ሌላው ዓላማው ሲሆን፤ ከባድ የሆነ የጥፋት ወንጀል የፈጸሙና በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂነታቸው ሊረጋገጥ የሚገባቸውን ሰዎች ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጥ ነው። ጉዳተኞችን መካስና መጠገን ሶስተኛው ዓላማው ነው።
ባለፈው የፖለቲካ ምዕራፍ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው፣ የሞቱ ሰዎች፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ንብረታቸው የተወሰደባቸው ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ ጉዳተኞች ከፊሎቹ በህይወት የሉም፤ ከፊሎቹ ግን አሁንም ያሉና የአካላዊና የስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ጉዳተኞች መካስ፣ መጠገንና መታገዝ አለባቸውና ይህንን ማድረግ መቻል ነው። አራተኛው ደግሞ ለሰብአዊ መብት ጥሰቱ ምክንያት የነበሩ ህጎችን ፖሊሲዎችን፣ልምዶችንና አሰራሮችን ማጥናትና በድጋሚ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት እንዳይሆኑ እንዲሻሻሉ ማድረግ ማለት ነው።
ይህ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ። ኃላፊነቱ የተሰጠው በአብዛኛው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ነው። ባለፈው አስተዳደር ውስጥ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ችግሮችን ለማጣራትና የመፍትሄ ሃሳብ ለመፈለግ ኃላፊነት የተሰጠው ይህ ተቋም ነው።
የሽግግር ወቅት ፍትህ የሚባለው አንደኛው አስተሳሰቡም ሰላምን ማረጋገጥና ህብረተሰብን ወደፊት እንዲሄድ ማስቻል ነው።ባለፉ በደሎች፣ጥፋቶችና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ታስረህ ሳትቀርብ ካለፈው ታሪክህ ጋር ታርቀህ ፍትህን አረጋግጠህ ህብረተሰብ ወደፊት መሄድ አለበት። ሁል ጊዜ ባለፈው ታሪክና ሁኔታ እስረኛ ሆነህ መቅረት የለብህም።
ኮሚሽኑ ራሱን በማደራጀት ሂደት ውስጥ እንዳለ አውቃለሁ ይህንን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ውጤቱን በቅርቡ እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በሌላ በኩልም መንግስት ባለፈው የፖለቲካ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያላቸው ሰዎች ላይ ክስ አቅርቦ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ርምጃ መጀመሩ ይታወቃል። ምንም እንኳን የፖሊሲ ሰነድ ባይቀመጥለትም የሽግግር ፍትህ አስተዳደር አካል ናቸው የሚባሉ ርምጃዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መወሰድ ተጀምሯል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ!
ዶክተር ዳንኤል፡- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
ዘላለም ግዛው