
ሁለተኛው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወደ ሥራ ከገባ ሰሞኑን አንድ ዓመት ይሞላዋል። በእዚህ መነሻ ይህን ዘካሪ መጣጥፍ ጫጫርሁ። እንደ ሀገር ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ጀምሮ እያለፍንባቸው ያሉ ፈተናዎች መነሻቸው የባጀ የከረመ ነው። የዛሬ አጀንዳዬ ትኩረት ኢኮኖሚው ስለሆነ በአብነት ላንሳ።
ከድህረ 97 ምርጫ ማግስት ኢህአዴግ መራሹ አገዛዝ አዋጭነታቸው በጥልቀት ያልተጠኑና ያልተተነተኑ ፕሮጀክቶችን አዥጎደጎደ። ይህ አልበቃ ብሎት ብዙዎቹ በተያዘላቸው በጀትና በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ባለመጠናቀቃቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኑበት። የስኳር ፋብሪካዎች፣ የባቡር መንገዶች፣ አውራ መንገዶች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የግድብና መስኖ፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ ወዘተርፈ በከፍተኛ የውጭ ኮመርሺያል ብድር፣ በብሔራዊና ንግድ ባንከ ብድር ወይም መንግሥት ከፍተኛ ብር አትሞ ወደ ገበያው ይበትን ወይም ይረጭ ስለነበር ሀገሪቱን ለዋጋ ግሽበት ለኑሮ ውድነት ለፊስካልና ሞኒታሪ ፖሊሲ መጣረስና መዛነፍ ዳርጓል።
በአናቱ የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት ችግሩን አባብሶታል። በእነዚህ አስገዳጅ ሁኔታዎች ነው የለውጡ መንግሥት ወደ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የገባው። ይህን ስል አሁንም ብልጽግና የኢህአዴግን ስህተት እየደገመው ነው የሚለውን ትችት ባላየ ባልሰማ ማለፍ አልችልም። አሁንም አዋጭነታቸው ባልተረጋገጠ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ገንዘብ እየወጣ መሆኑ ማሻሻያው ላይ የሚነሳ ጥያቄ ነው። ሌላው በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱ ጦርነቶች ለማሻሻያው ፈተና መሆናቸው አይካድም።
ሰሞነኛው የዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ሪፖርትም ይህን ስጋት ይፋ አድርጓል። በመደበኛና በትይዩ ገበያው ያለው የውጭ ምንዛሬ ግብይት ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ፤ ማሻሻያውን ተከትሎ በሕዝቡ ላይ የፈጠረው ያለው ጫናም ሌላው ስጋት ነው። ከአነ ውስንነቶቹ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከባሰና ከከፋ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ሀገሪቱን መታደጉ ሳይካድ አሁንም ትኩረትና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች አሉ። በተለይ የሰላሙ እና የዜጎች የመሸመት አቅም ከእለት ወደ እለት እየተዳከመ የመምጣቱ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል። ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልሁ የማሻሻያው ምንነት መለስ ብለን እንቃኝ።
የ2010 ዓ.ም የፖለቲካ ለውጥን ተከትሎ መንግሥት አያሌ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራትን አከናውኗል። ባለፉት ጊዜያት የተከማቹ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት ላለፉት ስድስት ዓመታት ማሻሻያዎችን ሲያደርግ እንደቆየ ይታወቃል። የዕዳ ጫና፣ ገና ብዙ ሥራ የሚፈልገው የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ አዝጋሚ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ዝቅተኛ የዘርፎች ምርታማነት፣ ዝቅተኛ የልማት ፕሮጀከቶች አፈጻጸምና የሀብት ብክነት፤ የተረከባቸው ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዕዳዎች ናቸው።
የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ሂደቶቹ ኢኮኖሚው ወደ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሸጋገር አዲስ ተስፋን አምጥተዋል። በ2011 በጀት ዓመት ወደ ትገበራ የገባው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ብዙ የፖሊሲ ሃሳቦችን በውስጡ ያካተተ እና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዓላማዎችንና ግቦችን ያሳካ ነበር። ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማረም፣ የዕዳ ጫናን ለማቃለል፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጮችን ለማስፋፋት፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለማረም በተደረገው ጥረት ውጤቶች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ ካሉ ሀገራት አንዷ ሆናለች። ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት 7.1 በመቶ ደርሷል። በዚህም ሀገራችን በአፍሪካ ኢኮኖሚ ምህዳር ጉልህ ሚና ያላት ሀገር ለመሆን በቅታለች። ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያላትን ቁርጠኝነትም አሳይታለች። ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ ገንብታለች። ከሰሃራ በታች ካሉ አፍሪካ ሀገራት የሦስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤትም ሆናለች። መንግሥት የግብር ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ ተሻሽሏል።
ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ቀሪ የማክሮ ኢኖኮሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ፕሮግራም በአራት ምሰሶዎች ላይ የተገነባ ነው፦
(1) የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሕቀፍ መመሥረት፤
(2) ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣
(3) የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር እና
(4) ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደግ ናቸው።
የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳችን ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት ይሆናል። ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። የውጭ ምንዛሪ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤማነት በማሻሻል፣ የመንግሥት ዕዳ ዛላቂነትን በማረጋገጥ፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት ትልቅ ሀገራዊ ግብ ተጥሏል።
ባለፉት ዓመታት፣ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ትግበራ ከፍተኛ የፋይናንስ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ጥረቶችና ድርድሮች ሲደረጉ ቆይተዋል። ድርድሮቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆኑን ለማረጋገጥ በእውቀትና በብስለት እንዲመሩ ተደርገዋል። በዚህም መንግሥት ባስቀመጣቸው ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዓላማዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ቅደም ተከተል መሠረት ስምምነት ላይ ለመድረስ ተችሏል።
ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንከ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፍ ነው። የተመሠረተውም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን እና በመካከለኛው ዘመን የኢንቨስትመንትና የልማት እቅዳችን ላይ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ቁልፍ ዓላማዎችና ግቦች፡-
(1) የውጭ ምንዛሪ መዛባትን ማስተካከል እና የረጅም ጊዜ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጉድለት ችግሮችን መፍታት፣
(2) የገንዘብ ፖሊሲ ማሕቀፉን በማዘመን የዋጋ ንረትን መቀነስ፣
(3) የዕዳ ተጋላጭነትን በመፍታት እና የሀገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል መፍጠር፣
(4) የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነት፣ ተወዳዳሪነትና ጤናማነት ማጠናከር እና
(5) የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ፤ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓትን መገንባት ናቸው።
ከላይ የተዘረዘሩትን ግቦች ለማሳካት የሀገር ውስጥ ተቋማትን ማጠናከር እና የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለ ድርሻ አካላትን በፖሊሲ ማሻሻያ አተገባበሩ ላይ በማሳተፍና ግልጽነት ለመፍጠር ተችሏል። ይሄም ሀገራችን ከፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ጋር ተያይዘው የሚመጡት አዳዲስ የልማት ፋይናንስ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በአግባቡ እንድትጠቀም ያስችላታል። እንዲህ ያለ የትብብር አጋርነትና ቅንጅት ሀገራዊ የግሉ ዘርፍ የሚመራው የዕድገት አቅጣጫ እንዲሳካ ለማድረግ ለግሉ ዘርፍ መጠነ ሰፊ እድሎችን ይፈጥራል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና ርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎችን በተመለከተ፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ለሀገራችን ኢኮኖሚ በርካታ ጥቅሞችን እና ውጤቶችን እንደሚያስገኝ ይጠበቃል። የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎችና የሚጠበቁ ሀገራዊ ፋይዳዎች የሚከተሉት ናቸው:-
በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት፦ የውጭ ምንዛሬ ግብይት በገበያው አማካኝነት እንዲበየን የማድረግ ሂደት ነው። በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ማረጋገጥ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል ይረዳል፣ የገቢ እና የወጪ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ዋጋ ከገበያ እውነታዎች ጋር እንዲጣጣም ያስችላል። በክፍያ ሚዛን ላይ ያለውን አለመመጣጠንም ለማስተካከል ይረዳል። ሌሎችም ጥቅሞች አሉት።
በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት፦ ሌላኛው ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የማሻሻያ ርምጃ የገንዘብ ፖሊሲ ማሕቀፉን ማዘመን ነው። የሦስት ዓመት የብሔራዊ ባንከ ስትራቴጂክ እቅድ ዝቅተኛ እና የተረጋጋ የዋጋ ንረት መኖሩን ማረጋገጥ እንደመሆኑ መጠን፣ ባንኩ ከንግድ ባንኮች ጋር በሚያደርገው የንግድ ግብይት በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እንዲፈጠር ቅድሚያ ይሰጣል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን የፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራ ጀምሯል።
የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፦ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያችን የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን እንዲቀንሱ ያደርጋል። ከላይ ከተጠቀሱ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ትክክለኛ የፖሊሲ መስተጋብር በመፍጠር ማክሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ያደርገዋል። የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያው ዋና ትኩረቱ የመንግሥት ገቢን ማሳደግ፤ የመንግሥት ወጪንና የድጎማ ሥርዓትን ውጤታማ ማድረግ፣ በጡረታ ፈንድ ሥርዓቶች ላይ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን መተግበር፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ተወዳዳሪ ማድረግ እና የመንግሥት ብድር አስተዳደር ውጤታማና አዛላቂ እንዲሆን ማረጋገጥ ናቸው። እነዚህ ርምጃዎች የበጀት አስተዳደር ውጤታማነትን እና የመንግሥት ዕዳ ተጋላጭነትን ያሻሽላሉ። በዚህ የተነሣ የልማት ፋይናንስ አማራጮቻችን ይሰፋሉ። እንዲሁም ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶቻችንን በሀገር ውስጥ አቅም ለማሳካት ምቹ መደላድል ይፈጥራሉ።
የልማት ፋይናንስ እድሎች እና የመንግሥት እዳ አስተዳደር ማሻሻያ፦ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ከተለያዩ አበዳሪዎቻችን ጋር በመነጋገር ከፍተኛ የእዳ ማሻሻያ ርምጃዎችን ለመውሰድ እየተሠራ ነው። በሌላ በኩል ይህ የፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢትዮጵያ አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በተለይም ከዓለም ባንክ፣ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ባንኮች እና ከሁለትዮሽ አበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ መንገድ ይከፍታል። በዚህም መሠረት ሀገራችን በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ትግበራ መሠረት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች። ይሄም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እየጠበቁ ካሉ ከሌሎች የልማት አጋሮቻችን ተጨማሪ የፋይናንስ ድጋፍን ለማሰባሰብም ያግዛል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በብቃት እና በውጤታማነት ለመተግበር መንግሥት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። ከላይ የተዘርዘሩት ዋና ዋና የፖሊሲ ርምጃዎች ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረጅምና የመካከለኛ ዘመን የልማት እቅዶቻችን ጋር ተጣጥመው ይከናወናሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበሩ መንግሥት ከፍተኛ የክትትልና የድጋፍ ማሕቀፎችን ይዘረጋል። ለዚህም በሁሉም በሚመለከታቸው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና በመንግሥታዊ ተቋማት በኩል አስፈላጊ ከትትልና ድጋፍ ይደረጋል። በሁሉም በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል የፖሊሲ ትግበራ አፈጻጸም ወጥነት እንዲኖር መንግሥት ጠንካራ የፖሊሲ ማሻሻያ አመራር መኖሩን ያረጋግጣል።
በሌላ በኩል መንግሥት እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ላሉ ቁልፍ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ተቋማዊ አቅምን ያጠናከራል። እነዚህ ተቋማት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣት፣ በመተግበር እንዲሁም ተጽእኗቸውን በመከታተልና በመገምገም ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። በተመሳሳይ መልኩ መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ድጋፍን ለማሰባሰብ ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር ግልጽነት ያለው ግንኙነት ይፈጥራል።
በተጨማሪም ተጋላጭ የኅብረተሰብ ከፍሎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉ። የማኅበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ድጎማ ይደረግላቸዋል። ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግሥት ሠራተኞች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ሊያስከትሉ ከሚችሉት የአጭር ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ አስፈላጊ የደሞዝ ድጎማና ማሻሻያዎች ለተወሰኑ ጊዜያት ይደረጋሉ። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን መንግሥት በከፊል የሚደጉም ይሆናል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሂደት ቀጣይነት ያለው ግምገማ ይደረግለታል። መንግሥት በወቅታዊ መረጃ ላይ በመመሥረት በፕሮግራሙ ላይ ወቅታዊ፣ አስፈላጊ እና ተገማች የፖሊሲ ማስተካከያዎችን ያደርጋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ-ወጥነት ለመከላከል መንግሥት የነቃ ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ ይወስዳል። የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን በተመለከተ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች በገንዘብ ሚኒስቴርና በብሔራዊ ባንክ በኩል በየጊዜው የሚገለጡ ይሆናል። በወቅቱ ምሁራን ምን ብለው ነበር የሚለውን እንቃኝ።
ለመሆኑ ማሻሻያው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ትርጉም ምንድን ነው? ማሻሻያውን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬስ ምን አንድምታ አለው? ስንል የዘርፉን ምሁራን ጠይቀናል፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተፈራ በሪሁን (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተራዘመ ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ጠግኖ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓትን እንደሚፈጥር ያነሳሉ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚለቅቋቸው ብድሮችና ድጋፎች ለበርካታ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማቃለል ረገድ የሚኖረው ሚና በቀላሉ እንደማይታይ ጠቁመው፣ ይህም በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ገልፀዋል። በተመሳሳይ የምጣኔያዊ ሀብት ከፍተኛ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርህ ተስፋ (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም ብለዋል። ኢትዮጵያ ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር አንዳንድ የኢኮኖሚ ምሶሶዎችን ማስተካከል የውዴታ ግዴታ እንደሚሆንና አሁን የተደረሰበት ውሳኔም ተገቢነት ያለው መሆኑን አክለዋል።
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ሲመቻቹ መቆየታቸውን የጠቀሱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ለአብነትም በመቋቋም ሂደት ላይ ያለው የካፒታል ገበያ ሥርዓት አንዱ እንደሆነና ይህም ኩባንያዎች ካፒታል በሚፈልጉበት ጊዜ ባንክ ሄዶ መበደር ብቻ ሳይሆን ገበያ ውስጥ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበትን እድል የሚሰጥ አሠራር መሆኑን ያስረዳሉ። በተለይ ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶች በአክሲዮን ሽያጭና ግዢ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ እንደልብ መንቀሳቀስ የሚችልበትን እድል የሚፈጥር አሠራር መሆኑን አብራርተዋል። ይህ አሠራር ኢትዮጵያ ያሏት የተፈጥሮ ሀብቶች አግባብና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚችሉበት ልክ ወደ ጥቅም የሚገቡበትን መንገድ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
እንደ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የሚፈጠረው ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ የውጭ ባንኮች መዋዕለ ነዋያቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ በር ይከፍታል። እንደ ውሃ፣ መሬት፣ ማዕድን የመሰሉ ኢትዮጵያ ባሏት ሀብቶች ላይ በሰፊው እንዲሰማሩ ያስችላል፤ ይህም ከፍተኛ ልምድና የገበያ ሰንሰለት ያላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረትን እንዲመርጡ በማድረግ ከፍተኛ በሆነ ደረጃ የውጭ ንግድ ዘርፉን ያሳድገዋል ብለዋል። ገበያ መር በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ቋሚ የገንዘብ ዋጋ አይኖርም ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ብር በዶላር ያለው ዋጋና የወለድ ምጣኔው በየጊዜው ከፍም ዝቅም ሊል እንደሚችል ጠቅሰው፣ ማሻሻያው በተደረገባቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የምንዛሬው መጠን ሊጨምር ቢችልም በቋሚነት እንደዚያው ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ አቅም እየጎለበተ በሄደ ቁጥር የውጭ ምንዛሬው እንደሚቀንስም አውስተዋል። ይህን ነጥብ ሲያብራሩም፣ “የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና ሌሎች አካላት ለኢትዮጵያ እየለቀቁላት ያለው ብድርና ድጋፍ ባንኮች በቂ የውጭ ምንዛሬ አግኝተው ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደውን የገንዘብ ፍሰት በመቀነስ ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል። አክለውም፣ “የሚለቀቀው ብድርና ድጋፍ የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ ከማጠናከር፣ ምርታማነትን ከማሳደግ፣ የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ከማመጣጠን አንፃር ሚናው ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ሸማች የምርት ፍላጎት በቀላሉ ሊስተናገድ የሚችልበት መንገድ ስለሚፈጠር የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱ እየረገበ ይሄዳል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዜጎችን አጠቃላይ ደህንነት ለማረጋገጥ ከሚተገበሩ የመፍትሔ አማራጮች መካከል እንደ አንዱ ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረዋል። ይህን ሃሳብ ሲያብራሩም፣ “መንግሥታት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ሶስት ዓላማዎች ያሏቸውን ርምጃዎች ይወስዳሉ። አንደኛው አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ማምጣት፣ ሁለተኛው የሥራ አጥነትን መቀነስ፣ ሶስተኛው ደግሞ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ናቸው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውም ይህንኑ ለማድረግ የተወሰነ ነው” ብለዋል። ማሻሻያውን ተከትሎ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የዋጋ ንረቱ እንዲቀንስ፣ የሥራ ዕድል እንዲሰፋና አጠቃላይ ኢኮኖሚው እንዲያድግ ያደርጋል ባይ ናቸው ተፈራ (ዶ/ር)።
የብር ዋጋ ሲቀንስ ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን በስፋት እንዲጠቀሙ ያስገድዳል በማለት፣ ሂደቱ የገቢ ንግድን በመገደብ የወጪ ንግድን እንደሚያበረታታ፣ አስፈላጊነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲቀንሱ በማድረግ የንግድ ሚዛንን እንደሚያስጠብቅ ገልፀዋል። አሁን መደረግ ያለበት የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ማሳደግ ነው ሲሉም መክረዋል።
እንደ ተፈራ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ማሻሻያው ተኪ ምርቶች ላይ እንዲተኮር ያስችላል። የውጭ ባለሀብቶች ጥቂት ዶላር ይዘው መጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የማድረግን እድል ስለሚያገኙ በብዛት ይመጣሉ። ይህም በጊዜ ሂደት የሀገር ውስጥ ምርታማነት አድጎ ለውጭ ገበያ የሚቀርብን ምርት ያበዛል። ብዙ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ያሳድጋል፤ በሀገር ውስጥ ደግሞ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ፍላጎት እንዳይኖር ስለሚያደርግ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት እንዲቀንስ ያስችላል ማለት ነው። አሁን ኢትዮጵያ ያደረገችው ማሻሻያም በረጅም ጊዜ ውስጥ ይህን ውጤት እንዲያስገኝ ታስቦ ነው። ማሻሻያው ለጊዜው የኑሮ ውድነትን እንደሚያስከትል እሙን ነው ያሉት ተፈራ (ዶ/ር)፣ አላስፈላጊና ተገቢነት የጎደለው ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ መክረዋል። አክለውም የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ የህብረተሰቡን ኑሮ መቀየር በሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲውል አበክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንፃር የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አስፈላጊ እንደሆነ የጠቆሙት ተፈራ (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው ሁኔታ ከእዚህ በላይ መቆየት ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሾች የመዳረግ እድሉ ሰፊ መሆኑን ገልፀዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሀገራት በእዚህ ስልት ተጉዘው ሊደርስባቸው ይችል ከነበረ ውድቀት መዳናቸውን በማውሳት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በአግባቡ ከተተገበረ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ መሆኑን ከሲንጋፖር፣ ህንድ እና ሌሎች መሰል ሀገራት መማር እንደሚቻል አብራርተዋል።
ተፈራ (ዶ/ር) የብር ዋጋ ከዶላር አንፃር መቀነሱ የሚያሳስብ ጉዳይ አለመሆኑን ሲያስረዱ፣ የጃፓን፣ የሩሲያ፣ የደቡብ ኮሪያ እና ሌሎች ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው ሀገራት ገንዘብም ከዶላር አንፃር ከኢትዮጵያ ብር በላይ የወረደ ዋጋ እንዳላቸው ማሳያ አድርገዋል። ዋናው ቁም ነገር የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድርገው ለስኬት የበቁ ሀገራትን ተሞክሮ ይዞ በተቻለ መጠን ኢትዮጵያ ያደረገችው ማሻሻያ ስኬታማ እንዲሆን በርትቶና ተጋግዞ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም መክረዋል። በተመሳሳይ ቆስጠንጢኖስም (ዶ/ር)፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተገቢነትና ስኬታማ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ሲያብራሩ፣ ኢትዮጵያ አስቀድማ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማድረጓና ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።
እስከ አሁን ባሉት ጊዜያት ውስጥ በሺህ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር መንገድ መዘርጋቷ፣ ሰፋፊ የገበያ ማመዕከላትን ማዘጋጀቷ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች፣ ግድቦች፣ የኃይል ማሰራጫዎች፣ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ያሏት ሀገር እንደመሆኗ የኢኮኖሚ ማሻሻያውና ይህንኑ ተከትሎ የሚመጣው የውጭ ምንዛሬ ለኢኮኖሚው ትልቅ መስፈንጠሪያ ይሆናል ብለዋል።
ከመንግሥት የሚጠበቀው በብድርና ድጋፍ የሚመጣውን ገንዘብ በትክክል በልማት ላይ የሚውልበትን እድል ማመቻቸት እንደሆነ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) መክረዋል። በተለይ ገንዘቡ ባንኮች እጅ ገብቶ በሕጋዊ የንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እንዲደርስ እና እነሱም በትክክለኛው መንገድ ለተባለው ጉዳይ ብቻ ማዋላቸውን በመከታተል ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል።
የነገ ሰው ይበለን !
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም