የሀይል ዘርፍ ሪፎርም ለማካሄድ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው። የፍኖተ ካርታው ዝግጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደተጠናቀቀ የሪፎርም ሥራው ይከናወናል። ሪፎርሙ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የራሱን ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ፖሊሲ ስትራቴጂና ኢንፎርሜሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ይሄይስ እሸቱ በፍኖተ ካርታው ዙሪያ ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡- የሀይል ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ ለምን አስፈለገ?
አቶ ይሄይስ፡- ትላልቅ ግድቦች ሲሰሩ ብዙ ቢሊዮን ብሮችን ነው የሚያስወጣው። ይህ ደግሞ በመንግሥት ሲሰራ ስለነበር ቀስ በቀስ እዳው ከፍ እያለ እንዲሄድ አድርጓል። በሀይል ዘርፍ ሌላ የግሉን ዘርፍ ማስገባትና እሱ ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ መንግሥት ከሌሎች የልማት አጋሮች የሚያገኘውን ገንዘብ ለሌላ ሊጠቀምበት ይችላል። ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት የግሉ ዘርፍ በኃይል ዘርፍ ላይ መሳተፍ ይፈልጋል። የግሉ ዘርፍ በኃይል ዘርፍ ገብቶ መሳተፍ ቢጀምር መንግሥት የተወሰነ ጫና ይቀንስለታል፡፡
ወደ ፊት ኃይል የሚያመነጩ የግል ዘርፎች ይኖራሉ ማለት ነው። የግሉ ዘርፍ እንዲህ አይነት ውስጥ ሲገባ ግልጽ የሆነ የማያሻማ አስተዳደር ያስፈልጋል። የዚህን ሥራ ዋናውን ኃላፊነት የሚወስደው ኢነርጂ ባለስልጣን ነው። ምክንያቱም ህግጋቱን ጠብቆ ኤሌክትሪክ ኃይልም ኃይል ያመነጫል፤ የግሉ ዘርፍም ኃይል ያመነጫል፡፡ እነሱን ደግሞ አንድ ላይ ሊያስተዳድር የሚችል ሥርዓት ያስፈልጋል ማለት ነው። ለዚህም ሪፎርም ያስፈልጋል።
የሪፎርሙ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ ነው። ፍኖተ ካርታው የኃይል ዘርፉ ምን መምሰል አለበት? የሚለውን ይዟል። የፍኖተ ካርታው ዓላማ ለደንበኞች ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት፣ ለማንም የማያዳላ ግልጽ የሆነ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል። የግል ዘርፍ በኃይል ዘርፍ ለመሳተፍ ሲመጣ የሚሳተፉበትን ሜዳ በደንብ ማወቅ አለባቸው። ህግና ስርዓት ከተቀመጠ በኋላ ነው በዚያ ሚናውን አይቶ ሊሰራ የሚችለው። ስለዚህ የኃይል ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ ጥሩ ህጎችና መመሪያዎች ከተዘጋጁ በኋላ የግሉ ዘርፍ በኃይል ዘርፍ ገብቶ ለመሳተፍ ያስችለዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ፍኖተ ካርታው ዝግጅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ እስከ መቼ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል?
አቶ ይሄይስ፡- ፍኖተ ካርታው ተጠናቆ በቀጣይ ዓመታት የተሻለ ነገር እንዲመጣ መንግሥት ይፈልጋል። የልማት አጋሮችም ክትትል እያደረጉ ነው። የጊዜ ገደብ ተቀምጧል። ጥቅምት ወር ውስጥ ፍኖተ ካርታው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይላካል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የግል ባለሃብት በኃይል ዘርፍ እየተሳተፈ አልነበረም ማለት ነው ?
አቶ ይሄይስ፡- ኃይል ማመንጨት ላይ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ከተከፈተ ቆይቷል። ነገር ግን የተደላደለ ነገር አልነበረም። ክፍተቶች ነበሩት። በመንግሥትና በግል አጋርነት ኃይል የማመንጨት ሥራ ክፍት ተደርጎ ነበር። የግል ባለሃብቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን ኃይል የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተጀምሮ ነበር። ነገር ግን የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ወደ ሥራ የገቡ የግል ኩባንያዎች አሉ ?
አቶ ይሄይስ፡- በዘርፉ እንዲሳተፉ እየተጋበዙ ነው። መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት ሊሰማሩ ያቀዱ አሉ። በጣም ፍላጎት አላቸው። ብዙ ተጫራቾች ናቸው ፍላጎት እያሳዩ ያሉት። ለምሳሌ ከጸሐይ ኃይል የሚያመነጩ ኩባንያዎች ጨረታ አሸንፈው ወደ ሥራ ሊገቡ ነው። እንደዚሁ ጂኦተርማል ላይ እየተደራደሩ ያሉ የግል ኩባንያዎች አሉ።
በአንዳንድ ሀገራት ጨረታ ወጥቶ የሚሳተፍ የሚታጣበት ሁኔታ አለ። በኢትዮጵያ ግን ብዙዎች ናቸው ፍላጎት እያሳዩ ያሉት። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ኃይል የሚያመነጩ በርካታ የግል ኩባንያዎች ወደ ሥራ ይገባሉ። ኩባንያዎቹ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል። የሀገር ውስጥና ውጭ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ። ለበርካቶች ሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎም ይታሰባል።
አዲስ ዘመን፡- የዘርፉ ሪፎርም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚኖረው እገዛ ምንድን ነው ?
አቶ ይሄይስ፡- ሪፎርሙ አማራጮችን ይሰጣል። የኃይል ዘርፉ እያደገ ነው። ፍጆታም እያደገ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ አነስተኛና ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች እየመጡ ነው። ይህንን ሁሉ ፍላጎት ለማሟላት የግድ ኃይል ያስፈልጋል። ለዛሬ ለነገ የሚባል አይደለም። ሁል ጊዜ ኃይል ሊቀርብ ይገባል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት መርሐ ግብር ይፋ ተደርጓል። እሱም ትልቅ እቅድ ነው።
የአገልግሎት ቅልጥፍና እና እስፔሻላይዜሽን የግድ ነው። ሁሉንም አግበስብሰህ ስትሰራው ጥራት አይኖረውም። እሱን ችግር ለመፍታት ሰዎችን ለተቋማት ኃላፊነት ሰጥተህ ያንን ሥራ ካልሰሩ ሊቀጥሉ አይችሉም ማለት ነው። የግሉን ዘርፍና የመንግሥት ኩባንያዎችን ማወዳደርም ይቻላል። ውድድር ሲመጣ ውጤታማነት ይጨምራል። ቅልጥፍናም ይጨምራል። እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ማሰብ የሚቻለውም ውድድር ሲኖር ነው። ከዛ አንጻር ሲታይ ፍኖተ ካርታው ተጠናቆ ሪፎርሙ ከተተገበረ ፋይዳው ሰፊ ነው። ዘርፉን በጣም ነው የሚቀይረው።
አዲስ ዘመን፡- መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለግሉ ዘርፍ መልቀቅ የራሱ የሆኑ አሉታዊ ጎን እንደሚኖረው ይታወቃል። የግሉ ዘርፍ በሚገባበት ወቅት መሰል ችግር እንዳይፈጠር ምን ታስቧል?
አቶ ይሄይስ፡- አዎ ነገሮችን ለግሉ ዘርፍ ሲለቀቅ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይታወቃል። ህግና ሥርዓት ተቀምጦ በዚያ ህግና ሥርዓት መጫወት ካልቻለ አስቸጋሪ ነው። መንግሥት ደግሞ ያንን የሚመራበትን አቅም ካላሳደገ አስቸጋሪ ነው። ይህ ሥራ ኢትዮጵያ ኃይል ባለስልጣንን የሚመለከት ይሆናል። የጨዋታውን ህግ አውጥቶ በኃይል ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ የመንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች ትክክለኛ መስመር ይዞ እንዲሄድ የሚያደርገው እሱ ይሆናል። ህግጋቶችንም ያወጣል። ለዚህም ባለስልጣኑ በብቁ የሰው ኃይል፣ በገንዘብና አስተዳደር ሊጠናከር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ይሄይስ ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ጥቅምት20/2012
መላኩ ኤሮሴ