ከህጎች ሁሉ የበላይ የሆንከው፤ ሁላችንም የምንገዛልህ፣ የምናከብርህ፣ በስምህ የታሰርንልህ፣ የተገረፍንልህ፣ የሞትንልህ ውዱ ህገ መንግስታችን (ከተለያየንበት ጊዜ ጀምሮ አልልህም) ከተገናኘንበት ጊዜ ጀምሮ ለጤናህ እንደምን አለህ? ካላንተ ፍቅርና ችግር በስተቀር እኛ ለጤናችን ደህና ባንሆንም አንድ ቀን ኢትዮጵያ ደህና ስትሆን ደህና እንሆናለንና እግዚአብሔር ይመስገን። ይህን ደብዳቤ እንድጽፍልህ ያስገደደኝ ምክንያት ወትሮውንም ቢሆን ደህና ሆነህ ባታውቅም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከሰሞኑ ያለው የጤንነትህ ሁኔታ ከምንጊዜውም በላይ እያሳሰበኝ በመምጣቱ ነው።
በአሁኑ ወቅት በሽታህ እየተባባሰ መጥቶ በጠና ታመህ ህይወትህ አደጋ ላይ በመውደቁ አንተን ከሞት ለመታደግና እኛን ለማዳን አስቸኳይ ጉባኤ መቀመጣቸውን “የግል ሃኪሞችህ” ሲናገሩ ሰምቼ ተጨንቄ ነው ይኼን ደብዳቤ የምጽፍልህ። እኛ አንተን የሁላችን አድርገን ማክበር ብቻ ሳይሆን አስከብረንህም ኖረናል።
ዳሩ እኛን ማስከበር ያለብህ አንተ ብትሆንም አንተን ለማስከበር እኛ ብዙ መከራ አይተናል። ክቡር የሆነው በህይወት የመኖር መብታችን እንዳይጣስና እኛ እንዳንሞት ጠበቃ መሆን የነበረብህ አንተ ብትሆንም፤ እኛ ግን አንተ እንዳትጣስ፣ አንተን በህይወት ለማኖር ሞተናል። ምክንያቱም ምንም ብታደርገን የሁላችን የበላይ አንተ ነህ፣ የእኛ ነህ ብለን ስለምናምን ነበር!
እስካሁን ድረስ “የሁላችንም ነህ” ብለን አብረንህ ብንኖርም በግል ጠበቆችህ አማካኝነት የሁላችን አለመሆንህን አንተው ራስህ ከነገርከን ለሃገር አስበን አለያም ለመኖር ብለን የተውነውን ነገር የደበቅንልህን ገመናህን ለመናገር እንገደዳለን።
ወትሮውንም የሁላችን አልነበርክም
በመሰረቱ ህገ መንግስት ማለት የአንድ አገር የበላይ መተዳደሪያና ሕዝብና መንግስት በጋራ የሚመሩበት የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ በመሆኑ በሁሉም ዜጎች ዘንድ እኩል ቅቡልነት ሊኖረው ግድ ይላል። ለዚህ ደግሞ አንድ ህገ መንግስት ጸድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የሃገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉም ባለ ድርሻ አካላትና ህዝቡ በበቂ ሁኔታ ሊወያይበት ይገባል። “የእኛ” ህገ መንግስት ግን ይህንንን መሰረታዊ የህገ መንግስት አዘገጃጀት መርህ ጥሷል። እናም ውዱ ህገ መንግስታችን ሆይ ወትሮውንም ቢሆን የእኛ ሆንክብን እንጅ የእኛ አልነበርክም፤ የሁላችን ተባልክ እንጅ በትክክል የሁላችንም አልነበርክም።
የሁላችሁም ወኪል ነኝ አልከን እንጅ በእውነታው የሁላችንም ወኪል አልነበርክም። ይህንንም በተጨባጭ በመረጃና በማስረጃ አስደግፈን እንንገርህ። እንዲያውም ምስጋና ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለሰላም ለሚተጉ ሃገር ወዳዶች ይሁንና የሁላችንም አለመሆንህንና ብትሆንም እንኳን ለአንዱ “እናት” ለሌላው “የእንጀራ እናት” መሆንህን ለማሳየት የምናቀርብልህ መረጃ ሩቅ ሳንሄድ በተዘጋጀህበት ወቅት እያንዳንዱ ማንነትህ የተመዘገበበትን ቃለ-ጉባኤ የተያዘበትን ሰነድ ነው።
ህገ መንግስቱ የተረቀቀበት መንገድ
ታዋቂው ፖለቲከኛና ደራሲ አስራት አብርሐም በዝግጅት ሂደቱ የነበሩ አጠቃላይ ሁኔታዎችን ህገ መንግስቱ በተረቀቀበትና በጸደቀበት ወቅት የነበረውን ቃለ-ጉባኤ መሰረት አድርገው እውነታውን ከባለቤቶቹ(From the Horse’s Mouth) ወስደው ያሳዩበትን “የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች” በሚል ርዕስ በ2009 ዓ.ም የታተመውን መጽሃፋቸውን በቀዳሚነት እናንሳ።
ጸሃፊው በመጽሃፋቸው መግቢያ ላይ፤ “…ይኼ በመቶ ሺዎች ተሰውተውለት፤ ሚሊዮኖች ደግሞ ታግለውለት የመጣ ነው” የሚባለው ህገ መንግስት፣ ኢህአዴግና አጋሮቹ ብቻ ዘብ የሚቆሙለት፣ በተቃራኒው ያሉት ወገኖች ደግሞ እንደ ህገ መንግስት ለመቀበል እንኳን የሚተናነቃቸው ህገ መንግስት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመናድ አሲረዋል ተብለው ብዙዎች የሚወነጀሉበትና የሚታሰሩበት ህገ መንግስት ሥራ ላይ ከዋለ ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላም ቢሆን የምልዓተ ህዝቡን ቅቡልነት ያገኘ አይመስልም” በማለት የህገ መንግስቱን ኢ-የሁሉምነት አስረግጠው ይገልጻሉ።
“ለምንድነው? ብለን ስንጠይቅ መልሱን የምናገኘው የህገ መንግስቱን ቃለ-ጉባኤ ስናይ፣ ህገ መንግስቱ የተረቀቀበትን የፀደቀበትን መንገድ ስንመረምር፣ የአርቃቂዎቹንና የአጽዳቂዎቹን ማንነት ስንፈትሽ ነው” የሚሉት ጸሃፊው የህገ መንግስቱ አርቃቂዎች ማንነትን እንደሚከተለው ያቀርቡታል።
ለህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽኑ ህገ መንግስት አርቃቂ ሆነው የተመረጡ የህግ ባለሙያዎችን ማንነት በተመለከተ አቶ አስራት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ጠቅሰው እንዳስቀመጡት አንዳንዶቹ በደርግ ህገ መንግስት አርቃቂነት የተሳተፉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በአብዮቱ ዘመን ተቋቁሞ የነበረው “የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት” አባል የነበሩ ሲሆኑ፤ ከውጭ የመጡ የተወሰኑ ምሁራንም በማርቀቅ ሂደቱ ተሳትፈዋል።
ይሁን እንጂ የአርቃቂ ኮሚሽኑ አባል ባይሆኑም የኢ.ፌ.ዴ.ሪን ህገ መንግስት እንዲሁም የንጉሱንና የደርግን ህገ መንግስቶች ያረቀቁት “የህገ መንግስቶቻችን አንድ ለእናቱ” የሆኑት ዶክተር ፋሲል ናሆም መሆናቸውን አንጋፋውን ፖለቲከኛና ደራሲ አቶ አሰፋ ጫቦን ዋቢ አድርገው በመጽሃፋቸው ገጽ 25 ላይ አስፍረዋል።
በዚህ መንገድ የህገ መንግስቱ አርቃቂዎችን ማንነት ግልጽ ካደረጉ በኋላ በፈጣሪዎቹ ማንነት የህገ መንግስቱን ምንነት ወደ ማሳየት ይገባሉ። በአርቃቂ ኮሚሽኑ ውስጥ እነርሱ በፈለጉት መንገድ እጅ መጠምዘዝ የሚችሉ የኢህአዴግ ቅርብ ሰዎች ከመኖራቸውም በአሻገር “የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተረቀቀው በኢህአዴግ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሥር መሆኑን የምንረዳው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የሰጡትን ምስክርነት ስንመለከት ነው” የሚሉት አቶ አስራት ሁኔታውን እንደሚከተለው እንደወረደ አስቀምጠውታል።
“በአርቃቂ ኮሚሽኑ ውስጥ ኢህአዴግ የተወከለው በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ(ኦህዴድ) እና በአቶ ዳዊት ዮሐንስ(ብአዴን) ቢሆንም፤ ማታ ማታ በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮች ስብሰባ ላይ ሁለቱ ተወካዮች በሚያመጡት ሪፖርት ላይ ተመስርቶ የየዕለቱ ውሎ ይገመገማል፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹ ተለይተው ይቀመጡና ቀጣይ ውይይቶች በምን አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣቸው ነበር።
በዚህ ላይ አቶ ዳዊት ዮሐንስ እጅግ ታማኝ የነበሩ ሲሆኑ፣ የህገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ፀሐፊና ቃለ-ጉባኤ ያዥ እንዲሆኑ የተደረገውም በዘፈቀደ አልነበረም። ይህም ኢህአዴግ ህገ መንግስቱ በራሱ ዕምነትና መንፈስ እንዲቀረጽለት ከነበረው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ ነበር ማለት ይቻላል”
ህገ መንግስቱ በዋነኝነት የተረቀቀው ከላይ እንደተገለጸው ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ እስካሁን የወጡትን ሁሉንም የኢትዮጵያ ህገ መንግስቶች ባረቀቁት የሃገሪቱ “ብቸኛ የህግ ባለሙያ” በዶክተር ፋሲል ናሆም መሆኑ ስለ “እንከን የለሹ” ህገ መንግስታችን ማንነት የሚናገረው ትልቅ ቁም ነገር አለ። አቶ አስራት በመጽሃፋቸው፤ “ከዚህም የምንረዳው ዶክተር ፋሲል ለሦስት የተለያዩ ወይም ሊገናኙ የማይችሉ መንግስታት (ማለትም ለንጉሱ፣ ለደርግና ለኢህአዴግ) የተለያዩ ህገ መንግስቶችን ሰርተው ማቅረባቸውን ነው። በተጨማሪም የህዝብን ሳይሆን የገዥዎችን ፍላጎት እየተከተሉ ህግ የሚሰፉ ሰዎች እንደነበሩንና እንዳሉን የሚያሳይ ነው›› ይላሉ።
ህገ መንግስቱ የተረቀቀው ከኢህአዴግ ቁልፍ ሰዎች ጋር በምክክርና የፓርቲውን የፖለቲካ ፕሮግራም በመከተል መሆኑን ያመላክታል። በኢህአዴግ ፖለቲካ ፕሮግራምና በህገ መንግስቱ ይዘት መካካል ያለው ተመሳሳይነት የሚነግረን እውነታም ይህንኑ ነው። ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራሙን ህገ መንግስታዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄዷል ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። “ይህንንም በእነ ዶክተር ፋሲል ናሆም እጅ የራሱን ሃሳብና ዕምነት እንዲጻፍለት ለማድረጉ ምንም ጥርጥር የለውም” የሚሉት አቶ አስራት ዛሬ ላይ ከብዙሃኑ በተለየ የተወሰኑ ቡድኖች “ህልውናውን ለመታደግ” የግል ጠበቃ ሆነው የቆሙለት ህገ መንግስታችን ወትሮውንም የሁላችንም እንዳልነበረ በመረጃ ይነግሩናል።
ህገ መንግስቱ የጸደቀበት መንገድ
ሌላው አንድን ህገ መንግስት ህገ መንግስት ከሚያስብሉና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነትን ከሚያስገኙ መመዘኛዎች መካከል ከማርቀቅ ሂደቱ በተጨማሪ የሚጸድቅበት መንገድም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የህገ መንግስት ጠቢባን ይስማሙበታል። ይሁን እንጅ በዚህ ረገድም የኢፌዴሪ ህገ መንግሰት በእጅጉ ችግር ያለበት መሆኑን በጉዳዩ ላይ የጻፉና ጥናት ያደረጉ ሁሉ የሚመሰከሩት ሃቅ ነው።
አቶ አስራት በበኩላቸው ህገ መንግስቱን የማጽደቁ ሂደት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል ደረጃ የተተወነው በኢህአዴግና በአጋሮቹ እንደነበር በመግለጽ የህገ መንግስቱን ኢ-ህዝባዊነት ይገልጻሉ። ይህንንም “የህገ መንግስቱ ጉባኤ አባላት ብዛት 543 ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ሰማንያ ስድስት በመቶ የሚሆነው በኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች እንደነበር ቃለ ጉባኤው ራሱ ያሳያል” በማለት በቀዳሚ መረጃ አስደግፈውታል። ይህም ብቻ አይደለም።
ኢህአዴግ የህገ መንግስቱን ጉባኤ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው በተወካዮች ቁጥር ብዛት ብቻ አልነበረም። እንደ አቶ አባይ ፀሐዬ ፣ አቶ ዓለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ወይዘሮ አረጋሽ አዳነ፣ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ አባተ ኪሾ፣ አቶ መሃሙድ ድሪር…የመሳሰሉ አሉኝ የሚላቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናቱን በማሰለፍ ጭምር እንጅ! እነዚህ ቱባ ቱባ የሥርዓቱ ባለስልጣናት የጉባኤውን ውይይቶች አቅጣጫ በማስያዝና በማርቀቅ ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ህገ መንግስቱ ኢህአዴግ እንደሚፈልገው ብቻ ሆኖ እንዲጸድቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። ከዚህም ባሻገር በህገ መንግስቱ ረቂቅ ልዩ ልዩ ክፍሎች ላይ በንዑሳን ኮሚቴዎች ሳይቀር በተደረጉ ውይይቶች ላይ መሪዎች ሆነው የተመረጡት ሙሉ በሙሉ የኢህአዴግና አጋር ድርጅቶች ከፍተኛ ባለስልጣናት ብቻ ነበሩ።
የህገ መንግስቱ ይዘት
የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ጉዳይ የሚመለከተው የህገመንግስቱ ይዘት ህገ መንግስቱን በበጎ ጎኑ ከሚያስነሱት ነጥቦች መካከል ዋነኛው ነው። ታዋቂው ፖለቲከኛና በቅድመ ለውጥ የኢህአዴግ ዘመን ብቸኛው ተቃዋሚ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ እንደሚሉት ይህም ቢሆን ለህገ መንግስቱ ጥሩነት በመከራከሪያነት ሊቀርብ አይችልም። ይህንንም ሃሳባቸውን ከላይ ለማስረጃነት በተጠቀምነው “የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች” በሚለው አቶ አስራት በጻፉት መጽሐፍ መግቢያ ውስጥ እንደሚከተለው አስፍረዋል። “ህገ መንግስቱ በሁለት ልብ እንደተጻፈ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም።
አንደኛውና የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራም የያዛቸው የብሔር፣ ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህወሓትን በስልጣን የመቆየት ቀጣይነት የሚያረጋግጥ አደረጃጀት…የመሳሰሉት ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ምዕራባውያን መንግስታት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ የሚያስችል የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ነጻ ኢኮኖሚ…ወዘተርፈ የመሳሰሉት ናቸው”። በተጨማሪም እንደ ሌሎች ማናቸውም መብቶች ሁሉ በተግባር ላይ ስለማይውሉ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በህገ መንግስቱ ውስጥ ተካተው ቢጻፉ ችግር የለውም በሚል የጥቅም ስሌት የገቡ በመሆናቸው የህገ መንግስቱን ጥሩነት ለማሳየት እንደመመዘኛ መወሰዳቸው ስህተት ነው።
“የህገ መንግስታችን” የመጨረሻዎቹ ህጋዊ ባለቤቶችና ማንነታቸው
እስካሁን ያቀረብነው መረጃ የሚያረጋግጥልን አንድ ዕውነት አለ። ይኸውም “ህገ መንግስታችን” ወደንም ባይሆን ተገድደን የሁላችንም ነው ብለን ተቀብለነው ኖርን እንጅ ወትሮውንም ቢሆን የእኛ የህዝቦቹ ሳይሆን የፓርቲዎቹ ማለትም የኢህአዲጎቹ መሆኑን ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከለውጡ በኋላ ተደጋግመው እየተሰሙ የሚገኙ የአንድ ወገን “የጥብቅና ድምጾች” ነባሩን የህገ መንግስቱን የህዝብ አለመሆን ዕውነታ የሚያረጋግጡልን አሁናዊ ማረጋገጫዎች ናቸው። አሁን ላይ በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ ህገ መንግስቱ የህዝብ አለመሆኑ ገሃድ ከመውጣቱ ባሻገር በባለቤቶቹ በኢህአዴጋዊያን መካከልም ህገ መንግስቱ የጋራ መሆን አቅቶት “የግሉ ጠበቃና ተቆርቋሪ” ፈጥሮ መታየቱ ነው።
ለዚህ ዋና ማሳያ የሚሆነን ህወሓትና አዴፓ ከሰሞኑ ያወጡትን መግለጫ ስንመለከት ነው። “ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በዚሁ ወቅት የትምክህት ኃይሎች በአመለካከትና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ጉልበት ፈጥረው አገር የሚያምሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በብዙ የአገራችን አካባቢዎች የሰላም እጦት እየተስፋፋ፣ በዚሁም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግስት የማይቆጣጠራቸው አካባቢዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ” ይላል ህወሓት
“ትናንት ትክክለኛው የፌዴራሊዝም ስርዓት መሬት እንዳይይዝ ሕዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች በያዙት የመንግስት ስልጣን ሕገ መንግስቱንና የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ሲጥሱ የነበሩ ቡድኖች ዛሬ ራሳቸውን ለሕገ መንግስቱ የቆሙና የፌዴራሊዝም ስርዓት ጠበቃ እንደሆኑ አድርገው በሕዝቡ ውስጥ ብዥታን ለመፍጠር የሚነዙት የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኦዲፒ ለማስገንዘብ ይወዳል” ይላል የኦዴፓ መግለጫ ደግሞ።
ታዲያ የአንድ ድርጅት ሁለት አካሎች በአንዱ ህገ መንግስታቸው ላይ አንዱ ከሳሽ ሌላው ጠበቃ፣ አንደኛው አፍራሽ ሌላኛው ከመፍረስ ተከላካይ ሆነው ከቀረቡ በእርግጥ ይሄ ጉደኛ ሕገ መንግስት የማን ነው? የህዝብ እንዳንለው የህዝብ አይደለም(የህዝብ ሆኖ አልተፈጠረም)።
የፓርቲ መሆኑ ዕውነት ሆኖ ሳለ ፓርቲው ራሱ “የእኔ ነው፣ የእኔ ነው” በሚል ሽሚያና ሽኩቻ የእርስ በእርስ እሰጣ አገባ ውስጥ ገባ እንጅ “የእኛ ነው” ብሎ አልተስማማ! እናማ ህገ መንግስቱ እንደ ፓርቲ የኢህአዴግ ነው የሚለው ለራሱ ለኢህአዴግም ካላስማማ ይሄ አድሏዊ የእንጀራ እናት ህገ መንግስት ከራሱ ከኢህአዴግ ውስጥም በተለመደው አድሏዊነቱ ተጠቅሞ “ልጅ እና የእንጀራ ልጅ” ፈጥሯል ብለን ለመጠራጠር እንገደዳለን። ስለሆነም አድልኦ የተደረገለትና ከህገ መንግስቱ የተለየ ጥቅም የሚያገኘው ኢህአዴግ ከልጅም በላይ ጠበቃ ሆኖ ቀርቧል የሚለው ምክንያታዊ ድምዳሜ ይሆናል ማለት ነው።
ታዲያ ከዚህ አኳያ ከጀመርነው አይቀር ታሪካዊና ወቅታዊ መረጃዎችን ተንተርሰን የህገ መንግስቱ የመጨረሻው ህጋዊ ባለቤት ማን መሆኑን አመላክተን ብንጨርስ ምን ይመስላችኋል?
ከታሪካዊው እንጀምር። “ህገ መንግስት የአንድ ድርጅት ፕሮግራም ማለት አይደለም። አንድ ሃገር በጠቅላላ የሚተዳደርበት ቋሚ ህጎችን የያዘ ሰነድ ማለት ነው…. አሁን ያለን ህገ መንግስት በዋናናነት ህወሓትና ኦነግ ሆነው አስቀድመው በሽግግሩ ቻርተር ያጸደቁት ነው ትንሽ ነገር ተጨማምሮበት ህገ መንግስት የሆነው። በመሆኑም ይህ የድርጅቶችን እንጅ የህዝቡን ፍላጎት ያቀፈ አይደለም” ሲል አቶ አስራት ፤ ዶክተር አረጋዊ በርሔ ‹‹ውራይና›› ለተባለ የትግርኛ መጽሄት የሰጡትን ቃለ ምልልስ ጠቅሶ ፅፏል።
ወትሮም በእርስ በእርስ ክህደት ምክንያት በታሪካዊ ጠላትነት የሚታወቁት ህወሓትና ኦነግ አንድ ላይ አብሮ ለመስራትና ለመተባባር መስማማታቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በአደባባይ ሲገልጹ ስትሰማ፤ ህገ መንግስቱ እንዳይጣስና ሃገርን ከጥፋት ለመታደግ ‹‹ፌደራሊስት ኃይል›› ለማቋቋም ጥሪ ሲያቀርቡና የህገ መንግስቱ ልዩ ዘብ ሆነው ሲቀርቡ ስታይ የእንከን የለሹ የህገ መንግስታችን የመጨረሻው ህጋዊ ባለቤት ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን የመጨረሻ ግቡም ምን እንደሆነ ሚስጥሩ ይገለጥልሃል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ይበል ካሳ