የጸረ እረፍት ትግሌን ለማጠናከር ስል የዓመት እረፍትን በጨረታ አወዳድሬ ልገዛ ነው፡፡ታዲያ የምላስ ትጥቄን ፈትቼ ማለት ነው፡፡(ዘመኑ የመሳሪያ ትጥቅ ብቻ ሳይሆን የምላስ ትጥቅንም ለመፍታት የግድ የሚል ስለሆነ) ሕዝብ ዳቦ ለመግዛት ሰልፍ በሚበዛባት አገር የዓመቱን የእረፍት (የዓመት ፈቃድ) ቀናቶች ለመግዛት ለሰልፍ ብቆም ከአገራችን የጨረታ ህግ ውጪ እንደሚሆን አውቃለሁ፡፡
ግን ደግሞ የሕይወታችን ጣዕም ምሥጢሩ ያለው በሰልፍ እጅ ላይ አይደል፡፡ ሰልፍን መጥላት ህይወትን መጥላት ነው፡፡ ስለዚህ የዓመት እረፍትን ለመግዛት ቸል የምለው ሰልፍ አይኖርም፡፡ እመኑኝ ማሳካቴ አይቀርም፡፡ ብዙ ወራትን ያለ እረፍት ቀጥ ብለን መስራት ያስቸግራል እኮ፡፡ እና ይህችን እረፍት በእኔ ላይ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ አዲስ መላ ዘየድኩኛ፡፡ የእኔ ቀናቶች ውስን ስለሆኑ ነው ሌላ የእረፍት ቀን ለመሸመት የምታትረው፡፡ በእኔ የጨረታ ህግ ውስጥ የስራ ኃላፊዬን ጣልቃ ገብነትን አልፈልግም፡፡ ግዥውን በጨረታ ገምጋሚ የኮሚቴ አባላት ይሁንታም አላደርገውም፡፡
የዓመት ፈቃድ ጨርሰው ከስራ በመቅረት ሰማይ ጠቀስ እረፍት የሚያደርጉትን ሳይ በመቅናቴ፤ በቅርቡ እንደ እርጉዝ ሴት ከሚያምረኝ ነገሮች መካከል የዓመት ፍቃድ አንዱ ነው፡፡ የዓመት እረፍት ስሙ ሲነሳ ያዛጋኛል፡፡ አሁን እረፍት ለመውጣት የምችልባት የኔዋ የእረፍት ጊዜ በጣም ጩጬ ከመሆኗ የተነሳ አንድ የክርስትና ድግስ እንኳን ለማስተናገድ አትበቃኝም፡፡
እናም የዓመት እረፍት ፈቃድ በገንዘብ ቀይሮ በጨረታ የሚሸጡልኝን ግለሰቦች እያፈላለግኩ ነው፡፡ በእኔ በኩል የዓመት ፍቃድን በጨረታ የመግዛት ፍላጎት ቢኖረኝም እስካሁን ግን ሻጮች ራሳቸው የመግዛት ፍላጎት ውስጥ በመግባታቸውና በዓመት እረፍት ድርቅ በመመታታቸው እኔ ከምሰራበት መስሪያ ቤት ውጪ ካሉት ላይ ለመግዛትም ስለላ ጀምሬያለሁ፡፡ የእነዚህን ሰዎች የዓመት እረፍት በውድ ዋጋ እየገዛሁ በማጠራቀም ወደ ፊት የዓመት ፈቃድ ውድነት ሲከሰት አትርፌ ለመሸጥም እያሰብኩ ነው፡፡ (ደግሞ ከእኔ ተሞክሮ ወስዳችሁ ለመተግበር ሞክሩ አሉ፡፡)
ይህ አካሄድ ቢሳካልኝ መንግሥት በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች፣ በሰው ኃይል፣ በበጀት፣ በሪፎርም ሥራዎችና ነጻነቴን ጠብቆ ያለምንም ጣልቃ ገብነት የዓመት ፈቃድ የመግዛት ሥልጣንና ተግባር ቢሰጠኝ ራሴን ችዬ አንድ ተቋም እመሰርት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ ከተጫራቾች የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና በርከት ያለ ብርም መሰብሰቤ አይቀርም፡፡ (የአጫራቾች ጥቅሙ ይሄ አይደል) እስኪ አሁን ማን ይሙት ሰዎችን ለማጫረት አስቀድሞ የጨረታ ሰነድ እያሉ ገንዘብ መሰብሰብ ጤንነት ነው? ለማንኛውም ለኔም ትምህርት ሰጥተውኛል፡፡
ምድር የላብና የትግል ሥፍራ በመሆኗ እርጉም ትመስለኛለች፡፡ በድህነት ዓለም ውስጥ ከኑሮ ወለል በታች ላሉት የእለት ጉርስን ፍለጋ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ መቅበዝበዙ ህይወት እስኪያበቃ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ነው እረፍት የሚያጥረን፡፡ አንዳንዴ ከማምሸት ውጪ ቅዳሜና እሁድንም በሥራ የምናሳልፍበት አጋጣሚ ስላለ፤ በአሁን ሰአት ያለኝ ስሜት ከመዛልም ያለፈ ነው፡፡ የሥራ መታከት እንዲሁ ድካም ብቻ ሳይሆን ከዚያ ያለፈ ነገር ነው፤ የስራው ብዛት ሳይሆን እረፍት አልባነት መሆኑ፡፡
ሰዎች በሥራቸው ሲታክቱ ሥራውን በስሜት አያከናውኑም፤ የሥራ ተነሳሽነት ያጣሉ፤ እንዲሁም ውጤታማነታቸው እየቀነሰ ይመጣል፡፡ በተለያዩ ጥናቶች እንደሚታየውም መታከት ከበርካታ ስሜታዊና አካላዊ የጤና ችግሮች ጋር ይያያዛል፡፡ መንግስት ለብዙ ሰው የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራው ሁሉ የዓመት እረፍትን በሚገባ የመስጠት እድልም ቢሰጥ እላለሁ፡፡ (በሚገባ የሚለው ይሰመርበት) እናም ስር የሰደደ የመዛል ስሜት፣ ኃይለኛ የሆነ መሰላቸትና አቅም ማጣት ሳይመጣብኝ ነው ከራሴ የእረፍት ቀን ውጪ የሌሎችን አጫርቼ ለመግዛት የወሰንኩት፡፡ (ሻጭ ከተገኘ)
ይህ የዓመት እረፍት ግዥ ለእያንዳንዳችን በነፍስ ወከፍ ሊኖረን የሚገባ አይመስላችሁም? በሕይወቱ እረፍት የሌለው ሰው ወደ ልቡ መመለስ አይችልም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የእረፍትን ጊዜ ከቤተሰብ አባላት ጋር አብሮ በማሳለፍ የቤተሰብን ህይወት የቀን ኑሮ (ማታማ ሁሉም ይሰበሰባል) በዓመት እረፍት ጊዜ በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጎጆ ቀልሶ መኖር በጠዋት አስቦ መነሣትን ፣ አልጋ ማንጠፍን ፣ ቤት መወልወልን፣ ምግብ ማብሰልን ፣ የቤት ውስጥ ሥራ አስቦ መሥራትን ፣ ወዳጅ ዘመድ የታመመ መጠየቅን ፣ የሽንት ጨርቅ ማጠብን ፣ክርስትና ማንሣትን ፣ ለቅሶ መድረስን እና መሰል ኃላፊነቶች መወጣትንና ማኅበራዊ ህይወትን አባይን በማንኪያ ያህል እንኳ መቅመስ ያስልጋል፡፡ በሉ ሠላም ቆዩኝ! የዓመት እረፍት ተጫራቾቼን ላስተናግድ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
አዲሱ ገረመው