እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ከስያሜው በቀላሉ ለመረዳት እንደ ሚቻለው ከውል ውጭ የሚመጣ አላፊነት በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት የውል ግንኙነት ሳይኖር በሌላው ሰው ላይ ለሚደ ርስ ጉዳት ተጠያቂነትን የሚያስከትል የፍትሐብሔር ግዴታ ነው። ኃላፊነቱ በስም ምነትና ሃሳብ ለሃሳብ በመግባባት ላይ የተመሰረተ አይደለም።ይልቁንም በውል ባልሆነ ግንኙነት ሰዎች ወደውና ፈቅደው ባልፈጸሙት አድራጎት ጉዳት ለደረሰበት ሰው ተጠያቂ የሚሆኑበት ፍትሐብሔራዊ አላፊነት ነው።(የወንጀል ጥፋት ያልሆነ ማለት ነው)
በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027 እንደተደነገገው ከውል ውጭ የሚደ ርስ ኃላፊነት ከሶስት ሁኔታዎች ይመነጫል። እነዚህም በራስ ጥፋት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ፤ አጥፊ ሳይሆን አላፊ ስለመሆን ማለትም የራስ ጥፋት ባይኖርም እንኳን በአንዳንድ በሕግ ተለይተው በተጠቀሱ አድራጎቶች ወይም ንብረቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ አላፊ መሆን ናቸው።
ከውል ውጭ የሚመጡ ኃላፊነቶችን በተመለከተው የፍትሐብሔር ሕጋችን መሰረት አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ለተፈጸሙ ተግባሮች አላፊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች ሶስት ናቸው።የመጀመሪያው ወላጆች ወይም በወላጆች እግር የሚተኩ ሌሎች ሰዎች አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ለሚያደርሱት ጉዳት አላፊ የሚሆኑበት ነው።
ሁለተኛው አንድ አሰሪ (መንግሥትን ጨምሮ) ሠራተኛው የተቀጠረበትን ሥራ ሲያከናውን ለሚደርሰው ጉዳት አላፊ የሚሆኑበት ነው።የአንድ ጽሁፍ ደራሲ፣ የጋዜጣ መሪ፣ የበራሪ ማስታወቂያ (ፓምፍሌት) አታሚ ወይም የመጽሐፍ አውጪ (ፐብሊሸር) በጽሁፍ ውስጥ ለተፈጸመ የስም ማጥፋት አላፊዎች የሚሆኑበት ሁኔታ ደግሞ ሶስተኛው ነው። በዚህ ጽሁፋችን አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ ለሚያደርሰው ጉዳት የሚመጣውን ተጠያቂነት እንዳስሳለን።
በተለመደው አነጋገር አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ሕጻናት ተብለው ነው የሚጠሩት።ሕጻን ማለት ደግሞ ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው ስለመሆኑ የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ ደንግጓል።ሕጻናት በሕግ ፊት ዋጋ የሚያወጣ ተግባር ለማከናወን ብቃት የሌላቸው ሰዎች ናቸው።ስለዚህ በህግ ተለይቶ ካልተፈቀደለት በስተቀር አንድ ሕጻን (ለምሳሌ ልጅ ወልዶ ከሆነ ሞግዚት የመሆን መብት፣ ከ15 ዓመት በላይ ከሆነ የሥራውን ምንዳ የመቀበል፤ አባትነትን ማመን፤ 16 ዓመት ከሞላው ኑዛዜ የማድረግ) የህግ ተግባሮችን ሊፈጽም አይችልም፡፡
እነዚህ የማህበረሰቡ ክፍሎች ታዲያ እንደማንኛውም ሰው በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት የሚያደርስ አድራጎትን መፈጸማቸው አይቀሬ ነው።ሕጻናት በሌላ ሰው ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት አላፊነት ያለበት አካል ማን ነው የሚለው ታዲያ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
በአገራችን ሕግ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ በሌላ ሰው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ወላጆቹ ወይም በወላጆቹ እግር የሚተኩ ሌሎች ሰዎች ተጠያቂ ስለመሆናቸው ተደንግጓል። በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2124 ላይ ሰፍሮ እንደምናነበው አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ኃላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሠራ እንደሆነ ኃላፊነት ያለበት አባት ነው ይላል።
ተከታዩ የህጉ አንቀጽ በበኩሉ የልጁ ሌሎች ጠባቂዎች በሚል ርዕስ ስር በአባት ኃላፊነት ምትክ ሆነው የሚጠየቁ ሰዎችን ይዘረዝራል።እነዚህም በልጇ ላይ በአባትነት ሥልጣን በምትሰራበት ጊዜ እናት፤ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ከአባቱ ቤት ውጭ ሲኖር በእምነት (በአደራ) የተሰጠው የልጁ ጠባቂ፤ ልጁ ትምህርት ቤት ካለ ወይም የሙያ ሥራ በሚማርበት ወቅት የቀለም ወይም የሙያ ሥራ አስተማሪው እንዲሁም በሕጉ መሰረት ለልጁ ኃላፊ ነው በሚባልበት ጊዜ አሰሪው ስለመሆናቸው በህጉ ተመልክቷል።
በ1952 ዓ.ም. ወጥቶ እስካሁንም ሳይ ሻሻል በሥራ ላይ የሚገኘው ይህ የሕጉ አነጋ ገር በተለይም ከአባትና ከእናት አላፊነት ጋር በተያያዘ ያስቀመጠው ድንጋጌ ሊያስገርም ይችላል። ሕጉ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ አላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሠራ እንደሆነ ኃላፊነት ያለበት አባት መሆኑን ከገለጸ በኋላ እናትን ደግሞ በልጇ ላይ በአባትነት ሥልጣን በምትሰራበት ጊዜ ኃላፊ እንደምትሆን ይደነግ ጋል። በአብዛኛው እናት አባታዊ ሥልጣን የሚኖራት አባት ከሞተ፣ ችሎታ ካጣ፣ ከጠፋ ወይም ከፍቺ በኋላ እናት የልጇ ሞግዚት እንድትሆን ከተወሰነ ነው።
አባትን የመጀመሪያው ተጠያቂ አድርጎ እናትን ደግሞ ምትክ ተጠያቂ የሚያደርገው ይህ ድንጋጌ አሁን ባለንበትና በጋብቻ ውስጥ የአባትነትና የእናትነት መብትና ግዴታ እኩል ሆኖ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች በተደነገገበት ወቅት በሥራ ላይ ሊውል የማይችል ነው።
እርግጥ ነው በዚያ ዘመን “ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት” የሚለውን ወርቃማ ቃል በዘነጋ መልኩ “ባል የቤተሰብ ራስ ነው” የሚለውን ብቻ በመያዝ ርዕሰ-ቤተሰብነት ለባል የተሰጠ ነበር።በዚህ መነሻ ይመስላል የፍትሐብሔር ሕጉ ለልጁ ጥፋት የመጀመሪያው ተጠያቂ አባት ስለመሆኑ የሚገልጸው።ይባስ ብሎም አዲስ በወጣው የቤተሰብ ሕግ ተሻረ እንጂ ሕጉ “ባል ሚስቱን መጠበቅ አለበት” በማለት የአባትን ራስነት አስረግጦ ደንግጎት ነበር።
ዛሬ ላይ በሕገ መንግሥቱ ሴቶች በጋብቻ ውስጥ በወንዶች ምትክነት ሳይሆን እኩል መብትና ግዴታ አላቸው።ከሁሉም በላይ የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ ቁጥር 219 አባትና እናት ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ሁሉ አካለ መጠን ላልደረሱት ልጆቻቸው የአሳዳሪነትና የሞግዚትነት የጋራ ሥልጣን አላቸው ሲል ደንግጓል።
የህጉ አንቀጽ 50 ደግሞ በቤተሰብ አመራር ረገድ ባልና ሚስት እኩል መብት እንዳላቸው፤ በማናቸውም መልኩ የቤተሰቡን ደህንነትና ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ልጆቻቸው በመልካም ሥነ ምግባር እንዲታነጹ፣ ተገቢ ትምህርት እንዲቀስሙና ኃላፊነት የሚሰ ማቸው ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ ለማድረግ መተባበር እንዳለባቸው የጋራ ግዴታ ይጥ ላል።
ከዚህ የምንረዳው ታዲያ በአሁኑ ወቅት የተጋቢዎቹ እኩልነት በሕግ የተረጋገጠ መሆኑን ነው።በዚህ መነሻም የወላጅነት ሥልጣን በአባትና በእናት በጋራ በእኩልነት የሚሰራበት ሆኗል ማለት ነው።እንዲህ ከሆነ ደግሞ አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆቻቸው በሌላ ሰው ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት አባትና እናት የሚኖርባቸው ኃላፊነት የፍትሐብሔር ሕጉ እንደሚለው ምትካዊ (በአባት ምትክ እናት) ሳይሆን የጋራ እና የእኩል ነው።
የፍትሐብሔር ሕጉን ሳንካ ይህን ያክል ከነቀስን ቀጥለን ደግሞ አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ በሚሰራው ስራ በሌላ ሰው ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ወላጆቹ አላፊ እንዲሆኑ በሕግ የመደንገጉን አመክንዮ እንመለከታለን።
ለልጁ ጥፋት ወላጆች ወይም የልጁ ሌሎች ጠባቂዎች የተባሉት የወላጆች ምት ኮች አላፊ እንዲሆኑ በሕግ የተደነገገው አካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ ጉዳት ሊያደርስ የቻለው የልጁ ወላጅ ወይም የወላጆቹ ምትኮች ልጁን በአግባቡ ስላልተቆጣጠሩ ነው በሚል የሕግ ግምት ላይ በመመስረት ነው።
በተለይም ወላጆች በልጆቻቸው አዕምሮ ውስጥ የሌሎች ሰዎችን መብትና ጥቅም የማክበር በጎ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።መምህራንና ሌሎች ለል ጆች አላፊነት ያለባቸው ሰዎችም ቢሆኑ በተመሳሳይ የሕጻናትን ቅርጽ በማቃናትና እንደ ችግኝ ዕለት በዕለት ተንከባክቦ ለፍሬ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።
ይህን ባለማድረጋቸው ታዲያ ልጆች በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ተጠያቂዎች መሆናቸው አይቀሬ ነው።የልጆቹ አድራጎት ወላጆች ወይም የወላጆች ተተኪዎች መልካም ሥነ ምግባርና ሥነ ሥርዓትን በልጆቹ አእምሮ ውስጥ አለመቅረጻቸውን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ለሚደርሰው ጉዳት አላፊ ይሆናሉ፡፡
ከእነዚህ አጠቃላይ እሳቤዎች የምን ረዳው አካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን በተመለከተ ወላጆችና የእነርሱ ተተኪዎች ከውል ውጭ የሆነ አላፊነት የሚጣልባቸው ያለባቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ እንደሆነ ብቻ ነው።ከዚህ ውጭ ግን የወላጅና የተወላጅ፤ የአሳዳሪና የልጁ ግንኙነት ወይም የመምህርና የተማሪ ግንኙነት በመኖሩ አልያም በልጁ አማካኝነት በተበዳዩ ላይ ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ብቻ ወላጆች ወይም የእነርሱ ተተኪዎች ካሣ እንዲከፍሉ ማስገደድ አይቻልም።
እዚህ ላይ መሰረታዊ የሆነ አከራካሪ ጉዳይ አለ። ከላይ በጽሁፉ መግቢያ እንዳየ ነው ከውል ውጭ የሚመጣ ኃላፊነት በራስ ጥፋት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት በማድረስ ወይም አጥፊ ሳይሆን አላፊ በመሆን ማለትም የራስ ጥፋት ባይኖርም እንኳን በአንዳንድ በሕግ ተለይተው በተጠቀሱ አድራጎቶች ወይም ንብረቶች አማካኝነት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሲደርስ የሚመጣ ነው።አካለ መጠን ላልደረሰ ልጅ የሚመጣው ተጠያቂነት ታዲያ ልጁ በጥፋት ላይ ተመስርቶ ተጠያቂ ስለሚሆንበት አላፊነት (በራሱ በሚፈ ጽማቸው ጥፋቶች) ነው ወይንስ ለሁሉም ዓይነት የልጁ ከውል ውጭ ለሆኑ ኃላፊነቶች ነው የሚለው አከራካሪ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ሕግ ዙሪያ ጥልቅ ምርምር ካደረጉ ግንባር ቀደም የቀለም ቀንዶች ውስጥ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆርጅ ችችኖዊች “The Ethiopian Law of Extra-Contractual Liability – የኢትዮጵያ ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ” በሚል በጻፉትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሳተመው መጽሐፋቸው ውስጥ አካለ መጠን ላልደረሰው ልጅ ያለው ኃላፊነት በጥፋቱ ላይ የተመሰረተውን ብቻ ሳይሆን ከውል ውጭ የሚደርሱትን ማናቸውንም የልጁን ኃላፊነቶች ሁሉ እንደ ሚያጠቃልል ያብራራሉ።
ይህ ማለት ለምሳሌ ልጁ ንብረት ቢኖረውና ንብረቱ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርስ የልጁ ኃላፊነት ያለጥፋቱ የሚመጣ ቢሆንም የልጁ ወላጆችም ተጠያቂዎች ይሆናሉ ማለት ነው።እናም አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ በጥፋቱ፣ ጥፋት ባልሆነ አድራጎቱ ጉዳት ቢያደርስ (ለምሳሌ ራሱን፣ ሌላን ሰው፣ ሃብቱን ወይም የሌላውን ሰው ሃብት በእርግጥ ሊደርስበት ከሚችል አደጋ ለማዳን ሲከላከል በሌላው ሰው ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ካደረሰ) ወይም በግል ንብረቱ ወይም ለግል ጥቅሙ በሚገለገልበት የሌላ ሰው ንብረት በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ቢያደርስ ወላጆቹ ወይም የእነርሱ ተተኪዎች ኃላፊ ይሆናሉ ማለት ነው በፕሮፌሰር ችችኖዊት ድምዳሜ።
“ከውል ውጭ ኃላፊነትና አላግባብ መበ ልጸግ ሕግ” በሚል ርዕስ በንጋቱ ተስፋዬ በተሰናዳው መጽሐፍ ደግሞ ከፕሮፌሰር ችችኖዊት በተቃራኒው የሆነ ዕይታ ነው የቀረበው።ሕጉ “አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ኃላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ…” በሚል ካስቀመጠው ድንጋጌ በመ ነሳት በመጽሐፉ እንደተብራራው የወላጆች ወይም የእነርሱ ምትክ የሆኑ ሰዎች ኃላፊነት አካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ አንድን ተግባር በራሱ ፈጽሞት ይህም ከውል ውጭ ኃላፊ የሚሆንበትን ጉዳት አስከትሎ ከሆነ ብቻ ነው።
ይህ ማለት የወላጆች ወይም የእነሱ ተተኪዎች ኃላፊነት በልጁ አድራጎት (ጥፋት ሆነም አልሆነም) በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት በሚያደርስበት ሁኔታ ላይ የተገደበ ነው ማለት ነው።ከዚህ ውጭ ግን ልጁ ያለጥፋቱም ቢሆን በማናቸውም ሁኔታ ከውል ውጭ ለሚያደርሳቸው ኃላፊነቶች ሁሉ ወላጆቹን ወይም የእነርሱን ተተኪዎች እንዲጠየቁ ሕጉ አያስገድድም።ለምሳሌ ልጁ ድርጊቱን በራሱ ሳይፈጽም ነገር ግን የእሱ ንብረት ወይም ለግል ጥቅሙ የሚገለገልበት የሌላ ሰው ንብረት ጉዳት ቢያደርስ ከራሱ ከልጁ በቀር ማንም በኃላፊነት መጠየቅ እንደማይገባው ነው የንጋቱ መጽሐፍ የሚያብራራው፡፡
የሆነው ሆኖ ፕሮፌሰር ችችኖዊች ትንታ ኔያቸውን የሚሰጡት “The father shall be liable under the law where his minor child incurs a liability.” በሚል በተገለጸው የሕጉ የእንግሊዝኛው ቅጅ ላይ ተመርኩዘው በመሆኑ ይህንን ብቻ በመያዝ ወላጆችና የእነርሱ ተተኪዎች ለሁሉም ዓይነት የልጁ ኃላፊነቶች ተጠያቂ ናቸው ወደሚል ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን።ይህ ደግሞ ከህጉ አጠቃላይ አረዳድ እንድንወጣ የሚያደርግ ነው።
በመሆኑም አካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የወላጆችና የእነርሱ ምትክ የሆኑ ሰዎች ኃላፊነት የተመሰረተው በአግባቡ አልተቆጣጠሩትም ከሚል የጥፋት ግምት እስከሆነ ድረስ አካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ በራሱ በሚፈጽማቸው ድርጊቶች እንጂ እሱ ባልፈጸማቸውና ያለጥፋቱ ኃላፊ በሚሆንባቸው በተለይም የእርሱ ንብረቶች በሚያደርሱት ጉዳት ሁሉ ሊጠየቁ አይገባም።
እዚህ ላይ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ሌላው ጉዳይ በወላጆች የተተኩ ሰዎች ኃላፊነትን የተመለከተው ነው።በዕምነት የተሰጣቸው የልጁ ጠባቂዎችና አስተማሪዎች ልጁ ኃላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሠራ እንደሆነ ተጠያቂነት አለባቸው።ኃላፊነታቸው ግን ልጁ ኃላፊነትን የሚያስከትለውን ሥራ በሚሠራበት ወቅት እነርሱ ልጁን የመቆ ጣጠር ሥልጣን የነበራቸው ከሆነ ብቻ ነው።
ልጆች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያ ሳልፉት በትምህርት ቤትና መሰል አካባቢዎች በጋራ በመሆኑ የአደጋ ሁኔታዎች ከፍተኛ ይሆናሉ።በእነዚህ አካባቢዎች ውስጥ ታዲያ ህጻናቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የመምህራን ነው።ነገር ግን በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መም ህራን በርካታ ናቸው።እንዲሁም ተማሪዎች በአብዛኛው እርስ በርስ የሚጎዳዱት መምህር ባለበት ሳይሆን በሌለበትና በእረፍት የጨዋታ ጊዜያቸው ነው።እናም ልጆች ለሚያደርሱት ጥፋት የትኛውን መምህር እንዴት ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል የሚለው ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በርካታ አገራት ይህንን ኃላፊነት ከመም ህራን ትከሻ ላይ አውርደዋል። በምትኩም ተማሪው በፈጸመው ተግባር ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሰው ወይም የትምህርት ተቋሙ መምህሩ ተማሪውን በመቆጣጠር ተግባሩ ላይ ያሳየውን ጉድለት በቅድሚያ እንዲያረጋግጥ የማስረዳት ሸክም እንዲኖርበት የሚያደርጉ ሕጎችን ይተገብራሉ።
የአገራችን ሕግ ግን አስተማሪ ተማሪውን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት በሚል ግምት ተማሪው ላደረሰው ጉዳት ኃላፊ እንዲሆን ያስገድደዋል። እናም ሕጋችን ወደፊት የመሻሻል ዕድል የሚገጥመው ከሆነ በአንድ በኩል መምህሩ ያለበትን የኃላፊነት ሸክም ለማቅለል በተማሪው ላይ ተገቢውን ቁጥጥር አለማድረጉን አስቀድሞ የማስረዳቱን ግዴታ በተማሪው ጉዳት ደርሶበታል በተባለው ተበዳይ ትከሻ ላይ ሊያደርግ ይገባል።በሌላ በኩል ካሣ የመክፈል ግዴታን (የመምህሩ ጥፋት ከባድ ካልሆነ በቀር) በትምህርት ቤቱ ላይ መጣሉ የተሻለ ስለመሆኑ ነው በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን የሚመክሩት።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
(ከገብረክርስቶስ)