ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹የመመሪያ አፈፃፀሙ የሠራተኞችን ዕንባ አፍስሷል›› በሚል ርዕስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በፍረዱኝ ገጽ ላይ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 12 ወደ ተቋማችን የመጣ ቅሬታን ማስተናገዳችን ይታወሳል። ሦስቱ ሠራተኞች በአቤቱታቸው፣ ያለ አግባብ ከሥራና ከደመወዝ በወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ እገዳ እንደተደረገባቸውና ይህን ተከትሎ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲደረጉ መወሰኑን አቅርበው ነበር። በተጨማሪም የሁለት ወራት ከ11 ቀናት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው መግለፃቸው ይታወሳል።
እኛም በዘገባችን የሠራተኞቹን ቅሬታ፣ የወረዳው ኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት እንዲሁም የወረዳው ፐብሊክ ሠርቪስና ሠው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምላሽ ብሎም የሰነድ ማስረጃዎችንና የወረዳው ዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔን አቅርበናል። ለዛሬም በዚሁ ጉዳይ ላይ የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ የክፍለ ከተማው እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሠው ሀብት ልማት ቢሮ የሰጡትን ምላሽ እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ምን ይላሉ?
የወረዳው ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አብራር ጋሻው፣ ሠራተኞችን በውሰት አዟዙሮ ለማሰራት ምክንያት የሆነው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ላይ ወረዳው የሠራተኛ እጥረት ስላለበት እንደሆነ ተናግረዋል። የህን ችግር ለማቃለልም በክፍለ ከተማው አቅጣጫ መሰረት፤ በጣም ጠንካራ፣ ባለጉዳይን በአግባቡ ሊያስተናግዱ የሚችሉና በሥራቸው ግንባር ቀደም የሆኑ ባለሙያዎችን ከፐብሊክ ሰርቪስ በባለሙያዎችና በአመራር ከተለዩ በኋላ፤ 11 ሠራተኞችን ወደ ጽሕፈት ቤቱ ገብተው እንዲያገለግሉ አወያዩ፤ ከእነዚህ መካከልም ሁለት ሠራተኞች ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹን ጨምሮ የተቀሩት ዘጠኑ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ይላሉ።
ሠራተኞቹ በውሰት እያገለገሉ ባሉበት ወቅት አዲስ የሠራተኛ ምደባ መጣ። ነገር ግን በዘርፉ የባለሙያ እጥረት እንዳለ የወሳኝ ኩነቶችና ምዝገባ ማስረጃ ኤጀንሲ ያውቃል። ይህንን ችግር ለማቃለልም ክፍለ ከተማው ባለሙያዎችን በጽሕፈት ቤቱ ለማሟላት ባለሙያ ተለይቶ እንዲላክ ተጠይቋል። በ03/05/2011 ዓ.ም ክፍለ ከተማው በጠየቀው መሠረት ዘጠኙ ባለሙያዎች በጽሕፈት ቤቱ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ሠራተኞቹ በተመደቡበት ጽሕፈት ቤት ገብተው ማገልገል ጀመሩ። ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ጫና ያለበት ጽሕፈት ቤት በመሆኑ ነው። የምደባ ደብዳቤው እንደደረሳቸው ገብተው መሥራት ጀመሩ።
በውሰት በጽሕፈት ቤቱ ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞች በነበሩበት እንዲቆዩ ማወያየታቸውን የሚያስታውሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በድጋሚ በ20/12/2011 ዓ.ም ኤጀንሲው ሰርኩላር ደብዳቤ ማውረዱን ይናገራሉ። በደብዳቤው ከዚህ ቀደም በውሰት በጽሕፈት ቤቱ ገብተው ሲያገለግሉ የነበሩ ባለሙያዎች ሌላ መመሪያ እስከሚመጣ በጽሕፈት ቤቱ እንዲያገለግሉ የሚያዝ ነበር። ደብዳቤው እንደደረሰ ሌሎች ሠራተኞች ፈቃደኛ ሆነው በጽሕፈት ቤቱ ሲያገለግሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግን ለመመሪያ ተገዢ ለመሆን ፈቃደኞች እንዳልነበሩ አቶ አብራር ያስረዳሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በሥራው ካለመስማማታቸው በተጨማሪ አላስፈላጊ ቃላቶችን ሲወረውሩ እንደነበርና ያሳዩ የነበሩት ሥነምግባር ፍጹም ትክክለኛነት የጎደለው ነበር በማለት ድርጊታቸውን ያወግዛሉ። ሦስቱ ሠራተኞች በእንቢተኝነት የወጡበትን ምክንያት ሲያስረዱ ጫና ስለሚበዛ ገብተው እንደማያገለግሉ ነው የገለጹት። ይሁን እንጂ በመመሪያው መሠረት የተቋሙ የሠው ኃይል አስተዳደር የሕብረተሰቡን እንግልት ለመቀነስ አንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ በውሰት ሠራተኛን አዘዋውሮ ማሰራት እንደሚችል ተቀምጧል። በዚህም ሠራተኞቹ በውሰት ለሰባት ወራት የሠሩ በመሆናቸው በጉዳዩ ላይ እንዲወያዩ ቢደረግም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው እንዲታይ ተደርጓል። ጥፋታቸው ለእግድ የሚዳርግ ነበር ወይ? ስንል ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፤ ለእግድ የሚያበቃ ሳይሆን ከሥራ የሚያሰናብት መሆኑን አስረግጠው ገልፀዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ በመመሪያው መሠረት ከሥራና ከደመወዝ የታገደ ሠራተኛ ሁለት ወር ባልበለጠ ውሳኔ ማግኘት እንዳለበት ያስቀምጣል። በዚህ ወቅት ውስጥ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል። የዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚያሳርፈው ውሳኔን የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ማሻሻልም ማጽደቅም ስለሚችል መመሪያውን መሠረት በማድረግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ተመጣጣኝ ውሳኔ እንዳሳረፉ ይናገራሉ። በሥራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በተለቀቀበት ወቅት የነዋሪነት መታወቂያና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሹ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች በበዙበት ወቅት ነው ጥለውን የወጡት።
መጀመሪያ እግድ የተደረገባቸው አራት ቢሆኑም አንዱ ሠራተኛ ግን በነበረበት ሕመም ሳቢያ መንገድ ላይ ወድቆ ሠዎች እንዳነሱት ሁሉ ማስረጃ ያለው ሠራተኛ በመሆኑ እርሳቸው በሥልጠና ላይ በነበሩበት ወቅት የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ መክረውና የሕክምና ማስረጃዎችን ተመልክተው እግዱውን እንዳነሱለት ገልፀዋል። ወይዘሪት ኢክራም ግን በውሰት ወደተመደበችበት የሥራ መደብ ስትሄድ ያለማንገራገር እንደገባች ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በወቅቱ በሙሉ ፈቃደኝነት ሥራዋን ስታከናውን እንደነበር ይናገራሉ። ባለሙያዋ ቀድሞ ትሠራበት በነበረው ጽሕፈት ቤት ከቅርብ የሥራ ኃላፊዋ ጋር ተግባብቶ የመሥራት ችግር ስለነበረባት በውሰት ለመሥራት የነበራት ዝግጁነት ከፍተኛ ነበር። እግድ ላይ በነበሩበት ወቅት በመጣው ሰርኩላር ምክንያት ወደ ሥራ ለመግባት ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳላነሱና ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያቀረቡት አቤቱታ ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል።
አቤኔዘር የተባለው ቅሬታ አቅራቢም የጽሕፈት ቤቱን ኃላፊ ቡድን በማደራጀት አመራር ለመደብደብና ጥቃት ለማድረስ ጥረት የሚያደርግ መሆኑ ተደርሶበታል። ኢክራም በተመሳሳይ በውይይት ወቅት “ተኝቶ የሚውል አመራርን አስገብተህ አሠራ›› የሚል ሥነምግባር የጎደለው ንግግር እንደተናገረች በመግለጽ፤ ባለሙያዎቹ መሠረታዊ የሥነምግባር ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል። የተወሰደው እርምጃም የማጥቃትና የመጠቃቃት ሳይሆን መመሪያን መሠረት ያደረገ ነው። ነገር ግን በዚህ ቅር የተሰኘ አካል በየደረጃው ቅሬታውን ሊያቀርብና በሕጉ መሠረት ሊዳኝ እንደሚችልም ይናገራሉ።
ወረዳው ሆደ ሰፊ ሆኖ ቅሬታ አቅራቢዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም አቶ አብራር ይገልፃሉ። ነገር ግን የቅሬታ አቅራቢዎቹ ዋነኛ ዓላማ ለውጥን የማደናቀፍ እንደነበርም ነው የሚያስረዱት። ማንም ሠው እንዲሰቃይ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ፤ በሥራ ላይ በደል ባደረሱ ሠራተኞች ክስ ለመመስረት መመሪያው የሚለው እስከ ሁለት ወራት ጊዜ መሆኑን እንጂ በ15 ቀናት ውስጥ ነው የሚለውን እንደማያውቁ ገልፀዋል። በወቅቱ ክስ መመስረት ለምን አልተቻለም? ሌላው ያቀረብነው ጥያቄ ነበር። እርሳቸውም ጉዳዩ ትክክል እንደሆነና ለዚህ ምክንያቱ ግን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላቱ በተለያየ ምክንያት ተሟልተው ባለመገኘታቸው እንጂ ሆነ ተብሎ ቀኑን ለማራዘም የተደረገ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
በተለይ ኢክራም የተባለችው ሠራተኛ ከፍተኛ የአመለካከት ችግር እንዳለባት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ። እኛም በንግግራችን መጀመሪያ ላይ በጽሕፈት ቤቱ በውሰት እንዲያገለግሉ የተመረጡት ሠራተኞች በነበሩበት ጽሕፈት ቤት የተሻሉና ለሌሎች አርዓያ ይሆናሉ ተብለው ግንባር ቀደም እንደነበሩ እንደገለጹልን በማስታወስ፤ የአመለካከት ክፍተት ያለበት ፈፃሚ እንዴት ግንባር ቀደም ሊባል ቻለ? በሚል ጥያቄ አነሳንላቸው። አቶ አብራርም ሁሉም የተሻሉ ናቸው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው ሲሉ መጀመሪያ ከሰጡት ምላሽ የሚቃረን አስተያየት ሰጥተውናል። ጽሕፈት ቤቱም የሚጠይቃቸው የትምህርት መስኮችና የሥራ ልምድ በመኖሩ እነዚህንም ከግንዛቤ በመክተት ታይተው እንደተመረጡ አስረድተዋል። በዚህ መልኩ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተው የቤት ሽልማት እንዲሰጣቸው ለውድድር የተላኩም ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ታግደው የቆዩበት እንዲሁም ከእግድ በኋላ ሥራ ላይ ገብተው በቆዩበት 11 ቀናት ውስጥ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ያቀርባሉና በዚህስ ላይ ምን ይላሉ? ሌላው ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ያቀረብንላቸው ጥያቄ ነበር። አቶ አብራር በምላሻቸው፤ ችግሩ የአስተዳደሩ እንደሆነ ያምናሉ። እግዱን ጨርሶ ወደ ሥራ የገባ ሠራተኛ ማግኘት ያለበትን ደመወዝ በወቅቱ ማግኘት እንደሚገባው ቢታወቅም፤ የክፍያ ደመወዝ የምትሠራው ባለሙያ ነፍሰጡር በመሆኗና ሌላ ሠራተኛ የማይሠራው በመሆኑ ሲሆን፤ አስተዳደሩ ግን ችግሩን ለማቃለል ባለው ቁርጠኝነት ገንዘቡ ወጪ ተደርጎ ለቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዲከፈል ከወረዳው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር ስምምነት ተደርሷል። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚያገኝ ተናግረዋል።
የዲሲፕሊን ኮሚቴው ው ሳ ኔ ባ ሳ ረ ፈ በ ት ወቅት ከከተማ ውጪ ለ ሥ ል ጠ ና ወ ጥ ተ ው እ ን ደ ነ በ ር ያ ስ ታ ው ሳ ሉ ። ወደ ሥራ ሲመለሱ ስለጉዳዩ ጠ ይ ቀ ው የ ተ ሰ ጣ ቸ ው ምላሽ፤ ከሳሾች ማስረጃዎችን እ ን ዲ ያ ቀ ር ቡ ቢ ጠ የ ቁ ም አ ለማ ቅ ረባ ቸ ው ን ነ ው ። ባ ደ ረ ጉ ት ማ ጣ ራ ት ም አመራሮቹ ያልተገኙበት መሠረታዊ ምክንያት በሥል ጠናና በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም የዲ ሲፒ ሊን ኮሚቴው ግን መረጃ ሳይቀርብለት የወሰነው ውሳኔ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ነበር።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከሳሽ ማስረጃ ባለማ ቅረባቸው ምክንያት ወደ ሥራ ይመለሱ የሚል ውሳኔ እንደተወሰነ ኮሚቴው የያዘው ቃለጉባዔ ያሳያል ይላሉ። በዚህ ላይም የኮሚቴውን ሰብሳቢ እንዳነጋገሩ ነው አቶ አብራር የሚገልጹት። ኮሚቴው ቀነ ቀጠሮ መስጠትና ያልተሟሉ ማስረጃዎች እንዲሟሉ ከማድረግ ይልቅ በደብዳቤ ለአመራሮች አሳውቆ ስላልተገኙለት ‹‹አመራሮቹ አልተገኙም›› በሚል እልህ በተጋባ መልኩ እግድ የተጣለባቸውን ሠራተኞች በነፃ ወደ ሥራ እንዲገቡ ወስኗል። ይህንን ተመልክተው ማስረጃዎችን ለኮሚቴው እንደሰጡና በድጋሚ ጉዳዩ እንዲያየው እንደመለሱት አቶ አብራር ይናገራሉ።
አመራሮች ከሥልጠና ሲመለሱከሳሽና ተከሳሽ በተገኙበት እንዲያዩት ለኮሚቴውሰብሳቢ ቢነግሯ ቸውም፤ አመራሮች ሳይመለሱ ውሳኔ እንደወሰኑ ይናገራሉ። ይህም የዲሲፕሊን ኮሚቴው ሕዝብን ሳይሆን የሠራተኛ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ እንጂ ሥራን መሠረት ያላደረገ ትስስር (ኔትዎርክ) እንዳለው የሚያመላክት ነው በማለት የኮሚቴውን ውሳኔ ይተቻሉ። በመቀጠልም አመራሮቹ ሲመለሱ ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ በደብዳቤ ይግባኝ ቢጠይቁም የዲሲፕሊን ኮሚቴው ሁለት ጊዜ በወሰነው ውሳኔ የሕግ ባለሙያ እንዳማከሩና ለሦስተኛ ጊዜመመልከታቸውም እንደሚያስጠይቃቸው ገልፀዋል። ይህም ተገቢ አለመሆኑን ሊያስረዷቸው ቢሞክሩም እንደሚከብዳቸው በመግለጽ፤ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ
ኃላፊ የሚወስነውን ግን እንደሚቀበሉት በውይይቱ ወቅት አቅርበዋል።
የኮሚቴውን ውሳኔ ባለመቀበል ሁለቱ ሠራተኞች አንድ ደረጃ ዝቅ እንዲሉ፤ በዚህም ከሚያገኙት ገቢ አንድ ሦስተኛ ተቆራጭ እንዲደረግ ሲወሰን፤ የወይዘሪት ኢክራም ደግሞ ሁለት ደረጃ ዝቅ እንድትልና ደመወዟም በተመሳሳይ ተቆራጭ እንዲደረግ መወሰናቸውን አቶ አብራር ይገልፃሉ። ውሳኔውን ሲወስኑም እንደ ችግራቸው ክብደትና ለመማር እንዳላቸው ዝግጁነት ተመልክተውና ውሳኔው አሳማኝና ተገቢነት ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
እኛም ይህንን ምላሻቸውን ካደመጥን በኋላ ወይዘሪት ኢክራም ከሌሎቹ ባለሙያዎች ጋር በተመሳሳይ ክስ እግድ ቢጣልባትም በስተመጨረሻ በዋና ሥራ አስፈፃሚው የተወሰነው ውሳኔ ግን ለብቻዋ ቢሮ በመገኘት እንድታነጋግርዎ ያቀረቡላትን ተደጋጋሚ ጥያቄ ባለመቀበሏ ከሌሎቹ ከፍ ያለ ቅጣት እንዲጣልባት ምክንያት መሆኑን በቅሬታ አቅርባለችና በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? በስተመጨረሻ ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ያነሳነው ጥያቄ ነበር።
ዋና ሥራ አስፈፃሚውም ቅሬታው ፍጹም መሠረተ ቢስና የፈጠራ ወሬ እንደሆነ ተናግረዋል። ለዚህም ማረጋገጫ የሆነ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማቅረብ እንደማትችልና ካለም ሊጠየቁ እንደሚችሉ በመግለጽ፤ ከዚህች ባለሙያ ጋር የተለየ ንግግር እንኳ እንደሌላቸውና ቢሯቸውም ከሌሎቹ እግድ ከተጣለባቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ጋር እንደሄደችና እንዳነጋገሯቸውም አስረድተዋል። ቅሬታው አመራርን ለማሸማቀቅ የተጠነሰሰ ሴራ ነው ሲሉም ተችተውታል። ውሳኔውም ቅሬታ አቅራቢዋ ባለችው መንገድ ሳይሆን ‹‹ተኝቶ የሚውል አመራር ስላለ እሱን አስገብተህ አሰራ›› እስከማለት የደረሰ ጽንፍ የወጣ ሥነሥርዓት የጎደለው ምላሽ ትሰጥ እንደነበርና የወረደ ሰርኩላርን ለመቀበል ልግመኛ እንደነበረች አስታውሰው፤ ውሳኔው እንደ ጥፋታቸው ክብደት በመመዘን በመመሪያው መሠረት የተሰጠ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል።
ክፍለ ከተማው
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና ፐብሊክ ሰርቪስና ሠው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ከበደ፤ ሁሉም ሥራዎች የሲቪል ሰርቫንት የዲሲፕሊን መመሪያን መሠረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ይገልፃሉ። ጉዳዩንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ በቃል ደረሰብን የሚሉትን በደል እንዳስረዱ ነው የሚናገሩት። ይህንንም ወረዳው ዘንድ ስልክ በመደወል ለማጣራት መሞከራቸውንም ነው የሚያስረዱት።
ጉዳዩ የዲሲፕሊን በመሆኑ በክፍለ ከተማ ለመመልከት በወረዳ ታይቶና ወረዳ ላይ ቅሬታ ቀርቦ ደስተኛ ያልሆነ አካል ክፍለ ከተማ በመሄድ በክፍለ ከተማው ፐብሊክ ሰርቪስና የሠው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የሠራተኛውን አቤቱታ ለሚመለከት አካል የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው። በዚህም በዲሲፕሊን ከተቀጡ በኋላ ደመወዝ እየተከፈላቸው አለመሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ መግለፃቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ያስታውሳሉ። በዚህ ላይም ከዋና ሥራ አስፈፃሚው ጋር መነጋገራቸውንም ነው የሚጠቁሙት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ቢቀጡም ደመወዛቸው ተቆራጭ የሚደረገው በተቀመጠው አሰራር መሠረት እየተቆረጠ ቀሪው ሊከፈላቸው እንደሚገባ ከወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ከወረዳውና ከክፍለ ከተማው ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ጋር መነጋገራቸውንና መግባባት ላይ መድረሳቸውን ያስረዳሉ። ነገር ግን የክፍያ ደመወዝ የምትሠራው ባለሙያ ነፍሰጡር በመሆኗ በጽሕፈት ቤቱ ባለመገኘቷ እንጂ ችግሩን ለመፍታት እየተሞከረ መሆኑ ከግንዛቤ መግባት ይኖርበታል ይላሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዋና ሥራ አስፈፃሚው የደረሰባቸውን በተመለከተ ግን ተጣርቶ ካልመጣ በስተቀር ተበድለዋል አልያም አልተበደሉም ብሎ ማለት ይከብዳል። ጉዳዩም በአሠራሩ መሠረት ነው የሚታየው። አሠራሩም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሁሉም የሚዳኝበት መሆን እንደሚጠበቅበትም ያብራራሉ። በዚህ መልኩም በየደረጃው ከወረዳ ጀምሮ የሚሰጠው ምላሽ የማያረካ ከሆነ በየደረጃው ቅሬታ የሚቀርብበት ስርዓት ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥያቄው በተደራጀ መልኩ እንዳልቀረበላቸው የሚናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ ተበደልን የሚሉት የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ቅሬታ ማንሳታቸውን ይገልፃሉ። ከዚህ ባለፈ የክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታውን በአግባቡ ካላየላቸው በተቀናጀ መንገድ ሚዛናዊ ሆነው እንዲያዩ የበላይ ኃላፊ በመሆናቸው ቢቀርብላቸው በዚህ መልኩ መታየት የሚችልበት ዕድል እንደነበር ይጠቁማሉ። ነገር ግን አሁንም የዘገየ ባለመሆኑ አቤቱታቸውን በየደረጃው እስከ መደበኛው ፍርድ ቤት ድረስ በማምራት ማቅረብ ይችላሉም ይላሉ።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ድርጊታቸው ያሳግዳል አልያም አያሳግድም ለማለት የሚቸግሩ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያስረዱት አቶ ቴዎድሮስ፤ መመሪያው በግልጽ በከባድ የዲሲፕሊን ግድፈት ውስጥ የሚወድቁ ተግባራት ካሉ ጉዳዩን ለማጣራት መረጃ ይጠፋል ሥራውንም ይጎዳል ተብሎ ከታመነ ሠራተኛው ታግዶ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ይደረግና ከሥራም ከደመወዝም ለሁለት ወራት እንዲታገድ ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል።
የቅሬታ አቅራቢዎቹን ጉዳይ ከመመሪያ ጋር አያይዘው ሲያስረዱም፤ ለኃላፊ አለመታዘዝ ብሎም ሥራን መበደል ከባድ የሥነ ምግባር ግድፈት ነው ይላሉ። በመሆኑም ድርጊቱ ከባድ የዲሲፕሊን ጥሰት ነው ተብሎ ከታመነ ከሥራም ከደመወዝም ሊታገዱ ይችላሉ። ድርጊቱም ተጣርቶ ከሥራው የማያሰናብተው ከሆነ ወደ ሥራው ተመልሶ የሚገባውን ጥቅማ ጥቅም እያገኘ የተወሰነበትን ቅጣት እየፈፀመ ቅሬታውን እያቀረበ መብቱ እየተከበረለት ይቀጥላል በማለት አሠራሩን ያስረዳሉ። በአሠራር ደረጃም ደመወዝ እንዳይከፈላቸው የሚከለክል መመሪያ አለመኖሩንም ያብራራሉ።
ክስ ሳይመሠረት ከአንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ ዕድሜ ለማስቆጠሩ የወረዳው ፐብሊክ ሰርቪስና ሠው ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት እንደ ምክንያት ያነሳው፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዲማሩ የሚል ነውና ይህስ እንዴት ይታያል? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ፤ ወረዳው በዚህ መልኩ ችግሮችን ለማቃለል ከተንቀሳቀሰ ክፍተት ነው በማለት ጉዳዩ ለውይይት የሚቀርብ አለመሆኑንም ያስረዳሉ። በመመሪያው መሠረት ሠራተኛው በ15 ቀናት ውስጥ የዲሲፕሊን ክሱ ሊደርሰውና ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባም ተናግረዋል። በዚህ መልኩ የፈፀመ አመራርም ሆነ ሠራተኛ ካለ ስህተት ነው በማለት ድርጊቱን ያወግዛሉ።
እኛም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሚያነሱት አንዱ ተጠያቂነት እንደሌለ በማመን ኃላፊዎች የሚፈጽሙት ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀም ነውና በተባለው መልኩ ስህተት የፈፀመ አካል እንዳለ ከተረጋገጠ ታዲያ ምን ዓይነት ቅጣት ያርፍበታል? በሚል ለአቶ ቴዎድሮስ ጥያቄ አንስተንላቸዋል። እርሳቸውም በምላሻቸው ይህንን የፈፀመ አመራር ተጠያቂ ነው በማለት ገልፀውልናል። አሠራር ባለመጠበቅ ሠው በማንገላታት አለአግባብ የተፈጠሩ ችግሮች ከተገኙ በሒደት ተጣርቶ ስህተት ሆኖ ከተገኘ ማስጠንቀቂያ ሊሰጠው ይችላል። ይህም በተወሰኑ አካላት የሚወሰን ሳይሆን በአጠቃላይ አመራር የሚታይ ነው የሚሆነው ። ከዚህ ውጪ ግን እንደ ሲቪል ሰራተኛ የአመራሩ ጉዳይ በዲሲፕሊን አይታይም ይላሉ።
በወረዳው ዲሲፕሊን ኮሚቴ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ የማሻሻል ሥልጣን ዘርፎችን አስተባብረው የሚመሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎች በመሆናቸው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥፋታቸው ከተረጋገጠ ግለሰብን ሳይሆን በድርጊታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ሊያርፍባቸው ይገባል። ክፍለ ከተማው መመሪያንና አሠራርን ለማስጠበቅና ችግሩን ለማቃለል ዝግጁ መሆኑንም ነው አቶ ቴዎድሮስ የሚገልጹት።
በክፍለ ከተማው ሰባት ሺህ የሚደርስ ሲቪል ሰርቫንት እንዳለ የሚገልጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ ይህንን ኃይል ለመምራትና ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ችግር አያጋጥምም ማለት አይቻልም ይላሉ። መንግሥት የሚያሰራቸውን ሠራተኞች መብት ማክበር እንዳለበት ይታመናል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያሉበት ወረዳ የወሳኝ ኩነት ሥራዎች የሚከናወኑበት በመሆኑ እናቶች ልጅ ይዘው፣ ነፍሰጡሮች እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የሚንገላቱበት ነው።
የወሳኝ ኩነትን ባለሙያ ለማሟላት ምደባ የሚደረ ገው በውድድር በመሆኑ መስፈርቱን የሚያሟላና ፍላጎት ያለው ሠራተኛ እንዲመደብ ይደረጋል። በዚህ መሠረት ለጽሕፈት ቤቱ የትምህርት አግባብነት፣ የሥራ ልምድ እንዲሁም የሥራ አፈፃፀም ይፈተሻል። በዚህም ለዚህ ጽሕፈት ቤት መንግሥት ያስቀመጠው አማራጭ ከዚህ ቀደም በጽሕፈት ቤቱ ሲሠሩ የነበሩ አገልግሎቱ ሰፊ ስለሆነ በተለይም ወደ ዘመናዊ አሠራር እየሄደ በመሆኑ ይህንን ማስተካከል ይገባል በሚል ከጽሕፈት ቤቱ የወጡ ሠራተኞችም ካሉ ተመልሰው መሥራት አለባቸው በሚል ሰርኩላር ደብዳቤ አውርዷል። በዚህ ፍቃደኛ የማይሆኑ ሠራተኞች ካሉም ያለምንም ምህረት የመንግሥትን መመሪያና አቅጣጫ ባለመቀበል ከሥራ እስከማሰናበት የሚደርስ ቅጣት እንደሚኖረው በግልጽ መቀመጡን ያብራራሉ። የበላይ የሥራ ኃላፊ ችግር ሊኖርበት ይችላል የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ሥራን ማዕከል ያደረጉ አቅጣጫዎችን በመቀበል ከዛ ውጪ ያሉትን ደግሞ ሕጋዊ በሆነ አግባብ መታገል ይገባል ይላሉ።
ከተማው ከሕግ አንጻር
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሠው ሀብት ልማት ቢሮ የሠው ሀብት ሥራ አመራር ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተመስገን፤ የሲቪል ሰርቪሱ ሕግ ዋነኛው የመንግሥት ሥራን ማዕከል አድርጎ ውጤታማ ከማድረግ አንፃር የውስጥ ሠራተኛውን አንቀሳቅሶ ወደ ሥራ የሚገባበት የስምሪት ዘዴዎች እንዳሉ ያስረዳሉ። ከዚህ ውስጥ አንዱ የትውስት ዝውውር ሲሆን፤ ሥራዎች ሲያስገድዱ እስከ አንድ ዓመት ለሚሆን ቆይታ ያለው ነው። ይህም የሚደረገው በአንድ የሥራ መደብ ላይ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን የባለጉዳይ መጉላላት ምላሽ የሚሰጥ ሠራተኛ አለመኖር፣ አጠቃላይ በመንግሥት ሥራ ላይ እንቅፋት የሚፈጥርና ሌሎች ቋሚ የሥራ መደቦች በቅጥርና በደረጃ ዕድገት በቋሚ ዝውውር ጊዜ በሚፈለገው ደረጃ ካልደረሰ እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ሠራተኛውን በትውስት አዛውሮ ለማሰራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ።
ሠራተኛው በትውስት ተዛውሮ ሲሠራ ከተጠያቂነት ጋር በመሆኑ በተመደበበት ዘርፍ ላይ ሙሉ ሰዓቱን በሥራ ሊያሳልፍ ይገባዋል። እስከ አንድ ዓመት በሚል የተቀመጠው የጊዜ ገደብም ከወራት እስከ ዓመት ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። በዚህ ውስጥ ግን አስተዳደሩ በተለይም የሚመለከተው ክፍል የሠው ኃይል አስተዳደሩ እስከዛ ድረስ ሠራተኛውን ማስቀመጥ ከደረጃ ዕድገት፣ ጥቅማ ጥቅምና ሌሎች ለውጦችን ማሰብ ይኖርበታል። ስለሆነም የሚመለከተው ክፍል የሥራ መደቡን በቋሚ ሠራተኛ በፍጥነት ማስያዝ ይኖርበታል።
ሥራው የሚሠራው ከተጠያቂነት ጋር በመሆኑና ብዙ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሁሉ መቀነስ መቻል አለበት። በዚህም ከአንድ ዓመት በላይ ሠራተኛው እንዲሰራ አይገደድም ብቻ ሳይሆን መሆን የለበትም። ከዚህ በላይ ከሆነ በርካታ ሊነሱ የሚችሉ የመብት ጥያቄዎች ከተቋሙ ጋርም ግጭት ሊፈጥሩ ይችላሉ። በመሆኑም ተቋሙ ከወዲሁ ማስተካከል የሚገባውን ጉዳይ መስመሩ ስላለፈ ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይቸግረዋል። ስለሆነም ተቋሙ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ የቤት ሥራውን በአግባቡ በመወጣት ከወዲሁ መጠናቀቅ የሚገባቸውን ተግባራት በትኩረት ሊያከናውን እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ያመለክታሉ።
ኃላፊዎች የአዋጅና የመመሪያዎችን አፈፃፀም በግልጽ ባለማወቅና ከሠው ኃይል ከአስተዳደሩ ጋር ቁጭ ብለው ሕጉ ምን ይላል? ሠራተኛውንስ እንዴት ነው አንቀሳቅሶ እያሠራ ያለው? በሚል ከአዋጁ ጋር አብሮ መገንዘብ ይገባቸዋል። በዚህ መልኩ ሲሆን፤ አዋጁንና መመሪያዎችን የሚፃረሩ ሰርኩላር ደብዳቤዎችም አይ ኖሩም።
ከአዋጅና መመሪያ አንፃር የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጉዳይ ላይ ዳይሬክተሩ በሰጡት ሙያዊ አስተያየት፤ እግድ ከባድ ነገር ነው ይላሉ። ከወሳኝ ኩነቶች ጋር ተያይዞ ቢሮው ያስተላለፈው ሰርኩላር ደብዳቤም ሥራውን የሚያውቁት ሠራተኞች ድልድሉ ወደሌላ ጽሕፈት ቤት ስለመደባቸው የሄዱበት ጽሕፈት ቤት እነዚህን ሠራተኞች የሚተካ ሠራተኛ እስኪገኝ መታገስ ይኖርበታል የሚለ ነበር።
ወሳኝ ኩነት ሕብረተሰቡ ፊት ለፊት ላይ የሚገኝ ትልቅ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመሆኑ ከነዋሪነት መታወቂያ ጀምሮ በርካታ ግልጋሎቶች ተደራሽ የሚደረጉበት በመሆኑ ቦታው ክፍት መሆን የለበትም። ስለዚህ እነዚህ ሰራተኞች ሲነሱ ለሌላ ሽግግር ደግሞ የተወሰኑ ሠራተኞችን አሰልጥኖና የሥራ መመሪያ በመስጠት ሥራውን አስተዋውቆ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል። በዚህም አመራሩ የጋራ መግባባት መውሰድ ይገባዋል። ምክንያቱ ደግሞ በዛው እንደሚቀጥሉ ሠራተኞቹ ስጋት ሊያድርባቸው ይችላልና ነው። በዚህ አሠራር ግን እግድ ደረጃ የሚያደርስ ሁኔታ አይኖርም ሲሉ ይናገራሉ።
ሠራተኛውም ተቋሙ ዋነኛ ዓላማው የመንግሥትን ሥራ ለማሳካት በመሆኑ አመራሩ የተገልጋዩን እንግልት ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ሠራተኛውም መታዘዝ እንዳለበት ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። ይህንንም ከግንዛቤ ከትቶ ለተወሰነ ጊዜ ሊረዳና ሕብረተሰቡን ሊያገለግል ይገባል። ጽሕፈት ቤቱ በርካታ የመረጃ ጥያቄዎች የሚነሱበትና ፈጣን ምላሽ የሚሻ በመሆኑ ሠራተኞቹ በሚቆዩበት ጥቂት ጊዜ ደመወዝ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ተቋማት እንዲያውቁት ተደርጓል። በዚህ መሀል በተፈጠረ ግጭት እገዳ የተሰጠ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጉዳዩ በዛ ደረጃ የሚያደርስ አይደለም ይላሉ።
እግድ የሚባለው በዲሲፕሊን ችግር ከሥራ እስከ መሰናበት የሚያደርስ ነው። ይህም ከሰነድ ማጥፋትና ሠራተኛው በሥራ ላይ ሆኖ ጉዳዩ ቢጣራ ችግር ይፈጠራል ተብሎ ሲታሰብ ብሎም ጥፋቱ ከባድ የሥነምግባር ጥሰት ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው እግድ የሚሰጠው። ነገር ግን ከዛ ውጪ አስተዳደራዊ ቅጣቶች ካሉ ማስኬድ ይቻል ነበር። እግድ ከተደረገ ደግሞ በመመሪያው መሠረት እግድ የደረሰው ሠራተኛ በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ሊከሰስ ይገባል። ከሁለት ወር በላይም በአጠቃላይ እንደማይታገድ አዋጁ ይደነግጋል።
ለእግድ መነሻ የተባሉ ምክንያቶችንም አዋጁ በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ ሠራተኛው ምንም ሳይሰራ ከቆየ ለመንግሥት ኪሳራም ነው። አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ካልተባረረ በስተቀር ያልተከፈለው የኋላ ክፍያ ተሰልቶ የሚያገኝበት ዕድል ሊኖር ስለሚችል ለመንግሥት ኪሣራ ያመጣል ሲሉ ያስረዳሉ።
እግዱን ሲጨርሱ ወደ ሥራ የሚመለሱና ደመወዝ የሚያገኙበት ቢሆንም ጉዳያቸው ግን መታየቱ ይቀጥላል። ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይንም የተቋሙ የበላይ ኃላፊ የዲሲፕሊን ኮሚቴን ውሳኔ ከጥፋቱ አንጻር እንዳለ ሊቀበለው፣ ሊያሻሽለው አልያም ላይቀበለው ይችላል። ይህም በአዋጁ የተሰጠው ሥልጣን ነው። በዚህ የማይስማማም ይግባኙን አቅርቦ ወደ አስተዳደር ፍርድ ቤት ሊያመራ ይችላል።
ከተቀመጡ ስድስት የቅጣት ዓይነቶች ውስጥ ከደረጃና ከደመወዝ ዝቅ መደረግ ተጠቃሽ ናቸው። በዚህ ሂደት አመራሮች ስህተት ፈጥረው ከተገኙ ሹመኛ በመሆናቸው አይታለፉም። በአገሪቱ ከሕግ በላይ የሚሆን የለም። ስለሆነም አመራሩ መሠረታዊ ስህተቶችን ፈጽሞ ከሆነ የማይጠየቅበት ምክንያት አይኖርም። በሕግም 78/2008 መመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በካቢኔ የፀደቀ በመኖሩ ተጠያቂነት ይኖራል። የሕግ የበላይነት ነው የሚኖረው።
የሠው ሀብት የሚመራበት ትላልቅ የሕግ ማዕቀፎች አሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ትልቁ አዋጁ መሆኑን ይጠቁማሉ።አዋጁን መሠረት ተደርገው የወጡ መመሪያ ዎችንም አመራሩ ከሚመለከተው የሥራ ክፍል ጋር በመሆን ሊደረግ ያሰበውን ሕጉ ምን ይላል? በሚል ተገናዝቦ በዚያ መሠረት ሊሠራ ይገባል። የአሠራርና የሕግ ጥሰቶች የተረጋጋ ሠራተኛ እንዳይፈጠር፣ በሕግ አይመራም እንዲሁም ግለሰቦች እንደፈለጉት ሕግን እየጣሱ ነው የሚል እሳቤን ያመጣል፡፡ በመሆኑም የሠው ኃይሉ የሚመራበት አዋጅና መመሪያዎችን በአግባቡ መተርጎምና በሥራ ላይ ማዋል ይገባል። ይህ ሲሆን አገልግሎት አሰጣጡ ውጤታማ መሆን ያስችለዋል፤ የተረጋጋ ሠራተኛንም ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2012
ፍዮሪ ተወልደ