የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳሥ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ያካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ከወትሮው የተለየ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ለዕለቱ ስብሰባው ከያዛቸው አጀንዳዎች መካከል የአስተዳደር ወሰንና የማንነትና ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የጋለ ክርክር አድርገው በታል፡፡ አባላቱ በኮሚሽኑ አስፈላጊነት፣ ሕጋዊነትና ገለልተኛነት ላይ በሁለት ጎራዎች ተከፍለው ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ አያስፈልግም፤ ሕጋዊም አይደለም›› ከሚሉ የኮሚሽኑ መቋቋም እጅግ ፍትሐዊና ወቅታዊ ነው እስከሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባል አቶ አፅብሃ አረጋዊ የኮሚሽኑ ረቂቅ አዋጅ የምርመራ ሂደት የሕዝብ ውይይት መድረክ የተዘጋጀበት ባለመሆኑ ተገቢነት የሌለው የረቂቅ አዋጅ የምርመራ ሂደትን የያዘ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ረቂቅ አዋጁ ብዙ የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችን ይጥሳል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንንና የማንነት ጥያቄ አጠያየቅ ስርዓትንም ይጋፋል፡፡ የመንግሥት አካላትን የአስፈፃሚነት ስልጣን በመጋፋትና ሕዝቦች የስልጣን ባለቤት እንዳይሆኑ በመንፈግ ሌሎች ችግሮችን ይፈጥራል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ክልሎችን ባለማሳተፉ ትልቅ ክፍተት አለበት፡፡ ሰፋፊ የሕዝብ ሃሳብ ማሰባሰቢያ መድረኮች ሊዘጋጁ ሲገባ የረቂቅ አዋጁ የምርመራ ሂደት ግን እነዚህን ቅደም ተከሎች ያልተከተለ ነው፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ገለልተኛ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ መሰረታዊ ችግር ያለበት በመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማፅደቁ ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ውጤቱ ግን አደገኛ ነው፤ በኋላ ችግር ያመጣል›› ይላሉ፡፡
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ መና አብርሃ ‹‹ውሳኔ የማይሰጥ ኮሚሽን ማቋቋም አስፈላጊነቱ ምንድን ነው?›› በማለት የኮሚሽኑን መቋቋም ተቃውመዋል፡፡ ኅብረተሰቡ በኮሚሽኑ አስፈላጊነት ላይ ውይይት ሳያደርግበት መቋቋሙ ተገቢ እንዳል ሆነም ይገልጻሉ፡፡
የኮሚሽኑን መቋቋም የሚደግፉት የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ግጭቶች በጥናት የተደገፈ ምክረ ሃሳብ ለማቅረብ ሁነኛ መሳሪያ እንደሚሆንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን እንደማይጋፋም ይሞግታሉ፡፡ አቶ ጌታቸው መለሰ የረቂቅ አዋጁን መጽደቅ ከደገፉ የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ኮሚሽኑ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች መፍትሔ የሚሰጥ አካል እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ የኮሚሽኑ መቋቋም ሕገ መንግሥቱን የሚያስከብር እንጂ የሚጥስ አይደለም፡፡
አቶ ናስር ካንሶ ‹‹ከረጅም ዓመታት በፊት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ባለመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እውቅና የተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ስለሆነና ችግሩን ለመፍታት ሕገ-መንግሥቱን ባከበረ መልኩ አማራጭ መንገዶችን መመልከት ተገቢ በመሆኑ የኮሚሽኑ መቋቋም ወቅታዊና አስፈላጊ ነው›› ይላሉ፡፡
ለአብነት ያህልም በአስተዳደር ወሰንና በማንነት ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ለእነዚህ ችግሮች የመፍትሔ ግብዓት የሚሰጥ አካል መቋቋሙ ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ተጋብዞ ‹‹ስልጣኔን ይጋፋል›› የሚል ተቃውሞ አለማቅረቡን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች እንደማይጥስና አማራጭ ምክረ ሃሳቦችን የማቅረብ እንጂ በራሱ ውሳኔ የማይሰጥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ ዝናቡ ይርጋ የኮሚሽኑ መቋቋም አስፈላጊና ወቅታዊ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ የኮሚሽኑ መቋቋም አገሪቱ ከአስተዳደር ወሰንና ከማንነት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ካሉባት ችግሮች አንፃር እጅግ አስፈላጊና ፍትሐዊ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያስረዱ ለማስቻል አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
ገለልተኛ የሆኑ ማስረጃዎችን ከማቅረብና በማንነት ጠያቂዎቹ ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ከማሳወቅ አንፃርም ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ኮሚሽኑ የማንነት ጉዳዮችን በሚያጣበት ወቅት የኅብረተሰቡን ሃሳብ ስለሚቀበል ሕዝቡ ሃሳቡ እንዲደመጥ ዕድል ይሰጣል፡፡ የማንነት ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት አግባብ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረንና የዜጎችን መብቶች የሚጥስ በመሆኑ ኮሚሽኑ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማሳወቅና የተነሱ ጥያቄዎች ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እገዛ ያደርጋል፡፡
‹‹የአገሪቱ የአስተዳደር ወሰኖች የተካለሉት ፖለቲካዊ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላ በመሆኑ ሕገ – መንግሥቱን መሰረት ያደረገ የወሰን አከላለል የለም›› የሚሉት አቶ ዝናቡ፣ የአስተዳደር ወሰንና ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስለሚነሱ ኮሚሽኑ መላ ኢትዮጵያን የሚመለከት መሆኑ እንደማይቀርም ይገልጻሉ፡፡
አቶ ዝናቡ የኮሚሽኑን አስፈላጊነት በይበልጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነት ካለመወጣቱ ጋር ያያይዙታል፡፡ ‹‹ምክር ቤቱ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና ቢኖረውም የሚያከናውነው ግን የፓርቲ ሥራ ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ለሚያነሱ አካላት ጥበቃ ማድረግ አልቻለም፡፡
እስከአሁን ድረስ ክልሎች የመብት ጥሰት ፈፅመዋል ብሎ ዕርምጃ እንዲወሰድም አላደረገም፡፡ ችግሮችን መፍታቱ ይቅርና ያባባሳቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ በተጨማሪም ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን የተሰጠው መሆኑን ረስቶታል፡፡ ‹ማንነታችን ይታወቅልን› የሚሉ አካላት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለመደ አሠራርና አሁን ባለው አፈና ጥያቄያቸውን ማክበርና መብታቸውን ማስከበር አይችሉም፡፡
የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ‹ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው› ተብለው ሲፈረጁ ቆይተዋል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ለመፈናቀል፣ ለእስራት፣ ለአካል ጉዳትና ለሞት ዳርጓል፡፡ ኮሚሽኑ ለፌዴሬሽንና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ስለሚያደርግ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ክልሎች አፍነው የያዟቸውን ጥያቄዎች እንዲታዩ ያደርጋል›› ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥራውን በአግባቡ እየሠራ ስላልሆነ ምክር በቱ ግዴታውን እንዲወጣ የኮሚሽኑ አስፈላጊነት አያጠያይቅም›› በማለት ይናገራሉ፡፡
የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ የሚቃወሙ ወገኖች ከሚያቀርቧቸው መቃወሚያዎች መካከል ኮሚሽኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንን ይጋፋል የሚለው ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ አቶ ዝናቡ ግን ኮሚሽኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ኃላፊነትን እንደማይጋፋ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ በራሱ የመወሰን ስልጣን ስለሌለው ከአስተዳደር ወሰንና ከማንነት ጉዳይ ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች ጥናት በማድረግና ምክረ ሃሳብ በማቅረብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እገዛ ያደርጋል፡፡ ለአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተሰጡት ኃላፊነቶች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥራውን በተሻለ መልኩ እንዲፈፅም ስለሚያግዘው ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን መቋቋም እንደ ስጋት ሊመለከተው አይገባም›› ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል የኮሚሽኑን መቋቋም የሚቃወሙት አካላት ኮሚሽኑን ገለልተኛ አይሆንም የሚል ስጋትም አላቸው፡፡ አቶ አፅብሃ የኮሚሽኑ ረቂቅ አዋጅ የምርመራ ሂደት የሕዝብ ውይይት መድረክ የተዘጋጀበት ባለመሆኑ ኮሚሽኑ ገለልተኛ እንዳይሆን ያደርገዋል ይላሉ፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ ዝናቡም ቢሆኑ የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመረጡና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሾሙ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ የኮሚሽኑ አባላት ለሥራው የሚመጥን የትምህርት ደረጃ ያላቸው፣ በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያስቀድሙ፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት የሚያምኑ፣ ሕዝቦች በፈቀዱት መንገድ እንዲኖሩ የሚያግዙ፣ ከብሔርና ከሃይማኖት ጥላቻ እንዲሁም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ነፃ የሆኑ፣ በብዝሃነትና በሕግ ልዕልና የሚያምኑና ለሙያቸው ታማኝ የሆኑ ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ ገለልተኛ ካልሆነ ሕዝቡም ተስፋ ይቆርጥና ወደማያባራ ጦርነት እንገባለን›› ይላሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ኮሌጅ መምህርና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ኮሚሽኑን ሊያጋጥሙት ከሚችሉ ፈተናዎች መካከል የገለልተ ኛነትና ነፃነት ጉዳይ አንዱ ሊሆን እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡ ኮሚሽኑን ከጥርጣሬ ነፃ በሆኑ ሰዎች ማዋቀርና ለኮሚሽኑ የሚመደቡ ሰዎች ምርጫም በጥንቃቄ መከናወን እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡ ያ ካልሆነ ግን ለተጨማሪ ግጭትና ጥፋት ምክንያት ይሆናል ይላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የክልሎች የሥራ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ የሚያደርጉት እገዛና ትብብር እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ኮሚሽኑ የሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች በክልሎች የበጀት ምደባ፣ የተፈጥሮ ሀብትና የፖለቲካ ስልጣን ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ከአስተዳደር ወሰንና ከማንነት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚሰማሩ የኮሚሽኑን አባላት ወደ አካባቢዎቹ እንዳይገቡ ሊያግዷቸው አልያም የተሳሳተ መረጃ ሊሰጧቸው ይችላል›› ይላሉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኮሚሽኑን መቋቋም አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የኮሚሽኑ መቋቋም ለዓመታት ሲንከባለሉ ለመጡ ጥያቄዎች በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሰረተ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል፡፡ የጥያቄዎቹ ስፋት፣ ብዛትና ውስብስብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩና ግጭቶች በመበራከታቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሰላም ሚኒስቴርና ሌሎች መንግሥታዊ አካላት ያላቸው ሕጋዊ ሥልጣንና ተግባር እንደተከበረና እንደተጠበቀ አስፈጻሚው አካል ለአንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለጉ አግባብነት እንዳለው በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ‹‹በሕገ መንግሥቱ ምላሽ አግኝተዋል›› በሚል ጥቅልና የግብር ይውጣ አያያዝ ምክንያት አግባብ የሆኑት ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ እና በአዋጁ በተገለጸበት አኳኋን ለሚመለከተው ክልል እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ የማይቀርብበት ሁኔታ በመኖሩ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ በመጣል ላይ እንደሚገኝ ያመለከተው መግለጫው፣ ጥያቄዎቹ ጥናትን መሰረት አድርገው መታየት እንዳለባቸውም ይጠቁማል፡፡
በመግለጫው እንደተብራራው፣ ኮሚሽኑ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑና በተደጋጋሚ እየተነሡ ያሉ ጥያቄዎችን ገለልተኛ በሆነና ሙያዊ ብቃት ባለው እንዲሁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያፈላልግና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ተቋም ነው፡፡ የኮሚሽኑ አባላትም ሕገ-መንግሥቱን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ለሕገ-መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ፣ በፌዴራል ስርዓቱ ላይ እምነት ያላቸው እንዲሁም በሁሉም ክልሎችና ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
አንተነህ ቸሬ