የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሰረቱ የግብርናው ዘርፍ ነው።ግብርናው ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ፣የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እና የሌሎች ልማት ሥራዎች ደጋፊ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።ሀገሪቱ ለዓመታት ባስመዘገበችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥም እንዲሁ ግብርናው የአምበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
ግብርናው እየጨመረ የሚመጣውን የህዝብ ብዛት ከመመገብ እና የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ከመሆን በተጨማሪ፣ በቀጣይ ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተከናወነ ባለው ተግባር አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ብዙ መስራት ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው ፣በግብርናው ዘርፍ በተ ከናወኑ ተግባሮች ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል።ይሁንና ዘርፉ ከሚጠበቅበት አንጻር ሲታይ ምርትና ምርታማነቱ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።ሀገሪቱ ስንዴ ከውጭ እያስመጣች ነው ፍላጎቷን እያሟላች ያለችው።መንግሥት ይህን በመገንዘብ ዘርፉን ማዘመን ላይ በትኩረት ለመስራት ወስኖ እየሰራ ነው።
ግብርናውን ለማዘመን በተለይም በመካናይዜሽን ላይ እንደሚሰራ በቅርቡም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም አስታውቀዋል። ለእዚህም ከቀረጥ ነጻ ማበረታቻ ጭምር እንደሚደረግም ተናግረዋል። የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻዎች ይህን የመንግሥትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ባለድርሻ አካላቱ ይህ ብቻውን ብዙ ርቀት እንደማያስጉዝ ነው የተናገሩት።ሌሎች ዘርፎችን እየደገፈ ለከፍታ ያበቃውን ግብርና የሚደግፉ የፋይናንስ ተቋማት እንደሌሉ ይጠቁማሉ። በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ካልሆነ በስተቀር ባንኮች ለአርሶ አደሩ የብድር አገልግሎት እንደማይሰጡ ተናግረው፣ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ እንደማይቅርብም ነው የሚገልጹት።
‹‹የሀገሪቱን ክፍለ ኢኮኖሚ 80 በመቶው የያዘው ግብርናው ትኩረት ተነፍጎታል›› የሚሉት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዋቅጅራ፣ ብዙ ነገሮች ከቀረጥ ነጻ በተጨማሪ ማበረታቻ ቢሰጣቸው የግብርናውን ምርትና ምርታማነት በመጨመር ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ተደራጅተው ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ለማዳበሪያ ኬሚካልና ምርጥ ዘር፣ ለመካናይዜሽን እንዲሁም ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የገንዘብ ችግር እንደሚገጥማቸው ያመለክታሉ።ግብርናውን ለማሳደግ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ቴክኖሎጂውን ከውጭ ለማስገባት ቢሞክሩም የውጭ ምንዛሪ ግን አይቀርብም ይላሉ።
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር ፤ማበ ረታቻው ለኅብረት ሥራ አዲስ አይደለም ይላሉ። ለመካናይዜሽን እና ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች በአዋጁ መሰረት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲቀርቡ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እንደሚደረግም ይጠቅሳሉ።
የአርሶ አደሮቹ መሰረታዊ ችግር ፋይናንስ የሚያቀርብላቸው ተቋም አለመኖሩ ላይ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣“ለገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፋይናንስ የሚያደርግ የፋይናንስ ተቋም እንደሌለም በመግለጽ የአቶ ተስፋዬን ሀሳብ ያጠናክራሉ።ብቸኛዋ የግብርናው ዘርፍ የሚደግፍ የፋይናንስ ተቋም የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ጠቅሰው፣ልማት ባንክ የሚደግፈው ባለሀብቶችን እንጂ አነስተኛ አርሶ አደሮችን አይደለም ይላሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና መካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ “ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በማስፋት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ፣ለመሠረተ ልማት፣ለት ራንስፖርት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለኮንስትራክሽንና ለመሳ ሰሉት የአገልግሎት ዘርፉ ሥራዎች የተሰጠው ትኩረት ለግብርናው ካልተሠጠ ዕድገቱ ዘላቂ ሊሆን አይችልም።
አቶ ታምሩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዳሉት፤ በመካናይዜሽን 70 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየት እንዲሁም የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ብክነትንም ከ15 እስከ 20 በመቶ በመቀነስ ምርታማነትን ከ30 እስከ 50 በመቶ መጨመር ይቻላል።ስለዚህ ግብርና መካናይዜሽን አማራጭ የለውም። አርሶ አደሮች በመካናይዜሽን ለመጠቀም ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ መደረግ አለበት።
አቶ ታምሩ ቀረጥ መቀነስ ብቻውን በቂ አለመሆኑን ተናግረው ፣መንግሥት ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚኖርበት ጠቁመዋል። እስካሁን ግብርናው ያፈራው ሀብት ወደ ሌላው ዘርፍ ሄዶ ዘርፉን ማሳደጉን ጠቅሰው፣ግብርናው ሌላውን ሲያሳድግ እሱ ጥሪቱን እያጣ መሆኑንና አሁን ራሱን በሚደግፍበት ደረጃ ላይ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ባንኮች ብድር በማቅረብ የውጭ ምንዛሪም በመፍቀድ ዘርፉን መደገፍ እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ።
‹‹ታክስ ቅነሳ ማድረጉ ግብርናው እንዲያድግ ጥሩና ትልቅ እርምጃ ነው።ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ መቅረብ ይኖርበታል።››ያሉት አቶ ታምሩ፣የሀገር ውስጥ አቅም መፈጠር እንደሚኖርበትም ያመለክ ታሉ።
እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ፤እነዚህን መሳሪያዎች በሀገር ደረጃ ማምረት ይገባል።ሁሉንም ከውጭ እያስገቡ አይቻልም።ብዙ ሀገሮች የራሳቸውን አቅም መፍጠር እስኪችሉ ጃፓን፣ ቻይና፣ ህንድ ከውጭ እያስገቡ ሰርተዋል። ለጊዜው ኢትዮጵያም በዛው ልክ ስለምትሰራ የግድ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልጋታል።
የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች በቅርቡ ከሱዳንና ከደቡብ አፍሪካ ከመጡ የልኡካን ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።ከውይይቱ በኋላ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ የግብርናው ዘርፍ በተለይ አርሶ አደሩ ግብርናውን የሚያሳድግበትን የፋይናንስ ድጋፍ እያገኘ አይደለም።አርሶ አደሩ ፋይናንስ እስከ አሁን እያገኘ ያለው ከቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት መሆኑን ጠቅሰው ፣ባንኮች ለዘርፉ ብድር የሚሰጡበት ሁኔታ እንደሌለ ገልጸዋል።በቀጣይ ይህን ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የግብርናው ዘርፍ ደጋፊ የፋይናንስ ዘርፍ ያስፈልገዋል። አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ማህበራት ብድር እያቀረቡ ቢሆንም የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ለመደገፍና ለማሳደግ እጅና ጓንት ሆነው መሥራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ