ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለ37 ዓመታት ዚምባቡዌን የመሯት ሮበርት ሙጋቤን፣ ተክተው ከሁለት ዓመት በፊት የፕሬዚዳንትነት መንበረ ስልጣኑን ሲረከቡ የሀገሪቱን የወደቀ ኢኮኖሚ ለማሻሻልና የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ቅድሚያ እንደሚሰጡ ቃላቸውን ሠጥተው ነበር።
ይህን ቃላቸውን ያደመጡ በርካቶችም ከሙጋቤ ዘመናት የተሻለች ዚምባቡዌን ይፈጥራሉ ብለው ከፍተኛ ዕምነት ያሳደሩባቸው ሲሆን እያደር የተስተዋለው የሀገሪቱ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያው ለውጥ ግን ፕሬዚዳንቱን ቃል አባይ ያደረገና ዚምባቡዌያውያንን ያስደሰተ አልሆነም።
ዜጎቻቸው ተስፋ እንዳጡባቸው የተገነዘቡት ምናንጋግዋ ‹‹ለምገነባት አዲሲቷ ዚምባቡዌ ጊዜ ስጡኝ›› ሲሉ ጥሪ ቢያቀርቡም ዜጎቻቸው ግን ይባስ ብለው የሙጋቤን ስህተት እየደገሙ ነው የሚል ‹‹ይበቃል በሚል መንፈስ›› ፊታቸውን አጥቁረውባቸዋል።
አገሪቱ በአሁን ወቅት ባለፈው አስር ዓመት ከነበረው በላይ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ቀውስ በከፋ ሁኔታ ውስጥም ትገኛለች። በቂ መጠባበቂያ ገንዘብ የለም። የነዳጅ እጥረትም ሕዝቡን ፈትኖታል። ግሽበቱም 300 ፐርሰንት መድረሱ ይገለፃል።
አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ፣ ነዳጅ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እንዲሁም መሰረታዊ የምግብ ፋጆታዎች ክፉኛ አጥረዋታል። የሥራ አጥነት መጠኑ ዘጠና በመቶ መድረሱ የሚነገር ሲሆን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀወሱም ነዋሪውን አስቆጥቶ በተደጋጋሚ ለተቃውሞ አደባባይ አስወጥቶትም ተስተውሏል።
በቱሪዝም፣ በግብርናና በማዕድን ሀብት በበለፀገችው አገር፣ አስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ታዲያ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከሁሉ በላይ ግን በሙጋቤ ዘመነ መንግስት «ዴሞክራሲን በአግባቡ መተግበር እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቀረት አልቻልሽም» በሚል እኤአ በ2003 በአሜሪካ መንግሥት የተጣለባት ማዕቀብ ኢኮኖሚዋ እንዳያንሰራራ ቀፍድዶ እንደያዘው ይታመናል።
ምንም እንኳን ይህ የዋሽንግተን መንግስት ማዕቀብ ምናንጋግዋ ወደ ስልጣን እንደመጡ እንደ ፖለቲካ ቁርጠኝነትና ማሻሻያ ትግበራ አፈጻጸማቸው ታይቶ ‹‹ሊነሳ ይችላል›› ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም ይባስ ብሎ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል።
ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ 85 ግለሰቦች እንዲሁም 56 ካምፓኒና ተቋማት ላይ ተፈጻሚ እንደሆነ የሚገለጸው ማእቀብ የፋይናንስ የጎዞ ዝውውር ክልከላን ይካትታል። ይህ ‹‹ማእቀቡ የአገሪቱን ተስፋ ከማጨለም ባለፈ የኢኮኖሚያችን ቀስ በቀስ አንኮታኩቷታል›› የሚሉት ፕሬዚዳንት፣ ምናንጋግዋ፣ እንደ ሙጋቤ ሁሉ ለምጣኔ ሃብት ቀውሱ ዋነኛው ምክንያት የመንግስታቸው ደካማ ፖሊሲ አሊያም አፈፃፀም ውስንነት ሳይሆን ዋሽንግተን ውሳኔ ነው ሲሉ አመክኝተዋል።
‹‹እኔ በተመረጡ ግለሰቦች፣ ካምፓኒና ተቋማት እንጂ ዚምባቡዌ ላይ እንደ አገር ማእቀብ አልጣልኩም›› የሚሉት ዩናይትድ እስቴትስም፣ አሁንም ቢሆን የባለሃብቶች በዚምባቡዌ ምድር ላይ መዋእለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ አለመከልከሉን በመጠቆም፣ የተቀሰረባት ጣት አግባብ አለመሆኑን ማስገንዘብ መርጣለች። የአውሮፓ ህብረትም ቢሆን እገዳው በአገሪቱ ላይ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት የሚፈጥር አለመሆኑን ስለመግለፁ የቢቢሲ ዘገባ አስነብቧል።
ምንም እንኳን አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ከተን››ኮታኮተው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጀርባ ምክንያት ሆነው ሊጠቀሱ እንደማይገብ ቢያስገነዝቡም፣ በርካታ የዚምባቡዌ ዜጎችም ሆነ የአገሪቱ መንግስት ግን ማእቀብ ለመቃወም አዲስ ክብረ በዓል ይፋ አድርገዋል።
ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሻሻል ብሎም ለብልጽግናዋ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑን የታመነበት የጸረ ማእቀቡ ቀን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በመዲናዋ ሃራሬ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚያን በተሳተፉበት ተከብራል። በበዓሉ ላይ የተገኙት ኤመርሰን ምናንጋግዋም ‹‹የምእራባውያን ማእቀብ ለኢኮኖሚያችን ካንሰር ሆኖበታል፣ በሚል ማእቀቡ ሳይውል ሳያድር እንዲነሳላቸው ጠይቀዋል። አንዳንዶች ግን፣ ከዚህ አይነቱ እርባና ቢስ በዓል ይልቅ ለተንኮታኮተው ኢኮኖሚ አፋጣኝ መድኃኒት እንፈልጋለን›› ሲሉ ተደምጠዋል።
‹ንቅናቄ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ› የተባለውና በኔልሰን ቻሚሳ የሚመራው የተቃዋሚ ፓርቲም የዚምባቡዌን ከተንኮታኮተ ኢኮኖሚ ለመታደግ ሁነኛና ሁለንተናዊ ማሻሻያ እንዲሁም ዲሞክራሲ ማስፈን ግድ ይላል፣ ከዚህ በተለየ መሰል የማእቀብ ተቃውሞ በዓል ማዘጋጀት፣ ደካማ የመንግስት አፈፃፀም ለመሸፋፈን የተቀመረ ፕሮፖጋንዳ ነው ሲሉ መወረፋቸውን ቢቢሲ አስነብቧል። በዚምባቡዌ የዩናይትድ እስቴትስ ኤምባሲም የኢኮኖሚ ቀውሱ የመንግስት የፖሊሲ ድክመት ውጤት ነው ሲል የበዓሉ አጀንዳ የተሳሳተ ስለመሆኑ የሚጠቁም አስተያየት ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዚምባቡዌን የተንኮታኮተ ኢኮኖሚ ለመታደግ የአገሪቱ ባንክ አዲስና መግዛት አቅሙ ጠንካራ ሆነ የመገባበያ ገንዘብ በማተም ላይ ስለመሆኑ የቢዝነስ ዴይ ፀሃፊው ክቨን ሳማታ ዘገባ አስነብቧል። እንደ ዘገባው ከሆነ የአገሪቱ የፋይናንስና ማርኬት ምክትል ዳይሬክተሩ ዊልያም ማንማንዚ ‹‹መቼ የሚለው መናገር ባልችልም፣ በቅርቡም አዲስ መገባበያ ገንዘብ ወደ ገበያ ይወጣል›› ሲሉ ለፓርላማው በጀትና ፋይናንስ ኮሚቴ ተናግረዋል። ታዋቂው ኢኮኖሚስት ጆን ሮበርተሰን በአንፃሩ፣ ማእከላዊ ባንኩ በርካታ መገበያያ ገንዘብ ወደ ገበያው ማስገባት ግሽበቱን ይበልጡን ሊያባብሰው እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።
ሁሉን ያስተዋሉት ታዋቂው ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ቶኒ ሃውኪንስ ና ሌሎችም ባለሙያዎች፣ ከዓመት ዓመት የተመዘገቡ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ አሁንም ቢሆን አስፈላጊ የተባሉ ሁነኛ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በአፋጣኝ መተግበር ካልተቻለ ኢኮኖሚ ድቀቱ እያደር እንደሚባብስ አትጠራጠሩ ››ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2012
ታምራት ተስፋዬ