በብዝሀ ሕይወት ሀብቱ በ2007 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩ.ኔ.ስ.ኮ) መዝገብ ላይ የሰፈረው ግዙፉ ጣና ሐይቅ ሕልውናውን አደጋ ላይ በጣለና ‹‹እምቦጭ›› በተባለ መጤ አረም ተወሯል፡፡ አረሙ በሀይቁ ላይ መታየቱ የተረጋገጠው በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ነበር፡፡ በመስከረም 2004 ዓ.ም የአካባቢ ጥበቃ ምሁራንና የስነ-ምህዳር ባለሙያዎች አረሙ በሐይቁ ላይ መከሰቱን ለአማራ ክልል ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡
በ2005 ዓ.ም በሐይቁ ላይ ከነበረው የእምቦጭ አረም ከ95 እስከ 99 በመቶ የሚሆነውን ማስወገድ መቻሉም መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ተከታታይ ሥራ ባለመሰራቱ በ2006 ዓ.ም እና በ2007 ዓ.ም ከአራት ሺ እስከ 10ሺ ሄክታር የነበረው የአረሙ ስርጭት ከ40ሺ እስከ 50ሺ ሄክታር ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡ ይባስ ብሎም በአንዳንድ የሐይቁ አካባቢዎች 20 ቀበሌዎችን ተቆጣጥሮ 120 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን የሐይቁን ዳርቻ አረሙ ሸፍኖት ችግሩን አባብሶታል፡፡
እምቦጭ አረም ቪክቶሪያ ሐይቅና የደቡብ አሜሪካ ውሃማ አካላት ላይ ተከስቶ ያስከተለውን ችግር ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ያህል በአጭር ጊዜ ሰፊ ቦታን የሸፈነ አረም የሚያክል ግን በዓለም ላይ አልታየም፡፡ ጣና ላይ የተከሰተው እምቦጭ የሐይቁን ብዝሃ ሕይወት ሙሉ በሙሉ አውድሞ የውሃውን ሕልውና የሚፈታተን ሆኖ ነው የተገኘው፡፡
የሀይቁን ሁኔታ የሚከታተሉ ባለሙያዎች ይፋ ያደረጉዋቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አረሙ በሐይቁ ውሃ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታትን እያጠፋቸው፣ውሃውን እያደረቀው ይገኛል፡፡ 240 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆነው የሐይቁ ክፍል ሕይወት አልባ መሆኑም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
ባለሙያቹ የአረሙን ስርጭት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት የሚያስችል ሦስት ዓይነት መንገዶች አመላክተዋል፡፡ አንዱ በሰው እጅ ወይም በማሽኖች መንቀል/ማጨድ ሲሆን፣ሁለተኛው ኬሚካሎችን መርጨት፣ ሶስተኛው ዘዴ ደግሞ አረሙን ነፍሳት እንዲበሉት ማድረግ ነው፡፡ ከሶስቱ አማራጮች የተሻለውና ውጤታማው ዘዴ አረሙን በሌሎች ነፍሳት የማስበላቱ (ስነ-ሕይወታዊ) ዘዴ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡ በኬሚካል በመርጨት አረሙን ለማስወገድ የሚደረግ ሙከራ በውሃው ውስጥ የሚገኙትን ብዝሃ ሕይወት በማጥፋት የባሰ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ አይመከርም፡፡ እስካሁን የጣናን እምቦጭ ስርጭት ለመቀነስ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል አረሙን በሰው ጉልበትና በአረም ማጨጃ ማሽኖች የማጨድ ተግባር ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ተግባር የአረሙን ስርጭት መቀነስ እንጂ ማስወገድ አልተቻለም፡፡
የ2010 ዓ.ም መረጃ እንደሚያሳየው ከ235ሺ በላይ ሕዝብ በእምቦጭ አረም ማስወገድ ላይ ተሳትፏል፡፡ በተጨማሪም የእምቦጭ ማጨጃ ማሽኖችን ከውጭ አገር በማስገባት አረሙን የማጨድ ስራ ለመስራት ተሞክሯል፡፡ በእነዚህ ጥረቶችም የአረሙን ስርጭት በዘላቂነት መግታት ባይቻልም ለጊዜው ማስተንፈሻ ሆነው ዘልቀዋል፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተሰርተው፣ በግል ባለሀብቶችና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የገቡት የማጨጃ ማሽኖች ቁጥርም ከአረሙ በፍጥነት የከመስፋፋት ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ የአረሙን ስርጭት መግታት አልተቻለም፡፡ በሰው ጉልበት የሚከናወነው የአረም አወጋገድም ጥንቃቄ የጎደለው በመሆኑ አረሙ ከመቀነስ ይልቅ እንዲስፋፋ በር ከፍቷል፡፡
በውሃው ውስጥና በሐይቁ ዙሪያ የአረሙ መስፋፋት ያስከተለው ችግር የውሃው መድረቅ ብቻ አይደለም፤የአሣ ምርት እንዲቀንስ፣ በውስጡና በአካባቢው የሚኖሩ ፍጡራን ሕልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከማድረጉ በተጨማሪ ሕይወቱን በጣና ላይ የመሰረተው እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋውን ህዝብም ተጎጂ አድርጓል፡፡
እምቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ መኖሩ ከታወቀበትና ባለሙያዎች ችግሩን ለክልሉ መንግሥት ካሳወቁ ድፍን ሰባት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ምሁራንና የስነ-ምህዳር ባለሙያዎች ትኩረቱን ጣናን መጠበቅና መንከባከብ ላይ ያደረገ ተቋም ተቋቁሞ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግ ያቀረቡት ሃሳብ ሰሚ ሳያገኝ ጣናም ሕመሙ እየጸና ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም ተቋማዊ ቅርፅ ይዘው ከመራመድ አንፃር ግን ሰፊ ውስንነቶች ይስተዋላሉ፡፡ እዚህ ላይ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተቋቁሞ ለሐይቁ ችግር ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት እየተጋ የሚገኘውን ዓለም አቀፉን የጣና ጥበቃና እንክብካቤ ጥምረት (Global Coalition for Lake Tana Restoration) የተባለውን ተቋም እውቅና ሳልሰጥና ሳላመሰግን ማለፍ ንፉግነት ይሆንብኛል፡፡ የመንግሥት ቸልተኝነት ግን የሚያበሳጭ ብቻ ሳይሆን ግራ የሚያጋባም ጭምር ነው፡፡
ያም አለ ይህ የጣናን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ዓላማው ልክ እንደጣና የገዘፈ ሳይንሳዊ ተቋም በማቋቋም እንጂ አረሙ እንዲጠፋ በመመኘት አልያም እንዲህ ያለውን አደገኛ አረም ከአርሶ አደር ጉልበትና ከሁለት ማሽኖች ጋር በማፋለም አይደለም፡፡ ሰሞኑን የክልሉ መንግሥት ‹‹ጣናንና ሌሎች ውሃማ አካላትን የሚጠብቅ ተቋም አቋቁሜያለሁ›› ቢልም እጅግ የዘገየ ውሳኔ ነው፡፡
ዓለም እንዲህ በቴክኖሎጂ ምጥቀት ጥግ በደረሰችበት በዚህ ወቅት እንኳ ለሰው ልጅ አእምሮ እንቆቅልሽ እንደሆኑ የቀሩት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም ዓይናችን እያየ ሊጠፉ የተቃረቡ ቅርሶች ሆነዋል፡፡ እንኳን በዓይኑ ላየው ይቅርና ስለአሰራሩና ስለታሪኩ በወሬ የሰማውንና በጽሑፍ ያነበበውን ሰው ሁሉ የሚያስገርሙት የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ፣ የአሰራር ጥበባቸው እስከዛሬም ድረስ ለሰው ልጅ አእምሮ እንቆቅልሽ እንደሆኑ ዘልቀዋል፡፡ ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጊዜ ጀምሮ እንደ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃ ያለ በዚህች ምድር ላይ እንዳልተሠራና ወደፊትም እንደማይሠራ የጻፉ ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡
‹‹… ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ብዙ ብጽፍም የሚያምነኝ ሰው ስለመኖሩ በጣም ያስጨንቀኛል፤ ያሳስበኛልም፡፡ እስካሁን ያልኩትንም እንኳ ቢሆን ‹ውሸት ነው› ነው የሚሉኝ፤ ነገር ግን የጻፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፤ ሆኖም ስሜ በቀጣፊነት እንዳይነሣ እሰጋለሁ፡፡ ይህን የሚመስል ስራ በዓለም ላይ እንደማይገኝም እገልፃለሁ!…››
ከላይ የተጠቀሰውን ንግግር የተናገረው እ.አ.አ በ1520 ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለስድስት ዓመታት ያህል እዚሁ የቆየውና የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስን ከጫፍ እስከ ጫፍ የጎበኘው ፖርቹጋላዊ አሳሽ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው፡፡ መቼም ይህን የአልቫሬዝን ንግግር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ያነበበ ሰው ሁሉ ያስታውሰዋል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡ መካነ ቅርሱ በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት የተሠሩና ከአንድ ወጥ ድንጋይ የታነፁ 11 አብያተ ክርስቲያናትን የያዘ እጅግ አስደናቂ ስፍራ ነው፡፡
ለዚህ ተዓምረኛ ስራ ገጣሚው በጥዑም ዜማና በሠናይ ቃና አዚሞለታል፤ የቅኔው ሊቅ ደግሞ ‹‹ሞት ወሕንጻ ላሊበላ ኩለሄ እንግዳ – ሞትና የላሊበላ ሕንጻ ሁልጊዜ አዲስ፣ ሁልጊዜ እንግዳ ነው፤ አይለመድም›› ብሎ ተቀኝቶለታል፡፡
ከባህር ማዶ የመጡት ጎብኚዎች በበኩላቸው ‹‹Incredible/ Spectacular/ Astonishing/ Amazing/ Surprising … (የማይታመን፣ ግሩም፣ ድንቅ፣ እጹብ …) እያሉ አሞግሰውታል፡፡ የአሰራሩን ምስጢር አምነው መቀበል የተሳናቸው የውጭ ሀገራት ሰዎችም ‹‹ኢትዮጵያውያንማ ይህንን አልሰሩትም›› ብለው አፋቸውን ሞልተው ተከራክረዋል፡፡ ላሊበላ ግን አሰራሩን ያመነውን አሳምኖ ያላመነውን ደግሞ ግራ አጋብቶና አስደንቆ ከ800 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በአጭሩ የላሊበላ የአስደናቂነቱ ነገር ተነግሮና ተፅፎ አያልቅም!
ይሁን እንጂ መካነ ቅርሱ ከህፃን እስከ አዋቂ በሁሉም አስደናቂነቱ ቢመሰከርለትም፣ በበርካታ ችግሮች ተጠፍንጎ ከመያዝ አልዳነም፡፡ ይህ በሮሃ ምድር ተፀንሶ ከድንጋይ ማሕፀን የተወለደው ጥበብ የተደረገለት እንክብካቤና ጥበቃ እንዲሁም የጎብኚዎቹ ቁጥር ከአሰራር ጥበቡ ጋር ሲነፃፀሩ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡
የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ከተጋረጡበት በርካታ ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል … አብያተ ክርስቲያናቱ ተገቢው ጥገናና እድሳት ስላልተደረገላቸው ተሰነጣጥቀዋል፡፡ በአካባቢው ያለው የእፅዋት ብስባሽ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ተከማችቶ አብያተ ክርስቲያናቱን ለብልሽትና ለጉዳት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ እነዚህን ችግሮች ለብዙ ዓመታት ተቋቁመው ቢዘልቁም አሁን ግን ከነዚህኞቹ ችግሮች የባሰ ትልቅ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት ከአውሮፓ ኅብረት በተገኘ የ11 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ አብያተ ክርስቲያናቱን ከፀሐይና ከዝናብ ለመከላከል የተሰራው የብረት ክዳን ለአብያተ ክርስቲያናቱ አደጋ ሆኖባቸዋል፡፡
ይህ ግዙፍ የብረት ክዳን በነፋስና በሌሎች ምክንያቶች አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ ከወደቀባቸው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለሱ ታሪክ ሆነው እንደሚቀሩ የአካባቢው ነዋሪዎችና ለቅርሱ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ሳይንሳዊ ጥናት ያካሄዱ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ሕዝብም የብረት ክዳኑ እንዲነሳ መናገር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የብረት ክዳኑ እንዲነሳ ወስኖ የቤተ-ክርስቲያኗ ፓትርያርክም መንግሥት የብረት ክዳኑን ለማንሳት የሚያስፈልገውን የገንዘብ፣ የቁሳቁስና ሌሎች እገዛዎችን እንዲደርግ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ደብዳቤ ፅፎ ነበር፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ላሉባቸው ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል የተባለ ጥናት በባለሙያዎች ተጠንቶ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተልኳል ከተባለ ቆየ፡፡
መንግሥት በበኩሉ (በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በኩል) ‹‹የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መካነ ቅርስ ከተጋረጡበት አደጋዎች ለመታደግ እየሰራሁ ነው›› ቢልም የብረት ክዳኑ በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የደቀነው አደጋና ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ሲታሰብ ደግሞ የመንግሥት ጥረትና ስራ ፈጣን እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ በእርግጥ የብረት ክዳኑን ማንሳት ቀላል ስራ እንዳልሆነ ጥናት ያጠኑት ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ መጠኑ ከባድ፣ አሰራሩ ደግሞ ውስብስብ የሆነውን ይህን ክዳት ለማንሳት በጥንቃቄ የተጠና አካሄድ እንደሚያስፈልግም ባለሙያዎቹ አበክረው ይገልፃሉ፡፡ የብረት ክዳኑ ሲሰራ የታዩትና ቀደም ብሎና በተለይ ደግሞ አሁን የአካባቢውን ሕዝብ ጥርጣሬ ላይ የጣሉት እነዚያ የአሰራር ሂደቶችም ክዳኑ በቅርሶቹ ላይ ከደቀነው ስጋት ይልቅ ክዳኑን የማንሳት ስራው ከባድ እንደሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫዎች ሆነዋል፡፡ የመንግሥት አካላቱ ‹‹አብያተ ክርስቲያናቱ ከተጠገኑ በኋላ ክዳኑ ይነሳል፤ የጥገና ስራ እየተከናወነ ነው›› ቢሉም የችግሩ አሳሳቢነትና የስራቸው ፍጥነት የሚገናኝ አልሆነም፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ለጣናም ይሁን ለላሊበላ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡
በጣናም ይሁን በላሊበላ ጉዳይ ላይ መንግሥት ያሳየው ቸልተኝነት እጅግ የበዛ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል ማወቅ ያለበት ሃቅ አለ…ጣና ውሃ ብቻ አይደለም፤ ላሊበላም የድንጋይ ሕንፃ ብቻ አይደለም! ጣና እንዲደርቅ ስንፈርድበት በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ እንደፈረድን ላሊበላም ሲፈርስ ዝም ብለን ስንመለከት ትናንት ‹‹እነርሱማ ይህንን አልሰሩትም›› ብለው የሞገቱን ሰዎች ነገ ደግሞ ‹‹አፈረሱት እኮ›› ብለው ሲሳለቁብን ለመስማትና ለማየት እየተዘጋጀን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል! ብዙ ሰው የጣናና የላሊበላ ችግር የገንዘብ እጥረት ይመስለዋል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ሁለቱንም ድንቅ ሀብቶች የሞት አፋፍ ላይ ያደረሳቸው የአመራር ችግር ነው ለማለት ያስገድዳል!
ሌላ ታሪክ መስራት ካልተቻለ እንኳ የተሰራውን ጠብቆ ማቆየትና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍም አንድ ቁም ነገር ነው፡፡ ሁለቱንም ማድረግ አለመቻል ደግሞ ወንጀልም፤ ነውርም ነው! ከዚህ በተጨማሪም ጣናንም ሆነ ላሊበላን ከጥፋት ሳንታደጋቸው ብንቀር፣ በሰው ልጅ ታሪክ ‹‹የምንጊዜውም ከባድ ስህተት›› ሊባል የሚችለውን ወንጀል እንደሰራን ማመን አለብን!ጣናንና ላሊበላን እንታደግ!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2011
አንተነህ ቸሬ