ዓለም ብዙ ውይይት እንደምትፈልግ የታየባቸው የተለያዩ ወቅቶች ነበሩ። ቀደም ብለው ከነበሩ ጦርነቶች አንስቶ እስከ የእርስ በእርስ ግጭትን መፍታት ድረስ ውይይቶች ተደርገዋል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ በእያንዳንዱ አህጉር ላይ ግጭት ማስቆም አልተቻለም። በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ውጥረት በመባባሱ ምክንያት ዜጎች ወደ አውሮፓ እየተሰደዱ እንደሚገኙ የአልጀዚራ ዘገባ ያሳያል። እነዚህን በርካታ አደጋዎች ፊት ለፊት ተጋፍጦ ችግሩን መፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመራር አባላት ድክመት ሆኗል።
አንዳንዶች በዛሬው ጊዜ ያሉት ፈታኝ ሁኔታዎች ታሪክ የፈጠራቸው ናቸው ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ አዳዲስ ክስተቶች ናቸው የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃሉ። ያም ሆነ ይህ ግን ትውልዶች በሚፈጠሩ ታሪኮች መጎዳታቸው የማይካድ ሀቅ ነው። በተለይ የግዛቶች መነሳት እና መውደቅ፣ የሕዝብ ብዛት እና መጎሳቆል፣ የሃይማኖቶች እና የባህል መስፋፋት እና መጥፋት፣ በየአስርተ ዓመታት አንድነት እና መለያየት መፈጠር ተጠቃሽ ክስተቶች ከሆኑ ሰነባብተዋል።
በእርግጥ ታሪክ ሙሉ በሙሉ አይደገምም። ሁልጊዜ ልዩነቶች አሉ። አሁን ያሉት የዓለም መሪዎች እርስ በርስ ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆን እየተስተዋለ ይገኛል። እንደዚህ ያሉ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ነበሩ፤ ነገር ግን በተቃራኒው ወይም በተመሳሳይ ጊዜ ዜጎች ተያያዥነት በሌላቸው ወይም በተመሳሳይ ጉዳዮች ይጠላለፋሉ። ይህ ወሳኝ ጉዳይ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት የሚካሄድባት አህጉር ነበረች። ከ20 ዓመታት በፊት በአንድ ሀገር ውስጥ ባለሥልጣን ለማውረድ ወይም አንድ የተመረጠ የሀገርን ወይም የመንግሥት መሪን ለማስወገድ አዋጅ መንገር በቂ ነበር። እንደዚህ ዓይነት ዜናዎችን ከየአገራቱ ዜጎች በፊት ዓለም ቀድሞ ሰምቶ ይማርበት የነበረው በሚደረጉ የርስበርስ ግንኙነቶች ነው።
በአሁን ጊዜ ከቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ጋር ተዳምሮ ዜጎች መብታቸውን ለማስጠበቅ እና ለውጥን ለማምጣት ዘመቻ ለማድረግ እንዲሁም በሰዎች እና በመንግሥት መካከል ከፍተኛ ትብብር ለመፍጠር ዛሬ ብቸኛ መንገድ ሆኖ እናያለን። በጣም ርቀው በሚገኙ የእስያ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ እና በሰሜን አሜሪካ የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶችን ማየት ይችላሉ።
ባለፈው ወር በኒውዮርክ 74ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሰበሰቡት ሀገራት መሪዎች እየተከሰቱ ካሉ ችግሮች ለማምለጥ ሙከራ አድርገዋል። ስለተከሰቱት ጉዳዮች የአገራቱ መሪዎች ሲናገሩ፤ እኩልነት የተከበረበት እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። ሆኖም ግን ትንሽ መነጋገርና መደማመጥ እንዲሁም ተጨማሪ እርምጃ መውሰድም እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። ነገር ግን ውሳኔውን ለማስፈፀም ቁርጠኝነት እንዳላቸው የታወቀ ነገር የለም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም እንዲሁ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል። የፀጥታው ምክር ቤት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እ.አ.አ. በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የተቋቋመ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ ዓላማ በዓለም ዙሪያ ሰላምን ማረጋገጥ እና መጠበቅ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ተስማሚነት ያለው ድምፅ ማግኘት ችግር እየሆነ ነው። ይህ ለስኬቱ ዋና ተግዳሮት እየሆነ መጥቷል። የዘር፣ የፆታ፣ የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ልዩነት ለሁሉም ሰብአዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነፃነቶች መከበር ውስጥ ሊኖር እንደሚገባ በቻርተሩ ውስጥ ተካቷል። 193 የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገሮች በቻርተሩ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የማክበር ግዴታ አለባቸው::
ይህ ማለት ሁሉም ሰው አንድ ነው፣ አንድ ዓይነት እምነት እና አንድ ላይ መኖር አለበት ማለት አይደለም። ሌሎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ እና ባህላዊ ሥነ-ምግባርን በተመሳሳይ መንገድ እንዲያስኬዱ የሚጠይቅበት ቅድመ ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አልደነገገም። በመሠረታዊ ልዩነቶች መከበር አለባቸው። ያለበለዚያ መሠረታዊ ነፃነቶች ሊኖሩ አይችሉም የሚሉ አገራት እየተበራከቱ መምጣት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ አባል አገራት መካከል ልዩነት እየፈጠረ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ለዓለም መንግሥታት ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣው ጉዳይ አንዱ አገር ከሌላው አገር ጋር ተባብሮ መስራት አለመፈለግ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉምን በእኩል መንገድ አዳምጦ ፍላጎታቸውን ጠብቆ ከነልዩነታቸው ማገልገል ይጠበቅበታል።
እ.አ.አ.በኅዳር 12 ቀን 2012 የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት ሆነው ከተመረጡ አራት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የተመረጡ ሌሎች ሀገራት አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኮትዲቯር፣ ኢስቶኒያ፣ ጋቦን ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ ፣ ጃፓን፣ ካዛኪስታን፣ ኬንያ ሞንቴኔግሮ፣ ፓኪስታን፣ የኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ሴራሊዮን፣ የተባበሩት አረብ ኢመሬት፣ አሜሪካና ቬንዙዌላ ናቸው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በታኅሣሥ 10/1948 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን አውጆ በሥራ ላይ አውሏል።
ይህን ታላቅ ታሪካዊ አዋጅ ተከትሎም ጠቅላላ ጉባኤው መላው የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት ይህንን ድንጋጌ እንዲያሳትሙና በሀገራትና በግዛቶች የፖለቲካዊ የአቋም ልዩነት ሳይገደቡ፤ በዋናነት በትምህርት ቤቶችና መሰል የትምህርት ተቋማት፤ አዋጁ እንዲታይ፤ እንዲሰራጭ እንዲሁም ለንባብና ትንታኔ እንዲውል አድርጓል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2012
መርድ ክፍሉ