የሐረሪ ቋንቋ «ሐረሪ ሲናን» ተብሎ ይጠራል:: አብዛኛው የሐረሪ ተወላጅ ቋንቋውን የሚጠራው «ጌይ ሲናን» ወይም የከተማዋ ቋንቋ በማለት ሲሆን «ጌይ ሲናን» የጥንታዊቷ ሐረር ጌይ የሥራ ቋንቋ ነው:: በዚህ ዘመን በታሪካዊቷ የሐረሪ ከተማና ሐረሪዎች በብዛት በሰፈሩባቸው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የመከኒሳ ሰፈር በመሳሰሉት አካባቢዎች አዘውትረን የምንሰማው ይህ ቋንቋ በጥንት ጊዜያት በጣም ሰፊ በሆነ የጂኦግራፊ ክልል የሚኖሩ ሕዝቦችን ያግባባ እንደነበር ጥናቶች እንደሚጠቁሙ የኢትኖግራፈር ባለሙያው አፈንዲ ሙጣቂ ይናገራል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን በሀገራችን ውስጥ የታዩትን ታላላቅ ክስተቶች የቋንቋውን አገልግሎት በሐረሪ ከተማና በአካባቢዋ ብቻ ገድበውታል። የሐረሪን ቋንቋ «ጌይ ሲናን» እያሉ መጥራት የተጀመረውም ከዚህም ዘመን በኋላ እንደሆነ ይታመናል። ከዚያ ወዲህ በዚሁ ስም ሲጠራው ቆይቷል።
ጌይ ሲናን ላይ፣ የእኔ እና የሪቻርዴ በርተን እይታ ለየቅል ነው የሚለው የምሥራቅ ሐረርጌ ገለምሶ ከተማ ተወላጅ እና የሐረሪ ባህል እና ቋንቋ ላይ ጥናት ያካሄደው የኤትኖግራፈር ባለሙያው አፈንዲ ሙጣቂ በሐረሪ ከተማ በከተምኩባቸው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ውስጥ የጌይ ሲናንን ባህሪ መረዳት በጣም ተቸግሬ ነበር። እያደርኩ ሳየው ግን አንዳንድ ምልክቶች ያነቃቁኝ ጀመር። ከወራት ቆይታ በኋላ ደግሞ «እንደዚህ ዓይነት ውበት የማየው በህልሜ ነው ወይስ በእውኔ?» የሚያሰኝ ሆኖ አገኘሁት ይላል።
«ሐረር ጌይ»ን በጥልቀት እንድመረምር ካነሳሱኝ ዋነኛ ምክንያቶች መካከልም አንዱ በጌይ ሲናን ላይ ያየሁት ተአምራዊ ውበት ነው። ድሮ በርቀት የማውቀው ይህ ድንቅ ልሳን ከሕዝቡ ጋር መኖር ከጀመርኩ ወዲህ «ዘርፌን ልቀይር እንዴ ?» አሰኝቶኛል። ድምጸቱ፣ ቃላቱ፣ ሀረጋቱ፣ ፈሊጦቹ፣ ምሳሌዎቹ፣ ተረቶቹ፣ ወዘተ … በጣም ያስደምማሉ:: ጌይ ሲናንን በማወቄ ቋንቋዎቻችን በረጅሙና ጥልፍልፍ የታሪክ ጉዞ የሚለዋወጡበትን ዑደት በጥቂቱም ቢሆን የማስተዋል ዕድል አግኝቻለሁ:: ጌይ ሲናንን በማወቄ ይላል አፈንዲ የአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ለሆነው አፋን ኦሮሞ ያለኝን ፍቅር እንዲጨምር አድርጎኛል።
ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት ከጌይ ሲናን ጋር የተገጣጠመው ሰር ሪቻርድ በርተን ቋንቋውን ከሰማው በኋላ «በላንቃ በተደጋጋሚ የሚፈጠር “ኸ” የሚለው ድምጽ ምቾት የሚሰጥና አዝናኘ አይደለም።» የሚል ዐረፍተ ነገር በማስታወሻው ላይ ማስፈሩ በርተን እንዲህ ያለው የግል ስሜቱን ለመግለጽ ብቻ ይመስለኛል። የማጠቃለያ አስተያየት መስጠቱ ከሆነ ግን ከርሱ ጋር አልስማማም ይላል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ሚስተር በርተን ሐረሪን ያያት ለአስር ቀናት ብቻ ነው።
በአስር ቀናት ብቻ ስለቋንቋው ባህሪም ሆነ ለአድማጭ ስለሚሰጠው ስሜት የመደምደሚያ አስተያየት መስጠት የሚቻል አይመስለኝም።በሁለተኛ ደረጃ በርተን በአንድ ድምጽ ላይ ብቻ በማተኮር ነው አስተያየቱን የጻፈው። በዚህ ሚዛን ደግሞ ቋንቋን የመሰለ ባህር መመዘን ቀርቶ መሞከሩ ራሱ አስገራሚ ነው። ሦስተኛውና በጣም የሚገርመው ነገር በርተን ጣቱን የቀሰረበት የ“ኸ” ድምጽ ከጌይ ሲናን ይልቅ እርሱን ጥርት አድርጎ በሚናገረው አረብኛ ውስጥ የሚበዛ መሆኑ ነው ይላል።
የሐረሪ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እዩብ አብዱላሂ በበኩላቸው ጌይ ሲናን የሚያስደንቅ ፊደል ሲናገሩት ደግሞ ውብ ድምጸት ያለው ሴማዊ ቋንቋ ነው። በሴም የቋንቋ ቤተሰብ ከሚገኙት አራት ምደቦች መካከል ጌይ ሲናንን የሚያቅፈው ደቡባዊ የሴም ቋንቋዎች ምድብ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ምድብ የሚገኙት የሴም ቋንቋዎች እንደገና በሦስት ንዑሳን ክፍል ስር ይጠቃለላሉ።
አንደኛው ንዑስ ክፍል የደቡብ አረቢያ ሴማዊያን እንደሚባሉ የሚናገሩት አቶ እዩብ በዚህ የሚካተቱት በደቡብ የመን የሚነገሩ ቋንቋዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። አረብኛ ከነርሱ ጋር እንደማይመደብ ልብ ማለት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ሁለተኛው ንዑስ ክፍል ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያ ሴማዊያን በመባል ይጠራል። በዚህ ክፍል እንደ ግዕዝ፣ ትግርኛና ትግረ ያለ ቋንቋዎች ይጠቃለላሉ። ሦስተኛው ንዑስ ክፍል የደቡብ ኢትዮጵያ ሴማዊያን የሚባል ሲሆን አማርኛ፣ ጌይ ሲናን፣ ስልጢኛ፣ አርጎብኛና ጉራጊኛን የመሳሰሉ የሀገራችን ቋንቋዎች ይካተታሉ።
ጌይ ሲናን በሴማዊነቱ ከሁለም ሴማዊ ቋንቋዎች ጋር የድምፅ፣ የቃል፣ የሰዋስው፣ ወዘተ ባህርያትን ይጋራሉ። ደግሞም የብቻ ቋንቋ በመሆኑ በሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ የማይታዩ ፀባዮችም አሉት። ሁለቱንም ባህርያት ሲያስረዱ በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋዎች ውስጥ “ደም” የሚል ቃል አለ። በአረብኛ ባህረ ቃላት ውስጥም “ደም” የሚል ቃል ይገኛል:: በጌይ ሲናንም ቢሆን “ደም” የሚለው ቃል አለ:: በንግግር ቋንቋነት በማያገለግለው ግዕዝም ሆነ በሌሎች የአገራችን የሴም ቋንቋዎች “ደም” አለ።
ጌይ ሲናን ሴማዊነቱን የሚያረጋግጥልን ዋነኛው ነጥብ በሺ የሚቆጠሩ ቃላትን ከሌሎች የሴም ቋንቋዎች ጋር የሚጋራ በመሆኑ ነው። በአረብኛ፣ በአርጎብኛ፣ በአማርኛ፣ በትግርኛና በግዕዝ የሚታወቁ ቃላት በጌይ ሲናን ውስጥም ከመገኘታቸው በላይ የጌይ ሲናንን ሴማዊነት የሚያረጋግጥልን ነጥብ በጭራሽ የለም። በሌሎች ቋንቋዎች የማይገኙ የጌይ ሲናን ቃላትም በሽበሽ ናቸው። ለምሳሌ ወኸበ (ገዛ)፣ ዲጀ (መጣ)፣ ሌጠ (ሄደ)፣ ሄጀ (ተመለከተ)፣ ቦአ (ገባ)፣ አማጀ (አሸነፈ) ወዘተ… እያልን በጌይ ሲናን ባህረ ቃላት የሚገኙ ቃላትን መደርደር እንደሚቻልም ይገልጻሉ። በዚህም የቋንቋውን ልዩነት መረዳት ይቻላል። ጌይ ሲናን እንዲህ ልዩ ሆኖ ባይገኝ ኖሮ «በኅብረተሰብ እድገት ሂደት የተፈጠረ ቋንቋ» የሚለውን እውቅና ይነፈግና እንደ ማንኛውም ድቅል ቋንቋ ነው ተብሎ ይታወጅ ነበር። እንደዚያ ያለ የቋንቋ ሳይንስ ሊቅ ግን እስካሁን ድረስ አልታየም ይላሉ።
በእያንዳንዱ ክልሎች እና ብሔረሰቦች በራሱ ባህላዊ ዕውቀት የደረጀ ድንቅ የመቻቻል፣ የሰላምና የፍቅር እሴቶች አሉት። ብንጠቀምባቸው የምናተርፍባቸው ናቸው፤ በሐረሪ የሚገኙትንና በተለያዩ ክልሎች እና ዞኖች ያሉ አገር በቀል እውቀቶች ይውጡ፤ ይተዋወቁ ደግሞም እንጠቀምባቸው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል አቶ እዮብ። መልካም ዕለተ ሰንበት!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
አብርሃም ተወልደ