የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2012 ጥቅምት 5 እስከ 10 ድረስ ባዘጋጀው ስድስተኛው የህያው የጥበብ ጉዞ ላይ ደራሲያን፣ ሰአሊያንና ቀራፂያን እንዲሁም የሙዚቀኞች ማህበር በርካታ ጋዜጠኞችን ጨምረው በአማራ ክልል ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ማቅናታቸው የሚታወስ ነው። በዚህ ጉዞ ላይ ካደረጉት ምልከታ ውስጥ ታሪካዊው የምኒልክ የጦር ግምጃ ቤት ይገኝበታል። የዝግጅት ክፍላችን በባህላዊ የቤት አሠራር ጥበብ ከዘመናት በፊት የተሰራውን ይህን ቅርስ በምናብ አስጉዞ ሊያስጎበኛችሁ ወደደ። መረጃውን የአገረ ማርያም ከሰም ወረዳ የባህል እና ቱሪዝም ቅርስ ጥበቃ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ደስታ ታደሰ በቃለ ምልልስ አድርሰውናል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረማርያም ከሰም ወረዳ የሚገኘው የአፄ ምኒልክ ‹‹የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት›› በከሰም ንዑስ ወረዳ በኮረማሽ ከተማ የሚገኝ ነው። የአፄ ምኒልክ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ከአዲስ አበባ 88 ኪሎ ሜትር ሲርቅ ከሰሜን ምሥራቅ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር ደግሞ በ661 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል:: በስተ ደቡብ ምሥራቅ ከዞኑ ርዕሰ ከተማዋ ደብረ ብርሃን ደግሞ 68 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።
የግምጃ ቤቱ ቅጥር ግቢ ስፋት 15ሺ595 ካሬ ሜትር እና የዙሪያ ርዝመቱ 532 ነጥብ 3 ሜትር ነው:: በግቢው ውስጥ የጥንት ይዞታቸውን የጠበቁ ሰባት ቤቶች ያሉ ሲሆን ሦስቱ ቤቶች በአዲስ መልክ የተሰሩ ናቸው። በተለይ በግቢው ውስጥ ሲደርሱ ውበቱ ቀልብ የሚስበው ተፈጥሯዊ የፅድ ዛፎች የታወከ መንፈስን የሚያድሱ ናቸው።
መቼ ተመሰረተ
የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ የተመሰረተው በ1890 ዓ.ም ነው። ምክንያቱ ደግሞ የጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር እና የአድዋ ጦርነት ነበር። አፄ ምኒልክ በ1888 ዓ.ም ወራሪውን ድባቅ መተው ድል ካደረጉ በኋላ ዳግመኛ ቢመጣ አገር የሚከላከሉበት የጦር መሣሪያ ማከማቸት እንደሚያስፈልጋቸው ተረዱ። በዚህም ጠላት በቀላሉ የማይደርስበት ስትራቴጂካዊ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው በማመናቸው መረጣ ማድረግ ጀመሩ። ለዚህም ሹማምንቶቻቸውን ያማክሩ ነበር።
በጊዜው ይህን የሰሙት የቡልጋው ገዢ ራስ ዳርጌም ከግዛታቸው ምቹ የሆነ ስፍራ እንዳለ ለአፄ ምኒልክ አሳወቁ። ንጉሱም ከስፍራው ተገኝተው ቦታውን በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ደስ አላቸው። ቦታውን ከዚህ ቀደም ባለማየታቸው ተገርመው ለስፍራው ‹‹ሳላይሽ›› የሚል ስያሜ እንዳወጡለት ይነገራል። እስከአሁን ድረስም የግምጃ ቤቱ እና የከተማው ስያሜ ሳላይሽ በመባል ይጠራል።
ግምጃ ቤቱ በምን ተገነባ?
ግምጃ ቤቱን ለመስራት ከአካባቢው የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከመጠቀም ባለፈ ከፈረንሳይ አገር ድረስ የተለያዩ ዘመናዊ የጣሪያ ክዳን እና ሌሎች ቁሶችን አምጥተዋል። በተለይ የጣራ ወራጅ ድጋፍ ምሰሶ የቆርቆሮ ማገር ለፎቅ ቤቱ ርብራብ እንጨት ሙገሬ ከሚባል ስፍራ በሰው ኃይል ማስመጣት ችለዋል። ግንባታው ግዙፍ ስለነበረም በርካታ የሰው ኃይል እንደተጠቀሙ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በተለይ ቆርቆሮና ሚስማር በወቅቱ ከፈረንሳይ አስመጥተዋል። ከፈረንሳይ እስከ ጅቡቲ በመርከብ ከዚያ ደግሞ እስከ ኮረማሽ በ500 ግመል እንዳስመጡም ይነገራል።
በወቅቱ በግቢው ውስጥ የተገነቡት ቤቶች 14 እንደነበር መዛግብት ይገልፃሉ። የጭቃ ማቡካት እና የድንጋይ ማቅረብ ሥራው ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን ሥራው ተጀምሮ የተጠናቀቀው በ1890 እንደሆነ እና በ6 ወራት ውስጥ መጠናቀቁ ይነገራል።
የአሠራር ጥበብ
ግምጃ ቤቶቹ በተለይ የሁለቱ በወቅቱ በነበረው የሕንፃ ጥበብ ተውበው የተሰሩ ነበሩ። በተለይ የሁለቱ ቤቶች ቅርፅ እና ስፋት አንድ ዓይነት ነው። ሁለቱም 16በ8ሜትር ሲሆኑ የምድር ፎቅና ምድር ቤት አላቸው። በውስጣቸውም በድንጋይ የተገነቡ ሁለት ሁለት እንደ ምሰሶ የሚያገለግሉ የፎቅ ርብራብ ያረፈባቸው ግድግዳዎች አሉ። ስፋታቸው ሁለት ሜትር በስድስት ሳንቲ ሜትር ውፍረት ሲኖራቸው በተጨማሪ በእንጨት ምሰሶ የታገዙ ናቸው።
ግምጃ ቤቱ በተለያየ ዘመን ለተለያዩ አገልግሎቶች ውሏል። በተለይ ተሰርቶ በተጠናቀቀበት ወቅት ንጉሱ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በማጠንከር ከፈረንሳይ የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችንና ጥይቶችን በማምጣት ያከማቹበት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለ36 ዓመት በጦር መሣሪያ ግምጃ ቤትነት ማገልገል ችሏል። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በግምጃ ቤቱ የነበሩት የጦር መሣሪያ ጥይቶች ወደ ሸረር ዋሻ እንደተወሰዱ እና የተረፈውም ለአርበኞች መዋጊያ እንደዋሉ ይነገራል።
ፋሽስት የጣሊያን ጦር ከአምስት ዓመት ቆይታ በኋላ ድል ተደርጎ ከወጣ ጀምሮ እስከ 1954 ግምጃ ቤቱን አፄ ኃይለስላሴ በጦር ካምፕነት ተጠቅመውበታል። ካምፑ አሌልቱ ወደተባለ ስፍራ ሲዛወርም የቡልጋ ገዢዎች በመቀመጫነት ተገልግለውበታል። በደርግ ዘመነ መንግሥትም ለተለያዩ መሰብሰቢያዎች በአዳራሽነት ማገልገሉን የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።
ቅርሱ በተለያየ ጊዜ የመፈራረስ አደጋ ገጥሞት ነበር:: በዚህ ምክንያትም የአማራ ክልል የፌዴራል መንግሥት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ጥረት ጥገናዎች እየተደረጉለት ለቱሪዝም መስህብነት ክፍት ሆኖ እስካሁን ድረስ ይገኛል። የዝግጅት ክፍላችንም ቦታው ድረስ በመገኘት ይህ ታላቅ ታሪካዊ ቅርስ የሚገኝበትን ሁኔታ ተመልክቷል። ጥቂት ቢሆኑም የአገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች በስፍራው እየተገኙ እንደሚመለከቱት ታዝቧል። ታሪካዊ ስፍራዎችን መመልከት የሚፈልጉ ዜጎች እዚህ ስፍራ ቢሄዱ አትርፈው እንደሚመለሱ ምንም ጥርጥር የለውም። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
ዳግም ከበደ