አዲስ አበባን በማለዳ ቃኘት ሲያደርጉ በየመንገዱ ልብስ ሳይደርቡ ከውሻ ጋር ተቃቅፈው የተኙ፤ ላስቲክን ልብስ ድንጋይ ትራስ ያደረጉ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ማየት የተለመደ ነው። ውሏቸው ቁርና ጸሀይ ላይ፣ ምግባቸው የሆቴል ትርፍራፊ ነው።አንዳንዴም ከዚህ ባስ ያለም መመልከት አይቀሬ ነው።ይህንኑ የጎዳና ልጆች ህይወት ለመቃኘት የተለያየ አካባቢ አቅንተን ነበር።
ሶስት የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ናቸው። ጥላ ስር ተቀምጠው ከፌስታል ላይ በእጃቸው እያፈሱ ይጎርሳሉ። እኛም ተጠጋንና ሰላምታ ሰጥተናቸው እንዴት እንደሚኖሩና ምን አይነት ተስፋ እንዳላቸው እንዲያወጉን ጠየቅን።ያው ምግባቸውን እስኪጨርሱ መጠበቁ ግድ ነውና እያየናቸው ቆመናል።ባህል ነውና ‹‹እንብላ›› ሲሉም ጋበዙን።ግብዣውን በምስጋና መለስን።
እነርሱ ግን አጥንቱን፣ ሶፍቱን፣ የጥርስ ላይ ቆሻሻ ማውጫ ሹል እንጨት (እስቲክኒ) ከትርፍራፊው ውስጥ እየመረጡ በመወርወር በመዳፋቸው ሙሉ እየዘገኑ ወደ አፋቸው ይልካሉ።ምን ይደረግ ሆድ ባዶ አያድር።ይህን እያሰብኩ ወደ ቃለመጠይቄ ገባሁ። በመጀመሪያ ሃሳቡን ያጋራን ያቆብ ይመረው ይባላል። ከሲዳማ ዞን ኢራቡረቻ አካባቢ ነው የመጣው። የጎዳና ህይወት ለብዙ ሱሶች ያጋልጣል፤ ድብደባና ስቃዩ አስከፊ መሆኑን ይናገራል። ከዚህ አስከፊ ችግር ተላቆ መስራት እንደሚፈልገ ይገልጻል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ቤት እንሰራለን ፤ የመንገድ ላይ አትክልቶችን እንዲንከባከቡ የስራ ዕድል እንፈጥርላቸዋለን” ብለው ሲናገሩ የዕድሉ ባለቤት እሆናለሁ የሚል ትልቅ ተስፋ አድሮብኛል። ይደረግልናል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ ይላል።
ከአርሲ አካባቢ እንደመጣ የነገረን ደግሞ ታዳጊ ወጣት በላይ ብሩ ይባላል። በበርካታ ስቃይ ውስጥ የጎዳና ህይወቱን እየገፋ መሆኑን ይናገራል። የሌሊቱ ብርድና ቁር ፣የክረምቱ ዝናብና ጎርፍ ፣የቀኑ ጸሀይ ትልቅ ፈተና ሆኖት እየኖረው ነው።ስራ ለመስራት መታመን ይጠይቃል። ምቹ ሁኔታ ያስፈልጋል።የጎዳና ተዳዳሪ ግን በህዝብም ሆነ በጸጥታ አካላት አመኔታ ስለማይኖር እንገለላለን ይላል።አሁን በመንግስት የታሰበው ፕሮጀክት እውን ከሆነ እኛም ሰርተን እንለወጣለን የሚል ተስፋን ሰንቋል።
ከሻሸመኔ እንደመጣ የሚናገረው ጀማል ገመዱ ደግሞ ፤ አልፎ አልፎ የሸከማ ስራ በመስራት ገንዘብ ያገኛል። ገንዘቡ ለምግብና ለቤት ኪራይ ቢያውለው ስለማይበቃው ማደሪያውን ስታዲየም ድልድይ ስር አድርጓል። ‹‹የጎዳና ተዳዳሪ በብዙዎች ዘንድ ሱሰኛና መስራት የማይወድ ተደርጎ ይወሰዳል።ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርለትም ከሱሱ አይጸዳም ይባላል።እውነታው ግን ይሄ አይደለም። ሰርቶ ማደር፣ ተምሮ መለወጥ የሚፈልግ የጎዳና ህይወት የመረረው ብዙ ሰው አለ። ስለዚህ ሰርቶ እንዲያድር ዕድሉ ሊመቻችለት ይገባል›› ይላል። ለጎዳና ተዳዳሪዎች ተብሎ የታሰበውን ፕሮጀክት ሌሎች ለራሳቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ተናግሮ በአፈፃፃም በኩል ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።
ከወላይታ እንደመጣና ፕላስቲክ እየሰበሰበ በመሸጥ ኑሮውን እየገፋ እንደሆነ የነገረን ደግሞ ቢኒያም ሰማያት ነው።በሥራ እንደማይታማ ይናገራል።ሆኖም ተያዥ ስለሌለው አምኖ የሚቀጥረውም ሆነ ቤት የሚያከራየው ባለማግኘቱ ለገሀር አካባቢ ጎዳና ላይ ተኝቶ እንደሚያሳልፍ ያስረዳል። አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር ከደረሰልን ከዚህ ችግር እንደሚያላቅቀኝ አስባለሁ። መማርና ራሴን መቀየርም እፈልጋለሁ።ይህ ካልተሳካ ግን ሁሉም ቀርቶብኝ ወደ ቤተሰቤ ተመልሼ የምሰራበት ሁኔታ ቢመቻችልኝ የአገሬን ህዝብንም ሆነ መንግስትን ምን ያህል እንደማመሰግነው አላውቅም›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች የመኖሪያ ቤት እንደሚሰራላቸው እና የሚተከሉ ችግኞችን እንዲንከባከቡ የስራ ዕድል እንደሚመቻችላቸው መናገራቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው
ፎቶ፡- በእዮብ ተፈራ