
ወደዚህ ቦታ መግባት ኢትዮጵያን በአራቱም አቅጣጫ ጎብኝቶ ዞሮ እንደመመለስ ማለት ነው፡፡ በቃ እዚህ ፓርክ ውስጥ ሙሉዋ ኢትዮጵያ አለች፡፡ ተፈጥሮ አለ፣ ሰው ሰራሽ ጥበብ አለ፣ ታሪክ አለ፡፡
አንዳንድ ነገሮችን አይተን የሆነ ስሜት ይፈጥርብናል፤ ይሄ የተለመደ ነው፡፡ ዳሩ ግን አንዳንድ ያልተለመዱ ስሜቶች ደግሞ አሉ፤ ይሄውም ከዚህ በፊት የነበረንን ስሜት ሙሉ በሙሉ ሲቀየርብን የሚፈጠር ነው፡፡ የራሴን የስሜት መቀየር ልንገራችሁ፡፡
ቤተ መንግስቱ ሙዚየም ሆኖ ህዝብ እንዲጎበኘው ክፍት ይሆናል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ መነጋገሪያ ነበር፡፡ የተባለውም ሆነና ባለፈው ወር መጨረሻ ተመርቆ በህዝብ ተጎበኘ፡፡ ያዩት ሁሉ አደነቁ፡፡ ያው እኔም እንደማንኛውም ሰው የበጎብኘት ጉጉት አደረብኝ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን የነበረኝ ጉጉት ታሪካዊነቱን ለማየት ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ ነገር አልጓጓሁም፡፡ የመሪዎች ፎቶ፣ የመሪዎች ታሪክ፣ የቀደምት ነገሥታት ታሪካዊ ዕቃዎች… የመሳሰሉትን ለማየት ነበር የጓጓሁት፡፡
ዕድሉን አገኘሁና አየሁት፤ እንኳንም አየሁት!
ከዚህ ይጀምራል፡፡ በሂልተን ሆቴል በኩል ባለው በር ይገባሉ፡፡ እዚህ ላይ ከኤርፖርት ጋር የሚመሳሰል ፍተሻ አለ፡፡ የጥበቃዎችና የአስተባባሪዎች ትህትና ራሱን የቻለ ጉብኝት ነው፤ ያለምንም ማደነባበርና ቁጣ የሚያዙና የሚከለከሉ ነገሮችን ያስረዳሉ:: ይህኛውን በር እንዳለፉ ቀጥሎ ደግሞ አንድ የትኬት መቁረጫ በር ያልፋሉ፡፡ እሱን ከጨረሱ፤ በቃ አሁን ገብተዋል!
እንደገቡ ‹‹ኢትዮጵያ››ን ያያሉ፡፡ ከለመለመው አረንጓዴ ሥፍራ ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል በትልቁ የተጻፈ ጽሑፍ ይገኛል፡፡ ይህ ሥፍራ ንጹህ አየሩ እና አረንጓዴ ሳሩ መንፈስን ያድሳል፡፡
እዚህ ቦታ ላይ ቆመው ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ የሚወስድ መንገድ አለ፡፡ በቀኝ በኩል ባለው እንሂድ፡፡
‹እንኳን ደህና መጡ›› የሚለውን የመግቢያ በር እንዳለፉ ቤተ መንግስት ግቢ ውስጥ መሆንዎን ይረሱና ‹‹ምን አይነት በረሃ ውስጥ ነው የገባሁት!›› ይላሉ፤ ግዴለም ይረጋጉ! የሚመለከቱት ዋሻ እና ገደል ሃይለኛ ሙቀት ሳይሆን ሃይለኛ ቅዝቃዜ ነው ያለው:: ለነገሩ ገና አንድ እርምጃ እንደተራመዱ የተንጣለለውን ሃይቅ ሲያዩ ‹‹ምን አይነት በረሃ ነው!›› ባሉበት አፍዎ ደግሞ ‹‹ምን አይነት ባህር ውስጥ ነው የመጣሁት!›› ይላሉ፡፡
እንዳይደነግጡ! በባህሩ ሲደመሙ ከባህሩ ማዶ አንበሳ ሲጎማለል ያያሉ፤ ጉድ ፈላ! አይዞዎት አንበሳው ባህሩን ተሻግሮ ወደ እርስዎ አይመጣም፡፡ እዚህ ቦታ ላይ የሚያዩት አንበሳ ፓርክ ውስጥ የሚኖር አይመስልም:: በቃ! እልም ያለ ጫካ ውስጥ እንደሚኖር ነው የሚቆጥረው፡፡ ያ ቦታ ለአንበሳው በተፈጥሯዊ ጫካ ውስጥ እየኖረበት እንደሆነ ነው የሚሰማው፡፡ ሰፊ ነው፣ አካባቢው ገደል እና ዋሻ ነው፤ ሳርና የተክል አይነቶች አሉበት:: ይሄ ፓርክ ገና አዲስ የተሰራ መሆኑን ሲያውቁ ደግሞ ነገሩ አስማት ይሆንብዎታል፡፡ ከዓመታት በኋላ ነው እንግዲህ ይሄን የአንበሳ ቦታ ማየት የተቻለው::
እዚህ ቦታ ላይ ቆመው አንበሳውን እያዩ ድንገት ወደ ዋሻው ውስጥ ይገባል፡፡ አንበሳው የሚገባበት የተለመደው የአንበሳ ፓርክ ቤት አይነት አይደለም፤ የተፈጥሮ ዋሻ የመሰለ ነው:: የአንበሳውን ስሜት ግን አስባችሁታል? በእሱ ቤት እኮ ሰው የሰራለት ቤት ውስጥ ሳይሆን ጫካ ውስጥ ሲንጎማለል ቆይቶ ወደ ዋሻ ውስጥ እየገባ ነው፤ ምስኪን የኔ አንበሳ!
እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ግርምት!
ከርቀት ሆነው የሚታየው ዋሻ ጠጋ ብለው ሲያዩት ሌላ ግርምትን ይፈጥራል:: አንድ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፤ የሰው ልጅ እንዲህ ተፈጥሮን አስመስሎ መሥራት ይችላል ማለት ነው? እርግጥ ነው በፊልም እና በፎቶ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን እናያለን፤ ዳሩ ግን እንዲህ አይነት ሳይሆን በቀላሉ የሚሰሩ ነገሮችን ነው:: ዋሻ እና ገደል መሥራት በተፈጥሮ ኃይል እንጂ በሰው ሃይል የተለመደ አልነበረም፡፡ ርዝመቱ እና ስፋቱ አይደለም የሚገርመው፤ ሙሉ በሙሉ የተፈጥሮ ዋሻ መምሰሉ ነው፤ ምንም የሰው እጅ የገባበት አለመምሰሉ ነው፡፡
ገና ከዋሻው በር ላይ ሲደርሱ አቧራ ይቀበልዎታል፤ ይሄ የተፈጥሮ ዋሻዎች ባህሪ ነው፡፡ ቀና ብለው ሲያዩ የገደሉ ቅርጽ የተፈጥሮ ገደል ቅርጽ ነው፡፡ የተፈጥሮ ዋሻዎች አንድ ወጥ ቅርጽ የላቸውም፤ ወጣ ገባ ይበዛባቸዋል፤ የሆነ ኪስ ነገር፣ ሸለቆ ነገር ይኖራቸዋል፤ ይህም የቤተ መንግስቱ ግቢ ዋሻ ልክ እንደዚሁ ነው፡፡
በዋሻው ውስጥ ብዙ ርቀት ይጓዛሉ፤ አንዳንድ ቦታ ላይ መረማመጃ ነገር ሲኖር አብዛኛው ቦታ ግን አቧራማ መንገድ ነው:: በዋሻው ውስጥ ሲሄዱ ጨለማ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የመብራት አምፖሎች አሉ:: መብራት ባይኖር ሙሉ ጨለማ ይሆን ነበር:: አንድ የፎቶ ባለሙያ እንደነገረኝ እዚህ ቦታ ላይ ፎቶ ቢነሱ አይወጣም፡፡ አልፎ አልፎ ግን የፀሐይ ብርሃን የሚገባበት ቦታም አለ፤ ይሄም ሌላው የተፈጥሮ ዋሻ ባህሪ ነው፡፡ የፀሐይ ጨረር የምትገባው ገማሳ ቅርጽ ባለው ዋሻ በኩል ነው፡፡ ልክ እንደ ተፈጥሮ ገደል አንዳንድ ቦታ ላይ ቅርጹ ገማሳ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ይህ ዋሻ የጥቁር አንበሳ ሥፍራ ይባላል፡፡
አሁን ከዋሻው ወጥተናል፡፡ ከዋሻው እንደወጣን አገር በቀል የእፅዋት አይነቶችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ እፅዋት ገና ለጋ እና አብዛኞቹ ደግሞ ገና እየተተከሉ ያሉ ናቸው:: ከአጠገባቸው የሚታየውም አዲስ አፈር ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ግቢ ከዓመታት በኋላ ምን ሊመስል እንደሚችል ሲያስቡት በጣም ያጓጓል፡፡
አዳዲስ የተተከሉት እና ገና ለጋ የሆኑት የእፅዋት አይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ የመድሃኒት አይነቶች አሉ፣ የምግብ አይነቶች አሉ፣ ለውበት አገልግሎት የሚውሉ እፅዋት አሉ፡፡ ጤና አዳም፣ ኮሰረት፣ ፌጦ፣ በሶ ብላ፣ ዝግባ፣ ዋንዛ… ይጠቀሳሉ፡፡ በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቃሪያና ቲማቲም የመሳሰሉ የአትክልት አይነቶችን ከውጭ እንደማያስገቡ ተናግረዋል፡፡
እዚህ የእፅዋትና የአረንጓዴ ሥፍራ አካባቢ ሆነው አዲስ አበባን በሸራተን በኩል ቁልጭ አድርገው ማየት ይችላሉ፡፡ ያኔ ነው መንፈስዎ ሀሴት የሚሰራው፡፡ ከአጠገብዎ የሚወጣው የተፈጥሮ ልምላሜ ንጹህ አየር ነው፤ ከፊት ለፊትዎ የሚታየው የአዲስ አበባ ገጽታ ነው፡፡ ፊትዎን ወደላይ ሲመልሱ ደግሞ እነሆ ዋናው ቤተ መንግስት ይቀበልዎታል፡፡
እስኪ ደግሞ ወደ ነገሥታቱ ታሪካዊ ሥፍራዎች እንዝለቅ፡፡ መጀመሪያ የምናገኘው እንቁላል ቤት የሚባለው ነው፡፡ ይህ ቤት ስያሜውን ያገኘው የእንቅላል ቅርጽ ያለው ስለሆነ ነው፡፡ እንቁላል ቤት የአጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ መኖሪያ ቤት የነበረ ነው፡፡ ከፊት ለፊቱ ደግሞ የፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) መኖሪያ ይገኛል፡፡ አጼ ምኒልክ አባ መላን በብዙ ነገር ስለሚያማክሯቸው ቤታቸው አጠገብ ለአጠገብ ነው፡፡
ይህኛው ደግሞ የአጼ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ነው፡፡ ስምንት ሺ ያህል ሰዎችን እንደሚይዝ ይነገርለታል፡፡ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ከዚህኛው ጫፍ ሆኖ ያኛውን ጫፍ ለማየት እንኳን ለአይን ይርቃል፡፡ ከዚህኛው ጫፍ ሆነው ከዚያኛው ጫፍ ካለ ጓደኛዎ ጋር በስልክ ካልሆነ በስተቀር መሰማማት አይችሉም፡፡ በአዳራሹም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ይታያሉ፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ዙፋን ቤት የሚባለውን እናገኛለን፡፡ ይህ ዙፋን ቤት ነገሥታቱ የተለያዩ የውጭ አገራት እንግዶችን ተቀብለው የሚያነጋገሩበትና የሚወያዩበት ነበር፡፡ በውስጡም የተለያዩ ቅርሶች እና የውጭ አገራት መሪዎችና ነገሥታት ፎቶና አጭር ታሪካቸው ይገኛል፡፡
በዚህ ቦታ ሥር ያለው ሌላው ታሪካዊ ሥፍራ ምድር ቤት የሚባለው ነው፡፡ ቦታው ቀዝቃዛ ነው፡፡ በነገሥታቱ ጊዜ የምግብና መጠጥ ማስቀመጫ የነበረ ሲሆን በደርግ ጊዜ ማሰሪያና መግረፊያ ነበር፡፡ በዚህ ምድር ቤት ውስጥ ብዙ ታሪክ ተጽፎ ይገኛል፡፡ በረጅሙ አግዳሚ የመስታወት ጠረጴዛ ላይ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ የተጻፈው ታሪክ በርካታ የአገሪቱን ሁነቶች የሚያሳይ ነው፡፡
እዚህ ጋ ደግሞ ‹‹የክልሎች እልፍኝ›› የተሰኘውን ሥፍራ ያገኛሉ፡፡ እዚህ ሥፍራ ውስጥ ከገቡ ከሁሉም ክልሎች እንደሄዱ ይቁጠሩት፡፡ የክልሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ታሪኮች ሁሉ ይታያሉ፡፡ ይሄ ብቻ እንዳይመስልዎ! ስለክልሎች ታሪክ፣ ባህልና ወግ የሚተርክ በድምጽና ምስል የታገዘ ማብራሪያም አለ፡፡ የክልሎች ስም የተጻፈበት ሀውልት መሰል ማሳያ ላይ ያገኙታል፡፡
ክልሎችን ከርቀት ሆነው መለየት ይችላሉ፡ለምሳሌ ከላይ መጥተው ወደ ክልሎች ሲገቡ በላሊበላ አምሳል የተሰራ አነስተኛ ላሊበላ ያገኛሉ፡፡ አሁን አማራ ክልል ውስጥ ነው ያሉ:: ቀጥሎ የአክሱምን ሀውልት ያያሉ፤ አሁን ትግራይ ክልል ውስጥ ነው ያሉት፤ ግመሏን ካዩ ሶማሌ ክልል ገብተዋል፣ ትልቅ ኦዳ ከርቀት ይታይዎታል? የኦሮሚያ ክልል ነውና ቀጥ ብለው ይሂዱ፡፡
የኤርታሌን እሳተ ገሞራ ማየት ይፈልጋሉ? አፋር እስከሚሄዱ ድረስ አምሳለ ኤርታሌን ከአንድነት ፓርክ ያገኙታል፡፡እዚህ ቦታ ላይ ትንሽ ሞኝ ሆነው መቆም አለብዎት፤ እንደኔ ሞኝ ካልሆኑም እንዴት እንደተሰራ ገብቶዎታል ማለት ነው፡፡ ከአምሳለ ኤርታሌው ሥር ቀይ ቀለም ያለው ውሃ ሽቅብ ሽቅብ ይፈላል፤ ውሃው የሚወጣበት የጉድጓዱ ዙሪያ የእሳት ፍም የመሰለ ነገር ይታይበታል፡፡ በኤሌክትሪክ እንደሚሰራ መገመት ነው፡፡
አንድ ነገር ይታወቅልኝ፡፡ አንድነት ፓርክ የሚነገር ሳይሆን የሚታይ ነው፡፡ እዚህ ፓርክ ውስጥ መግባት፤ መዝናናት ነው፣ አገርን ማወቅ ነው፣ ተፈጥሮን ማየት ነው፤ ማየት ብቻ ሳይሆን መመራመር ነው፡፡ በአንድነት ፓርክ ውስጥ ኢትዮጵያን ይጎብኙ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
ዋለልኝ አየለ