ፈጠራ የጠለቀ ክህሎት የሚጠይቅ፤ ሳይንሳዊ ስሌቶችን ከግምት ያስገባ በጥረት ድግግሞሽና በብዙ ልፋት የሚካኑት ጥበብ ነው።ፈጠራ በላቀ ክህሎትና በምጡቅ አዕምሮ ታስቦ ወደ ተግባር የሚለወጥ፤ ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ፤ በሳይንስ ፅንሰ ሀሳቦች የሚለካ ልዩ ችሎታ ነው።እንደማህበረሰብ በፈጠራ ስራ ላይ የተካበተ ልምድ ባይኖረንም አዲሱ ትወልድ በዘርፉ ትልቅ እመርታ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
አንዳንዱ ከእድሜው ዘለግ ባለ፤ ከኖረበት ዘመን በላቀ ምጥቀት የሚከውነው ተግባር ያስደምመናል።እድሜውን አስልተን ያለበትን ደረጃ ስናይና ከፍ ያለ ተግባር ላይ ስናገኘው መገረማችን ይበዛል።ፈጠራ በልዩ ሁኔታ ተጠብበውበት በራሳቸው አዕምሮ ያፈለቁትን ተግባር ላይ አውሎ ለሌላው የሚያሳዩት ጥበብ እንደመሆኑ ስናየው አዲስነቱ ቢያስደንቀንም አያስገርምም።የፈጠራ ባለሙያዎች የሚታደሉት ልዩ ክህሎት ተጠቅመው የሚያፈልቁት የፈጠራ ስራ ተግባራዊ ሆኖ ሲታይ ለፈጣሪው ደስታ፤ ለኛ ለተገልጋዮቹ ደግሞ አግራሞት መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ሳይንስ በራሱ መንገድ ትናንትን በትዝታ፤ ዛሬን በምናየው ሁነት፤ ነገን ደግሞ በእሳቤ ቀምሮ ሁሉንም እደጃችን ያቀርብልናል። ኑሮንና አኗኗርን ቀይሮ ለሰው ልጅ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ቀጥሎበታል። በርዎን ቆልፈው ሩቅ ተጉዘው ከስራ ቦታዎ ደርሰዋል። ነገር ግን፤ በቤትዎ አንድ የቤተሰብዎ አባል ወይም ሌላ እንግዳ ጉዳይ ገጥሞት መጣ።እቤትዎ በር ላይ የቆመው ባለጉዳይ ተቸግሮ አልያም የቤተሰብዎ አባል ወደቤት መግባት ፈልጎ ቁልፍ ነውና ከበር ቆሟል፡፡
ይሄኔ የቤትዎ መቆለፍ ያሳስብዎታል፤ ለጉዳይ የመጣው እንግዳ ቤት ሳይገባ መሄዱ፤ አሊያም ቤተሰብዎ የተዘጋው ቤት ውስጥ መግቢያ አጥተዋልና ሊቸገሩብዎ ስለሆነ ወደቤት ተመልሰው በሩን መክፈት ወይም ቁልፉን ማቀበል ግድ ይልዎታል።ከስራ ቦታዎ እቤትዎ ድረስ ያለውን ርቀት አስበው ይሰላቻሉ። ለዚያውም ስራዎን ጥለው መመላለስዎ ያስከፋዎታል።ዛሬ ግን ይህን በቀላሉ እዚያው ቢሮዎ ሆነው በስልክዎ ብቻ በርዎን ሲፈልጉ መክፈት ሲያሻዎ ደግሞ መዝጋት የሚችሉበት መተግበሪያ በሀገርዎ ልጅ ተፈጥሮሎታል፡፡
ሌላም ህይወትን ቀላል የሚያደርግልዎ ፈጠራ ልንገርዎ።እቤትዎ የሉም። ነገር ግን ቤትዎን ሊያወድም፤ አሊያም ንብረትዎን አመድ ሊያርግ የሚችል የእሳት አደጋ ሊከሰት አንዳች ጭስ መሰል ነገር ቢመለከቱ፤ ወይም ተቀጣጣይ ነገር በቤትዎ ውስጥ ቢፈጠር እርስዎ ስልክዎን ብቻ በማየት የተፈጠረውን ችግር የሚረዱበት መልዕክት ይደርስዎታል።ይሄንንም ትንሽ ትዕግስት ይኑርዎ እንጂ፤ በሀገር ልጅ ለዚያውም ገና ለአካለ መጠን ባልደረሰ ብላቴና ተፈጥሮ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል።ሀገርዎ ይህን ቴክኖሎጂ ሰርታ ለዓለም ልታቀርብልዎ ነው።
ምን ይሄ ብቻ፤ የምግብ ማብሰያ ስቶቮን ስልክዎን ብቻ በመጠቀም ማብራትና ማጥፋት የሚያስችልዎ መተግበሪያ (አፕልኬሽንም) ከርስዎ ሊደርስ ጥቂት ትዕግስት ያደርጉ እኔ ሰርቼ አቅርቤዋለሁ፤ ወደአርስዎ ሊደርስ በሂደት ላይ ነው ይለናል የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ እንግዳችን ወጣት ኢዘዲን ካሚል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የፈጠራ ስራዎች ላይ ተወዳድሮ አሸናፊ በመሆን በተደጋጋሚ ተሸልሟል።
ታዳጊው ኢዘዲን እስካሁን ከ28 የማያንሱ የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅና በመተግበር ልዩ ክህሎቱን ማሳየት የቻለ ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ነው። በዚህ ዓመት በተካሄደው የጣና ሽልማት ላይ በማህበራዊ ድህረ ገፅ በሚያወጣቸው የሳይንስ ነክ መረጃዎች በሣይንስና የቴክኖሎጂ መረጃ ዘርፍ አሸናፊው ኢዘዲን ካሚል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን እድሜው ገና 17 ዓመት ነው።
ተወልዶ ያደገው በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ጉብሬ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በጉብሬ አባ ፍራንሷ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ለፈጠራ ስራ ልዩ ፍቅር ያደረበት ኢዘዲን የወዳደቁ እቃዎችን አንስቶ መልሶ ጥቅም እንዲሰጡ በመጠጋገን፤ የተበላሹ የኤሌትሪክ መሳሪያዎችን መልሶ በመጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ በማድረግ ክህሎቱን እንዳሳደገ ይናገራል።በአሁኑ ወቅት እዚያው ጉብሬ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አባ ፍራንሷ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡
ወደ ፈጠራ ስራ የገባበት አጋጣሚ፡-
ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ በሬዲዮ በተደጋጋሚ የፈጠራ ስራ ምንነት ሲነገር ትኩረት ሰጥቶ በልዩ ሁኔታ ይከታተል እንደነበር ይናገራል።በዚህም የፈጠራ ስራ ፍቅር በውስጡ ያድርበታል።መምህሩ ክፍል ውስጥ የማግኔት ዋልታዎችን መሳሳብና ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ መገፋፋት በምክንያት ሲያስረዱ ያየውን በተግባር ለመፈተሽ ማግኔቱን በሌሎች እቃዎች ላይ በማድረግ እቃዎቹ እንዳይጋጩ በማድረግ የመኪና ግጭት ለመከላከል ያስችላል ያለውን የፈጠራ ስራ እውን ለማድረግ ሙከራ ጀመረ።ይህ ሙከራ ተደጋግሞ ባላሰለሰ ጥረት ቁጥራቸው የበዛ የፈጠራ ስራዎችን መፍጠር አስቻለው፡፡
የፈጠራ ስራዎቹ ምንነት፡-
ወጣት ኢዘዲን ካሚል እስካሁን ሰባት የተለያዩ የሞባይል መተግበሪያ ወይም አፕልኬሽኖችን ጨምሮ ከ28 ያላነሱ ፈጠራዎች ማበርከት ችሏል።እነዚህ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙ የፈጠራ ስራዎቹ ዋና ዋናዎቹ በስልክ አጥፍቶ ማብራት የሚቻል ስቶቭ፤ በስልክ ከፍቶ መዝጋት የሚያስችል የቤት በር፤ የእሳት አደጋ መፈጠሩን በስልክ የሚያሳውቅ መተግበሪያ፤ በፀሀይ ብርሀን አንዴ ሀይል ተሞልቶ (ቻርጅ ተደርጎ) ብዙ መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችልና ለመብራት አገልግሎት የሚውል ጫማ፤ በፀሀይ ብርሀንና በኤሌክትሪክ ቻርጅ ተደርጎ በሰዓት እስከ 40 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ብስክሌት ዋና ዋና ስራዎቹ ናቸው።
በፈጠራው የተገኘ እውቅናና ሽልማት፡-
ወጣት ኢዘዲን በተለያዩ ሀገር አቀፍ የፈጠራ ስራ ውድድሮች በመሳተፍ እውቅናና ሽልማቶችን አግኝቷል።በ2010 እና በ2011 ዓ.ም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በፈጠራ ስራ አሸናፊ በመሆን የብር ሜዳሊያና ሰርተፍኬት አግኝቷል።የውሃና መስኖ ኤነርጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመሆን ባዘጋጀው የፈጠራ ስራ ውድድር ላይም ተካፍሎ የሰርተፊኬትና የገንዘብ ሽልማት፤ በአሜሪካ ኤምባሲ በተካሄደ የፈጠራ ስራ ውድድር ላይ የፈጠራ ስራዎቹን በማቅረብ እውቅናና ሰርተፊኬት፤ በክልል፤ በዞንና በወረዳ ደረጃ በ2009፣ በ2010 እና በ2011 ዓ.ም በተዘጋጁ የፈጠራ ስራ ውድድሮች ላይ በመሳተፍና በማሸነፍ የተለያዩ ሽልማቶች አግኝቷል።
ቀጣይ እቅድ ፡-
ከእድሜው ባለፈ ብስለት ላይ መገኘቱን በሚያሳብቅ ንግግሮቹ ወደፊት ያለውን ህልምና ተስፋውን የሚገልፀው የፈጠራ ባለሙያው ኢዘዲን፤ በፈጠራ ስራው ከፍተኛ ደረጃ መድረስ የሚፈልግ፤ በእርሱ የፈጠራ ስራዎች ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ሆኖ ማየት የሚመኝና ለወጣቶች ብዙ የስራ እድሎችን ፈጥሮ ለውጣቸውን ማየት የሚናፍቅ ለዚህም የሚተጋ መሆኑን ይናገራል።
በግል ጥረቱና በተለያዩ አካላት እየተደረገለት ባለው ድጋፍ ስኬታማ እንደሚሆን ሙሉ እምነት ያለው ኢዘዲን፤ በሳይንስና በምርምር እንዲሁም በፈጠራ ስራ የራሱን ትልቅ አበርክቶ ለሀገሩና ለወገኑ የማበርከት ብርቱ ምኞት አለው።ዘንድሮ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን በመማር ላይ የሚገኘው ኢዘዲን፤ ወደፊት በኮምፒዩተር ሳይንስ፤ በተለይም የኮምፒዩተር ሶፍት ዌር እንጂነሪንግ አጥንቶ የተሻሉ የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ያልማል።እኛም ለዚህ ታዳጊ ወጣት ስኬታማ ጉዞ ተመኘን። ቸር ይግጠመን፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ተገኝ ብሩ