ሕዝብ ቅሬታውን ለመንግሥት የሚያሰማበትና ተቃውሞውን የሚገልጥበት አንዱ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ አገራት ሕዝቦች ፍትህ ሲጓደል፣ ሰብዓዊ መብት ሲረገጥ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲነፈግ… ወዘተ. በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን በሚያስተጋቡበት ወቅት፤ አምባገነን መንግሥታት ለሰላማዊ ትግል አደባባይ የወጣውን ሕዝብ እንደቅጠል አርግፈዋል። በአንጻሩ በሕዝብ ለተነሱ ቅሬታዎች ዓይነተኛ መፍትሄ በመስጠት ሕዝባቸውን ከአደጋ፤ አገራቸውን ከመበታተን የታደጉ ጥበበኛ መሪዎችም በዓለም ላይ ባለፉት ዘመናት ታይተዋል።
ዛሬም ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም ላይ ሥልጣኔና ዴሞክራሲ ከትናንት ዛሬ እያበበ ቢመጣም፤ በአንዳንድ አገሮች ኢፍትሐዊነት፣ ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተንሰራፋ በመምጣቱ የተለያዩ የተቃውሞ ድምጾች ሲስተጋቡ ይሰማሉ።
ከነዚህ መካከል ባለፉት ሳምንታት ከሊባኖስ እስከ ስፔን፤ ከቺሊ እስከ ግብጽ ድረስ ሚሊዮኖች የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፤ በነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች የተለያዩ የሚመስሉ ጥያቄዎች የተነሱ ቢመስልም ሁሉንም የተቃውሞ ሰልፎች የሚያመሳስሏቸው የጋራ ጉዳዮች አሏቸው። እነዚህን በቅርቡ በዓለም ዙሪያ የተካሄዱና እየተካሄዱ ያሉ ሰላማዊ ሰልፎች መንስኤዎቻቸው ምን ምን እንደሆኑ ለዛሬ በአራት ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ከፋፍለን ለመዳሰስ ወድደናል።
ኢፍትሃዊነት:-
በዚህ በኩል ያሉ የተቃዋሚ ሰልፈኞች የአገራቸውን ሀብት በእኩል መንገድ እየተከፋፈሉ አይደለም ብለው የሚምኑና የወሳኝ አገልግሎቶችና ምርቶች ዋጋ መናር የሚቃወሙ ሲሆኑ፤ ለዚህ ቀዳሚ ምሳሌ የሚሆኑት ኢኳዶራውያን ናቸው። በያዝነው ጥቅምት ወር በኢኳዶር የተጀመረው ተቃውሞ መነሻው መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ብድር ለማግኘት ሲል በነዳጅ ዋጋ ላይ ያደርገው የነበረውን ድጎማ እንደሚያቆም ማስታወቁ ነበር።
ይህንን የመንግሥት ውሳኔ አንዳንድ የአገሪቱ ዜጎች የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ የመጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ ስለሚያስከትልና ተያይዞ ደግሞ የምግብ ዋጋም እንዲንር ስለሚያደረግ፤ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ኢኳዶራውያን የችግሩ ዋነኛ ገፈታ ቀማሽ ይሆናሉ በማለት መንግሥትን ሞግተዋል።
ውሳኔውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምርና ከዜጎች አቅም በላይ እንዲሆን ማድረጉን ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች ዋና ዋና መንገዶችን ዘግተዋል፤ የሀገሪቱን ፓርላማ አውግዘዋል፤ እንዲሁም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል። በመጨረሻም ሰልፈኞቹ ባደረጉት ተከታታይ ተቃውሞ መንግሥት ውሳኔውን ቀልብሶ በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በሌላ በኩል፤ ቺሊ በላቲን አሜሪካ ሀብታም ከሚባሉት ሀገራት ብትመደብም ከፍተኛ ኢፍትሃዊነት እንደተንሰራፋባት ይነገራል። በዚህም የተነሳ የመጓጓዣ ክፍያዎች በእጅጉ መጨመራቸው ያማረራቸው ቺሊያውያን በዋና ዋና የአገሪቱ አደባባዮችና መንገዶች በመውጣት ተቃውሟቸውን ለዓለም ሕዝብ አሰምተዋል።
ምንም እንኳን መንግሥት «በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና የባቡር አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረግኩት ለኃይል ማመንጨት የማወጣው ወጪ ከፍ በማለቱና የአገሪቱ ምንዛሪ ደካማ በመሆኑ ነው» ቢልም፤ ዜጎች ግን «ደሃውን ለመጫን ሆን ተብሎ የተደረገ ነው» ሲሉ የመንግሥትን ውሳኔ በአደባባይ ኮንነዋል።
በመጨረሻ የቺሊ መንግሥት የዋጋ ጭማሪውን «ትቼዋለሁ፤ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ» ብሎ ለዜጎች መልዕክቱን ቢያስተላልፍም፤ ሰልፈኞቹ «እንዲያውም ሌሎች ብዙ ያልተመለሱልን ጥያቄዎች አሉ።» በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለውበታል።
በቅርቡ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎችን ከአስተናገዱ አገሮች አንዷ ሊባኖስ ናት። የተቃውሞው መነሻ ደግሞ መንግሥት በአገሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የማህበራዊ ሚዲያና የስልክ ጥሪ አገልግሎት በሚሰጠው ‘ዋትስአፕ’ ላይ ግብር እጥላለሁ ማለቱን ተከትሎ የተጀመረው ተቃውሞ አድጎ ወደ ኢፍትሀዊነት፤ ሙስናና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከፍ ብሏል።
ሙስና:-
ሙስና ስር ከሰደደባቸው አገሮች አንዷ ሊባኖስ በመሆኗ አሁንም በዚህኛው ምድብ ውስጥ ተካትታለች። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የአገሪቱ ዜጎች እንደሚሉት፤ ደሃው ዜጋ በከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት ሰዓት መሪዎች የራሳቸውን ሀብት ለማካበት ሲሰሩ ይታያሉ።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዕለትም የሊባኖስ መንግሥት የተቃውሞ ሰልፎቹን ተከትሎ የተለያዩ የጥቅማ ጥቅም አሠራሮችን ያበጀ ሲሆን፤ የመንግሥት ኃላፊዎችን ደመወዝ ለመቀነስም ሃሳብ አቅርቧል።
በሌላ በኩል፤ በኢራቅ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች የተቀሰቀሱ ሲሆን፤ ሰልፈኞቹም በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ሕዝቡን በችግር ውስጥ ከቶታል ሲሉ ተደምጠዋል። ሌላኛው ጥያቄያቸው ደግሞ፤ የመንግሥት ኃላፊዎች ምደባ በእውቀታቸውና በልምዳቸው ሳይሆን በዘርና በኃይማኖት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ ገልጸዋል።
«ይህ አሠራር ኃላፊዎቹ የአገሪቱን ሀብት እንዲበዘብዙና በደሃው ሕይወት እንዲቀልዱ በር ከፍቶላቸዋል» ሲሉም በምሬት ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ለዓለም ሕዝብ አሰምተዋል።
የአፍሪካዋ ግብጽም የዚሁ ሰለባ ከሆኑት አገሮች አንዷ ሆናለች። በግብፅ ባሳለፍነው መስከረም ወር የተጀመረውን ተቃውሞ አንድ ሞሀመድ አሊ የተባለ በስፔን በጥገኝነት የሚኖር ግብጻዊ ባለሀብት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ እና በአገሪቱ በከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለሥልጣኖች በሙስና መዘፈቃቸውን በማጋለጥ ተቃውሞውን አቀጣጥሏል።
በዚህም አያሌ ግብጻውያን ተቃውሞውን በመቀላቀል አደባባይ ወጥተው ለዓለም ሕዝብ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፤ ተቃውሞውም «ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን ይልቀቁ» ወደሚል ጥያቄና ግፊት በመሸጋገሩ በግብጽ መንግሥትና ዜጎች አይጥና ድመት ሆነው ተቀምጠዋል።
ፖለቲካዊ ነፃነት:-
ከፖለቲካዊ ነፃነት ጋር በተያያዘ ለወራት የቆየው የሆንግ ኮንግ የተቃውሞ ሰልፍ የዓለም መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል ብትሆንም፤ «አንድ ቻይና ሁለት አስተዳደር» በሚል ሥርዓት ሆንግ ኮንግ እራስ ገዝ አስተዳደር በመሆኗ፤ የቻይና እና የሆንግ ኮንግ የሕግ ሥርዓት የተለያየ ነው። ነገር ግን ቤጂንግ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከሆንግ ኮንግ ወደ ቻይና ተላልፈው እንዲሰጡ የሚያስችል ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዷን ተከትሎ በሆንግ ኮንግ የተቀሰቀሰው የተቋሞ ሰልፍ መቋጫ አጥቷል።
በሌላ በኩል፤ የካታላን ግዛት ከስፔን መገንጠል አለባት የሚል ሃሳብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፖለቲከኞች ለእስር የተዳረጉት እ.አ.አ በ2017 ሲሆን፤ በስፔኗ ባርሴሎና የካታላን መሪዎች መታሰራቸውን የተቃወሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ለዓለም ሕዝብ አስተጋብተዋል።
ምንጭ:- ቢቢሲ እና አልጀዚራ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2012
ሶሎሞን በየነ