ኢትዮጵያ በእንሰሳት ሀብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ብትሆንም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አላገኘችም። ይሁን እንጂ የእንሰሳት ሀብት አጠቃቀማችንን ከዘልማዳዊ አሠራር ተላቆ ዘመናዊ በማድረግ ለኢኮኖሚው ያለውን ፋይዳ እንዴት ማሳደግ እንችላለን? ስንል ምሁራንን አነጋግረናል።
በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቀንድና የጋማ ከብቶች ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፍሬው ካሳ እንደሚያስረዱት ሀገሪቱ የእንሰሳት ሀብት ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ የምትችለው አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የምርምር ውጤት የሆኑ የሥጋም ይሁን የወተት ከብቶችን በዘመናዊ መንገድ ማርባት ሲንችል ነው።
በእንሰሳት ዘርፍ ምርምር የሚያደርጉ ሙያተኞ ችም ዘወትር ራሳቸውን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማቆራኘት ህብረተሰቡን ማገዝ አለባቸው። ዶክተር ፍሬው የእንሰሳት ልማት ሥራ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የግል ባለሀብቶችን ወደዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ አሠራርን ለማሻሻልና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ አጋዥ ነው ይላሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የእንሰሳት ምግብና መኖ ስፔሻሊስት አቶ ታሪኩ ተካ የዶክተር ፍሬውን ሃሳብ ያጠናክራሉ። መንግሥት የሰብል ምርትን ለማሳደግ ማዳበሪያን ከውጭ ሀገር እያመጣ ለገበሬው በብድር እንደሚሰጥ ሁሉ የእንሰሳት ዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በሚፈለገው ደረጃ ማስተዋወቅና መደጎም እንደሚገባው ይመክራሉ።
እንሰሳት በሥጋ ፣ በወተትና በወተት ተዋጽኦ በቆዳና ሌጦ ወዘተ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከሚጫወቱት ሚና በተጨማሪም እርሻ በማረስ ፣ በመውቃት፣ ዘርንና ምርትን በማጓጓዝ በሰብል ምርት ዘርፍም 47 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። በአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ውስጥ እንሰሳት የጀርባ አጥንት መሆናቸውን አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።
የሀገራችን አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች እንሰሳትን በቴክኖሎጂ ታግዘው ስለማያረቡ የራሳቸውንም ሆነ የሀገራቸውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ አልቻሉም ሲሉ አመልክተዋል።
በአንቦ የኒቨርሲቲ የአግሮ ኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ሚልኬሳ ዋቅጂራ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት ካለን የእንሰሳት ሀብት አንጻር ዘርፉን ማዘመን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ከፍተኛ አበርክቶ አለው።
በተለይ የእንሰሳት ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢን ለማሳደግ ከታሰበ ከገበያው ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ምርትን ማምረት የሚያስችል ምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ ይላል። ስለሆነም የሀገራችንን ዝርያዎች ማሻሻል የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የስጋም ሆኑ የወተት ከብቶችን የውጭ ዝርያ ካላቸው ጋር ማዳቀል ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል። ልክ እንደ እህል እየተዘራ ለከብቶች የሚቀርብ መኖንም ማስተዋወቅ በምርት ላይ እድገት እንዲጨምር እንዲያደርግ አስታውቀዋል። በሙያው የሰለጠኑ ሰዎችን ማሰማራትና ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መጠቀም ግድ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ታሪኩ አስተያየት አብዛኛው ህብረተሰብ ለዝናና ለክብር ይህን ያህል እንሰሳት አለኝ ከማለት በዘለለ ‹‹በዓመት ይህን ያህል ወተት ወይም ዕንቁላል አገኛለሁ›› ብሎ ገበያን አስልቶ አያረባም። ምርታማ የሆኑ ምርጥ ዘሮችንም አይይዝም። ስለሆነም ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ማነቆዎችን በመለየት መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ይመክራሉ።
ዝርያዎችን በመምረጥ የወተትና የሥጋ ከብቶችን መለየት፣ እንሰሳት የሚጠቀሙትን መኖ በጥራትም በመጠንም ማሻሻል፣ ጤንነታቸውን መንከባከብ፣ አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር አረባብን እንዲከተልና በሰለጠነ ሙያተኛ እንዲታገዝ ማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ ያስችላል ይላሉ አቶ ታሪኩ።
የእንሰሳት ዘርፍ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር ተገቢውን ትኩረት እንዳላገኘ የሚናገሩት ዶክተር ፍሬው መንግሥት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ መሥራት እንደሚገባ አመልክተዋል። እንደኬኒያ፣ ሱዳንና ሩዋንዳን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት የወተት ምርቶችን ለአውሮፓ ገበያ በመቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ በዘርፉ መልካም ሥራ ከሚሠሩ ሀገራትም ተሞክሮ መውስድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በሀገራችን የገበያ ሁኔታ እንኳን አንድ የሥጋ ከብት ከሰማንያ አስከ ዘጠና ሺ ብር መሸጡን ያስታወሱት ምሁሩ ዘርፉ ቢሠራበት የህብረተሰቡን ህይወት ከመቀየር አንጻር ተወዳዳሪ እንደሌለው ገልጸዋል።
በሀገራችን ያለው የተለያየ የአየር ንብረትና መልክዓምድር የተለያዩ እንሰሳትን ለማርባት አመቺነት እንዳለው የተናገሩት ዶክተር ሚልኬሳ ለዶሮ፣ ለቀንድ ከብት፣ ለበግ፣ ለግመልና ለመሳሰሉት የሚመቹ ቦታዎችን በመለየት በሙያተኛና በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ ማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ያሳድጋል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2012
ኢያሱ መሰለ