አዲስ አበባ፦ ተቋሙ በምርምር ሥራው ከፍተኛ ውጤት ያመጣው በአገዳና የብርዕ ሰብሎች ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ዋና ዳይሬክተር ተናገሩ።
ዋና ዳይሬክተሩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በርካታ የምርምር ሥራዎችን በመሥራትና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ረጅም ዓመትን ያስቆጠረ ቢሆንም እጅግ የተሳካ ውጤትን እያገኘ ያለው በአገዳና በብዕር ሰብሎች ላይ ነው ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በቆሎን ከ 20 ዓመት በፊት የነበረው ምርታማነት አሁን ላይ በእጥፍ ከማደጉም በላይ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል እየተገኘ ነው፤ይህ ውጤት የመጣው ደግሞ የማዳቀል ሥራው ከፍተኛ ውጤት ስላመጣ መሆኑን በመናገር እንደ ስንዴና ማሽላም ያሉ ሰብሎ በተመሳሳይ ውጤታማ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በጣም ተሠርቶበት ግን ውጤት ያላመጣው ቡና ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ቡና ላይ የማዳቀል ሥራው አንሶ ሳይሆን የተዳቀለውን ቡና ወስዶ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የማድረግ አቅማችን ውስን በመሆኑ የመጣ የውጤት መቀነስ መሆኑን አብራርተዋል።
ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆነው ደግሞ በሌሎች ቦታዎች እንደሚደረገው አርሶ አደሮቹን ለተወሰነ ጊዜ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ማቀፍና ወደተሻሻሉት ዝርያዎች ማስገባት መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
እፀገነት አክሊሉ