የኢትዮጵያ ክለቦች አጭር፣ መካከለኛ ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት መካሄዱን ቀጥሏል። የሻምፒዮናው ሁለተኛ ቀን ውሎ ሰባት የፍጻሜና በሁለቱም ጾታዎች የ100 እና የ400 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች ተከናውነዋል። የሴቶች የ4 በ 1 ሺ 500 ሜትር ድብልቅ ሪሌይ ውድድር ነው። ውድድሩ አጓጊና ጥሩ ፉክክር የታየበት ቢሆንም የመከላከያ ክለብ አሸናፊ ሆኗል። የሴቶች የ110 ሜትር መሰናክል ሌላው የተከናወነ ውድድር ሲሆን የመከላከያ አትሌት ክለቡን ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት እንዲሆን አስችላለች። ሌላው በእለቱ አጓጊ በሆነው በሴቶች ከፍታ ዝላይና የ4 በ 1 ሺ 500 ሜ ድብልቅ ሪሌይ ውድድር መከላከያ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የሜዳሊያውን ቁጥር ከፍ ማድረግ ችሏል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ከማለዳ ጀምሮ በድምቀት ሲካሄድ ባረፈደው ውድድርም መከላከያ ሁለት ወርቅ በማስመዝገቡ የሻምፒዮናነት ግምትን እንዲሰጠው ያደረገ ሆኗል። ውድድሩ በተጀመረ እለት በሴቶች የርዝመት ዝላይ አንደኛና ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ሁለት ሜዳሊያዎችን የሰበሰበው የኢትትዮጵያ ንግድ ባንክ መከላከያ ወደ ሻምፒዮናነት የሚያደርገውን ጉዞ ይገዳደራል ተብሎ ይጠበቃል። ክለቡ በቀጣይ ቀናቶች በሚደረጉ ውድድሮች ሜዳሊያዎችን በዚህ መልኩ መሰብሰብ ከቻለ የአምናውን የሻምፒዮናነት ገድል የሚደግም ይሆናል። አምና በተካሄደው ሻምፒዮና መከላከያ በ381 ነጥብ 1ኛና የዋንጫ ተሸላሚ፣ኢትዮጵያ ባንክ በ183 ነጥብ 2ኛ፣ሲዳማ ቡና በ166.5 ነጥብ 3ኛ በመሆን ነበር ያጠናቀቁት።
በሁለተኛው ቀን የሻምፒዮናው ውሎ ሌሎች የተከናወኑ ውድድሮች የነበሩ ሲሆን፤ በሁለቱም ጾታዎች 100 ሜትርና 800 ሜትር ውድድር ፣ከፍታ ዝላይ ፣የወንዶች አሎሎ ውርወራ ፣የወንዶች 110 ሜትር መሰናክል ውድድር ተከናውኗል። በውድድሩም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ 25 ክለቦች የተወጣጡ 706 አትሌቶች በሻምፒዮናው ላይ የሚተሳተፉ ሲሆን ለተወዳዳሪዎች በድምሩ ከ200 ሺ ብር በላይ ሽልማት ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ አጭር፣ መካከለኛ፣ እርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።
ዓመታዊው ሻምፒዮና ለአጭር፣ መካከለኛ፣ የሜዳ ተግባራትና የርምጃ ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ በክለቦች መካከል የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትን አላማ ያደረገ ነው ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
ዳንኤል ዘነበ