የአንዳንድ ጀግኖችን ታሪክና ውለታ መፃፍ ትርጉሙ ‹‹ሳይፃፍ ከሚቀር ይሻላል እንጂ በቂ ነው ብሎ ማሰብ ቀልድ ነው…›› ሊባል የሚችልበት አጋጣሚ አለ። በተለይ ደግሞ የጀግንነታቸውንና የውለታቸውን ልክ ለመዘርዘር የሚበቃ ወረቀትና ለመግለፅ የሚያስችሉ ቃላትን ማግኘት አዳጋች ሲሆን! ‹‹ሳይፃፍ ከሚቀር ይሻላል እንጂ ይቺ እንኳ እዚህ ግባ የማትባል ሙከራ ናት›› ያሰኛል። ዛሬ በዚህ አምድ ‹‹ውለታቸውን የምናወሳቸው›› የታላቁ ጀግና ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ታሪክም የዚህን ዓይነት ስሜት ይሰጣል። ስለሆነም ‹‹ሳይፃፍ ከሚቀር ይሻላል›› ብለን እናስብና ታሪካቸውን እናስታውስ፤ውለታቸውን እንዘክር።
ለገሰ ተፈራ በ1934 ዓ.ም. ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴና ከወይዘሮ ተናኜ ተክለ ወልድ ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ ሆኖ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለደ። አቶ ተፈራ የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ልጅ የልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ ባለሟል ስለነበሩ ሕፃኑ ለገሰ ከልዕልት ጸሐይ ባለቤት ከሌተናል ጀኔራል ዐቢይ አበበ ጋር የመገናኘት እድል አገኘ። ሌተናል ጀኔራል ዐቢይ ከአቶ ተፈራ ጋር በነበራቸው ቅርበት ‹‹ለገሰን ስጠኝ›› ብለው ወስደው ያሳደጉትና የለገሰን የወደፊት እጣ ያመላከቱት እርሳቸው እንደሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል።
ሕፃኑ ለገሰ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው ወደነበሩት የኔታ ቸርነት የተባሉ መምህር ዘንድ እየሄደ የቄስ ትምህርት ተምሯል። የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በደጃዝማች ወንድይራድ እና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል።
ሌተናል ጀኔራል ዐቢይ ለቤተ መንግሥቱ ብዙ ቅርበትና ተሰሚነት ስለበራቸው ለገሰን ከመኳንንቱና ከሹማምቱ ጋር ያስተዋውቁት ነበር። ይህም ለወደፊት ጉዞውና ማንነቱ እጅግ እንደጠቀመው የሚካድ አይደለም። የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ልጅ ልዑል መኮንን ሲያገባ ለገሰ በንጉሰ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ ሚዜ ሆኖ ነበር። በዕለቱም ቁመናውንና ወታደራዊ አለባበሱን ያየ ሰው ሁሉ ‹‹ከዓይን ያውጣህ›› ይለው ነበር።
ለገሰ ቁመናው ብቻ ሳይሆን አእምሮውም ውብ ነበር። በትምህርት ደረጃቸው ከተወዳዳሪዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ነበር። ከአካዳሚክ ትምህርት ባሻገር ጉብዝናው በሙዚቃ፣ በስፖርትና በሌሎችም መስኮች የተመሰከረለት ነበር። ጊታርና ፒያኖ በደንብ ይጫወታል። ሌተናንት ጀኔራል ዐቢይ አበበ ለገሰን ጥሩ መሪ አድርገው ለማሳደግ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል። ገና በልጅነቱ የንባብ ፍቅር እንዲያድርበት አድርገዋል።
ለገሰ ሐረር የጦር አካዳሚ እንዲገባ የተደረገውም በንጉሰ ነገሥቱና በሌተናል ጀኔራል ዐቢይ ምርጫና ምክረ ሃሳብ ነው። ለገሰ የተቀላቀለው አካዳሚ በልዩ ባለሙያዎች የተዋቀረና የተደራጀ የላቀ ወታደራዊ ዕውቀት መቅሰሚያ ማዕከል ነበር። ማዕከሉ እንደ እንግሊዙ ‹‹ሳንድኸርስት ሮያል አካዳሚ››፣ እንደ አሜሪካው ስመጥር ‹‹ዌስት ፖይንት›› ወታደራዊ አካዳሚ የጠለቀ የውጊያ ስልት፣ የአመራርና የአስተዳደር ችሎታ፣ የአካል ብቃትና በኮሌጅ ደረጃ የሚሰጡ የቀለም ትምህርቶች እንዲሁም የወታደራዊ ሳይንስ ስነ ምግባር ስልጠናዎች የሚሰጡበትና ልዩና ብቁ የሆኑ አይነተኛ የጦር መኮንኖችን የሚያፈራ ተቋም እንደነበርም ስለአካዳሚው የተጻፉ ድርሳናትና በስልጠናው ያለፉ መኮንኖች በተደጋጋሚ መስክረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር አየር ኃይል ለበረራ የሚቀበላቸው እጩ መኮንኖች በቂ የሆነ የወታደራዊ ስልጠና ያገኙ መሆን አለባቸው የሚል መመሪያ አወጣ። የአየር ኃይል ትምህርት ክፍል ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ እየሄደ መመልመል ጀመረ። ለገሰ ተፈራ አየር ኃይል የሚፈልገውን መስፈርት አሟልተው ከተገኙ መካከል አንዱ ሆነ፤የአየር ኃይል የበረራ ትምህርት ቤት አባልም ለመሆን በቃ። የበረራ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅም ጀት አብራሪ እና የበረራ አስተማሪ ሆነ። በሀገር ውስጥ ካገኙት የበረራ ትምህርት በተጨማሪ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፍ ያለ ወታደራዊና የበረራ ትምህርት ቀስመዋል። በተለይም በአሪዞና የአየር ኃይል ማሰልጠኛ ተቋም ከበረራ ጋር የተያያዘ የመሳሪያ አጠቃቀም ትምህርትን አጥንተዋል።
በ1962 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የጨበጠው የሶማሊያው መሪ ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ቅኝ ገዢ ኃይሎችና የሶማሊያ ቀድሞ መሪዎች ያስተጋቡት የነበረውን ‹‹ታላቋ ሶማሊያ››ን የመፍጠር ሕልም ለማሳካት ጦሩን ሲያደራጅ ቆይቶ ኢትዮጵያን ወረረ። በዚህ ወቅት ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ የዘጠነኛው ስኳድሮን አባል ሆነው ተሰለፉ።
ሐምሌ 14 ቀን 1969 ዓ.ም የአየር ለአየር ውጊያ ተጀመረ። የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያን የሲቪል አውሮፕላን መትቶ ጣለ። ይህ እንደተሰማም ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስና ኮሎኔል መንግሥቱ ካሣዬ ወደ ቦታው በረሩ። ሁለት የሶማሊያ ሚግ-21 የጦር አውሮፕላኖች ተመሳሳይ ጥፋት ለማድረስ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ እየበረሩ አገኟቸው። ኮሎኔል በዛብህ እና ኮሎኔል መንግሥቱ ውጊያ ለመግጠም ፊታቸውን አዞሩ።
ኮሎኔል በዛብህ ቀረብ ብሎ በታያቸው የሶማሊያ ጦር አውሮፕላን ላይ ሲተኩሱበት አውሮፕላኑ ለሁለት ተገምሶ ወደቀ። ኮሎኔል መንግሥቱ ደግሞ ወደ ሌላኛው የሶማሊያ የጦር አውሮፕላን ለመተኮስ ሲዘጋጁ የሶማሊያው ፓይለት ፊቱን አዙሮ ሸመጠጠ። ኮሎኔል መንግሥቱና ሶማሊያዊው ፓይለት የያዟቸው የጦር አውሮፕላኖች በፍጥነትም ሆነ በጉልበት ስለማይመጣጠኑ ወራሪው ፈርጥጦ ነፍሱን አተረፈ። ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስና ኮሎኔል መንግሥቱ ካሣዬ በድል አድራጊነት ተመለሱ።
በአየር ለአየር ውጊያ የጦር አውሮፕላኗን ያጣችው ሶማሊያ ለበቀል እርምጃ ሦስት ሚግ-21 አውሮፕላኖችን አሰማራች። አውሮፕላኖቹ የሶማሊያን የአየር ክልል ሳያልፉ የራዳር ሰራተኞች ስላዩዋቸው ትዕዛዝ መጣ። ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ተነገራቸው። ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ ኪዳኑ አብረዋቸው ተመደቡ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ለባልደረቦቻቸው ‹‹ሦስት ሚጎች ናቸው፤ታዲያ እንግዲህ አንድ አንድ ይድረሰና!›› አሉ በቀልድ መልክ። ሦስቱም ጀግኖች ወደ ኤፍ-5 የጦር አውሮፕላኖቻቸው ገቡ። ተንደርድረው ወደ ሰማይ ተፈተለኩ።
የራዳር ሰራተኞች የጠላት አውሮፕላኖች የት እንዳሉና በምን ያህል ከፍታ እንደሚበሩ ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ አስታወቁ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ደግሞ መረጃውን ለባልደረቦቻቸው ገለፁ። ከላይ ወደታች ለማጥቃት በማሰብ ከጠላት አውሮፕላኖች በላይ ከፍ ብለው መብረር ጀመሩ። የጠላት አውሮፕላኖች በመሳሪያቸው የዒላማ ወሰን ውስጥ ሲገቡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ሰንጥቀው (ዳይቭ አድርገው) ገቡ። የሶማሊያ ፓይለቶች እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ አጋጥሟቸው ስለማያውቅ በጣም ደነገጡ።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መተኮስ ሲጀምሩ ጎን ለጎን የነበሩት የጠላት አውሮፕላኖች ወደግራና ወደ ቀኝ ታጠፉ። ብዙም ሳይቆዩ እርስ በእርስ ተላተሙና ብትንትናቸው ወጣ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ፈገግ ብለው ወደባልደረቦቻቸው ሲመለከቱ ኮሎኔል ባጫ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ የተረፈውን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላን ሲያባርሩ ተመለከቱ። እርሱም ብዙ ሳይሄድ ከመሬት ጋር ተላተመ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰም ‹‹የሰውን መሬትና አየር በግፍ ጥሶ የገባ እኛ ብቻ ሳንሆን ተፈጥሮም ይታገለዋል›› አሉ።
በሁለት ቀናት የአየር ለአየር ውጊያ የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ አራት የጦር አውሮፕላኖቿን አጣች። የሁለቱን ቀናት ጨዋታ ኢትዮጵያ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈች። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰና ባልደረቦቻቸውም አስደናቂ የጀግንነት ጀብድ ፈፅመው በድል አድራጊነት ተመለሱ።
የሶማሊያ ጦር ኃይሉን አጠናክሮ መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ ከፍቷል። የኢትዮጵያ ጦር በከፍተኛ ወኔ እየተዋጋ ቢሆንም እርዳታ ካላገኘ ድሬዳዋ በጠላት እጅ መውደቋ ስለማይቀርና አየር ኃይል ድሬዳዋን የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት ስለተጣለበት የአየር ኃይል አባላት ለዘመቻው ተዘጋጁ። በወቅቱ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ የተመደቡት ለአየር በአየር ውጊያ ነበር።
የአገር ፍቅር፣ ጀግንነት፣ እልህና ቁጭት የተቀላቀለበት የአየር ላይ ጉዞ ወደ ድሬ … ለቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች የተመደቡት እነ ብርጋዴር ጀኔራል አምሃ ደስታ (በኋላ ሜጀር ጀኔራል እና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ) በድሬዳዋና አካባቢው ሰፍሮ የነበረውን የሶማሊያን ጦርና ከባድ መሳሪያዎቹን አመድ አደረጉት። አሁን ተራው የነብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ነው። ከራዳር ሰራተኞች የመጣው መልዕክት ደረሳቸው። ሁለት የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ዕይታቸውና ኢላማቸው ውስጥ ሲገቡላቸው ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ‹‹በግፍ ስለደፈራችኋት ኢትዮጵያ››፣ መቶ አለቃ አፈወርቅ ደግሞ ‹‹ስለ ድሬ›› ብለው ሁለቱን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ወደአመድነት ቀየሯቸው። ሁሉም የአየር ኃይል አባላት የድሬዳዋን እንባ ጠርገው በድል ተመለሱ።
ከዚህ በመቀጠል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋነኛ ትኩረት በሶማሊያ ጦር ከባድ መሳሪያዎችና አየር መቃወሚያዎች ላይ ሆነ። ‹‹ … የሶማሊያ ጦር አየር መቃወሚያና ከባድ መሳሪያ ጂግጂጋ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግረኛ ጦር እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኖበታል …›› የሚል መልዕክት ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መጣላቸው።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እና ብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ገብረፃድቅ ተመድበው ወደ ቦታው ሄዱ። ወዲያው ግን ሁለት ሚግ-21 የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖች ከሃርጌሳ ወደብ መነሳታቸው ለነብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተነገራቸው። ሁለቱም በፍጥነት ወደላይ በመውጣት የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖችን ዒላማቸው ውስጥ በማስገባት ፋታ ሳይሰጡ አጋዩዋቸው። ከዚች ቀን በኋላም የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖች ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ሳያዞሩ ቀሩ።
ጦርነቱ ሲጀመር ሶማሊያ 28 ሚግ-21፣ ኢትዮጵያ ደግሞ አራት ኤፍ-5 ተዋጊ አውሮፕላኖች ነበሯቸው። ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ሶማሊያ ከ20 በላይ የጦር አውሮፕላኖችን አጥታ አራት ብቻ ቀሯት። ከነዚህ መካከል ደግሞ አምስቱን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ያረገፏቸው ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ናቸው።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እና ብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ገብረፃድቅ ከግዳጅ በድል ተመልሰው ምሳ ለመብላት እየተዘጋጁ ሳለ የሶማሊያ ጦር በኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ እየተመራ በባሌ በኩል ከፍተኛ ጥቃት ስለከፈተ እርዳታ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበላቸው። አንድ ጉርሻ ሳይጎርሱ ከነድካማቸውና ከነረሃባቸው ለግዳጅ ተሰማሩ።
በዕለቱ ግዙፉንና እጅግ በጣም ከባድ ለሆኑ ውጊያዎች የሚሰማራውን ካምቤራ ቢ-52 የጦር አውሮፕላን ለማጀብ የተጓዙት ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ፣ የጠላት አሰላለፍ እንዴት እንደሆነ ለካምቤራው አብራሪ ብርጋዴር ጀኔራል መስፍን ኃይሌ ለማሳወቅ ዝቅ ብለው መብረር ሲጀምሩ የሶማሊያ ጦር ሁሉንም መሳሪያዎቻቸውን ተኮሱ። ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳካላቸው፤የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ አውሮፕላን ተመታች። ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ ጭስ በጭስ ሆኗል። ጭሱ እርሳቸውን ለመዋጥ እየተሳበ እየመጣ ነው። ኃይለኛ ሙቀትም ተከሰተ። ሁኔታውን ለብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ለመንገር ሬድዮናቸውን ቢሞክሩ እምቢ አለ። በአደጋ ጊዜ መገናኛ በኩል ግንኙነት ለማድረግ ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀረ።
‹‹ትንሽ ትሂድና ከጠላት ዕይታ ልዳን ብለው›› በረራ ቀጠሉ። አውሮፕላኗ ግን ከዳች። መውረድ ጀመረች። ፓራሹቱ በደንብ የሚዘረጋበትና የሚሰራበት ተገቢ ከፍታ ላይ እንዳልነበሩ ቢያውቁም አብሮ ላለመቃጠል ሲሉ ዘለሉ። ጀግናውና አውሮፕላናቸው በተለያየ አቅጣጫ ወደ መሬት ወረዱ። የስፖርት ሰው መሆናቸው ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ተደምሮ አየር ላይ ብዙ ሳይቆዩ ወረዱ። የጠላት ወታደሮች ግን ፓራሹቱ ሲወርድ አላዩትም ነበርና ወዲያውኑ አልያዟቸውም። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ራሳቸውን አንበሳ፣ ነብርና ሌሎች ግዙፍና ጥቃቅን ፍጥረታት በሚርመሰመሱበት ጫካ ውስጥ አገኙት። ስለቀጣይ እጣ ፋንታቸው እያሰላሰሉ ባሉበት ቅፅበት ከነድካማቸውና ከነረሃባቸው እንቅልፍ ሸለብ አደረጋቸው።
እንዳይነጋ የለም ነጋ። ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ የአካባቢው ልጃገረዶች ከወንዝ ውሃ ቀድተው ሲመለሱ ተመለከቱ። ልጃገረዶቹ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ሲያዩዋቸው ተደናገጡ። በእጃቸውም ‹‹ና›› የሚል ምልክት አሳዩዋቸው። ይዘውት ከነበረው ውሃም አጠጧቸው። ወደ ቤት ይዘዋቸው ሄደውም የሚበላና የሚጠጣ ሰጧቸው። ልጃገረዶቹ የኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ወታደሮች ቤተሰቦች ስለነበሩ ‹‹ባይተዋር ሰው ከሰፈራችን መጥቷል›› ብሎ የሚናገር ሰው ወደ ወታደሮቹ ልከው ነበር። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ በስድስት ታጣቂ ወታደሮች ተከበቡ። ‹‹እጅህን ስጥ›› ተባሉ። መሳሪያቸውንም እንዲያስረክቡ ተነገራቸውና አስረከቡ።
ኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ራሱ መኪናውን ይዞ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ካሉበት ቦታ ድረስ መጣ። የማሸነፍ ስሜት ይታይበታል። ዛሬ ሶማሊያ በለስ ቀንቷታል። የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ዋርካ ጥላለች።
ማስተር ቴክኒሺያኖቹ ኰሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ሞቃዲሾ ላለው የዚያድ ባሬ መንግሥት ስለሁኔታው ያስተላለፈውን መልዕክት ጠልፈው ሲያገኙት የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መማረክ በኢትዮጵያ ጦር ዘንድ ታወቀ። ኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ወደ ሞቃዲሾ ላከ። ምርኮኛውን ከኮሎኔል አብዱላሂ ተረክበው ለዚያድ ባሬ እንዲያስረክቡ የተላኩት ሁለት ሰዎች (የዚያድ ባሬ የሃይማኖት ዋና መሪ የነበሩት ሼህ መሃመድ አሊና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀኔራል መሃመድ አሊ ሰመተር) ነበሩ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ የታሰሩበት ተፈትቶላቸው ከሁለቱ ሰዎች ጋር ስለብዙ ጉዳዮች እየተጨዋወቱ ነበር ሞቃዲሾ የደረሱት።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰም ከገቡ በሕይወት ተመልሰው ወደማይወጡበት ‹‹ሸሌ ሞርቶ›› በተባለው እስር ቤት በልዩ ስሙ ሳታንቡር ተብሎ ወደሚታወቀው ክፍል ተላኩ። በእስር ላይ በነበሩባቸው ጊዜያትም የጦሩ አባላት በተለይ የአየር ኃይል ባልደረቦቻቸውና ሰራዊቱ መንግሥት ከእስር እንዲያስፈታቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችንና ተማፅኖዎችን ያቀርቡ ነበር። ከ11 ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ተለቀቁ። የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚም ሆኑ። የአሁኑ የኩባ ፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ ደግሞ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ከነቤተሰቦቻቸው በእንግድነት ጋብዘዋቸው ነበር።
ወደሚወዱት ሙያቸው ቢመለሱም ቀድሞ ከሚያውቁት ፈፅሞ የተለየ አደረጃጀት ስለጠበቃቸውና በወቅቱ ተቋሙን ከተቆጣጠሩት ጋር አብሮ ለመስራት ባይተዋር ሆኑ። ወደ በረራው ዓለም ተመልሰው ማስተማር ቢጀምሩም በርካታ የበረራ ባለሙያዎችን ማፍራት ሲችሉ ለእርሳቸው ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ተገለሉ። ከሚወዱት ሰማይ ተለዩ።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ የበረራ ትምህርት ሲያስተምሩ የሚጠቀሙት ቀላል መንገድ ነው። ፈፅሞ ስሜትን የሚነካ ነገር አይናገሩም፤ በዚህም ምክንያት ተማሪዎቻቸው ያከብሯቸዋል፤ይወዷቸዋል።
ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ለበረራ የተፈጠሩ ልዩ ሰው ነበሩ። ሳይሰለቹ መብረር፣ በአየር ላይ መገለባበጥ፣ ኢላማ ማስገባትና ምንም ጭስ ሳያሳዩ ማረፍ የእርሳቸው ልዩ ተሰጥኦዎች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። የእግረኛውንም ውጊያ ስልት በደንብ ያውቁታል። ሐረር የጦር አካዳሚ በደንብ ተምረውታል። ከዚህ ባሻገር አመጋገባቸው ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር። የሚያውቋቸው ሁሉ ‹‹ስፖርት ስለሚያዘወትሩ ሸንቀጥ ያሉ፣ ደልዳላ ሰውነት ያላቸው … በአጠቃላይ ለዓይን የሚማርክ ቁመና ባለቤት ነበሩ።
ሰዎች ባጠገባቸው ሲያልፉ ዘወር እያሉ የሚያዩዋቸው ይበዛሉ። የደንብ ልብስ ሲለብሱ ከሰርገኛ በበለጠ ይደምቃሉ፤ የልብሳቸው ተኩስ እንደ ጎራዴ ስለት ያለው ይመስላል። ቁልፎቻቸው፣ የደረት ባጃቸው፣ ቀበቷቸውና ጫማቸው ዘወትር እንዳንፀባረቁ ናቸው። አዲስ የተቀበሏቸው ይመስላሉ›› በማለት ቁመናቸውን ይገልጿቸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ወይዘሮ አልማዝ አመሃን አግብተው ነፃነት ለገሰ እና ሉሊት ለገሰ የተባሉ ልጆችን አፍርተዋል።
የ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ተሰደዱ። በዚያው ሲኖሩ ቆይተውም መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም አርፈዋል። አስክሬናቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስርዓተ ቀብራቸው ተወልደው ባደጉባት፣ ከራሳቸው በላይ በሚወዷትና ዋጋ በከፈሉላት እናት አገራቸው ምድር ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
አንተነህ ቸሬ