
በዘመነ ደርግ በነበረው ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው እናቶች ጨዋታ ይዘዋል:: ዛሬ እርጅና ገጻቸው ላይ የሚያፏጭባቸው የያኔዎቹ ኮረዶች ያሳለፉትን ክፉና ደግ እያነሱ ይስቃሉ፤ ደግሞም ይተክዛሉ:: ወጣት ሴቶችን ማደራጀት ላይ በስፋት የተሳተፉ ነበሩ:: በየአውራጃው ተዘዋውረው በርካታ ሴቶች አደራጅተዋል:: በየመሃሉ ለሀገር መስራት፣ ስለሀገር መሰዋት በእኛ ጊዜ ቀረ ይላሉ::
በጨዋታቸው መካከል ያነሱት አንድ ታሪክ ቀልቤን ሳበው:: አንዷ ጓዳቸው ከባለቤቷ ጋር መሰማማት አልሆን ይላታል:: ባል ሁለት ሶስቴ በሰው ቢጠየቅ የዘመኑን ፖለቲካ መቃወም ተደርጎ ይቆጠርብኛል ብሎ በመስጋት የማይግባቡበትን ምክንያት ከመናገር ይቆጠባል:: በሂደት ግን የሚስቱ ሁኔታ በመሻሻል ፈንታ እየባሰ በመሄዱ ለሽምግልና ይቀመጣሉ:: በዚህ ጊዜ አባወራው የተቸገረበትን ነገር አፍረጠረጠው:: ምሽቴ ከትዳሯ የፖለቲካ ሥራዋ በልጦባታል:: ለቤተሰቧ ጊዜ መስጠት አልቻለችም:: ቤቷን ትታ አውራጃ ለአውራጃ ትዟዟራለች:: ይህን ነገርሽን ተይ ብላት አልሰማ አለች ብሎ ገላግሉኝ ሲል አቤት አለ:: በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎቹ ምን ሲደረግ ብለው ምሽቲቱ ላይ አፈጠጡባት:: ወጣት በዚያ ላይ ደግሞ ትንታግ ፖለቲከኛ የነበረችው ሚስትም ብድግ ብላ ምርጫዋን በሁለት ቃላት ቁጭ አድርጋ፣ ቁጭ ብድግ የሚያደርግ መልስ ሰጠቻቸው:: ቆፍጠን ብላ “ከቤቴ አቢዮቴ” አለቻቸው:: ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ:: ከቤቷ አቢዮቷን መረጠች:: ተለያዩ:: ይህች ቆራጥ ከዚያ በኋላ ጎጆ እንዳልቀለሰች ሲናገሩ ሰማሁ::
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ችግሮችም ከሀገራቸው ጥቅም ይልቅ ሆዳቸውን የሚያስቀድሙ ከቤቴ አቢዮቴ ባዮች ናቸው:: እነዚህ ወገኖች የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ሀገራቸውን ለመቅበር አያመነቱም:: ሆዳቸው ይሙላ እንጂ ከሰይጣን ጋር አብረው ይሰለፋሉ:: የሚገርመው ነገር እነዚህ ባንዳዎች ራሳቸው ሀገሬ የሚሏት ጉድጓዷን የሚቆፍሩላትን ምስኪን ነው:: ከቤቴ አብዮቴ ያለችው የያኔዋ ወጣት ምናልባት ሌላ ቤት መስርታ ይሆናል:: እኒህ ሰዎች ግን ሌላ ሀገር የመመስረት ዕድል የላቸውም:: አይበለውና ይህች ሀገር ብትፈርስ ሀገር አልባዎች ናቸው::
የማያንቀላፉት የኢትዮጵያ ታሪካዊ “ወዳጆች” አጥብቀው “የሚወዷትን” ሀገር “ለማቆም” የሚጠቀሙት እነዚህን ሆድ አደሮች ነው:: እነርሱን መሳሪያ አድርገው ሰባት ቀናት 24 ሰዓታት አንድነቷን ኢላማ አድርገው ይተኩሳሉ:: ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር አያውቁም::
የእኒህ የእፉኝት ልጆች አንጎል ምን እንደጎደለው እንጃ! ጉድለቱ የእውቀት ማጣት ቢሆን ከቤቴ አቢዮቴ ባዮችን ቁጭ አድርገን ባስተማርናቸው ነበር:: ዳሩ አውቆ የተኛን ነው ነገሩ:: እንጂማ ከእውቀት ነጻ የመሆን ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የከበደ ሚካኤልን ታሪክና ምሳሌ 3 ኛ ምጽሐፍ መዥረጥ አድርገን ስናበቃ ስለሀገር ምንነት እንነግራቸው ነበር:: እንዲህ እያልን… አገር በታሪክ በቋንቋ በሀይማኖት በልምድ በተስፋ በደስታና በመከራ ተሳስሮ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው::
አገር ማለት አያት ቅድመ አያት የተወለዱበት አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግሥት የሚጠቅም ሥራ ሠርተው ዕድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻቸውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ነው:: በመወለድ እትብት በመሞት አካል ከአፈሩ ጋራ ስለ ሚዋሐዱ የአገሩ አፈር ሕዝብ በላዩ የሚኖርበት ማለት ነው:: እግዚአብሔር ከምድርዋ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝበት በማድረጉ አገር እየጠባች የምታሳድግ ፍቅርዋ በአጥንት በሥጋ ገብቶ የማይደመሰስ የሆነች እናት ናት::
ከልጅነት ጀምሮ ወንዙን፤ ተራራውን፤ ሜዳውን፤ ቆላውንና ደጋውን በማየት ስለማደግ አባቶች በሕይወትና በሞት የሰሩበት ደግ ሥራ በአእምሮ ታትሞ የሚቀርበት እና በአገር እስካሉ በፍቅርና ናፍቆት የሚያሳድር አገር ነው:: አገር አባት እናት ዘመድ ምግብ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድህነትና ጥቃት በመጣ ቁጥር እስከ ሞት ድረስ እንዲሠራበት ከአያት ከቅድመ አያትና ከአባቶች በጥብቅ የተሰጠ ያደራ ገንዘብ ነው::
እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የቅርብና የሩቅ ወዳጆቻችን ተጠራርተው ከቤቴ አቢዮቴ ባዮችን ተጠቅመው እየዘመቱብን ነው:: ኢትዮጵያን ለማመስ የብሔር እና የሃይማኖት ልዩነቶችን እንደ ቤንዚን ስትጠቀም የኖረችው የሩቅ ወዳጃችን በዘመናት ውስጥ ያፈሰሰችው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር በጀት አንዳች ነገር ባይፈይድላትም ዛሬም ተስፋ አትቆርጥም:: የመሸ በመሰላት ቁጥር በጨለማ ውስጥ ጥቀርሻ እቅዷን ይዛ ትከሰታለች:: ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶችን በመጠቀም ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ ያልጫረችው የእሳት አይነት ባይኖርም አንዱም አልነደደላትም:: ቢሆንም ራሷ እየነደደችና እየተናደደች እዚህም እዚያም መክለፍለፏን እንደቀጠለች አለች::
ለበርካታ ሺህ ዘመናት የአባይ ወንዝ ውሃን ያለምንም ከልካይ ብቻዋን ስትጠቀም የኖረችው የሩቅ ወዳጃችን ኢትዮጵያ የምታስገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ድርሻዬን ይቀንስብኛል ብላ ዋይታዋን ማቅለጥ ከጀመረችው ደርዘን ዓመታት አልፈዋል:: ያላስታጠቀችው ቡድንና ያላከችው የሰላይ አይነት የለም:: በርካታ ዓለምአቀፍ ዘመቻዎችን ብትከፍትም የታላቋን ኢትዮጵያ የእድገት በር መዝጋት አልቻለችም:: በውስጣዊና ውጫዊ ግጭቶች የተወጠረች የተዳከመች ኢትዮጵያን የመፍጠር እቅዷ አልሰመረም::
የቀይ ባሕር ምልክት ሆና የኖረች የቀንዱ ቀንደኛ ሀገርን ከቃተኛው ለማራቅ የተራቀቀችበት ልክ ወይ ልክን አለማወቅ ያሰኛል:: በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ በኩል ለቅርቧ ወዳጃችን በላከችው መልዕክት “የቀይ ባሕር አካል ያልሆነ ማንኛውም ሀገር በባሕሩ ላይ የባሕር ኃይል እንዲያቋቁም አልፈቅድም” ብላ ከአቅሟ በላይ ተንጠራርታለች::
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ተኳርፋለች ብለው ባሰቡ ጊዜ ‹‹የሶማሊያን ሉዋላዊነት ለማክበርና የሀገሪቷን ጦር ለማጠናከር ተስማምተናል›› ብለው የሶስትዮሽ ጋዜጣዊ መግለጫ እስከመስጠት ደርሰዋል::
ከዓመታት በፊት የቅርቧ ወዳጃችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ባሕር ክልሌ ገብተዋል ያለቻቸውን በአምስት ጀልባ ከደቡባዊ የቀይ ባሕር ተነስተው አሳ በማጥመድ ላይ የነበሩ የሩቅ ወዳጃችንን 120 አስጋሪዎች በቁጥጥር ስር አዋልኩ ማለቷን ተከትሎ የለየለት ውጥረት ውስጥ ገብተው ነበር:: ከዚያ ወዲህ ተቀዛቅዞ የቆየው የሁለቱ ወዳጆቻችን ግንኙነት በጋራ አጀንዳቸው ምክንያት ዳግም አንሰራርቷል:: እናም ፍቅር እንደገና እያሉ ነው:: በፍቅር ወድቀው ከእኛ ወዲያ ላሳር እያሉ ነው:: በተፈጸመባት ሸፍጥ ወደብ አልባ የሆነችው ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የራሷን ወደብ ለማግኘት እና የባሕር ኃይል ለማቋቋም በምታደርገው እንቅስቃሴ በርግገው በአንድ መሶብ ካልበላን፤ በአንድ ሳፋ ካልጠጣን እያሉ ነው::
ሁለቱ ወዳጆቻችን በጦርነት የተተራመሰች እና የተዳከመች ኢትዮጵያን መፍጠርና ሀብቷን መቀራመትና መመዝበር የቀን ከሌት ቅዠታቸው ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ይረብሻቸዋል:: በፕሪቶሪያው ስምምነት ሁለቱም ወዳጆቻችን ለረጅም ጊዜ ታምመዋል:: አሁን በፕሪቶሪያ ስምምነት ስልጣን ተቀማን የሚሉ ከቤቴ አቢዮቴ ባዮችን ተጠቅመው ታላቋን ሀገር ለማመስ ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ:: በአማራና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ግጭቶችንም ለመጠቀም እንደልማዳቸው ቢሊየን ዶላሮችን ሲረጩ መክረማቸው አደባባይ ሚስጢር ነው::
ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንዲሉ መላ ዜጋዋን ለወታደራዊ ግዳጅ የጠራቸው የቅርቧ ወዳጃችን ጸብአጫሪ ተግባራትን ስትፈጽም ቆይታ ከሰሞኑ የውጭ ሃገራት አምባሳደሮች እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊን ጠርታ የድረሱልኝ ጩኸቷን አቅልጣዋለች:: ሰው ቤት ሲደረግ አይታ እኔስ ለምን ይቅርብኝ ብላ በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ “ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንድታከብር ጫና እንዲያደርጉ ስትል የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እና የሚመለከታቸው አካላትን እጠይቀለሁ” ብላ እርፍ ብላለች።
የቅርቧወዳጃችን በቀጣናዊ ግጭቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ስለመሆኗ የሚቀርብባትን ክስ ጨዋ ያሳደገኝ ነኝ ስትል ክዳለች:: ማንም ባይጠይቃትም በኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት ላይ ያላትን አቋም ካልገለጽኩ ሞቼ እገኛለሁ ብላም “የተዛባ እና ጊዜው ያለፈበት የባሕር ዳርቻ ፍላጎት” ብላ አካኪ ዘራፍን ዘርፋለች። በዚህ ሳታበቃ የኢትዮጵያ የባሕር በርና የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ምኞቷም ግራ የሚያጋባ ነው ስትል ተደምጣለች። በድፍረት በፍርኃቷ ገፍታም “ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ወይም በወታደራዊ ኃይል የባሕር ላይ መዳረሻ እና የባሕር ኃይል ሰፈር ለማግኘት ባላት የተሳሳተ እና ጊዜው ያለፈበት ምኞት ግራ ገብቶኛል ” ብላለች።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካበቃ በኋላም የሉአላዊነት መዳፈር ቆይታዋ እንዳላበቃ ሆዷ ያውቃል:: ዳሩ በሽምጠጣ ሽምጥ መጋለብ ልማዷ ነውና፤ በዓለም አቀፍ እውቅና ወደተሰጠኝ ድንበር ተመልሻለሁ። ሠራዊቴ አሁንም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንዳለ የሚናገር ማንኛውም ሰው ለኢትዮጵያ የውስጥ ችግር፣ የእኔን ስም በመጠቀም ለማምለጥ የሚሞክር ነው ስትል ሸምጥጣለች።
ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ የቅርቧ ወዳጃችን ላይ ያቀረቡትን ውንጀላም፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አድርጌ ስለምመለከተው በዚህ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለኝም ብላ አይኔን ግንባር ያድርገው ነው ያለችው::
በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርና በሕወሓት አንጃ መካከል እየተካሄደ ባለው የውስጥ ግጭት ውስጥም ፈትፋች መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ሚና የለኝም ስትልም የሚቀርቡባትን ውንጀላዎችና ክሶችን ሙሉ በሙሉ አልቀበልም ብላ በቀይ ባሕር ስም ምላለች።
ሁለቱ ወዳጆቻችን ሙያ በልብ ነው ብለው በአዳባባይ እየማሉና እየተገዘቱ የለንበትም የሚሉት ትርምስ የመፍጠር አጀንዳ እስከወዲያኛው የሚገታው ኢትዮጵያውያን ለማትተካው ሀገራችን መስዋዕትነት ለመክፈል በመቁረጥ ደጀን ለመሆን ስንቆርጥ ብቻ ነው:: ከቤቴ አቢዮቴ ባዮችም አደብ የሚገዙት ሲላተሙት እንደብረት የሚጠነክር ጠንካራ የሕዝቦች አንድነት ሲኖር ነው:: አለበለዚያ ግን ከውጭ ኃይሎች የሚላክላቸው ፍርፋሪ የጣፈጣቸው የእንጀራ ልጆች ውዷ ሀገራችንን ራሳችን ላይ እንዲንዷት እንፈቅዳለን::
የሚላክላቸውን የዶላር ፍርፋሪ መጠን ለመጨመር ሲሉ ሀገራቸውን ከማፍረስ የማይመለሱት ከቤቴ አቢዮቴ ባዮች አንድ ተረትን ያስታውሱኛል:: ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል:: በአንድ የገጠር መንደር ውስጥ የሚኖሩ ድሃ ባልና ሚስት ገበሬዎች ነበሩ:: ከዕለታት አንድ ቀን ከሚያረቧቸው ዶሮዎች መካከል አንዷ የወርቅ እንቁላል ጣለች:: ገበሬዎቹ ባልና ሚስቶች በሆነው ነገር እየተደነቁ እንቁላሉ የወርቅ መሆኑ እንዲመረመር የመንደሩ ሊቅ ወደ ሆኑ አዛውንት ዘንድ ወሰዱት:: አዛውንቱም እንቁላሉ ንጹህ ወርቅ እንደሆነ ነገሯቸው::
ባልና ሚስቱ እንቁላሉን ለወርቅ ነጋዴዎች በውድ ዋጋ ሸጡት:: በማግስቱም ዶሮዋ ሌላ የወርቅ እንቁላል ጣለች ፤ በቀጣዮቹ ቀናትም እንዲሁ:: ገበሬዎቹ ባልና ሚስቶች በገጠማቸው እድል እየተደሰቱ በየቀኑ አንድ የወርቅ እንቁላል እያገኙ በሀብት ደረጁ:: ከቀን ቀን ሀብታቸው እየጨመረ ሲመጣ አባወራው በየቀኑ አንድ አንድ እንቁላል ከመልቀም ይልቅ በአንድ ቀን ብዙ የወርቅ እንቁላል ማግኘትን ተመኘ::
እንዲህም አለ “ይህች ዶሮ በአንድ ቀን የምትጥለው አንድ የወርቅ እንቁላል ብቻ ነው:: ባርዳት ግን ሆዷ ውስጥ ያለውን የወርቅ እንቁላል በሙሉ በአንድ ጊዜ ማግኘት እችላለሁ” በማለት ሚስቱን ጠርቶ ሀሳቡን አካፈላት:: ባለቤቱ ዶሮዋን እንዳያርዳት አጥብቃ ብትለምነውም አሻፈረኝ አለ:: በመጨረሻም የወርቅ እንቁላል የምትጥልላቸውን ዶሮ አረዳት ፣ ነገር ግን ከሆዷ አንድም እንቁላል አላገኘም:: አባወራው ገበሬ የወርቅ እንቁላሉን ማግኘት የሚችለው ዶሮዋ ስትኖር ብቻ መሆኑን ዘንግቷል:: ቅጥ ያጣ የገንዘብ ፍቅር በአንድ ቀን የመክበር ጉጉቱ ውስጥ ዘፍቆት ማመዛዘን እንዳይችል ስላደረገው ዶሮዋን አረደ:: ስለዚህም ልብ ያለው ልብ ይበል::
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም