‹‹ሀገራዊ ምክክሩ አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ነው›› – ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)

– ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን ኮሚሽነር

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በተቀመጠለት የሶስት ዓመት የሥራ ዘመኑ ያላጠናቀቃቸው ተግባራት በመኖራቸው የሥራ ጊዜው ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም መደረጉ ይታወቃል። ይህ ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የሌላ አካል ተጽዕኖ ነፃ የሆነው ኮሚሽን፤ ሥራውን በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ አለማጠናቀቁ ምክንያቱ ምንድን ነው? የተራዘመው እስከ የካቲት ወር 2018 ዓ.ም ድረስ ስለሆነ ሥራው ከጠቅላላ ምርጫ ጋር አይጋጭም? በተለያዩ ክልሎች በትጥቅ ትግል ላይ ካሉ አካላት ጋር በቀጣይ ምን ለማድረግ ታስቧል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑትን ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)ን አዲስ ዘመን በተጠየቅ አምዱ ይዞ ቀርቧል።

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ በተቀመጠለት ሶስት ዓመታት ውስጥ ሥራውን አለማጠናቀቁ አንኳር ምክንያት ምን ይሆን?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- አንኳር የሚባሉ ችግሮች ነበሩ፤ ነገር ግን በዋናነት የመጀመሪያውና ትልቁ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ምክከር አዲስ ባይሆንም፤ ‘ምክክር ኮሚሽን ግን እንደ ተቋም አዲስ ነው። ስለዚህ ስንጀምር ተቋማዊ ብቃት አልነበረውም። አሠራሩ፣ አጀንዳ አሰባሰቡም ሆነ ራሱ አጀንዳ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አልነበረም። ሁሉን ነገር መጀመር የነበረብን ራሳችን ነን። የጀመርነውም ከባዶ ነበር፤ በመሠረቱ በኮሚሽኑ ውስጥ ያለን ሁሉ የመጣነው ከ11 የተለያዩ ቦታዎች እንደመሆናችን እርስ በርሳችን እንኳ አንተዋወቅም፡፡

አንድን ተቋም ለመጀመርም ሆነ ለማስቀጠል በመጀመሪያ ደረጃ መተዋወቅ ትልቁን ቦታ ይይዛል፤ ከዚህ ጎን ለጎን ሀገራችንን በቅጡ ማወቅ ተገቢ ነው። እኛ ውስጥ ግማሹ ከሀገር ውጭ የነበረ ነው፤ ሀገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኞች በመሆናችን ግን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አጋርነታቸውን ያሳዩ መሆናቸው አንድ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ከተሰባሰብን በኋላ እንደ ተቋም ስትራቴጂክ እቅድ ማውጣት እንዲሁም የኢትዮጵያን አውድ ማወቅ ነበረብን፤ በርግጥ የተወሰንን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበርን ብንሆንም፤ ሌሎቹ ደግሞ ኢትዮጵያን በማወቅ ደረጃ በተመሳሳይ የእውቀት ደረጃ ላይ አልነበሩምና አንዱ እንቅፋት እሱ ነው። ሌላው ፈተና በየቦታው አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው ግጭት ነው። እንደፈለግን ሁሉም ቦታ በአንድ ጊዜ ተንቀሳቅሰን እቅዳችንን መተግበር ባለመቻላችን እንደ እንቅፋት የሚታይ ጉዳይ ነው። ደግሞም ምክክር እንዲኖር ያስፈለገውም የግጭቶቹ መኖር ነው። ግጭትን በዘላቂነት ለመፍታት ከመዋጋትና ከመገዳደል ይልቅ በዋናነት የሚያስፈለገው መነጋገር ነው። ስለዚህ አንዱ መሬት ላይ የነበረው እንቅፋት ግጭት ነው።

ሌላው እንቅፋት ነበር ሊባል የሚችለው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የሰፍሩ መልዕክቶች ናቸው፤ መልካም የሆኑ መልዕክቶች የመኖራቸውን ያህል ብዙዎቹ ግን የተዛቡ በመሆናቸው የሕዝቡን አዕምሮ የሚበርዙ ናቸው። በኋላ ላይ ግን እንቅፋት የሆኑ መልዕክቶች እየተስተካከሉ የመጡበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል።

ነገር ግን ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁንና ሕዝባችን እጅግ በጣም ለሀገራዊ ምክክሩ ጥማቱ ስለነበረው፣ አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ 80 እና 90 በመቶው የተባበሩንና አብረውንም የሆኑ ናቸው። በርግጥ ጅማሪያችን አካባቢ ይመለከቱን የነበረው በጥርጣሬ ዓይን ነው። ነገር ግን እያደር እነርሱን ጨምሮ ከሲቪል ማኅበረሰቡ፣ ከምሁራኑና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመተባበር እንቅፋት ሆኖው የነበሩትን ሁሉ ቀርፈን በተሳካ ሁኔታ ሥራችንን መጀመር ቻልን።

ይሁንና በተባለው በሶስት ዓመታት ውስጥ መጨረስ አልቻልንም። ትግራይና አማራ ክልል ያለውን አላጠናቀቅንም። እንዲሁም ሌሎች ሥራዎቻችንንም አልጨረስንም። በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወይም በፌዴራል ደረጃ የሚከናወነው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ስላልተካሔደ እና የመጨረሻዎቹ አጀንዳዎችም ስላልተሰባሰቡ እነዚያን ማጠናቀቅ ስላለብን የአንድ ዓመቱ ጊዜ አስፈልጎናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ የተጨመረለት የአንድ ዓመት ጊዜ፤ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ታካሂዳለች ተብሎ ከሚጠበቀው ጠቅላላ ምርጫ ጋር የሚጋጭ አይሆንም?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡– ቀጣዩ ምርጫና ሀገራዊ ምክክሩ በአንድ ዓመት ውስጥ መካሄዳቸው የሚያጋጫቸው ምንም ነገር አይኖርም። ምክንያቱም እኛ የተጨመረልን የአንድ ዓመት ጊዜ እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ያለው ነው። ምርጫው ደግሞ በ2018 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የሚካሔድ ነው። ምርጫ ሀገሪቱን እየመራ ላለው መንግሥት ነው፤ ሀገራዊ ምክክር ግን ለሀገራዊ መንግሥት ነው። እኛ ምርጫ ቢኖርም መስመራችንን ይዘን እንቀጥላለን። ፍርድ ቤት ይቀጥላል። ፖሊስም ይቀጥላል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ስሙ እራሱ እንደሚጠቁመን ሀገራዊ ነው፤ ምክክሩ የብልፅግና ፓርቲ ወይም የኢዜማ አሊያም የኦነግ አይደለም። ፓርቲዎች እንደየዘመኑና እንደየሁኔታው የሚፈጠሩ እና ኢትዮጵያን የሚያሳድጓት ናቸው። ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም የምትኖር ናት። ከዚህ የተነሳ ሁሌም ወደፊት ለምትቀጥል ሀገር የየራሳቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ ናቸው። ስለዚህ በዚህ ብዥታ ሊፈጠርም አይገባም። ሀገራዊ ምክክር እና ምርጫው አንዱ ለሌላው እንቅፋት አይሆንም፤ በሳይንሱ መሠረት የሚያጋጫቸው ምንም ነገር የለም፡፡

እኛ የሕዝብ አጀንዳን ለመንግሥት ማቅረብ ሥራችን ነው፤ ለምሳሌ ከመሬት ባለቤትነት ጋር በተያያዘ፣ ከቅርጸ መንግሥት ጋር በተያያዘ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት፣ በአሁኑ ጊዜ ሶስት አራት መንግሥት የሚመስል ጉዳይን በተመለከተ፣ ሌሎችም ብዙ አጠያያቂ ጉዳይ የሆኑና ለሀገር ህልውና የሚያሰጉ ነገሮችን በተመለከተ የሕዝብ ድምጽ ምንድን ነው? የሚለውን ለመንግሥት ማቅረብ ነው። ምክንያቱም ይህ ከሕዝብ የተሰበሰበ አጀንዳ ስለሆነ ነው። ይህ አጀንዳ ደግሞ ውሳኔ እንዲያገኝ ማድረግ አለብን። የራሳችንን የመከታተያ ቅጽ ስላዘጋጀን መፈጸሙንም መከታተል አለብን።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሶስት ዓመታት በምትንቀሳቀሱበት ወቅት በዋናነት ድጋፍ ሲሰጣችሁ የነበረ አካል ማን ነው?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- ድጋፍ ሲሰጠን የነበረው የመጀመሪያውና ትልቁ ሕዝብ ነው፤ ጦርነት ሰለቸን፤ ከጦርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት አለብን በሚል ብዙዎች ሃሳባቸውን ሲሰነዝሩ ነበር። ሁሉም ከጦርነትና ግጭት ውስጥ መውጣትን አጥብቆ የሚፈልግ ነው፤ በመሆኑም ይህን ሀገራዊ ምክክር እየተጠባበቀ ነው። ይህን ስል ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ እንዲሁም ውጭ ሀገር ያለውም ሁሉ የሚመለከት ነው። ምክንያቱም ሁሉም ምክክር እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ቆይተዋል። ምክክሩን እንደሚያምኑበትም ጭምር ሲገልጹልን ሰንብተዋል፡፡

ሁለተኛው ድጋፍ ሲያደርግልን የነበረው መንግሥት ነው። መንግሥት ደግሞ እንደሚታወቀው በምርጫ የመጣ ነው። በመፈንቅለ መንግሥት ወይም ደግሞ ከጫካ ውስጥ የመጣ መንግሥት አይደለም። ከሕዝብ ውስጥ የወጣ፣ በሕዝብ የተመረጠ ሕዝባዊ መንግሥት ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የሚጥር ነው። የሚያዋጣኝ ስትራቴጂ፤ ከደኅንነትና ከመከላከያም በተጨማሪ በዋናነት በሀገሬ ውስጥ ያለውን መዋቅራዊ ችግሮችንና ግጭቶችን በመፍታት ሰላምን መገንባት ነው ብሎ የሚያምን ነው። ስለዚህም አዋጩ ሀገራዊ ምክክር ነው ብሎ በጀት መድቦና ቢሮ ሰጥቶ በማስቀጠል ላይ የሚገኝ ነው። ስለዚህ መንግሥት፣ አንዱ የሰላም ስትራቴጂ ነው ብሎ ስላመነበት ለአምስት ዓመታት በተሰጠው ኮንትራት ውስጥ የቤት ሥራውን የሠራው መንግሥት ነው።

ኮሚሽኑም ሕዝብን አድምጦ፣ አመካክሮ፣ ለዘላቂ ሰላም መሠረተ ድንጋይ እንዲጥል፤ ቢቻለው ደግሞ ችግሮቹን እንዲፈታና ወደፊትም እንዳይከሰቱ ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ለማስቀመጥ የሚያቋቋመው መንግሥት ነው፤ መንግሥት የሚፈልገው ይህ እንዲሆን ነው። ይህ አንዱ የመንግሥት ድጋፍ ነው። ሌላው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ነው። ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን የኢትዮጵያ ሰላም የራሷና የአካባቢዋ ሰላም ብቻ ሳይሆን የዓለምም ሰላም ጭምር ነው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰላም የሁሉም ሰላም ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዲፕሎማቶች ይህንን እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ይደግፋሉ፡፡

ከዚህም የተነሳ ባለፈው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ስለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሲናገሩ ነበር። ሌሎችም ልዑካን እንዲሁ መጥተው ስንነጋገር ነበር፤ ለምሳሌ ያህል ባለፈው የአይርላንድ የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡ ሲሆኑ፣ ወደ እኛ መጥተው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል። በተለይም ከተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ጋር  ተያይዞ በሀገራቸው ያጋጠማቸውን ችግር እንዴት አድርገው በምክክር መፍታት እንደቻሉና ወደ ሰላም እንደተሸጋገሩ ያላቸውን ልምድ አካፍለውናል። ስለዚህም የዓለም አቀፉ ትብብር አለ ለማለት እወዳለሁ፡፡

በዋናነት ማንም እጃችንን ሳይጠመዝዝ፤ ሀገራዊ ምክክሩን እናግዛለን የሚሉ የውጭ ሀገር አካላት ለዩ.ኤን.ዲ.ፒ ገንዘብ ይሰጣሉ፤ እኛ ደግሞ ከእነርሱ የሚያስፈልጉ ተሽከርካሪዎችን፣ በመንግሥት አማካይነት ተፈራርመን እንወስዳለን። ይህን የምለው ያለውን የዓለም አቀፉን ድጋፍ ለማሳየት ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሶስተኛውና ትልቁ ድጋፍ ነው ብዬ የማስበው ልክ ከሕዝብ የማይተናነሰው የሲቪል ማኅበራት ድጋፍ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የተቋቋሙት ሲቪል ማኅበራት እጅግ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ናቸው። እኛ ወደ ሕዝቡ ከመድረሳችን በፊት ቀደም ብለው በየአካባቢው ስለ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት ለሕዝቡ በመግለጽ ሕዝቡን ሲያዘጋጁ የቆዩ ናቸው፡፡

ሌሎቹ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። በርግጥ እንደጀመርን አካባቢ ይደግፉን የነበሩት ጥቂቶች ናቸው። እኛ ሳናስብ የሆነ ስህተት ፈጥረን ከሆነ እንኳ በመምከርና ከእኛ ጋር በመሆን አብረውን በመሥራት የሚያግዙን ናቸው። ሌላው ቀርቶ አካሄዳችሁ በዚህ ቢሆን በሚል የራሳቸውን ጽሑፍ ሁሉ የሰጡን የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደግሞ የእዚሁ ኮሚሽን የአማካሪ ኮሚቴው አባል ናቸው። በቅርቡ የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አዲስ ሲቀየር ከእርሳቸው ጋርም በቅርበት አብረን እየሠራን እንገኛለን። ምክንያቱም ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ፣ የሰላም ግንባታ፣ የሀገር ግንባታ እና የዜጋ ግንባታ ሂደትም ነው።

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የሃይማኖት ተቋማት ድጋፍ ያደረጉልን ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ስንንቀሳቀስ የምንጠቀመው የየዩኒቨርሲቲዎችን ካምፓስ ነው። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲ ማለት ትንሽዋ ኢትዮጵያ እንደ ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የመጀመሪያውን ስምምነት የተፈራረምነውም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ባለፈው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከታጣቂ ኃይሎች መካከል በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መርጠው ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ አባላት የራሳቸውን አጀንዳ ማስያዛቸው የሚታወስ ነው፤ በቀራችሁ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአማራ ክልል በትጥቅ ትግል ላይ ካሉት ጋር በመነጋገር ወደ ምክክሩ እንዲመጡ የታቀደ ነገር ይኖር ይሆን?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- በሚገባ! ስንሰራም ስናስብም የነበረው በተለያዩ መንገዶች ነው። አንዱ በኦሮሚያ ክልል በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩና ከመንግሥት ጋር አብሮ በሰላም ለመሥራት፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመታገል፣ እንዲሁም ለሰላም አስተዋጽኦ ለማድረግ የመጡ አሉ፤ በቀጣይም በተመሳሳይ በአማራ ክልል በቅርብ ጊዜ በክልል ደረጃ ሀገራዊ ምክክር ስለምናደርግ እዛው እነርሱም እንዲሳተፉ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ለክልሉ መንግሥትም እዛው በአካል ተገኝተን የተለመደውን ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈናል።

በአማራ ክልል በአራት ክላስተሮች ማለትም፤ በጎንደር፣ ባህር ዳር፣ በደብረ ብርሃንና በደሴ ከሕዝቡም ጋር ስንነጋገር ቆይተናል። በወቅቱ አንዱ ሲያነሱ የነበረው ጉዳይ ‹የተመለሱ ወገኖቻችንን አሳትፏቸው› የሚል ነበር፤ ይህ ቀጥታ የሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ ይህን ጥያቄ መመለስ ግድ ነው። እንዲሁ በጫካ ውስጥ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉትን ትጥቃቸውን ሳይፈቱ (ምክንያቱም ትጥቅ የማስፈታት ሥራ የመንግሥት ነው፤ እኛ ትጥቅ ይፍቱ የሚል ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥም) ስለዚህ ትጥቃቸውን እንደያዙ፤ ነገር ግን በውክልና ለመሳተፍ ወደ እኛ መላክ ይችላሉ። ይህንንም ሃሳብ በይፋ ውጭ ላሉ ሚዲያዎች አስተላልፈናል። ምክንያቱም ያለውን ችግር መፍታት የሚቻለው በመነጋገር ነው። ስለዚህ ይህን በትጋት ቀጥለናል፡፡

ሌላው በዲፕሎማቶችና በአምባሳደሮች አማካይነት የሚደረገው ጥረት አለ። ቀጥታ ስለሚያገኟቸው በተለይ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር እኛ ድረስ ጠርተናቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ለሀገራችን ሰላም መስፈን በመጣር ላይ እንገኛለን። አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም የተሟላ እንዲሆን የራሳቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ለእነርሱም ኢንቨስትመንትና ንግድ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ትልቅ ፋይዳ ስላለው ፈቃደኛ ሆነው እየተባበሩን ይገኛሉ።

ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩት ወደ ሰላማዊው ትግል መጥተው ከእኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተሳካ ሁኔታ ተደምድሟል። የአማራውም እንዲሁ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ሌሎቹም አሉና ወደፊት ይፋ የምናደርጋቸው ይሆናል። መቼም ቢሆን የሚያዋጣን ነገር ቢኖር ምክክር፣ ምክክር፣ ምክክር ነው። ሌላ ምንም አማራጭ የለንም።

አዲስ ዘመን፡- ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል ያለው ሰላም ጥሩ የሚባል ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ኮሚሽኑ በዚያ ክልል ያስበው ነገር ምንድን ነው?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- እሱን በተመለከተ ሁለት ሶስት ጊዜ ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንቱ ጋር ተገናኝተን ተነጋግረናል። እርሳቸው በአካልም እኛ ዘንድ መጥተው ተነጋግረናል። ከዚህ በተጨማሪ አሁን የፖለቲካ አመራሩንም ለመጥራት በእኛ በኩል ዝግጅቱ አለ። እኛ በምንችለው ሁሉ በዓለም አቀፍ አጋሮቻችን አማካይነት ይሁን በራሳችን የሃይማኖት መሪዎች አማካይነት ይሁን በማናቸውም በተገኘ መንገድ ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፡፡

ዳሩ ግን የፖለቲካ አመራሩ እና አስተዳደሩ አካባቢ፤ ሕዝቡ እንደሚያውቀው ያለመግባባት ነገር አለ። ይህ የአለመግባባቱ ሁኔታ በመፈጠሩ ሕዝቡን እራሱ ያስቆጣው እንደሆነም እየተደመጠ ነው። እኛም ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን። ሁኔታዎች ሲመቻቹ ደግሞ ሌሎቹ ዘንድ ያደረግነውን እዚያም ሄደን እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን፡- በቀራችሁ የአንድ ዓመት ጊዜ ዲያስፖራውን ለማሳተፍ እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ አለ?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችን ዘንድ እስካሁንም በተለያዩ መንገዶች እየደረስን ነበር። የመጀመሪያ እዚሁ የእነርሱን ተወካዮች በአካል ማግኘት ነበር። ባገኘናቸውም ጊዜ አብዛኞቹ ያሳዩን አቀባበል አዎንታዊ ነበር። በጣምም ደስተኞች ሆነው አግኝተናቸዋል። ዲያስፖራውን ያገኘንበት ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በያሉበት በበይነ መረብ አማካይነት ነው።

ለምሳሌ በተለያዩ አህጉራት ያሉ ወገኖቻችንን ለማግኘት በኢትዮጵያውያን ሰዓት አቆጣጠር ሲታይ እንደየአሉበት ሀገር አንዱ ዘንድ ምሽት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ቀን ሊሆን ይችላል። ይሁንና እኛ እንደየሀገሩ የሰዓት ሁኔታ በመጠበቅ ያለአንዳች ማመንታት በእኛ ሰዓት አቆጣጠር ውድቅትንም ቀትርንም ማለዳውንም ሆነ ምሽቱንም በመጠቀም ልናገኛቸው ተግተናል፡፡

አብዛኞቹም በርግጥም የኢትዮጵያን ሁኔታ መቀየር የሚያስችል መስመር ውስጥ ናችሁና በርቱ፤ እና የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉን ነበር። የሚቃወሙ ሰዎችም ሲሉ የነበረው እኛ ንግግሩን አንቃወም፤ አገዛዙንና ሥርዓቱን ነው እንጂ በሚል ስለ ምክክሩ ያላቸውን ስሜት በግልጽ ተናግረዋል። እዚህ ያሉት እንደ ሌሎቹ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሁሉ የራሳቸውን አጀንዳ ሰጥተዋል።

አሁን አንዱ የሚቀረን የመጨረሻው ሂደት ቢኖር ወደሚገኙበት ሀገር ሄደን የእነርሱን አጀንዳ መሰብሰብና ከእነርሱም ደግሞ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉትን ማስመረጥ ነው።

ዲስ ዘመን፡- የተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቅቆ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል፤ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የማጠናቀቁ ነገር እውን ይሆናል? ከዚህ አንጻር በተጨማሪ ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን የቻሉ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ካለ ቢገልጹልን?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡– የሌሎች ሀገሮች ልምድ የሚያሳየው በተለይ እንግሊዝ ሀገር በነበርኩበት ጊዜ መጀመሪያ ያቀናሁት ወደአይርላንድ ነውና የምክክር ሂደት ምን እንደሚመስልና ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ማጤን ችያለሁ። የሚፈልገውም ጊዜ በጣም ረጅም ነው። ረጅም ሲባል ደግሞ እንደ እኛ ሀገር በሶስትና አራት ዓመታት የሚያልቅ ሳይሆን፣ ከአስር ዓመትም በላይ የሚወስድ ነው።

በተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካን ለማየት ችያለሁ። የተመራው በሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ነው። ማዕከላቸው ያለው እኔ ሶስተኛ ዲግሪዬን የሠራሁበት ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፣ በተለይ ከሰላም ጋር በተያያዘ እንማር የነበርን ተማሪዎች እርሳቸውን በዚያን ጊዜ ማግኘት እንችል ነበር። እርሳቸውም በጊዜው ሲያካፍሉን የነበረው፤ በጥቁርና በነጭ መካከል የነበረውን ግድግዳ እንዴት አድርገው አፍረስው ወደ ሰላማዊ መንገድ ማምጣት እንደቻሉ ነበር። ይህን መረጃ ይሰጡን የነበረው ከኢስያ፣ ላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና ከተለያዩ ቦታዎች ለመጣን ሰላም ላይ አተኩረን የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለምንማር ተማሪዎች ነበር።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አሁን የተቀመጠው ጊዜ በጥቅሉ አራት ዓመት ይሁን እንጂ ሥራችን መሠረት መጣል ነው። ሶስቱ ዓላማዎች መዘንጋት የለባቸውም። የመጀመሪያው ዓላማ ሀገራዊ መግባባትን ማምጣት፣ ሁለተኛው ዓላማ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጠንካራ እምነት እንዲፈጠር ማድረግ በተመሳሳይ በሕዝብና ሕዝብ መካከልም እምነት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ሶስተኛውና በጣም ወሳኙ ኢትዮጵያ ውስጥ ምክክርን ባሕል ማድረግ ነው። ይህን ባሕል ለማምጣት ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ይህ ባሕል እንዲመጣ አስር ወይም ሃምሳ ዓመት የሚጠበቅ ሳይሆን በራሱ ሂደት ነው፤ ሁሌም የሚቀጥል ነው፡፡

የምክክርን ባሕልን ማምጣት ማለት አመለካከታችንን፣ ባህሪያችንን መቀየር ማለት ነው። ሁልጊዜ መጥፎ ቃላትን በመለዋወጥ፣ ጥላቻን በመዝራት፣ እርስ በእርሰ በመገፋፋት፣ በዘርና በሃይማኖት መደብ በመከፋፈል ወዳልተገባ ጉዳይ ከመሄድ ይልቅ ችግራችንን በመግባባት መፍታት ያስፈልጋል። እርስ በእርስ በመነጋገር እንጂ በመገዳደል መፍትሔ ስለማይመጣ ምክክርን ባሕል ማድረግ ወሳኝ ነው። ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜን የሚፈጅ ነው።

ሌላው የኮሎምቢያን ልምድ ለመውሰድ በቅርቡ በእዚያ ነበርን። ልምዱ የሚያሳየን ረጅም ጊዜ መውሰዱ ነው። በወቅቱ ባለሥልጣናቱን ባነጋገርናቸው ጊዜ ቢቻላቸው ወደ ሀገራችን መጥተው ልምዳቸውን በትጥቅ ትግል ላይ ላሉት ወገኖቻችን እንዲያካፍሉ ጠይቀናቸው ነበር፤ ያገኘነውም ምላሽ አዎንታዊ ነው።

ስለዚህ በተለያዩ ሀገራት ያለው ልምድ እንደሚያሳየው በምክክር ጉዳይ፤ ጊዜ ማራዘም በጣም የተለመደ መሆኑ ነው፤ እንዲያውም የሌሎች ሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየው አንዴ ሳይሆን ሁለት ሶስት አራት ጊዜ ያራዘሙበት ሁኔታ መኖሩ ነው። የሊባኖሱን መጥቀስ ይቻላል። ሌላው ደግሞ የመንን ብንወስድ የሚታወሰው እኤአ የ2011ዱን ነው፤ ብዙ ሰው አያስታውሰውም እንጂ የጀመሩት እኤአ በ1983 ነው። በዚህ መሃል ስንቴ እንደተራዘመ ማሰብ ይቻላል። ያውም የሚዘወረው በውጭ አካል ነው።

የእኛ ግን ባለቤቱ እራሱ ሕዝቡ ነው። 99 በመቶ የሚሆነውም ገንዘብ የሕዝብ ነው። ከውጭ የሚሰጠን ገንዘብ ቢኖር እንኳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰጥ እንጂ ለእኛ አይደለም። ስለዚህ ለስኬታማነቱ ምንም የሚያጠራጥረን ነገር የለም። በጥቅሉ የውጭ ልምድ በምክክር ጉዳይ ላይ የሚያሳየን በተለያየ ጊዜያት የተራዘሙ፣ በጣም አስጨናቂ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፉ መሆናቸውን ነው። ዋናውና ትልቁ ግብ ግን ዓላማውን ማሳካት መቻል ነው። የምክክሩ ዋና ዓላማ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊ የሚለይበት ሳይሆን ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ነው። በዚህች ሀገር ሰላም ባሕል ሆኖ እንዲዘልቅ እንፈልጋለን፤ እኛ ሥራችን ዘላቂ ሀገር የምንገነባበትንና በተቻለ መጠን ስጋት የምንቀንስበትን መሠረት መጣል ነው። ስለዚህም መራዘሙ ግድ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ፋይዳው እስከየት ድረስ ነው?

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡- በመሠረቱ የሰላም ፍልስፍና የሚለው ነገር ቢኖር ‹‹ሰላም አይከፋፈልም›› ነው። ሰላም አይከፋፈልም ሲባል ውስጥ ሰላም ከሌለ ከምናገረው ቃላት የተነሳ ለምሳሌ አንቺን ላስቀይም እችላለሁ። ስለዚህ የእኔ ሰላም የአንቺም ጭምር ነው ማለት ነው። የጎረቤት ሰላም የእኔም ጭምር ነው። አንድ አስተማሪ በቤቱ ሰላም የሚያጣ ከሆነ ለማስተማር ክፍል ከገባ ከተማሪዎችም ጭምር ይጣላል። ሰላም በጣም የተሳሰረ ነው፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለሱማሊያም፣ ለሱዳንም ለኤርትራም ሰላም ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ሱዳናውያን ሰላም ከማጣታቸው የተነሳ ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ላይ ሲሆኑ፣ በተለይም ጎንደር አካባቢ በብዛት ይታያሉ። ይህን ስናጤን የፍልሰተኛው ብቻ መምጣት ሳይሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርም፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም አብሮ የሚመጣ ይሆናል። ይህ የሚያሳየን አንዱ ዘንድ ሰላም ሲታጣ ሌላውንም ጭምር እንዴት ሰላም እንደሚነሳ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም የአካባቢው ሰላም ማለት ነው። ለምሳሌ በተጨባጭ ሲገለጽ ኢትዮጵያ ግድብ አላት፤ ከግድቡ የምታመነጨውን ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ያስፈልጋቸዋል። ለጅቡቲ መብራቱ ቀርቶ ከኢትዮጵያ ውሃ ለማግኘት የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ያስፈልጋቸዋል። የኢትዮጵያ ሰላም ከኤርትራ ጋርም ሆነ ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ ለሌላው ሀገር ጭምር አስፈላጊ ነው። ስለዚህ የእገሌ ሰላም የእገሊት ሰላም የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም ሰላም አይከፋፈለም። የአንዱ ሰላም የሌላው ሰላም ነው። በጥቅሉ የኢትዮጵያ ሰላም የጎረቤት ሀገራት ሰላም ነው። የአህጉርና የዓለም ሰላም ጭምር ነውና ለሰላማችን ተግተን እንሥራ። የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም ስለሰላም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።

ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You