የስፖርት መድረኮች ለማህበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ፣ ለፖለቲካዊ፣ ለባህላዊና ተፈጥሯዊ ልማት አወንታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው ተደጋግሞ ይነሳል። ከነዚህም ጠቀሜታዎቹ ውስጥ የምጣኔ ሃብት እድገት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ ጤናማና ታታሪ ትውልድን ማፍራት፣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መጨመር፣ የስራ እድልን መፍጠርና የከተሞች መስፋፋት በዋናነት ሲጠቀሱ ስፖርት ለሰላም ያለው ፋይዳም በጉልህ የሚጠቀስ እውነታ ነው። ይህንንም በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ለመመልከት ችለናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች ይስተዋላሉ። ከዚህም ጎን ለጎን በተለይም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ በየስቴድየሞቹ የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር አሳሳቢነቱ ቀጥሏል። ስፖርት የሰላም ማስፈኛ መድረክነቱ ተዘንግቶም የሁከትና የግጭት መንስዔ ሲሆን በተደጋጋሚ ተስተውሏል። በየስቴድየሞቻችን በሚካሄዱ ጨዋታዎችም የስፖርት ትልቅ አላማ የሆነው «ሰላም» ተግባራዊ ከመሆን ይልቅ በተቃራኒው ሲመነዘር እያየን ነው።
የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ግን ዓመታዊ የክለቦች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦች «ስፖርት ለሰላም» በሚል መርህ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንዲያካሂዱ በማድረግ ከወዲሁ የውድድር አውድማዎች ሰላማዊ አየር እንዲተነፍሱ ለማስቻል እየሰራ እንደሚገኝ አሳውቋል።
ስድስተኛው አገር አቀፍ የቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከታህሳስ 15 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በትንሿ ሁለገብ ስፖርት ማዕከል የሚካሄደው የአቋም መለኪያ ውድድር ሁለት አላማዎችን የሰነቀ ነው። የመጀመሪያው ስፖርት የሰላም መሳሪያ መሆኑን በማሳየት ክለቦች ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት ነው። በሌላ በኩል ክለቦች ወደ ዋናው ውድድር ከመግባታቸው አስቀድመው ያሉበትን አቋም የሚመዝኑበት ነው።
ይህን መሰረት በማድረግ ውድድሩ ከትናንት በስቲያ ሲጀመር ሁለት ጨዋታዎች በወንዶች ተከናውነዋል። ሐዋሳ ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያካሄዱ ክለቦች ሲሆኑ ሐዋሳ ከተማ ስልሳ ስድስት ለሃያ ዘጠኝ በሆነ ቅርጫት ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቋል። በተመሳሳይ ሁለተኛውን ጨዋታ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ክለብ ፓንተርስ ክለብ ላይ ሃያ ቅርጫት በማስቆጠር አንድም ሳይቆጠርበት ጨዋታውን ደምድሟል።
ሁለቱ ተሸናፊዎች ማለትም ፓንተርስና የካ ክፍለ ከተማ ዛሬ እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን፤ በተመሳሳይ አሸናፊዎቹ ሐዋሳ ከተማና ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ውድድሩ ሲጀመር በሴቶች ጨዋታቸውን ያደረጉት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሲሆኑ የአካዳሚው ታዳጊዎች ሰላሳ አምስት ለሃያ ሰባት በሆነ ቅርጫት ማሸነፍ ችለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
ቦጋለ አበበ