የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር
የመጀመሪያ ዲግሬያቸውን ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ሳይንስ ዘርፍ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአግሮኖሚ የትምህርት መስክ ሰርተዋል፤ የዶክትሬት (ሶስተኛ ) ዲግሪያቸውን ደግሞ በጄኔቲክስና እጽዋት ማዳቀል የትምህርት መስክ አግኝተዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ለአራት አመታት ሰርተዋል፡፡ ከዚያም ወደትምህርት ቤት ቢመለሱም እንደገና ወደ ተቋሙ በመምጣት ለሁለት ዓመት አገልግለዋል።
የዓለም ባንክን ፕሮጀክት በማስተባበር እንዲሁም የኦክስፋም አሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆንም ሰርተዋል። ለዩኤን ዴሳ ለአንድ ዓመት በተመድ የዘላቂ የልማት ግብ /ሰስቴኔብል ዲቨሎፕመንት ጎል /አማካሪ በመሆንም አገልግለዋል። ከዚህ ሁሉ በኋላ የስራውን አለም ‘ሀ’ ብለው በተቀላቀሉበት የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዳይሬክተርነት እያገለገሉ ነው፤ የዛሬው እንግዳችን ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ። እኛም በኢንስቲትዩቱ የስራ እንቅስቃሴና የወደፊት እቅዶች ዙሪያ ከእሳቸው ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፦ ወደ ምርምር ተቋሙ በዳይሬክተርነት ሲመጡ ቀድሞ ከሚያውቁት በምን ያህል ተሻሽሎ እንዲሁም ምን ዓይነት ጉድለቶችን ይዞ አገኙት?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ወደ ኢንስቲትዩቱ ስመጣ በፊት የነበረው የአሰራር ስርዓት፣ የሰዎች የስራ ጥንካሬ፣ የምርምር ውጤቶች ፍጥነትና ተደራሽነት በተለይም ከመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ (ቢፒአር) ጋር በተያያዘ ተበላሽቶ ነው ያገኘሁት።
በሌላ በኩልም የሚሰራውም የማይሰራውም ተከማችቶ ነበር፤ በዚህ መካከል ደግሞ የሚሰሩትን ለማበረታታት የማይሰሩትን ደግሞ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት ጠፍቶ ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙን ወደ ቀድሞ ማንነቱ ለመመለስ ያከናወኑት ስራ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የምርምር ስርዓት ለመገንባትና አቅም ለመፍጠር፣ የመስሪያ ቤቱን ገጽታ ለመገንባት ፣በወቅቱ በዋናው መስሪያ ቤት ላይ ተከማችቶ የነበረውን የሰው ሀይል ወደ ምርምር ማዕከላት እንዲመለሱ ለማድረግ፣ የሚሰራና የማይሰራ ሰራተኛ ሊለይ የሚችል ስርዓት ለመዘርጋት፣ በኢንስቲትዩቱ የማዕከል፣ የሴክተር ዳይሬክተርና የፕሮግራም አስተባባሪዎች በውድድር እንዲመደቡ ለማድረግና ይህ አሰራርም ስርዓት ሆኖ እንዲዘልቅ ተሰርቷል፤በዚህም ውጤት ተገኝቷል።
ሌላው በኢንስቲትዩቱ በሶስተኛ ዲግሪ ደረጃ ብዙ ሰው ስለሌለ 70 በመቶ የሚሆነው የሰው ሀይል ስራ ላይ እንዲቆይ ፣30 በመቶው ደግሞ እንዲማር በማድረግ የእውቀት አቅማችንን በመገንባት የምርምር ውጤቶቻችን ፈጣንና ወቅቱን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፦ የምርምር ተቋሙ በዚህ ደረጃ ከተደራጀና አቅም ባለው የሰው ሀይል እንዲኖረው ከተደረገ የምርምር ስራዎቹ ለምን በትንንሽ ማሳዎች ላይ ተወስነው ቆዩ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ቀደም ሲል በትንንሽ መሬት ላይ የተሻሻሉ ዘሮችን በማስተዋወቅ ስንሰራ ቆይተናል። አሁን 10 ሄክታርና ከዛ በላይ በሆነ መሬት እየሰራን ነው፤ ይህ ደግሞ ምርቱን ለሚያየው አርሶ አደር ወይም የልማት ሰራተኛ ሰፊ የሆነ ቦታ ትልቅ ለውጥ ምርቱም ሲለካ ብዙ ስለሚሆን ለማመንም አይከብድም፤ አሁን ግን በትንንሽ መሬቶች ላይ የምንሰራው ተቀይሯል።
አዲስ ዘመን፦ ግብርና ምርምርን ከውጭ ሆነን ስናየው ብቻውን የቆመና ከሌሎች ለምሳሌ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም መሰል ተቋማት ጋር አብሮ የመስራት ነገር ብዙም የማይታይበት ነው፤ ይህ ለምን ሆነ ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ አሁን ከግብርና ማሰልጠኛዎች፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከግብርና ኤክስቴንሽንና ግብይት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ቢያቀርቡልኝ ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ለምሳሌ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ወደ ተቋሙ በመምጣት የምርምር ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ ፤ይህ ደግም በግብርና ሙያ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት ያግዛል። የምርምር ባለሙያዎች ደግሞ የተግባር አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ወደ ተቋማቱ እየሄዱ እንዲያስተምሩ በጋራ የትብብር ስምምነት ተፈራርመን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ዋናው የግብርና ተዋናዮች ክልሎች ናቸውና እነሱ እናንተን በመደገፍ እናንተም ከእነሱ ጋር በመቀናጀት የምርምር ውጤቶቻችሁ በትክክል አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ የምታደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ከክልሎች ጋር መጣመራችን የበለጠ ተደራሽ ያደርገናል፤ ከሁሉም ክልልች ጋር እኛ ምን እናግዛለን? ከእነሱ ምን ይጠበቃል? የሚለውን ውል ተፈራርመን እየሰራንና የምርምር ውጤቶችም ለአርብቶ አደሩና ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን ተደራሽነት እያሰፋን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ውጤታማነቱን እንዴት ይለኩታል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ውጤቱ በጣም ትልቅ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እኛ ገንዘብ ይኖረንና በመስክ ላይ ሰው አይኖረንም፤ እነሱ ደግሞ ሰው አላቸው፤ገንዘብ ግን የላቸውም፤ ይህንን እያሰባጠርን አብረን መስራታችን ጥሩ ውጤት አምጥቷል። በሌላ በኩልም በዞን፣ በቀበሌና በወረዳ ያሉትን የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በመጨመርና በማስተሳሰር አምና በ80 ወረዳዎች ፣ ዘንድሮ ደግሞ 200 ወረዳዎች ላይ ስራዎችን አስፍተናል።
አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አኳያ የምርምር ውጤቶቹ ተደራሽ ናቸው ብሎ ለማለት ይቻላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ተደራሽነትን በተመለከተ የዝናብ እጥረት መመልከት ይቻላል፤ መካከለኛ ዝናብና ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙ የአገሪቱ ክፍሎችን በመለየት በምን መልኩ ነው ፍትሀዊ የሆነ ተደራሽነት ሊኖረን የሚገባው በሚለው ላይ ሰርተናል፤ በተለይም በዝናብ አጠር አካባቢዎች ላይ መስራቱ አዋጭ መሆኑን ከልምዳችን ስለምናየው ለእነሱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው።
ሆኖም አሁን ያለው የዘር ስርጭት ተደራሽነት አነስተኛ ነው፤ ይህንንም እንደ አገር ስትራቴጂ ነድፈን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እየሰራን ሲሆን፣ የምርምር ስርዓታችንን እያጠናከርን የሰው ሃይላችንን እየገነባን የምርምር ውጤቶቻችንን ደግሞ በአርሶ አደሩ፣በአርብቶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ህይወት ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ሰንሰለቱን ጠብቀን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ የምርምር ውጤቶቻችሁ ተደራሽ እንዲሆኑ መስራታችሁ ጥሩ ነው፤ነገር ግን 50 ዓመት አልፎታል የሚባለውን የእንሰት አመንምን በሽታ እንኳን ለማጥፋት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በእንሰት አመንምን ላይ በምርምር የተያዙ ውጤቶች አሉ፤ ነገር ግን ተሰራጭተው ችግሩን በዘላቂነት ፈትተዋል ብዬ አላምንም፤ በሽታው ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ከመሆኑም በላይ ተላላፊ ነው። መፍትሔው ደግሞ በንጹህ ዘር (ችግኝ)መተካት ብቻ ነው። ለዚህም የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ከበሽታው ነጻ የሆነ የማባዣ ስርዓት ፈጥሮ ስራውም በላብራቶሪ ደረጃ ጨርሶ ችግኝ እያባዛ ነው ። ይህ የላብራቶሪ ውጤት በበሽታው ለተጠቁት አካባቢዎች ሁሉ ተደራሽ ይሆናል ወይ ? በቀጣይስ ምን ማድረግ አለበት ? የሚለው ገና ስራ ይፈልጋል።
ከዚያ ውጪ ግን ተክሉ እንደ በቆሎ፣ ማሽላ ወይም ሌሎች ምርቶች የሚዳቀል ወይንም ወዲያው በሚወሰድ እርምጃ የሚሻሻል አይደለም፤ ረጅም ጊዜ ይፈልጋል። በኬሚካል መከላከሉም ከሰው ጤና አንጻር ችግር ሊፈጥር ይችላል።
ሌላው እርምጃውን በቶሎ ላለመውሰዳችን ምክንያቱ የማባዣ ኬሚካሉ በአገር ውስጥ አለመኖሩና ከውጭ አገር የመግዛት ፍቃድ ቶሎ ካለማግኘት ጋር የተያያዘ ነው። ከዚያ ውጪ ግን የዛሬ ስድስት ወር ወይም ዓመት ላይ መፍትሔ ይገኛል የሚል እምነት የለኝም። መፍትሔው ቢገኝ እንኳ ተክሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ለምግብነት አይደርስም ።
አዲስ ዘመን፦ የተቋሙን ዓይነት ስራ ከሚሰሩ እንደ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት አይነት ተቋማት ጋር ስምምነት የላችሁም ፤ አብሮ መስራት ላይ ደካማ ናችሁ ይባላልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ አንዱ ቅደመ አደረጃጀቱን አበላሸው ያልኩት እንዲህ አይነቱ ጉዳይ ነው። ቀድሞ ብዝሀ ህይወት፣ ምርምር ፣ምርጥ ዘር አንድ ላይ ነበሩ፤ አሁን ቴክኖሎጂውን የሚያመነጨው አካል አንድ ቦታ፤ የሚያባዛው ሌላ ቦታ፤ ለቴክኖሎጂው እንደ ግብዓት የሚቆጠሩ ነገሮችን የሚያቀርበው አካልም እንደዛው ተበትኖ ነው ያለው ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ትስስሩን አጠፋው እና ስራው የተበታተነ ተቋማቱ የማይናበቡ ሆኑ ።
ወደፊትም የአወቃቀር ለውጥ ካልመጣ በቀር ወደቀድሞው አሰራር መግባት ያስቸግራል። ምክንያቱም እዚህ የሚወጣው አዳዲስና ዲቃላ ዝርያ ምርጥ ዘር ውስጥ ገብቶ እንዲባዛ ለማድረግ አሁን ሁለት መስሪያ ቤት ስለሆኑ ስራው በሰዎች ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሆኗል። ወደፊትም ይህ ሁኔታ ካልተስተካከለ በጣም ያስቸግራል ።
አዲስ ዘመን፦ በተለይ ተቋሙ ከሚመደብለት ገንዘብ፣ ካለው ዓለም አቀፍ ድጋፍ አንጻር የሚሰራው ስራ ምናልባትም ተፈጥሯዊ የሆኑትን እጽዋት ለማልማት ቢውል የተሻለ ይሆን ነበር የሚሉ አሉና በዚህ ላይ የእርስዎ ሀሳብ ምንድን ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የተሻለ ለውጥ አይመጣም፤ ለምንድን ነው የማይመጣው መሰለሽ የህዝብ ቁጥር ትንሽ በነበረበት ጊዜ ጤናማና ተፈጥሯዊ ምግብን ከጫካ በመሰብሰብ መመገብ ይቻል ነበር፤ የህዝብ ቁጥሩ እያሻቀበ ሲሄድ ግን በተፈጥሮ የሚገኘው ብቻ ሰዎችን መደገፍ አልቻለም። ስለዚህ ሰዎች ምርታማ የሆኑትን እያመጡ በየአካባቢያቸው እንዲላመዱ ማድረግ ጀመሩ፤ ይህም ችግሩን መፍታት ሲያቅተው እነዚያኑ ሰብሎች ምርታማነታቸውን መጨመር ላይ ሰሩ ፤ይህም አልሆን ሲል ማዳቀል ጀመሩ ፤ አሁን የደረስንበት ደግሞ በጄኔቲክ ኢንጂነሪንግ የሚፈለገውን ሰብል ከአንዱ ወስዶ ወደሌላ የሚደረግበት ደረጃ ነው። ይህንን ሁሉ ተጽዕኖ ያመጣው የህዝብ ቁጥር መጨመርና የአየር ንብረት ለውጥ ነው። በመሆኑም በዚህ መልኩ እያሻሻልንና ምርታማነቱን እየጨመርን ካልሄድን ያለንን ሰው አብልተን የምግብ ዋስትናውን አረጋግጠን መሄድ በጣም ይከብደናል ።
ተፈጥሯዊው የሚበቃ ቢሆን እኮ ይህ ሁሉ ገንዘብ አይፈስም ነበር ፤ በሌላ በኩል ያሉትን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንንከባከባቸው ቢባልም እንኳን ምርታማነታቸው በጣም አናሳ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ምናልባት ተፈጥሯዊዎቹ ምርታማነታቸው አናሳ ሊሆን ይችላል ፤ነገር ግን የጤና ጥቅማቸው ደግሞ ከፍተኛ ከመሆኑ አኳያ ይህንን አቻችሎ መሄድስ እንዴት ነው የሚቻለው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በዚህ የማሻሻል ሂደት ውስጥ የምናጣቸው ነገሮች አሉ፤ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ሰብሎች ምርታማነታቸውን ፈልገን ባጠበብናቸው መጠን በውስጣቸው ልናገኝ የሚገባንን ጥቅም እናጣለን ይላሉ፤ አዎ ላናገኝ እንችላለን።
ለምሳሌ ተፈጥሯዊው (ስፒሻሊቲ) ቡና ተሻሽሎ ከቀረበው በዓለም ላይ ዋጋው እኩል አይደለም። ተፈጥሯዊው በጣም ውድ ነው። ሌላውም እንደዛው ነው። ለምሳሌ ቅቤ መግዛት የሚፈልግ ሰው ገጠር ወርዶ ብዙ ወጪ አውጥቶ ከምንጩ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ካልተደረገበት ከብት የሚያገኘውና በከተሞች አካባቢ የሚሸጠው የይዘትም የጥራትም እንዲሁም ከተመገብን በኋላ የምናገኘው ጥቅምም የተለያየ ነው። ይህ እንግዲህ ምናልባት የገንዘብ አቅምን ይጠይቃል። ነገር ግን አሁን ያለውን ህዝብ መግቦ ለማስቀጠል በማዳቀል ማሻሻል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።
አዲስ ዘመን፦እዚህ ላይ ሰዎች መከራከሪያ ብለው የሚያነሱት እኛ ብዙ ምርት ይሰጡናል እያልን እያዳቀልን የምንጠቀማቸው ነገሮች ሌላው ዓለም በጤና ላይ ችግር ስላስከተለ የተተው ናቸው፤ እኛስ ቀጣይ እጣ ፈንታችን ምንድን ነው ይላሉ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በመዳቀላቸው የሚመጣ የጤና እንከን የለም። የጤና ችግር የሚመጣው ሌሎች ግብዓቶች ጥቅም ላይ ውለው ወደ ዘሩ ሲሄዱ ነው። ይህም ቢሆን ግን በሳይንስ የተረጋገጠ ነገር የለውም።
እኛ ዲቃላ ከምንላቸው ሰብሎችና እንስሳት ሰዎች ጄኔቲክ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም የሚሉት ሌላ ነው። ጄኔቲክ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም የሚባለው የአንድ እንስሳ ወይም ተክል ዘረመል ወደሌላው ሲዛወር ነው፤ ይህ ምናልባትም ለጤናችን ፣ለስብዕናችን ፣ ለባህላችን ጥሩ አይደለም በማለት ሰዎች ክርክር ያነሱበታል ፤ነገር ግን ጥሩም ነው መጥፎም ነው ለማለት በሳይንስ የተረጋገጠ ውጤት የለም፤ በዚህ የተነሳም ይህን በፍራቻ የማይመገቡ ሰዎች አሉ የሚመገቡም አሉ። በዚህ መልክ የተዳቀለው ሰብል ለጤና ችግር አለው ብሎ በመረጃ ደረጃ ያበቃ የለም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ሰዎች ሊናገሩ የሚችሉት ለተባይ ማጥፊያ የሚረጩ ኬሚካሎች ተጽዕኖ ሊኖራቸው ይችላል የሚል ነው፤ ያ ሊኖረው ይችላል፤ የተጽዕኖው ደረጃ ግን ሰውን ሊያሳምምና ሊገድል ይችላል ወይ? የሚለውም በተጨባጭ የተረጋገጠ አይደለም። ግን ውሸት ነው ለማለትም መረጃ የለኝም።
ብንችል ለጤናችን በተፈጥሮ የሚገኙ ምርቶችን ብቻ ብንመገብ ጥሩ ነው፤ ግን ከዚያ በተቃራኒው ያለ ነገር ስንጠቀም አደጋ ሊያስከትል ይችላል፤ነገር ግን አደጋውን እየወሰድን መኖር አልያም አደጋውን ፈርተን መሞት ነው አማራጩ ።
አዲስ ዘመን፦ የምርምር ተቋሙ እስከ አሁን ስራዎቹ ምን ያህል ውጤታማ ነኝ ይላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በምርምር ስራችን በጣም ውጤታማ የሆንባቸው የአገዳና የብዕር ሰብሎች ናቸው። በቆሎን ብትመለከቺ ከ20 ዓመት በፊት የነበረው ምርታማነት አሁን በእጥፍ አድጓል።ይህ የሆነው የማዳቀል ስራው ከፍተኛ ውጤት ስላመጣ ነው። አሁን በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ይገኛል። ስንዴም ማሽላም ተመሳሳይ ናቸው።
በጣም ተሰርቶበት ግን ውጤት ያላመጣው ቡና ነው። ውጤታማ ያልሆነው የማዳቀል ስራው አንሶ ሳይሆን የተዳቀለውን ቡና ወስዶ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የማድረግ አቅማችን አነስተኛ በመሆኑ ነው። ምን ለማለት ፈልጌ ነው አንድ አርሶ አደር አንድ ሄክታር ቡና ቢኖረው ለበርካታ ዓመት ያንኑ እያፈራረቀ በመትከል ይጠቀምበታል ፤ ሆኖም እነዚህን አዳዲስና ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆነ ዝርያዎችን ወስዶ እንዳይጠቀም ያለችው መሬት ትንሽ ስለሆነች እሱን አንስቶ ሌላ አዲስ ቡና ቢተክል ለሶሰት ዓመት የሚበላው የለውም። ሆኖም ሰፋፊ እርሻ ላላቸው አንድ ሁለት ሄክታር እየተባለ ማዳረስ ይቻላል ፤ነገር ግን ህይወታቸው እዚያ ላይ ለሆነ ይህንን ማድረግ ይከብዳል። ከዚህ አንጻር በአገር ደረጃ ምርታማነቱ ሲታይ እንደሚፈለገው ሊሄድ አልቻለም።
ለዚህ ችግር መፍትሔ ቢሆን ብለን እየተነጋገርን ያለነው ልክ በሌሎች ቦታዎች እንደሚደረገው አርሶ አደሮቹን ለተወሰነ ጊዜ በሴፍቲኔት ፕሮግራም በማቀፍ ወደተሻሻሉት ዝርያዎች ማስገባት ነው።
አዲስ ዘመን፦ የእኛ ብቻ የሆኑ የሰብል ዝርያዎች አሉን ፤ ልክ እንደ ጤፍ፣ ቡናና ሌሎችም የእኛነታቸው እንዳይጠፋና ወጥተው እንዳይቀሩ በተለይም በምርምር ወቅት የሚደረገው ጥንቃቄ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ እስከ አሁን ያደረግነው ጥንቃቄ አጥጋቢ አይደለም፤ የህግ ማዕቀፍ ማውጣት፣መከልከልና ሌሎችም ብዙም አያድኑንም ። እኔ መደረግ አለበት ብዬ የማምነው ያሉንን አገር በቀል የሰብል ዝርያዎች በሙሉ ልክ ለሰው ልጅ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት እንደሚሰጠው ሁሉ መዝግቦና ማንነታቸውን የሚገልጽ መለያ ማስቀመጥ ነው ።ይህ ከሆነ ሌላ አገር ቢሄዱ በተሰጣቸው መለያ ተከራክረን ማስመለስ እንችላለን። አሁን ግን ያንን ማድረግ ስላልቻልን ሰብል ቢወጣም መከራከሪያ የለንም።
እስከ አሁን ጤፍ እና ቡና ወጥተዋል ፤ባሉበት አገር ላይ የኛ ናቸው ብንል ምን ማስረጃ አላችሁ ስለሚባል ማስመለስ አልተቻለም። ስለዚህ ወደፊትም ለምርቶቻችን መታወቂያ ማዘጋጀት የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ የእድሜውን ያህል አገርን ሊቀይር ግብርናውን ሊያዘምን ህዝቡን በምግብ እህል ራሱን የሚያስችል የምርምር ስራ አልሰራም፤ እንዳውም የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆኗል የሚሉ አሉና በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ምርምር በባህሪው የረጅም ዓመት የስራ ውጤት ነው፤ ዛሬ ተሰርቶ ለነገ ውጤቱ አይታይም። ሰዎች አንድን ነገር በተለያየ መንገድ ይመዝናሉ፤ በእኔ ሚዛን ተቋሙ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ ይህም የሚታወቀው ወደኋላ ሄደን የት ነበርን? አሁን የት ደርሰናል? የሚለውን በማየት ነው።
ባለን የእርሻ መሬት ላይ ምርታማነታችን የጨመረው በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የስራ ውጤቶች ነው። ለምሳሌ እኔ ስራ ስጀምር በቆሎ በሄክታር 15 ኩንታል ነበር የምናገኘው ፤አሁን 40 ኩንታል እያገኘን ነው፤ ይህ በምርምር ስራ የመጣ ውጤት ነው።
የግለሰብ ተጠቃሚነት ለተባለው ሰዎች ጥቅምን ምናልባት ከመማር ጋር አገናኝተውት ከሆነ ባለሙያዎቹ በየጊዜው ተምረው ራሳቸውን መለወጥ ካልቻሉ ውጤታማ አይሆኑም፤ ለዚህ ሲባል ኢንስቲትዩቱ ሰዎችን ያስተምራል፤ ከተማሩ በኋላ ግን የተሻለ ነገር ፈልገው ወደተለያዩ ዓለም አቀፍና አጉራዊ ድርጅቶች ይሄዳሉ። ይህም ተፈጥሯዊ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም ። ከዚህ አንጻር ካልሆነ ግብርና ምርምር በመስራቱ ሀብታም የሆነ ተመራማሪ የለም።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ግብርና ካለበት ከፍ እንዲል እርስዎ እንደ ባለሙያ ምን ይስፈልጋል ይላሉ?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ ግብርናችን ላይ ኢንቨስት አድርገን ከፍተኛ ምርት ለማግኘት የሚያስችል አቅም የለንም። በመንግስት በኩልም ገፍቶ ኢንቨስት አድርጎ ለውጥ ለማምጣት ገንዘቡም ድፍረቱም የለም። በመሆኑም መንግስትም ማድረግ የሚገባውን ያህል ቢያደርግ ሰውም ጠንካራ ሰራተኛ ቢሆን ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
በሌላ በኩልም ግብርና እንደ ቢዝነስ ካልታየ የአርሶ አደሩን አእምሮ ለውጦ አንዴ ማምረት ብቻ ሳይሆን ሁለቴም ሶስቴም ማምረት ካልተቻለ ከዚህ የባሰ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ እንደምንገባ መታወቅ አለበት።
መንግስት የሚመራበትን ስትራቴጂ ማስተካከል አለበት፤ ለምሳሌ ወረዳና ቀበሌ ላይ አርሶ አደሩን ያማክራሉ ተብለው የሚመደቡ ባለሙያዎች አንዳንድ ጊዜ ስራ አጥተው ደመወዛቸውን እየበሉ ይቀመጣሉ፤ ይህ ከሚሆን አሁን የቀጠርነውን 70 እና 80 ሺ የልማት ሰራተኛ በግማሽ በመቀነስና የሌሎቹን ገንዘብ እነሱ ላይ በመጨመር ውጤታማ ስራ እንዲሰሩ ቢደረግ የበለጠ ውጤት ይመጣል።
ለውጡ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብሎ ማለት ከባድ ቢሆንም፣ የህዝብ ቁጥራችን በጣም እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ግን ከችግራችን እየተማርንም ቢሆን ለውጥ እናመጣለን።
አዲስ ዘመን ፦ ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ምን ዓይነት አዳዲስ ስራዎችን ለማከናወን አቅዷል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ አሁን አግሮ ኢንደስትሪዎቹ ተሰርተው ቁጭ ብለዋል፤ በእኔ እምነት ግን መሆን የነበረበት ከምንበላው የበለጠ ማምረት ስንችል ቢሆን ጥሩ ነበር፤ አሁን ትኩረት አድርገን የምንሰራው እነዚህን ኢንደስትሪዎች ታሳቢ ያደረገ ስራ ነው። ከዚያ በተጨማሪ ከውጭ የምናመጣውን ሊያስቀሩ የሚችሉ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ ፣ አኩሪ አተርና ስኳር ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን፤በዚህም ሌሎችንም እናግዛለን።
በሌላ በኩልም ስትራቴጂክ ኮሞዲቲ እንደሚያ ስፈልገን በጥናት በለየነው መሰረት ለምግብ ዋስትና ፣ለውጭ ንግድ ፣ለኢንደስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች ላይ ምርምር ለማድረግና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለማቅረብ አቅደናል።
ከዚህ ውስጥ እንግዲህ አንዱ ስንዴ ነው፤ ሁለተኛው በቆሎ ነው ። እዚህ ላይ አሁን በበቆሎ ራሳችንን ችለናል፤ በስንዴ ግን ይቀረናል ፤በመሆኑም እዚህ ላይ ምን ብንሰራ ከምን ተነስተን የት እንደርሳለን? እንዲሁም መቼ ራሳችንን ችለን ወደውጭ እንልካለን? የሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ሆነን ሰራን፤ ይህ አካሄድ ደግሞ በከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ ትኩረት በማግኘቱ በአሁኑ ወቅት ስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አጀንዳቸው አድርገው እየሰሩበት ነው።
ከዚህ አኳያ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በስንዴ ራሳችንን እንድንችልና ከዚያ ቀጥሎ ባሉት ሶስትና አራት ዓመታት ደግሞ ምርቱን ወደውጭ መላክ እንድንችል አቅጣጫ አስቀመጥን እቅድ አቅርበን ስራው መቼ ይጀመር ? ማን ምን ይስራ? የሚለውን ለይተን አምና ወደ ተግባር ገብተናል ፤ ዘንድሮ በጣም ተስፋፍቶ ሄዷል፤ ውጤቱ እንግዲህ ወደፊት ነው የሚታየው።
አዲስ ዘመን ፦ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
እፀገነት አክሊሉ