
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶች መረቁ
ጎንደር፦ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ ከማህበረሰብ ጋር ያለው ቁርኝት በማጠናከርና በሥነምግባር የታነፁ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅበታል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለፁ ።
ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በአራት ቢሊዮን ብር ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶችን በትናንትው ዕለት በይፋ መርቀዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት ፤ አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊና ተቋማዊ ራዕይን ለማሳካት ምቹ ጎዳና ላይ ይገኛል። የተመረቁት ፕሮጀክቶችም የዚሁ ጉዞ አካል ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆኑ በመረዳት ከምንጊዜውም በላይ በመትጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ ፕሮጀክቶቹ እውን እንዲሆኑ ከጎንደር የመታደስና ዳግም የመለወጥ ግብ ጋር አስተሳስረው የቅርብ ድጋፍና ክትትል ያደረጉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመስግነዋል ።
ዩኒቨርሲቲው ከታሪካዊነቱ ባሻገር ለሌሎች ተቋማት አርአያ የሚሆኑ እሴቶች ገንብቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው የጎንደር የቃል ኪዳን ቤተሰብ የተሰኘ ድንቅ ባህላዊ እሴቶችን መገንባቱን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን ከማህበረሰቡ ጋር በማስተሳሰር ለሀገራዊ አንድነት ፍቅር እያበረከተ ያለው ሥራ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ የማድረግ ታሪካዊ ምዕራፍ ለማሽጋገርም ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀው ፤ ባለፉት ዓመታት ባገኘው ልምድ ታግዞ ራሱን ወደ ልቀት ከፍታ እንዲያደርስም አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከስምንት አንጋፋ የምርምር ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልፀው፤ ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በጎንደር ከተማ በሚገኙ ካምፓሶች ያስገነባቸውን 22 ፕሮጀክቶች በጤና፣ በትምህርት ፣ በግብርና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል። ፕሮጀክቹ በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባታቸውን ገልፀዋል፡፡
አምስቱ ፕሮጀክቶች በቀድሞ አመራሮች የተገነቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ 17 አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የካንሰር የጨረር ህክምና ማዕከል፣ የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ ፋብሪካ (ፕላንት)፣ ሰው ሠራሽ እግር ማምረቻ፣ የቅድመ ህክምና ቤተ ሙከራ፣ የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች፣ የዲጂታላዜሽን እና ሲስተም አውቶሜሽን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር፣ በጤና፣ በግብርናና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለማህበረሰቡ ብሎም ለአጎራባች አካባቢዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል እያከበረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የፕሮጀክቶቹ ምርቃት በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ ሚኒስትሮች እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም