በኢትዮጵያ ሎተሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ የዋለው በ1954 ዓ.ም ነው፡፡ የሽልማት መጠኑም 50,000 ብር ነበር፡፡ የሎተሪው አሸናፊዎች አምስት የኤርትራ ነዋሪዎች ነበሩ፡፡ የዕጣ አወጣጥ ሥነሥርዓት የተካሄደው ደግሞ በጃንሜዳ ነበር፡፡ ስለሎተሪ ለመጻፍ የተነሳሁት ነገ ዓርብ ታህሳስ 19 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያው የሎተሪ ዕጣ ከወጣ 57 ዓመት ስለሚሆነው ነው፡፡
አንድ ሰው ሎተሪ ማሸነፉን ባረጋገጠበት ቅጽበት ድንጋጤ፣ ደስታ፣ ጥርጣሬ፣ ፍርሃት እና ጉጉት ቦታ እየተቀያየሩ እንደተጣደ ወጥ የሚያንተከትኩት ይመስለኛል፡፡ ራሱን ሊስት የሚችል ሰውም ይኖራል፡፡ የወግ ፀሐፊው መስፍን ሀብተማሪያም በህዳር ወር 2002 ዓ.ም በሮዝ መጽሔት ሎተሪን አስመልክቶ በጻፈው ወግ ተከታዩን ታሪክ አስፍሯል፡፡ ሰማኒያ ዓመት የሞላቸው አንድ የደከሙ ሽማግሌ ታላቁን የዓለም ሎተሪ ይቆርጡና የሰባት ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ እርሳቸው ግን ቲኬቱን ይዘዋል እንጂ ማሸነፋቸውን አያውቁም፡፡
እኒህ የደከሙና ሞትን የሚጠባበቁ ሽማግሌ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ማሸነፋቸውን ቢሰሙ በደስታና በድንጋጤ ልባቸው ቀጥ እንዳይል ተሰጋ፡፡ እናም የሽልማቱ መጠን ሲነገራቸው ሞት ቀርቶ ጤናቸው እንኳን ጫፉ እንዳይነካ እያዋዛ እያጫወተ የሚያበስራቸው ምራቁን የዋጠ የምስራች ነጋሪ ተፈለገ፡፡ አንድ አዋቂ ሰው ተገኘና ሲያጫውታቸው ዳር ዳር ሲል ቆይቶ በመጨረሻ ‹‹ለመሆኑ ሎተሪ ቢደርሶ ምን ያደርጉበታል?›› ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ የቀለደባቸው ያፌዘባቸው መስሏቸው ይሁን በሌላ አይታወቅም ‹‹ማ እኔ›› ይሉታል ሰውዬውም ‹‹አዎ እርስዎ ራስዎ›› ይላቸዋል፡፡ ወዲያውኑ ምንም ቃል ሳይጨምሩ ‹‹ግማሹን ላንተ እሰጥሃለሁ›› ይሉታል፡፡ ይሄኔ የምስራች ነጋሪው ልቡ ቀጥ አለ፡፡ መተንፈስ አቆመ (ስንብት)፡፡
ጳውሎስ ኞኞ በአንድ ወቅት ስለሎተሪ ሲናገር ‹‹ማንም ሀብታም ቢሆን ሚሊዮን ቆጠርኩ የሚል የለም፡፡ የባንክ ሰራተኞችም ቢሆኑ ሚሊዮን የሚደርሱ አይመስለኝም፡፡ በሂሳብ ነው፡፡ ሚሊዮን ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በውኑ ይሄ ነገር ሳላረጅ እና ሳልሞት የሎተሪ እጣ ክፍያ ሚሊዮን ቢደርስ ደስ ይላል›› ብሎ ነበር፡፡ በዘመናችን የሎተሪ ሽልማት አስር ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ሚሊዮን የሒሳብ ቁጥር እንጂ የማይደረስበት ነው ያለው ጳውሎስ ኞኞ ዛሬ በሕይወት ኖሮ ከህዝብ ጉሮሮ እየነጠቁ በቢሊዮን ብሮች ጢባጢቤ የሚጫወቱትን ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ቢመለከት ምን ይል ይሆን?
በሎተሪ ዙሪያ የሚነገሩ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ እኔ በበኩሌ ከሰማኋቸውና ካነበብኳቸው በተከታዩ ታሪክ እደመማለሁ፡፡ አሜሪካን ሀገር ውስጥ የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ ሎተሪ ለመቁረጥ የተሰለፉ ሰዎች ተራቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ አንድ ጎልማሳ ተሰላፊዎቹን ከምንም ሳይቆጥር ወደፊት አመራ፡፡ አይኑን በጨው አጥቦ ተረኛ ከነበረው ሰው ፊት ለፊት ተደነቀረ፡፡ ተረኛው ዝም አለ፡፡ ጎልማሳው ያለተራው ሎተሪውን ቆርጦ በመጣበት ፍጥነት ተፈተለከ፡፡ የሎተሪው መውጫ ቀን ደረሰ፡፡ ከፍተኛ ሽልማት የሚያስገኘው ዕጣ ከነዚህ ሁለት ሰዎች ለአንደኛው መድረሱ ተረጋገጠ፡፡ ያለተራው የቆረጠው ጎልማሳ መንገድ ጠራጊ ነበር፡፡ ተራውን የተነጠቀው ሰው ዕድለኛ ሆነ፡፡ ‹‹ዕድለኛ ሰው ወደ ባህር ቢወረውሩት በአፉ አሳ ይዞ ይወጣል›› ነው ነገሩ፡፡
የሎተሪ ነገር ሲነሳ ግርም ድንቅ ከሚለኝ ነገር አንዱ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዕድለኞችን የሚያስተዋውቅበት መንገድ ነው፡፡ በርግጥ እያንዳንዱ ነጠላ ቲኬት ጀርባ ላይ አስተዳደሩ የሎተሪ አሸናፊዎችን ማንነት እንደአስፈላጊነቱ ለህዝብ ይፋ የማድረግ መብት እንዳለው አስፍሯል፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ሎተሪውን ከገዛ ስምምነቱን እንደተቀበለ ተደርጎ ይወሰዳል ማለት ነው፡፡ ታዲያ የአሸናፊዎቹ ማንነት የሚለው ሀረግ ወሰኑ የት ድረስ እንደሆነ አለመጠቀሱ ነው የሚገርመኝ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሎተሪ አሸናፊዎች ማንነት ሲገለጽ ለዘራፊ ቁልጭ ያለ አቅጣጫ ለመስጠት ጥረት የሚደረግ ነው የሚመስለው፡፡ እስቲ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰዱትን ተከታዮቹን ምሳሌዎች እንመልከት፡፡
ለረጅም ዓመታት በጥበቃ ሰራተኛነት ሲተዳደሩ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ምንም ገቢ የሌላቸው አቶ ተፈሪ ጎርፌ ባለፈው ሃሙስ ነሐሴ 04 ቀን 2009 ዓ.ም በወጣው 1576ኛ መደበኛ ሎተሪ የ450,000 ብር እድለኛ ሆነዋል፡፡
አቶ ተፈሪ የ56 ዓመት ባለፀጋና በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13 ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ተፈሪ የሶስት ልጆች አባት ሲሆኑ በአጠቃላይ የአምስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡
ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ከተማ ቤቴል አካባቢ የሆነውና በልደታ አካባቢ በሚገኘው ሬነሰንስ ትምህርት ቤት የቤተመጻህፍት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ባይነስ ቶምቦላ ሎተሪ በ2ኛ ዕጣ የባለሶስት መኝታ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ ሆኗል፡፡
ሁለቱን አሸናፊዎች ለመግለጽ ዕድሜ፣ የተሰማሩበት የስራ መስክ፣ የሚኖሩበት ክፍለ ከተማ፣ ቀበሌ፣ የቤተሰብ ብዛት እና የሚሰሩበት ቦታ ተጠቅሷል፡፡ አልበዛም እንዴ? ሌላ ጊዜ ደግሞ የአሸናፊዎቹ ማንነት ሲገለጽ ከላይ ከተጠቀሱት መረጃዎች በተጨማሪ የግለሰቦች ገበና አደባባይ ይወጣል፡፡
ጄኔራሉ የደረሳቸውን ባለአንድ ፎቅ ከነሙሉ ዕቃ ወላጅ አልባ ለሆነችውና ለሚያሳድጓት ልጃቸው ሊያወርሷት ነው፡፡
ዕድለኛው ብ/ጄኔራል ገ/መስቀል አዝብጤ በ2009 ዓ.ም በወጣው ቶምቦላ ሎተሪ የ1ኛ ዕጣ ባለአንድ ፎቅ ሙሉ ቤት ከነሙሉ ዕቃ ጋር የደረሳቸው ሲሆን የ75 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ በቤት ሰራተኛነት ቀጥረው ሲያሰሯት የነበረችውን እናትፋንታ ጥላሁን ከተፈተነችው 10 ትምህርት 9 ኤ በማምጣት ስላስደሰተቻቸው ‹‹ከዛሬ ጀምሬ ልጄ ነሸ›› በማለት እያሳደጓት ያሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጂማ ዩኒቨርሰቲ የ5ተኛ ዓመት የሜዲሲን ተማሪ ነች፡፡
እንግዲህ ልጅት ማን እንደሆነች እንኳን አብረዋት የሚማሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ነፍስ ያወቁ ህጻናትም ያርፋሉ፡፡ በዚህ መልኩ ማንነቷ እንዲገለጽ ፈቃድዋን ሠጥታ ከሆነ እሰየው ካልሆነ ግን ያስገርማል፡፡
ገንዘብ ያታልላል ተብላችሁ ብትጠየቁ ምን ትላላችሁ? እኔን ብትጠይቁኝ ምን ጥርጥር አለው በደንብ ነዋ፡፡ የራሳቸው ያልሆነን የሎተሪ ዕጣ ይዘው ወደሸላሚው አካል የሚፈረጥጡ ከዳተኞች ለዚህ አባባሌ ምስክር ናቸው፡፡
በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካን የገባው ጆሴ አንቶኒዮ ኩዋቶክ የ750 ሺህ የአሜሪካን ዶላር አሸናፊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ስደተኛ ባለመሆኑ አሸናፊ ነኝ ብሎ ቢቀርብ ወደ መጣበት ሀገር እንዳይመልሱት ይሰጋል፡፡ ስለዚህ ገንዘቡን ለመካፈል ተስማምተው ለአለቃው ቲኬቱን አሳልፎ ሰጠው፡፡ አለቃው ቃሉን አጠፈ፡፡ ገንዘቡን ለብቻው ወሰደ፡፡ በ2012 ጉዳዩን የተመለከተ ፍርድ ቤት ጆሴ አንቶኒዮ ኩዋትኮ ቲኬት ሲገዛ የሚያሳየውን የተቀረጸ ምስል ከተመለከተ በኋላ አለቃው ሽልማቱን እንዲመልስ ፍርድ ሰጠ፡፡
እኛም ሀገር ተመሳሳይ ታሪክ ተፈጥሮ እንደነበር በአንድ ወቅት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ ሎተሪ የደረሳት እንስት የደስደስ ጓደኞቿን ትጋብዛለች፡፡ በግብዣው መሃል ከጓደኞቿ መካከል ለአንዷ ቲኬቱን ያዥልኝ ብላ ትሠጣታለች፡፡ ጓደኛዋ ሎተሪውን ይዛ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደሩ በመሄድ ሽልማቱን ለመውሰድ ስትሞክር ትክክለኛዋ ባለዕድል በፍርድ ቤት እንዲታገድ ታደርጋለች፡፡ አራት ዓመት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ ፍርድ ቤቱ ለሁለት እንዲካፈሉ ወሰነ፡፡ የሲስተም ችግር ማለት ይህ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ቢኖር እንደ ጆሴ አንቶኒዮ ኩዋትኮ ቲኬቱን ማን የት ቦታ እንደገዛ አረጋግጦ ለእውነተኛው ባለዕድል መፍረድ ይቻል ነበር፡፡ ዳሩ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በሎተሪ ቲኬት ጀርባ ከሚጽፋቸው ሕጎች አንዱ ሎተሪውን ይዞ ለመጣ ሰው ክፍያ እንደሚፈጸም የሚገልጽ ነው፡፡
ሎተሪ ብታሸንፉ መጀመሪያ የምትገዙት ነገር ምንድን ነው? መኪና፣ ቤትና አክስዮን እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ ቦብ ኸርብ የተባለው ሰው ያደረገው ነገር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ያገኘውን ከፍተኛ ገንዘብ ማሪዋና የተሰኘው ዕጽ ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ዘመቻ ለማድረግ አውሎታል፡፡ ‹‹ወይ ጉድ!›› አያሰኝም ?
ጥቂት የማይባሉ የሎተሪ ዕድለኞች ገንዘባቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አባክነው ወደቀደመ ህይወታቸው ይመለሳሉ፡፡ ሻሮን ቲራባክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድገው ይህች አሜሪካዊት የአውቶብስ ሹፌር እ.አ.አ. በ2004 የአስር ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር ሎተሪ አሸናፊ ሆነች፡፡ ገንዘቧን ትልቅ ቤት፣ ቅንጡ መኪና፣ ቄንጠኛ ዲዛይን ላላቸው ልብሶች፣ አስገራሚ ጉዞዎች ለማድረግ፣ ቤተሰቧን ለማዝናናት እና ለጓደኞቿ ስጦታ ለመስጠት አዋለችው፡፡ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ ግን ወደ አውቶቡስ ሹፌርነቷ ለመመለስ፤ ተጨማሪ ሰዓት ስራ ለመስራት እና በኪራይ ቤት ውስጥ ለመኖር ተገደደች፡፡ እንደ ዕድል የተወሰነ ገንዘቧን በስድስት ልጆቿ ስም ሃያ ስድስት ዓመት ሲሞላቸው ከባንክ እንዲያወጡት ማስቀመጧ መጽናኛ ሆኗታል፡፡
የሎተሪ አለቃ የሚል መጠሪያን ለማትረፍ የበቃው ሮማኒያዊው ስደተኛ ስቴፈን ማንዴል ሎተሪ እንዲያሸንፍ የሚያስችለውን ሚስጥራዊ ቀመር ሲፈልግ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ታዲያ ተሳክቶለታል አስራ አራት ጊዜ ሎተሪ ማሸነፍ ችሏል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሎተሪዎቹን ያሸነፈው በአራት የተለያዩ ሀገራት መሆኑ ነው፡፡ ይህን ቀመር ለማወቅ አልተመኛችሁም …
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
የትናየት ፈሩ